መግቢያ
የሎተሪ ጨዋታ ከጥንት ማኅበረሰብ ጀምሮ እንደመዝናኛ ወይም የእድል መሞከሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል የኖረ ነው። በተለይም በጥንታዊ ሥርዓቶች ውስጥ የነበሩ የንጉሳዊ ቤተሰቦች እንደ እጣፈንታ መወሰኛ ወይም በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደኃይል ማሳያነት ሲጠቀሙበት የኖረ (የቆየ) የጨዋታ አይነት ነው።
በአሁኑ ጊዜ የሎተሪ ንግድ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቆጥሮ ትልልቅ ዓለምዓቀፍ ተቋማት በድንበር ተሻጋሪነትም (Site-Based) ሆነው ጭምር የሚሰሩት ሆኖ ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃነትም አድጓ ይስተዋላል። በኢትዮጵያ የሎተሪ ዕጣ ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ የዋለው በ1954 ዓ.ም በቀዳማዊ አጸ ኃይለ-ሥላሴ ዘመን መንግሥት ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቅርፅ፣ በሽልማት መጠንና በአደረጃጀት እያደገ መጥቶ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ስር በሚዘጋጁት ሎተሪዎች እንኳ በአሁኑ ሰዓት እስከ 50,000,000 (ሃምሳ ሚሊዮን) የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት መጠን ያላቸው ሎተሪዎች በገበያ ላይ ይገኛሉ።
በተለይ አሁን አሁን ከቴክኖሎጂ እድገትና የዲጂታል ገበያው መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሎተሪ አጨዋወት ዘዴ በፍጥነት በመዘመን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለምሳሌም አንዳንድ ድርጅቶች ከአካላዊ ውርርድ እስከ አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ ዌብሳይት፣ መተግበሪያዎችና መሰል ዘዴዎችን በመጠቀም የሎተሪ እጣዎችን የሚሸጡበት ወይንም ውርርዶችን የሚያካሂዱበትን ሁኔታ እናስተውላለን። በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለሎተሪና ውርርዶች ምንነት፣ የሕግ መሠረት፣ የአሠራር ቅድመ ሁኔታዎችና መሠፈርቱን አሟልቶ አለመሥራት ሊያስከትል ስለሚችለው የሕግ ተጠያቂነት ተዳሷል።
ሎተሪ ምንድነው ?
ሎተሪ ቃሉ የእንግሊዝኛ ሲሆን በአገራችንም እንዳለ ተወስዶ ለቃሉ የሕግና የመዝገበ-ቃላት ፍች ተሰጥቶት እናገኛለን። ለዚህም እንደምሳሌ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሎተሪ የሚለውን ቃል “ተከታታይ ቁጥሮች የተሰጧቸው ብዙ ትኬቶች ለሰዎች ከተሸጡ በኋላ እጣ በመጣል አሸናፊ ለሆነው ቁጥር የተወሰነለትን ገንዘብ ወይም እቃ በመስጠት የሚካሄድ ተግባር ነው” የሚል ፍች ሰጥቶታል። በሌላ በኩል የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀጽ 2(1) መሠረት “ሎተሪ” ማለት የሽልማት አሸናፊው በእድል በእጣ አወጣጥ ወይም በማንኛውም ሌላ ዘዴ የሚታወቅበት ጨዋታ ወይም ድርጊት ሲሆን ቶምቦላን ወይም ራፍልን፣ ሎቶን፣ ቶቶን፣ ፈጣን ሎተሪን፣ የቁጥር ሎተሪን የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪን፣ የፕሮሞሽን ሎተሪን፣ ቢንጎን፣ የስፖርት ውርርድ ሎተሪንና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን እንደሚጨምር ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን።
በተጨማሪም ተጠቃሹ ደንብ ከመውጣቱ በፊት በስራ ላይ በነበረው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 535/1999 ስር ተካተው የነበሩ ከአስር በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የሎተሪ ዓይነቶችን ከነትርጓሜያቸው እንዲቀጥሉ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ በዚህም አሁን ላይ አንዳንዶችን በሁለት ጎራ ከፍሎ የሚያከራክረውን የስፖርት ውርርድ (ለጊዜው በአዲስ አበባ ደረጃ የተከለከለ) ጨምሮ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በመተግበሪያዎችና በዌብ ሥርዓት የሚደረጉትን እንዲሁም ወደፊት ሊጨመሩ የሚችሉ መሰል የእጣ ውርርዶችን ሊጨምር የሚችል ሰፊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በሎተሪ ሥራ ለመሰማራት መሟላት ያለባቸው ቅድመ–ሁኔታዎች
በደንቡ አንቀጽ 2(13) ስር የሎተሪ ሥራ ምንነትን አስመልክቶ የተቀመጠውን ትርጓሜ ስንመለከት፣ የሎተሪ ስራ ማለት ‘በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ማንኛውንም ሎተሪ በማዘጋጀት በአገር ውስጥ መሸጥ፣ ማከፋፈል፣ ማጫወትና ዕጣ ማውጣት ወይም ሌላ ተመሳሳይ ተግባራት ማከናወን ነው በሚል ሰፍሯል። በዚህ መሠረት ማንኛውም አካል፣ ግለሰብ ይሁን ድርጅት እነዚህን በመሰሉ የሎተሪ ሥራ ተግባራት ላይ ለመሰማራት በዚህ ደንብ አንቀጽ 12 ጀምሮ በዝርዝር የሰፈሩትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትና ማክበር እንዳለበት ተመላክቷል። ከእነዚህ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች መካከልም፣-
- የሎተሪ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተሰጠ የፀና ፈቃድ፣
- በሎተሪ ሥራ ለመሰማራት በአዋጁ በግለሰብ ወይንም ከመንግሥት ጋራ በጣምራ ሊሰራ የሚችል መሆኑን መለየት፣
- ተገቢ ክልከላዎችን ማክበር፣ (ዝቅ ብሎ እንደተመላከተው)
- ፈቃዱ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ወይም የአገሪቱን ደኅንነት የሚጎዳ የወንጀል ተግባር ላይ እንዳይውል የማድረግ ግዴታ
- እንዲሁም በወንጀል አስቀጭ ተብለው ከተዘረዘሩ ተግባራት በመቆጠብ የሎተሪ ሥራን በህጋዊ መንገድ ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በደንቡ አንቀጽ 2(5፣6፣7፣8፣9 እና 110) ስር የሰፈሩት ማለትም፣-ቶቶ፣ ፈጣን ሎተሪ፣ የቁጥር ሎተሪ፣ የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪ እና ዘመናዊ የቢንጎ ሎተሪን በአስተዳደሩ ብቻ የሚካሄዱ በመሆናቸው ምክንያት ግለሰብ ወይም የግል ድርጅት በእነዚህ የሎተሪ ተግባራት ላይ መሰማራት አይችልም። በሌላ መልኩ በአንቀጽ 2(3፣4፣19 እና 12) ስር የተካተቱት ማለትም የቶምቦላ ወይም ራፍል ሎተሪ፣ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ፣ ኮንቬንሽናል ቢንጎና የፕሮሞሽን ሎተሪ በማንኛውም ሰው ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ ሌላ በተለይ የቶቶና ፈጣን ሎተሪዎችን አስተዳደሩ አስፈላጊው ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና የእውቀት አመራር ያላቸው የግል ተሳታፊዎች ጋር በጋራ ሽርክና ሊሰራቸው የሚችሉ ስለመሆናቸው ተመላክቷል።
ከዚህ ባለፈ ደንቡ በአንቀጽ 17 ስር ውስን ክልከላዎችን ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም፣- ማንኛውም ሰው ከአስተዳደሩ የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውንም የሎተሪ ሥራ ማካሄድ አይቻልም፣ በተጨማሪም ማንኛውም ሰው የሎተሪ ሥራ ለማካሄድ የተሰጠውን ፈቃድ ያለአስተዳደሩ ስምምነት ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠት የተከለከለ ተግባር መሆኑ ተደንግጓል።
ክልከላዎችን መተላለፍና የወንጀል ተጠያቂነት
በደንቡ አንቀጽ 20 ስር ግልፅ የወንጀል ክልከላዎች የተቀመጡ ሲሆን በዚህም በወንጀል ሕጉ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ማንኛውም ሰው የፀና ፈቃድ ሳይኖረው የሎተሪ ሥራ ያካሄደ እንደሆነ ከሃምሳ እስከ መቶ ሽህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል። እንዲሁም ማንም ሰው የህንፃ ይዞታውን ለሕገ-ወጥ የሎተሪ መሸጫ እንዲውል ያከራየ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የፈቀደ ወይም በአስተዳደሩ ለቁጥጥር የተላከን ሠራተኛ እንዳይገባ የከለከለ ወይም የቁጥጥር ሥራው እንዳይካሄድ በማንኛውም መንገድ ያሰናከለ ከብር አስር ሺህ እስከ ሃያ ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እና ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት ይቀጣል።
ከእነዚህ በዝርዝር ከሰፈሩት የሚያስቀጡ ተግባራት በተጨማሪ እንደተፈፀመው ድርጊት ሁኔታ የወንጀል ሕጉ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ። በዚህም ለምሳሌ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 692 ስር አታላይነትን አስመልክቶ የሚከተለው ሰፍሯል፣-
ማንም ሰው የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር፣ ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም ፣ በማድረግ ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው አታሎ የራሱን ወይም የሦስተኛ ወገን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ አድራጎት እንዲፈፀም ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
በመጨረሻም ምንም እንኳ በዚህ ጽሑፍ የተሸፈነውን አዋጅ ቁጥር 535/1999 በግልፅ ባይሽረውም በ2001 ዓ.ም በይዘት ከአዋጁ ብዙም ያልተለየ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ደንብ ቁጥር 160/2001 በሥራ ላይ ይገኛል። ደንቡ በአዋጁ ከተካተቱት የወንጀል ቅጣቶች በተጨማሪ ዝርዝር አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ያካተተ ሲሆን በተለይም በሐሰተኛና በተጭበረበረ ማስረጃ የተገኘ ፈቃድ ሲሆን፣ ፈቃዱ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ወይም የአገሪቱን ደኅንነት የሚጎዳ የወንጀል ተግባር ሲሰራበት፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ (በየበጀት አመቱ) ያላሳደሰ እንደሆነ እንደሁኔታው ከማገድ እስከ ፈቃድ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ይችላል።
ማጠቃለያ
የሎተሪ ጨዋታ ራሱን የቻለ በእድል ጨዋታ የተመሰረተ የስራ ዘርፍ (Gaming Profession) ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አሁን በሥራ ላይ ባለው የንግድ ሕግ በተለይም አንቀጽ 5 ስር እንደተመላከተው ነጋዴ ሊባሉ የሚችሉ ስላልሆኑ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ማድረግ አይጠበቅባቸውም። በአንፃሩ ከፍ ብሎ እንደተብራራው በሎተሪ ሥራ ውስጥ የሚሰማራ ማንኛውም ሰው ግንኙነቱ የሚመራው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 እና እሱን ተከትለው በሚወጡ መመሪያዎች መሠረት ሆኖ ግንኙነቱም በዚሁ ደንብ ከተቋቋመው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ይሆናል።
ሌላው በዚህ ጽሑፍ ሽፋን የተሰጠው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም የወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 ሲሆን ነገር ግን ደንቡ በተለይ በአንቀጽ 20 ላይ የደነገጋቸው የወንጀል ቅጣቶች ከደንቡ በፊት በሥራ ላይ ከነበረው አዋጅ 535/1999 በቀጥታ የመጡ እንደሆኑና በኢ/ፌ/ዲ/ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(5) በሰፈረው መሠረት የወንጀል ሕግ የሚወጣው በፌደራሉ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ብቻ በመሆኑ የወንጀል ቅጣት የያዘው የአዋጁ ድንጋጌ ያልተሻረ ስለመሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ፡፡