በወንጀል ክስ ላይ የሚቀርብ መቃወሚያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ክርክር ሂደት ተከሳሾች ክስ ሲቀርብባቸው የቀረበባቸው ክስ ሊቀርብባቸው እንደማይገባ በመግለፅ ወደ ዋናው ክርክር ከመገባቱ በፊት ክሱን ሊቃወሙ የሚችሉባቸው ምክንያቶች በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ሥነ -ሥርአት ህጎች ተደንግጎ ይገኛል። በዚህ ጽሑፍ በወንጀል ክርክር የሚቀርብ የክስ መቃወሚያን ምንነት፣ የመቃወሚያዎቹን አይነት እና ስለሚቀርብበት ሥርአት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የወንጀል ክስ መቃወሚያ ምንነት

የወንጀል ክስ መቃወሚያ ማለት ተከሳሾች በሥነ ሥርአት ህጉ የተደገጉ ምክንያቶችን በመግለፅ ወደ ዋናው ክርክር መግባት ሳያስፈልግ የቀረበው ክስ ውድቅ እንዲሆንላቸው የሚቀርብ ተቃውሞ ነው። በወንጀል ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 130 መሠረት ተከሳሽ የቀረበበትን የክስ ቻርጅ ይዘት እና ፎርም እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በማንሳት ሊቃወም እንደሚችል ደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁ ሕግ ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ እንደተገለፀው ተከሳሽ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያ ካለው እንዲያቀርብ ሲጠይቀው ወዲያውኑ ካላቀረበ ከዚያ በኋላ ከማቅረብ እንደሚከለከል ደንግጎ ይገኛል፡፡ በህጉ ላይ እንደተደነገገው ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የተለያዩ መቃወሚያዎች ካሉት መቃወሚያዎቹን እንዲያቀርብ ሲጠየቅ በአንድ ላይ በማድረግ አስቀድሞ ማቅረብ ያለበት ሲሆን በዚህ አግባብ ሲጠየቅ ያልቀረበ መቃወሚያ ኪዚያ በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ነገር ግን ያልቀረበው መቃወሚያ ፍርድ ቤቱን ተገቢውን ፍትሀዊ ውሳኔ ከመስጠት የሚያግደው ከሆነ ፍርድ ቤቱ በየትኛውም ደረጃ እንዲቀርብ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የወንጀል ክስ መቃወሚያ አንድ በፍርድ ቤት ክስ የቀረበበት ሰው ፍርድ ቤቱ የቀረበበትን ክስ ከወዲሁ በማየት ወደ ዋናው ክርክር መግባቱን በማስቀረት ክሱን ውድቅ እንዲያደርግ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮች ለፍርድ ቤቱ የሚቀርቡበት ሥርአት ነው፡፡ ከወንጀል ክርክር አንፃር የሚቀርቡ መቃወሚያዎች በዋናነት በሁለት የሚመደቡ ሲሆን እነዚህም ክሱን በጊዜአዊነት እና በዘለቄታው የሚያቋርጡ መቃወሚያዎች ናቸው፡፡

ክሱን በጊዜአዊነት የሚያቋርጡ መቃወሚያዎችም በወንጀል ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀጽ 130(1) ላይ የተገለፁ ሲሆን እነዚህም ከክሱ ፎርም ወይም ይዘት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜም የወንጀል ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 119 ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት የቀረበው ክስ ያልተካተተ ወይም በስህተት የተካተተ መሠረታዊ ጉዳይ ካለው እና ይህ ስህተትም ተከሳሹን ሊያሳስተው ይችላል ተብሎ ሲታመን ፍርድ ቤቱ ከውሳኔ በፊት በማናቸውም ጊዜ ክሱ እንዲቀየር፣ እንዲስተካከል ወይም በአዲስ መልክ እንዲቀርብ ሊያዝ እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም እነዚህ በዋናነት ከክሱ ፎርም ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ክሱን በቋሚነት የሚያቋርጡ ሳይሆን በጊዜአዊነት የሚያቋርጡ እና ተስተካክሎ ሲቀርብ ክርክሩ እንዲቀጥል የሚያደርጉ መቃወሚያዎች ናቸው፡፡

ክሱን ለዘለቄታው የሚያቋርጡ መቃወሚያዎች ደግሞ በቀረበው ክስ ላይ ከተነሱ እና ስለመኖራቸው በማስረጃ ከተረጋገጡ የቀረበውን ክስ እስከወዲያኛው እንዲዘጋ የሚያደርጉ መቃወሚያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መቃወሚያዎችም፡-

  1. ጉዳዩ በሌላ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ካለ
  2. ከቀረበው ክስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ክስ ነፃ ተብሎ ወይም ተቀጥቶ ከሆነ
  3. የቀረበው ክስ የክስ ማቅረቢያ ጊዜው ወይም የይርጋ ጊዜው ያለፈበት ከሆነ
  4. የቀረበው ክስ በይቅርታ ወይም ምሕረት የታለፈ ከሆነ
  5. ተከሳሹ ከሌሎች ጋር አብሮ የሚዳኝ ከሆነ መብቱን የሚያጣብበት ከሆነ
  6. ክስ የማቅረብ ፍቃድ ለሚያስፈልገው ክስ ሆኖ ፍቃዱ ሳይገኝ የቀረበ ከሆነ
  7. በሌላ ክርክር እየታየ ያለ ጉዳይ ውሳኔ ካላገኘ ክሱን ለማየት የማይቻል ከሆነ

እነዚህ መቃወሚያዎች በሕግ የተመለከቱ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ መቃወሚያዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ይሄም በህጉ ላይ የተዘረዘሩት መቃወሚዎች እነዚህ ብቻ ናቸው በሚል ዝግ አገላለጽ ሳይሆነን ጠቋሚ ወይም አመላካች በሆነ መልኩ የተደነገጉ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህም – የሚነሳ የክስ መቃወሚያ በዋናነት ወደዋናው ጉዳይ በመግባት ክሱን ለማየት የሚከለክል እስከሆነ ድረስ ሌላም መቃወሚያ ሊነሳ እንደሚችል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተለያየ ጊዜ በሰጣቸው ውሳኔዎች በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ በሌላ በኩል -የወንጀል ክስ መቃወሚዎች ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት መቃወሚ እንዳለው ሲጠየቅ ወዲያው ማንሳት ያለበት ሲሆን በዚህ ጊዜ ምላሽ ካልሰጠ ቀጥሎ በሚኖረው ክርክር እንዳያነሳ ፍርድ ቤት ሊከለክለው ይችላል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ መቃወሚያው ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ ጠቃሚ ነው ብሎ ካመነ በክርክር ሂደቱ መቃወሚው ሲነሳ ሊቀበል እንደሚችል በህጉ አንቀጽ 130(3) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የወንጀል ክስ መቃወሚያ አቀራረብ እና ውሳኔ አሰጣጥ ሥርዐት

የወንጀል ክስ መቃወሚያ የሚቀርብበት እና ውሳኔ የሚሰጥበት ሥርአት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁ አግባብ የወንጀል ክስ መቃወሚያ ከተነሳ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህጉ በመቃወሚያው ላይ ያለውን አስተያየት የሚጠይቀው ሲሆን በሚሰጠው አስተያየት መሠረት ጉዳዩ የሕግ ክርክር ከሆነ ወይም የተነሳው መቃወሚያ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክርክር ካላነሳ ወዲያውኑ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ የተነሳው መቃወሚያ አካራካሪ እና በማስረጃ መረጋገጥ የሚገባው ከሆነ ፍርድ ቤቱ ማስረጃው ሳይዘገይ እንዲቀርብ በማድረግ ሰምቶ እና መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑ በህጉ አንቀጽ 131 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም የሚሰጠው ውሳኔ እንደ መቃወሚየው አይነት ክሱ ተስተካክሎ እንዲቀርብ፣ ክሱ እንዲዘጋ ወይም የተነሳውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ወደ ክርክር እንዲገባ በማድርግ ወደ እምነት ክህደት ቃል መስማት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የወንጀል ክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ አይቶ ውሳኔ እንዳይሰጥ የሚከለክል አለአግባብ የቀረቡ ክሶች እና ተያያዝ ጉዳዮችን በማጥራት የክስ መዝገብ እንዲዘጋ ወይም ክስ ተስተካክሎ እንዲቀርብ የሚያደርጉ መቃወሚዎች ናቸው፡፡ በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ዜጎች በየወንጀል ክስ መቃወሚያነት ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት በክርክር ሂደት በወቅቱ በማቅረብ የልተገባ ፍርድ እንዳይሰጥባቸው ማደረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ