መግቢያ
የወንጀል ድርጊት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል ተግባር ነው። ይህንኑ አሉታዊ ተፅህኖ ቢቻል ለማስወገድ ካልተቻለም ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለመቀነስ ድርጊቶቹ በሕግ አግባብ የሚያስቀጡበትን ስርዓት መቅረፅ ተገቢ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የወንጀል ድርጊቶችን ምንነት እና የሚያስከትሉትን ቅጣት በተመለከተ በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ላይ በሰፊው እንዲሁም ሌሎች የወንጀል ቅጣት ድንጋጌዎችን በያዙ አዋጆች ላይ የተለያዩ የወንጀል አይነቶችና ቅጣቶቻቸው ተዘርዝርው እናገኛቸዋለን። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ከተዘረዘሩ ዘርፈ ብዙ የወንጀል ዓይነቶች መካከል “በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም” ወንጀል አንዱ ነው። ይህ የወንጀል ዓይነት በንብረት መብቶች ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሲሆን አስቀጪነቱም በወንጀል ህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የዚህን ወንጀል ምንነት እና የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት በአጭሩ የምንመለከት ይሆናል፡፡
በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም ወንጀል ምንነት
በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም ወንጀል በግለሰቦች የንብረት መብት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሲሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 702 መሠረት በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም ማለት በሕግ ወይም በውል ግዴታ የሌላን ሰው የንብረት ጥቅም እንዲጠብቅ ወይም ስራውን እንዲመራ አደራ ተቀብሎ፣ በተሰጠው ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል ወይም የተጣለበትን ግዴታ ባለመፈፀም በሚጠብቀው የንብረት ጥቅም ላይ ወይም ለሚሰራበት ድርጅት በሚፈፅመው አገልግሎት ላይ አስቦ ወይም በቸልተኛነት ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ ነው። ለምሳሌ፡- አንድ ግለሰብ ንብረቱን ለማስጠበቅ በማሰብ ሌላኛውን ግለሰብ በጥበቃ ሠራተኛነት በውል መሠረት ቢቀጥረውና ይሄው ተቀጣሪ ግለሰብ በውሉ መሠረት የተጣለበትን የመጠበቅ ኃላፊነት አስቦም ሆነ በቸልተኛነት ሳይወጣ በመቅረቱ በቀጣሪው ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገ እንደሆነ ‘በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት ማድረስ’ ወንጀል ፈፅሟል ሊባል ይችላል።
የወንጀል ተጠያቂነት
ወንጀሉ ታስቦ ሲፈፀም
ከፍ ሲል በተጠቀሰው መልኩ ማለትም አንድ ሰው አስቦ በሕግ ወይም በውል የተጣለበትን የሌላውን ሰው ንብረት የመጠበቅ ወይም እንዲመራው በኃላፊነት የተሰጠውን ስራ በአግባቡ የመምራት ግዴታውን በመተላለፍ የተጣለበትን ግዴታ ሳይፈፅም በመቅረቱ ወይም ኃላፊነቱን ያለአግባብ በመገልገሉ ምክንያት በሚጠብቀው ንብረት ላይ ወይም ስራውን እንዲመራ በኃላፊነት የሰጠው ግለሰብ ወይም ድርጅት ላይ ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በወንጀል ህጉ አንቀጽ 702(1) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በሌላ በኩል በወንጀል ህጉ አንቀጽ 702(3) መሠረት ወንጀል ፈፃሚው የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው የንብረት ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስቦ እንደሆነ ከ1 ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት እና ከ30ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።
ወንጀሉ በቸልተኛነት ሲፈፀም
አንድ ሰው በሕግ ወይም በውል ግዴታ የሌላን ሰው የንብረት ጥቅም እንዲጠብቅ ወይም ስራውን እንዲመራ አደራ ተቀብሎ፣ በተሰጠው ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል ወይም የተጣለበትን ግዴታ ባለመፈፀም በሚጠብቀው የንብረት ጥቅም ላይ ወይም ለሚሰራበት ድርጅት በሚፈፅመው አገልግሎት ላይ በቸልተኛነት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገ እንደሆነ በመቀጮ ወይም ከ6 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል (አንቀጽ 702(2))።
ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች
በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም ወንጀልን የሚያከብዱ ሁኔታዎች በተመለከተ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 703 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ። የማክበጃ ሁኔታዎቹ ወንጀሉን ከፈፀመው ሰው ማንነት፣ በወንጀል ድርጊቱ ጉዳት ከደረሰበት አካል ማንነት እና ከወንጀሉ አፈፃፀም ሁኔታ ሚመዘዙ ናቸው።
ወንጀሉን የፈፀመው በተሰጠው ሥልጣን ስራውን በማከናወን ላይ በሚገኝ ወይም በተለይ ታማኝነት በተሰጠው ሞግዚት፣ ጠበቃ፣ የንብረት አስተዳዳሪ፣ ሂሳብ አጣሪ ወይም የተለየ እምነት የተጣለበት ማንኛውም ሌላ ሰው ወይም ተመሳሳይ ኃላፊነት የተሰጠው ማንኛውም ሰው የሆነ እንደሆነ ወይም ደግሞ ጉዳቱ የደረሰው በመንግሥት ወይም በሕዝብ ንብረት ላይ እንደሆነ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከ50ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል (አንቀጽ 703 (1)(ሀ) እና(ለ))፡፡ እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ሌላኛው ነጥብ በመንግሥት ወይም በሕዝብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረገው ሰው በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቃለል ከሆነ ጉዳት እንዲደርስ ያደረገው ሰው ለጉዳዩ አግባብነት ባለው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል።
ሌላው ወንጀሉን የሚያከብደው ሁኔታ ወንጀል ፈፃሚው በተሰጠው ኃላፊነት ወይም ተግባር መሠረት ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ከሌላ ሰው ላይ ማናቸውንም ዓይነት ጥቅም የጠየቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ከ1 ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ7 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከ20ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ሲሆን ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከ5 ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከ100ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑ በህጉ አንቀጽ 703(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል። ወንጀል ፈፃሚው በተሰጠው ኃላፊነት ወይም ተግባር መሠረት ማድረግ የሚገባውን ለመፈፀም ሲል ወይም ከፈፀመ በኋላ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ፣ ያገኘ ወይም ከባለጉዳይ የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከ1 ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከ10ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል (አንቀጽ 703(3))።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በሌላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ ጉዳት መፈፀም ወንጀል በግለሰቦች የንብረት መብት ላይ ጉዳት የሚያደርስና አለፍ ሲልም በህብረተሰቡ ሰላምና ደኅንነት ላይ ስጋት የሚፈጥር ወንጀል በመሆኑ የፍትሕ አካላት ወንጀሉን በመከላከል ረገድ ጠንክረው መሥራት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ህብረተሰቡም የወንጀሉን አደገኛነት ተረድቶ ወንጀሉን በመከላከልም ሆነ ተፈፅሞ ሲገኝ የወንጀል ፈፃሚዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ሂደት ለፍትሕ አካላት ተባባሪ በመሆን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ