የፌዴራል የመንግስት ሰራተኛ የሥራ ውል ስለሚቋረጥበት ሁኔታ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

የሥራ ውል በሕግ እንደተቋቋመ ሁሉ የሚቋረጠውም በሕግ መሠረት ነው። የሥራ ውል በሁለቱም ወገኖች ስምምነት ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም በአንድ ወገን ፍላጎትም ሊቋረጥ ይችላል። ውሳኔው ለባለቤቱ የተሰጠ ቢሆንም ሌላውን ወገን እንዳይጎዳ የተወሰነ የማስጠንቀቂያ ጊዜ እንዲኖር በሕግ ተደንግጓል፡፡ በዚህ ጽሁፍ በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 የሥራ ውል የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎችን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

በራስ ፈቃድ የሥራ ውልን ስለ ማቋረጥ

በአዋጁ በአንቀጽ 135 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በማንኛውም ጊዜ የሁለት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሥራውን በፈቃዱ ሊለቅ ይችላል፡፡ መስሪያ ቤቱ ሠራተኛውን በቀላሉ ሊተካው የሚችል ከሆነ የሁለት ወሩን ጊዜ ሳይጠብቅ ስንብቱን ሊፈቅድለት ይችላል። ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛው ለሥራው እጅግ አስፈላጊና በቀላሉ ለመተካት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ወደ ፊት ከሚቀጠርበት መስሪያ ቤት ጋር በመስማማት የመልቀቂያ ጥያቄው ሠራተኛው ካመለከተበት ቀን ጀምሮ ከአራት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ተደንግጓል። የሁለት ወር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግሎቱን ያቋረጠ የመንግሥት ሠራተኛ ግዴታውን ባለመወጣቱ ለሚደርሰው ጉዳት እንደተገቢነቱ በፍትሐብሔር እና በወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

በሕመም ምክንያት የሥራ ውልን ስለ ማቋረጥ

በአዋጁ አንቀጽ 136 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 66(2) ወይም (4) በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ማለትም የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ ቢወስድም ሕመሙ ከደረሰበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ባለው አሥራ ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከስድስት ወር ወይም በአራት ዓመት ውስጥ ከአሥራ ሁለት ወር ወይም የሙከራ ጊዜውን ያላጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሥራ ለመመለስ ካልቻለ በሕመም ምክንያት አገልግሎቱ ይቋረጣል፡፡ ሆኖም በሥራ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 84(3) መሠረት የጉዳቱ መጠን ታይቶ በህክምና ማስረጃ በሚገልፃው መሠረት ድኖ ወደ ሥራው እስከሚመለስ ወይም በጉዳቱ ምክንያት ለዘለቄታ መሥራት የማይችል መሆኑ በሕክምና ማስረጃ እስከሚረጋገጥ ድረስ የሕመም ፈቃድ ከሙሉ ደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ለዘለቄታው መሥራት ያለመቻሉ በሕክምና ማስረጃ ከተረጋገጠ ግን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 85 መሠረት የጉዳት ጡረታ አበል እና የጉዳት ዳረጎት የሚከፈለው ሆኖ አገልግሎቱ ይቋረጣል፡፡ እንዲሁም አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በጤና መታወክ ምክንያት በያዘው የሥራ መደብ ወይም ባለበት የሥራ ቦታ ላይ ሊሰራ አለመቻሉ በሕክምና ማስረጃ ሲረጋገጥ በተመሳሳይ ደረጃ ሊመደብ የሚችልበት ክፍት የሥራ መደብ ከሌለና ደረጃው ተቀንሶ ወደ ሚስማማው የሥራ መደብ ዝቅ ባለ ደረጃ ለመሥራት ፈቃደኛ ካልሆነ በአዋጁ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ (3) (ለ) መሠረት የሥራ ውሉ ይቋረጣል፡፡

በችሎታ እና ብቃት ማነስ ምክንያት ከሥራ ማሰናበት

የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር በሥራ አፈፃፀም ውጤቱ የችሎታ ማነስ ከታየበት ምክርና ተገቢው የአቅም ማጎልበት የሚሰጠው ሆኖ የመንግሥት ሠራተኛ በተመደበበት ሥራ ላይ የሥራ አፈፃፀም ውጤቱ በበጀት ዓመት ለሁለት ጊዜ ያህል ከመካከለኛ ውጤት በታች ካገኘ በአዋጁ አንቀጽ 137 መሠረት በዕቅድ አፈፃፀም የችሎታ ማነስ ምክንያት ከሥራ ይሰናበታል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ከተመደበበት ሥራ ጋር በተያያዘ በብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሂደት በስድስት ወር ለሁለት ጊዜ ያህል ተመዝኖ ከዝቅተኛ ማለፍያ ውጤት በታች ካገኘ በብቃት ማነስ ምክንያት ከሥራ ይሰናበታል። ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛውን ከሥራ ማሰናበት የሚቻለው እንደ አስፈላጊነቱ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 47 የሥራ አፈፃፀም ምዘና ዓላማ እና አንቀጽ 136 ላይ የጡረታ መብት ተጠብቆ አገልግሎትን ስለማቋረጥ የተደነገገውን በመከተል ይሆናል፡፡

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የሥራ ውልን ስለ ማቋረጥ

በፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ አንቀጽ 138 መሠረት የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በሥራ ገበታው ላይ ካልተገኘ ምክንያቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመስሪያ ቤቱ ማሳወቅ አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ሪፖርት የተደረገለት የመንግሥት መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ወይም ተወካዩ ሠራተኛው ከሥራ ገበታው ላይ የተለየበት ምክንያት ከአቅም በላይ መሆኑን ካረጋገጠ የመንግሥት ሠራተኛው ይዞት የነበረውን የሥራ መደብ ለሦስት ወር ክፍት አድርጎ መጠበቅ አለበት፡፡ ሆኖም የመንግሥት ሠራተኛው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራው ካልተመለሰ ከሥራ ማሰናበት ይቻላል፡፡

ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛው ከሦስት ወር በላይ በሥራ ላይ ያልተገኘው በእስር ምክንያት ከሆነና ከተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት በነፃ ስለመለቀቁ ማስረጃ ካቀረበ የመንግሥት መስሪያ ቤቱ ባለው ክፍት የሥራ መደብ ቀደም ሲል ይከፈለው የነበረውን ደመወዝ እያገኘ ወደ ሥራ እንዲመለስ ማድረግ አለበት፡፡ በተጨማሪም የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ ባልታወቀ ምክንያት ለተከታታይ ሰባት የሥራ ቀናት ከመደበኛ የሥራ ቦታው ላይ ከተለየ በየሰባት ቀናት ልዩነት በተከታታይ ለሁለት ጊዜ በማስታወቂያ ተጠርቶ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ካላደረገ ከሥራ ይሰናበታል፡፡ በማስታወቂያ ጥሪ የተደረገለት የመንግሥት ሠራተኛ ከሥራ ከተለየበት ቀን ጀምሮ አንድ ወር ከመሙላቱ በፊት ወደ ሥራው ለመመለስ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ካደረገ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ሠራተኛው ከሥራ የቀረበትን ምክንያት በመመርመር የሚወስደው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ሥራው እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ ከሥራ ከቀረበት ቀን ጀምሮ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከሥራ የቀረበት ምክንያት ከአቅም በላይ ለመሆኑ ለመሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ካደረገና በቂ ማስረጃ ካቀረበ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ ክፍት የሥራ መደብ ከተገኘ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ወይም ተወካዩ ሲፈቅድ ወደ ሥራ ሊመለስ ይችላል፡፡ የሙከራ ጊዜውን ያላጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ ባልታወቀ ምክንያት ለአሥራ አምስት ቀናት በሥራ ገበታው ላይ ካልተገኘ ያለተጨማሪ ሥነ-ሥርዓት የሥራ ውሉ ይቋረጣል፡፡

በሠራተኛ ቅነሳ ምክንያት ከሥራ ማሰናበት

ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የሥራ መደቡ ሲሰረዝ፣ መሥሪያ ቤቱ ሲዘጋ እና ትርፍ የሰው ኃይል ሲኖር፤ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ለመደልደል ካልተቻለ ወይም የመንግሥት ሠራተኛው ዝቅ ባለ የሥራ ደረጃ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ካልሆነ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኛው በመሥሪያ ቤት ውስጥ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ላይ ካሉ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ሲወዳደር በሥራ ውጤቱና ባለው ችሎታ ዝቅተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ በአዋጁ አንቀጽ 139 መሠረት ከሥራ ይሰናበታል፡፡

በዲስፕሊን ምክንያት ከሥራ ማሰናበት

አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 97/1/ረ መሠረት ከሥራ የመሰናበት ቅጣት ሲወሰንበት፣ ማለትም በአዋጁ አንቀጽ 98 እና 100 በከባድ የዲስፕሊን ጥፋት ተከሶ ወይም መጠነ ሰፊ የዲስፕሊን ችግር ያለበት መሥሪያ ቤት ላይ በሚወሰድ ልዩ የዲሲፕሊን እርምጃ መሠረት ከስራ እንዲሰናበት የተወሰነበትና በይግባኝ ውሳኔው ያልተሰረዘለት የመንግሥት ሠራተኛ አዋጁ በአንቀጽ 140 ላይ የስራ ውሉ ይቋረጣል፡፡ ሆኖም ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፣ ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፣ የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈፀም፣ የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፣ ከላይ የተመለከተውን ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት በማጥፋት ከስራ እንዲሰናበት በመስራቤቱ የበላይ ኃላፊ ከሥራ የመሰናበት ውሳኔ የተላለፈበት ሠራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 99(5) መሠረት በአዋጁ ወይም በሌላ ሕግ በተቋቋመ ማንኛውም አስተዳደራዊም ሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊታይ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

በዕድሜ ምክንያት አገልግሎት ስለማቋረጥ

ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 145 መሠረት አገልግሎቱ ካልተራዘመ በስተቀር በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 አንቀጽ 18(1) ሐ መሠረት 60 ዓመት ከደረሰበት የመጨረሻ ወር የመጨረሻ ቀን ጀምሮ አገልግሎቱ እንደሚቋጥ በአዋጁ በአንቀጽ 141 ላይ ተደንግገጓል፡፡ በጡረታ ለሚሰናበት የመንግሥት ሠራተኛ ጡረታ ከመውጣቱ ከሦስት ወር በፊት በጽሑፍ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

በሞት ምክንያት አገልግሎት ስለማቋረጥ

ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ከሞተበት ቀን ጀምሮ በአዋጁ አንቀጽ 142 መሠረት አገልግሎቱ ይቋረጣል፡፡ አገልግሎቱ በሞት ምክንያት የተቋረጠ የመንግሥት ሠራተኛ የሞተበት ወር ሙሉ ደመወዙ እንዲሁም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 64 ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ላልተወሰደ የዓመት እረፍት ፈቃድ የሚፈጸም ክፍያ ለትዳር ጓደኛው፣ የትዳር ጓደኛ ከሌለው ለሕጋዊ ወራሾች ይከፈላል፡፡ በተጨማሪም አግባብ ባለው የጡረታ ሕግ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሞት ምክንያት አገልግሎቱ ሲቋረጥ ለሚሠራበት መሥሪያ ቤት በጽሁፍ ላሳወቃቸው የትዳር ጓደኛው ወይም በሥሩ ይተዳደሩ ለነበሩ ቤተሰቦች የሦስት ወር ደመወዝ በአንድ ጊዜ ይከፈላል፡፡ በዚህ መሠረት የሚሰጠው ክፍያ ከግብርና ከጡረታ መዋጮ ነፃ ይሆናል፡፡ እንዲሁም በዕዳ ሊከበር ወይም በማቻቻያነት ሊያዝ አይችልም ፡፡ ሆኖም የትዳር ጓደኛውን ወይም በሥሩ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹን ሳያስመዘግብ የሞተ እንደሆነ ሥልጣን ካለው አካል ወይም ፍርድ ቤት በሚሰጥ ማስረጃ መሠረት ክፍያው የሚፈፀም ይሆናል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ፡፡