የወንጀል ቅጣት በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ወንጀል የማኅበረሰብን ብሎም የአገርን ሰላምና ደኅንነት የሚጎዳ በመሆኑ በወንጀል ሕግ የተመለከቱ የወንጀል ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ወንጀል የሚፈፅም ሰው ለጥፋቱ በሕጉ የተመለከተውን ቅጣት መቀጣቱ የግድ ነው፡፡ በአገራችንም ወንጀሎችን ከነቅጣታቸው የሚደነግግ የወንጀል ሕግ እና ሌሎች ልዩ አዋጆች በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የቅጣት ዓላማ፣ በወንጀል ሕጉ የተመለከቱ የወንጀል ቅጣት ዓይነቶችን፣ የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶችን በአጭሩ የምንመለከት ይሆናል፡፡

  የቅጣት ዓላማ

አሁን ባለንበት ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት የቅጣት  ዓላማ ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ለቀጣይ ከወንጀል ተቆጥበው መልካም ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ እና ወንጀል የተፈፀመባቸው ሰዎች ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህ እሳቤ በአገራችን በ1996 ዓ/ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ሥር በግልፅ ሰፍሮ የሚገኝ ነው፡፡ ይኸውም የወንጀል ሕጉ ቅጣት የሚጥልበት ምክንያት ሕጉን ጥሰው ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎችን በመቅጣት ሌላ ወይም ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈፅሙ ለመከላከል፣ ለወደፊት እንዲታረሙ ለማድረግ እና ሌሎችም ከዚህ ተምረው ወንጀል እንዳይፈፅሙ ለማስተማር ነው፡፡

  የቅጣት ዓይነቶች 

ለአዋቂ የሚጣሉ ቅጣቶችን በተመለከተ የወንጀል ሕጉ በዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት እና ለአዋቂ የሚሰጡ የጥንቃቄ እርምጃዎች በሚል ከፋፍሎ አስቀምጧል፡፡ ዋና ቅጣቶች እንደ ስማቸው በዋናነት በወንጀል ፈፃሚዎች ላይ የሚጣሉ መደበኛ የቅጣት ዓይነቶች ሲሆኑ የሚከተሉትን ያካትታል፡፡

የገንዘብ መቀጮ፣ የንብረት ማገድ እና መውረስ

መቀጮ በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ሰው ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ነው፡፡ መጠኑን በተመለከተ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በቀር በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90 መሠረት ከብር 10 (አስር) እስከ ብር 10,000 (አስር ሺ) የሚደርስ ሲሆን ጥፋተኛ የተባለው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ ከብር 100 (አንድ መቶ) እስከ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺ) ይደርሳል፡፡ ይህ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተጠቀሰው የገንዘብ መቀጮ ጣሪያ በሌሎች የወንጀል ቅጣት በሚደነግጉ ሕጎች (ለምሳሌ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ) ከፍ ሊል እንደሚችል መገንዘብ ይገባል።

በሕጉ ልዩ ክፍል የእሥራት ቅጣት ብቻ በተደነገገ ጊዜና ተቀጪው የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት በሆነ ጊዜ እስከ 5 ዓመት ቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር አስር ሺ፣ እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር ሀያ ሺ፣ እስከ አስር ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር ሀምሳ ሺ እና ከአስር ዓመት ፅኑ እስራት በላይ ለሚያስቀጣ የወንጀል ዓይነት እሰከ አምስት መቶ ሺ ብር ለመድረስ በሚችል መቀጮ ይቀጣል።

ፍርድ ቤት የመቀጮውን ልክ ሲወስን የወንጀሉን ክብደት፣ የአደጋኛነቱን መጠን፣ የሀብቱን ሁኔታ፣ የገቢ ምንጩን፣ ስለቤተሰቦቹ አስተዳደር ያለበትን ሸክም፣ የሙያ ሥራውንና ከሥራው የሚያገኘውን የገቢ መጠን፣ ዕድሜውንና የጤንነቱን ሁኔታ በማመዛዘን መሆን ይገባል።  

በሌላ በኩል ንብረት ማገድና መውረስ ሕጉ በግልፅ በደነገገ ጊዜ ወንጀለኛው ጥፋተኛ በተባለበት ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኘውም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ያገኘው ንብረት የሚወረስበት የቅጣት ዓይነት እንደሆነ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 98 መረዳት ይቻላል፡፡

የግዴታ ሥራ እና ነጻነትን የሚያሳጡ (የእሥራት) ቅጣቶች

የግዴታ ሥራ የተፈፀመው ወንጀል ቀላል ሆኖ የሚያስቀጣው ጊዜ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት በሆነ ጊዜ ወንጀለኛው መሥራት የሚችልና ለሕብረተሰቡ አደገኛ አለመሆኑ ታይቶ ነፃነቱ ሳይገደብ ቁጥጥር እየተደረገበት የግዴታ ሥራ እንዲሰራ የሚደረግበት የቅጣት ዓይነት ነው (አንቀጽ 103(1))፡፡

በሌላ በኩል እሥራት ነጻነትን ከሚያሳጡ ቅጣቶች ዋነኛው ሲሆን በወንጀል ሕጉ መሠረትም ቀላል ወይም ፅኑ እሥስራት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንቀጽ 106 መሠረት ቀላል እስራት ወንጀሉ መካለኛ ሆኖ ጥፋተኛው ለሕብረተሰቡ እጅግ አደገኛ መስሎ ባልታየ ጊዜ የሚጣል ቅጣት ነው፡፡ ይህም  በመርህ ደረጃ ከአስር ቀን ጀምሮ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ሲሆን ነገር ግን ከወንጀሉ ከባድነት የተነሳ በሕጉ ልዩ ክፍል ተደንግጎ ሲገኝ ወይም በቀላል እሥራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩ ወይም ወንጀለኛው በተደጋጋሚ ሲቀጣ የቀላል እሥራቱ ጣሪያ እስከ አምስት ዓመት (5 ዓመት) ሊደርስ ይችላል፡፡

በአንፃሩ ፅኑ እሥራት የሚወሰነው ከባድ ወንጀል ባደረጉና በተለይም ለሕብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ እንደሆነ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 108 መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም  ከአንድ ዓመት (1 ዓመት) እስከ ሀያ አምስት ዓመት (25 ዓመት) ወይም እንደወንጀሉ ክብደት በሕጉ ተገልፆ የተደነገገ ሲሆን እስከ እድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ሊደርስ ይችላል፡፡ የፅኑ እሥራት ግቡ ተቀጪው እንዲታረምና ወደ ማኅበራዊ ኑሮ እንዲመለስ ከማድረግ በተጨማሪ በተለይ ለሕብረተሰቡ ደኅንነት በጥብቅ ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ለማድረግ ነው።

የሞት ቅጣት

የሞት ቅጣት የሚጣለው እጅግ ከባድ ለሆኑ ወንጀሎች ሲሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 117(1) መሠረት የሞት ቅጣት የሚወሰነው፡-

  • ወንጀሉ በጣም ከባድ በመሆኑና ወንጀለኛው በተለይ አደገኛ በመሆኑ ለወንጀሉ ቅጣት እንዲሆን በሕጉ ልዩ ክፍል በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ፣
  • ወንጀሉ ፍፃሜ ያገኘ ማለትም በሙከራ ደረጃ ላይ ያልተገታ እንደሆነ፣
  • ቅጣቱን የሚያቀልለት ምንም ዓይነት ማቅለያ ምክንያት የሌለ እንደሆነ፣
  • አጥፊው ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ እድሜው 18 የሞላዉ ከሆነ ነው፡፡

   ተጨማሪ ቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃዎቸ

ተጨማሪ ቅጣቶች ከዋና ቅጣት ጋር ተደርበው በወንጀል ፈፃሚ ላይ የሚጣሉ ናቸው፡፡ ተጨማሪ ቅጣት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 121 እና ተከታዮቹ መሠረት የሚፈፀም ሲሆን ለአብነት ከመብት መሻር ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በአዋቂ ላይ የሚደረጉ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ደግሞ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 130 እና ተከታዮቹ መሠረት በተወሰነ ቦታ እንዲቀመጥና እንዲታከም ማድረግ እና የመሳሰሉ የእርምት እርምጃዎችን የሚያካትት ነው፡፡

   የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች

ቅጣትን የሚያከብዱ ምክንያቶች ጠቅላላ እና ልዩ ተብለው የተለዩ ሲሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84 እና 85 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ ጠቅላላ የወንጀል ማክበጃ ምክንያቶች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84/1/ከ (ሀ) እስከ (ሠ) የተመለከቱ ሲሆን የወንጀሉ አፈፃፀም፣ የወንጀለኛው የቀደመ የወንጀል ታሪክ፣ ወንጀል የተፈፀመበት ሰው ሁኔታ እና ሌሎች በድንጋጌው በዝርዝር የተቀመጡ ምክንያቶችን ያካትታል፡፡ ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች ደግሞ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 85 ሥር የተመለከቱ ሲሆን የወንጀሎች መደራረብ እና ደጋጋሚነት ሲኖር በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 184 እና 188 ቅጣት የሚከብድበት ነው፡፡

   የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች

እንደ ቅጣት ማክበጃ ሁሉ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችም ጠቅላላ እና ልዩ ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 82/1 ከ(ሀ) እስከ (ሠ) ባለው ስር የተዘረዘሩ ሲሆን የወንጀለኛው የቀደም የባህሪ መልካምነት፣ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ያሳየው መፀፀትና ለመታረም ዝግጁ መሆን፣ የወንጀል ተጎጂው ወንጀሉ እንዲፈፀም በወንጀል ፈፃሚው ላይ ያደረሰው ፈተና ወዘተ የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ዝምድና እና የጠበቀ ወዳጅነት በመኖሩ ምክንያት ወንጀል የፈፀመ ዘመዱን ወይም ጥብቅ ወዳጁን ለቅጣት ለውርድት፣ ለከባድ አደጋ ላለማጋለጥ ብሎ ወንጀልን ሳያሳውቅ ለቀረ፣ ሀሰተኛ መረጃ ለሰጠ እና መሰል ድርጊቶች ለፈፀመ ሰው የተፈጸመው ወንጀልና የደረሰው ጉዳት አነስተኛ እንዲሁም የነበረበትን የሞራል ተፅዕኖ በመረዳት በልዩ ሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆን እንደሆነ ከአንቀጽ 83 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ 

   ማጠቃለያ

በሀገራችን የወንጀል ሕግ መሠረት በአዋቂ ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ከላይ የተገለፁት ሲሆኑ ቅጣት ግላዊ ባህሪ ያለው በመሆኑ አድራጊዎች እድሜ፣ የወንጀሉ ክብደትና አፈፃፀም፣ የትምህርት ደረጃ እና የመሳሰሉት እንዲሁም የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ምክንያቶች ቅጣት በሚወሰንበት ጊዜ ግምት ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡

                    በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ፡፡