የህጋዊ ሥነ-ልክ ሥርዓት በኢትዮጵያ ህግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሥነ-ልክ (ሜትሮሎጂ) መለኪያ እና አተገባበሩን የሚመለከት ሳይንስ ሲሆን በተለያዩ መስኮች ትክክለኛነትን እና ወጥነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለማምረት እና ለዕለት ተዕለት ግብይቶች ወሳኝ ነው። ይህም ለታማኝነት እና በመለኪያዎች ላይ ለሚኖር አስተማማኝነት መሠረት ይሰጣል። በአለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ ለማለት በሚቻል ደረጃ ከትልቅ እስከ ትንሽ ከቀላል እስከ ከባድ በልኬት ሊመዘኑ ይችላሉ። ሶስት ዋና ዋና የሥነ-ልክ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነሱም ሳይንሳዊ፣ ኢንዱስትሪያዊ እና ህጋዊ ናቸው። በዚህ ጽሁፍ የምንመለከተው ህጋዊ ሥነ-ልክን ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ የሕጋዊ ሥነ-ልክ አዋጅ ቁጥር 1344/2016 ስር ሽፋን ተሰጥቶታል። ይኸውም በንግዱ፣ በደኅንነት እና በሸማቾች ጥበቃ ላይ መለኪያዎችን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት የዘረጋ ሲሆን በአዋጁ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች በዚህ ጽሑፍ በአጭሩ ይዳሰሳሉ።

የሕጋዊ ሥነ-ልክ ምንነት

በሕጋዊ ሥነ-ልክ አዋጅ ቁጥር 1344/2016 አንቀጽ 2/1 መሠረት “ሕጋዊ ሥነ-ልክ” ማለት በሕግ የተቀመጡ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ ልኬትን፣ የልኬት አሀዶችን፣ የመለኪያ መሣሪያዎችን እና የልኬት ዘዴዎችን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ ሕግን በሚያስፈጽሙ ተቆጣጣሪ አካላት የሚከናወን ተግባር ነው። “ልኬት” ማለት አንድን መጠን በተሻለ ሁኔታ የሚገልፁ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ በሙከራ የተገኙ መጠናዊ ገላጮችን የመወሰን ሂደት ሲሆን “የልኬት አሀድ” ማለት ደግሞ በዓለም አቀፍ ስምምነት የተወሰነ እና ተቀባይነት ያገኘ እውነተኛ ቁሳዊ መጠን ሆኖ ከሌሎች ተመሳሳይነት ካላቸው ቁሳዊ መጠኖች ጋር በጥምርታ በማነጻጸር በአሀዝ የሚገለጽበት ነው (አንቀጽ 2(8) እና 2(9)።

የሕጋዊ ሥነ-ልክ ሥርዓትን የመደንገግ አስፈላጊነት

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የህጋዊ ሥነ-ልክ ሥርዓትን ለማውጣት ያስፈለገባቸው ምክንያቶች በአዋጁ መግቢያ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ይኸወም

ከንግድ ልውውጥ፣ ከጤና፣ ከደኅንነት እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ልኬቶችንና የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የሰውን እና የእንስሳትን ጥቅም፣ ጤንነትና ደኅንነት ማስጠበቅ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን መከላከል አስፈላጊ መሆኑ

  • የታሸጉ ምርቶች ወደ ገበያ ከመግባታቸው በፊት እና ከገቡም በኋላ መግለጫቸውና የተጣራ መጠናቸው ትክክለኛነት የሚረጋገጥበትን የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ሸማቾች ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑ
  • የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የቁጥጥር ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ
  • ከዓለም ዓቀፍ የሕጋዊ ሥነ-ልክ የአሠራር ሥርዓት ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ሕግ ማውጣት የንግድ እንቅፋትን በማስወገድ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ እና
  • ሀገራችን ከደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተጣጣመ ሕግ በማውጣት ግልጽና ተአማኒ የአለካክ ሥርዓት ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ እንደሆነ በግልፅ ተዘርዝሯል፡፡

ይህ አዋጅ ለንግድ ልውውጥ፣ ለሰውና ለእንስሳት ጤናና ደኅንነት እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት በሚውሉ የኢትዮጵያ ደረጃ በወጣላቸው ልኬቶች፣ የመለኪያ መሣሪያዎች እና እነዚህን መሳሪያዎች በሚያመርት፤ በሚገጣጥም፣ ወደ ውጭ ሀገር በሚልክ፣ ወደ አገር ውስጥ በሚያስገባ፣ በሚያከፋፍል፣ ለገበያ በሚያቀርብ፣ በሚጠቀም፣ በሚያረጋግጥ፣ በሚጠግን፣ እና በማናቸውም የታሸጉ ምርቶች የተጣራ መጠን እና እነዚህን ምርቶች በሚያመርት፣ በሚያሽግ፣ ወደ ውጭ ሀገር በሚልክ፣ ወደ አገር ውስጥ በሚያስገባ፣ በሚያከፋፍል፣ ለገበያ በሚያቀርብ እና በሚያረጋግጥ ማንኛውም ሰው ላይ ተፈጻሚ ሲሆን ለወታደራዊና ለብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት በሚውሉ የመለኪያ መሣሪያዎች እና የታሸጉ ምርቶች ቁጥጥር ላይ ግን ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ከአዋጁ አንቀጽ 3 መረዳ ይቻላል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥልጣን እና ተግባራት

በአዋጁ እንቀፅ 4(1) መሠረት

  • የሀገሪቱን የህጋዊ ሥነ-ልክ ሥርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ መሆኑን መቆጣጠር
  • የመለኪያ መሳሪያዎች የኢትዮጵያ ደረጃዎች እንዲዘጋጁ እና እንዲከለሱ ለሚመለከተው አካል ሀሳብ ማቅረብ ሲጸድቁም ለሕዝብ ማሳወቅ
  • በመለኪያ መሳሪያዎች ላይ የሚተገበሩ የማረጋገጫ ምልክቶች የአጠቃቀም፣ የአስተዳደር እና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፣ ተግባራዊነቱን መቆጣጠር
  • እንዳስፈላጊነቱ የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነት፣ የአይነት እና የንድፍ ብቃት ማረጋገጫ ላቦራቶሪ ማቋቋም
  • የመለኪያ መሣሪያዎችን ዓይነት ወይም ንድፍ መመርመር፣ ማፅደቅ፣ መመዝገብ፣ የተስማሚነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት
  • በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ወይም እንዲረጋገጡ ማድረግ መመዝገብ፣ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የትክክለኛነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት
  • ለሕጋዊ ኦፊሰርና ጠጋኝ ፈቃድ መስጠት
  • የፈሳሽ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ቦቴዎች፣ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከሮች እና ዴፖዎች፣ የተሸጋጋሪ ሚዛኖች እና ሌሎች አገልግሎታቸው በአንድ ክልል ውስጥ ብቻ ያልተወሰነ የመለኪያ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ እንዲረጋገጡ ማድረግ፣ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የትክክለኛነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት፤ የተረጋገጡ የመለኪያ መሣሪያዎች ብቻ በሥራ ላይ መዋላቸውን መቆጣጠር
  • በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የታሸጉ ምርቶችን የተጣራ መጠን እና መግለጫ ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ ለሽያጭ መቅረብ የሚችሉ ስለመሆኑ የይለፍ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት
  • የኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርቶችን ያላሟሉ የመለኪያ መሣሪያዎች እና የታሸጉ ምርቶች ከሀገር እንዳይወጡ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ ለሽያጭ እንዳይቀርቡ፣ ከገበያ እንዲሰበሰቡ፣ እንዲወገዱ ወይም አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ማድረግ ወይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ
  • በአዋጁ መሠረት በሚወጣ መመሪያ የተመለከቱትን መመዘኛ መስፈርቶች ለሚያሟላ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ኦፊሰር እና ጠጋኝ ፈቃድ መስጠትና መቆጣጥር
  • በሥልጣን ክልላቸው ስር የሚወድቁ የመለኪያ መሳሪያዎችን እና የታሸጉ ምርቶችን ትክክለኛነት የመቆጣጠር ሥልጣን ያላቸውን አስፈጻሚ አካላት ማስተባበርና አፈጻጸማቸውን መከታተል
  • ሕጋዊ ሥነ-ልክን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ተግባራትን ማከነወን፣ ሥልጠና መስጠት፣ ሀገር አቀፍ የመረጃ ቋት ማደራጀት
  • የሀገሪቱ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ድርጅት የሕግ እና የአሠራር ሥርዓት ማዕቀፍ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ
  • ሕጋዊ ሥነ-ልክን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ደረጃ ሀገሪቱን መወከል፤ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች መሳተፍ፣ ኃላፊነት ካላቸው ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማካሄድ፣ ማስተባበር፣ ማስተዳደር
  • በቁጥጥር ሂደት ሕገ-ወጥ ወይም ከደረጃ በታች ሆነው የተገኙ የመለኪያ መሳሪያዎችና የታሸጉ ምርቶች ስለሚወገዱበት ሁኔታ መመሪያ ማውጣት
  • ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሠረት ክፍያዎችን የማስከፈል
  • ከሕጋዊ ሥነ-ልክ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ተግባራት ማከነወን

በአዋጁ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አግባብነት ያለው አካል ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ እና በአዋጁ እንቀፅ 4(2) ስር የተዘረዘሩትን ተግባራት እንደሚያከናውን ተደንግጓል።

የልኬት አሀዶች ሥርዓት

በአዋጁ ከተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የልኬት አሀዶች ሥርዓት ሲሆን የኢትዮጵያ የመለኪያ አሃዶች እና የመለኪያ አሀዶች ብዜቶች ሥርዓት በዓለም አቀፍ የሜትሪክ ሥርዓት (እንደ ርዝመት፣ ሚዛን፣ መጠን፣ ሙቀት ወዘተ ነገሮችን ለመለካት ጥቅም ላይ የሚውል ዓለም አቀፍ የመለኪያ አካል) መሠረት እንደሚሆን እና ይህንንም ሕዝቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግ በአንቀጽ 5(1) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከቱትን የልኬት አሀዶች ብዜቶች በመጠቀም የመሸጥ ግዴታ አለበት። ይሁንና ሚኒስቴሩ በምርምር ደረጃ ወጥቶላቸው ጥቅም ላይ የሚውሉ ሀገር በቀል የልኬት አሃዶችን በመመሪያ ሊወስን ይችላል (አንቀጽ 5(3))፡፡

የመቆጣጠሪያ መለኪያ መሳሪያዎችን ስለመጠቀም

ማንኛውም ኢንስፔክተር ወይም የሕጋዊ ሥነ-ልክ ኦፊሰር የመለኪያ መሣሪያን ወይም የታሸገ ምርትን የተጣራ መጠን ትክክለኛነት በሚያረጋግጥበት ጊዜ ካሊብሬት የተደረገ የመቆጣጠሪያ መለኪያ መሳሪያን መጠቀም አለበት፡፡ ማንኛውም ተጠቃሚ ወይም ደንበኛ የመቆጣጠሪያ መለኪያ መሳሪያዎችን ተጠራጥሮ ቅሬታ ቢያነሳ የማመሳከሪያ መለኪያ መሳሪያዎች ውጤት የመጨረሻ የትክክለኛነት መጠን ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ያለው አካል በተጠቃሚው የግብይት ስፍራ በመግባት መደበኛ፣ ድንገተኛ ወይም የቀረበ ቅሬታን መሠረት በማድረግ የመለኪያ መሳሪያ ምርመራ ማድረግ የሚችል ሲሆን ማንኛውም ተጠቃሚ በሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ባለው አካል ሲጠየቅ የመለኪያ መሳሪያን የማስመርመር ግዴታ አለበት (አንቀጽ 12)፡፡ የማመሣከሪያ መለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነት በሦስተኛ ወገን ዕውቅና በተሰጠው የካሊብሬሽን ላቦራቶሪ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ካሊብሬት መደረግ እንዳለበት በአንቀጽ 7(2) ስር ተደንግጓል፡፡

ክልከላዎች

በአዋጁ አንቀጽ 17 አስተዳደራዊ ተጠያቂነት እንዲሁም በአንቀጽ 19 የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ክልከላዎች በዝርዝር ተመልክተዋል፡፡ አስተዳደራዊ እርምጃን በተመለከተ እንደየጥፋቱ ምርቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ፣ ከሀገር እንዳይወጡ፣ ወደ መጡበት ሀገር እንዲመለሱ፣፣ ስርጭታቸው እንዲቆም፣ እንዲወገዱ ከማድረግ ጀምሮ የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሆነ ከአዋጁ አንቀጽ 17 መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ በአዋጁ አንቀጽ 19 ሥር የተደነገጉ የወንጀል ድንጋጌዎችን መተላለፍ እንደየጥፋቱ በመቀጮ፣ በቀላል እስራት እንዲሁም በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ነው፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ አዋጁ የመለኪያ መሣሪያዎች እና የታሸጉ ምርቶች ምዝገባ፣ አያያዝ፣ ትክክለኛነት ማረጋገጥ እና ምርመራን፤ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ኦፊሰሮች፣ ጠጋኞች እና ኢንስፔክተሮች ተግባርና ኃላፊነትን፤ ስለአስተዳደራዊ እርምጃዎች እና ስለቅጣት ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች የተደነገጉ ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆነው በአዋጁ የተከለከሉ ድርጊቶች መፈጸም የሚያስከትለውን ቅጣት ደንግጓል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ