መግቢያ
መደራጀት በዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ማዕቀፍ እንዲሁም በበርካታ ሀገራት ሕግጋት ዉስጥ የተፈቀደ መብት ነዉ፡፡ ሰዎች በማህበር በመሆን የግልና የጋራ መብታቸውን ለማስከበር እና የጋራ ግዴታቸውን ለመወጣት፣ የጋራ ጥቅም ለማግኘት ወይም ጥቅሞቻቸውን ለማረጋገጥ፣ የሀገር ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ ዓላማ ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመደራጀት መብት በልዩ ሁኔታ በጠባቡ ሊገደብ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚህ ፅሑፍ የመደራጀት መብት በዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች እና በሀገራችን ያለውን የሕግ ጥበቃ እንመለከታለን፡፡
የመደራጀት መብት የሕግ ማዕቀፍ
ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማህበር የመደራጀት መብት እንዳለው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 31 ተመላክቷል፡፡ ሀገራችን አፅድቃ የህጓ አካል ያደረገቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) በአንቀጽ 20 እንዲሁም የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) በአንቀጽ 22 ማንኛዉም ሰው የመደራጀት ነጻነት እንዳለው ደንግገዋል፡፡ በተጨማሪም ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) ማንኛዉም ሰው ያለፈቃዱ የማህበር ወይም የድርጅት አባል ያለመሆን መብት ጭምር ያለዉ መሆኑን ደንግጓል፡፡
በዚህም መነሻነት በሀገራችን የመደራጀት መብትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የተለያዩ ሕግጋት በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ለአብነት በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት ሠራተኞችና አሠሪዎች እንደ አግባቡ የሠራተኞች ወይም የአሠሪዎች ማኅበር ለማቋቋምና ለመደራጀት፣ የማህበር አባል ለመሆንና በማህበርም ለመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት ሰራተኞች በማህበራት በመደራጀት ከአሰሪዎች እና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ደሞዝን፣ በሥራ እድገትን፣ የእረፍት ጊዜን እና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን በተመለከተ ለመደራደር እና መብታቸውን ለማስከበር የሚያግዛቸው ነው፡፡
በተጨማሪም ዜጎች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በሙያ ማህበራት፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ በብዙሀን ማህበራት፣ በድርጅቶች ህብረቶች እና መሰል ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች መደራጀት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ተደራጅተው በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የሚፈልጉ ደግሞ በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ሥርአት አዋጅ 1162/2011 እና በማሻሻያው መሠረት መደራጀት ይችላሉ፡፡
የመደራጀት መብት በሕግ ክልከላ የሚደረግበት አግባብ
የመደራጀት መብት በዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ሰነዶች እንዲሁም በሀገራችን ህገ መንግሥት የተደነገገ መብት ሲሆን ሳይሻራረፍ እንዲከበር የሕግ ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡ ይህ መብት ለሀገር ደኅንነት፣ ለሕዝብ ሰላምና ጸጥታ፣ ለሕዝብ ጤና እና ሞራል እንዲሁም የሌሎችን መብትና ነጻነት ለመጠበቅ ሲባል በዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ በሕግ በተደነገጉ ገደቦች ብቻ በጠባቡ ሊገደብ የሚችል ሲሆን ከዚህ ውጪ ምንም አይነት ገደብ ሊጣልበት እንደማይገባ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) በበግልፅ አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 31 መሠረት አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ህገወጥ ተግባራት ለመፈፀም መደራጀት የተከለከለ ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡
ማጠቃለያ
የመደረጀት መብት ዓለም ዐቀፋዊ ጥበቃ እንዲሁም በሀገራችን የሕግ ጥበቃ የተደረገለት መብት በመሆኑ በሕግ በልዩ ሁኔታ በግልፅ ከተደነገጉ ገደቦች ውጪ ሊገደብ አይችልም፡፡ በመሆኑም ዜጎች ይህን መብትና ግዴታቸውን አውቀው በመጠቀም ከራሳቸው አልፈው ለማህበረሰባቸው እና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ይጠበቃል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ