መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ያሏቸው መብቶችና ነፃነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶችና ነፃነቶች በዓለም ዓቀፍ እና ብሔራዊ ህጎች እውቅናና ጥበቃ የሚደረግላቸው ሲሆን በዚህ ፅሑፍ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው፣ ክስ የቀረበበት ሰው እንዲሁም ቅጣት ተወስኖበት በፍርድ የታሰረ ሰው ያለውንና ሊጠበቁለት የሚገቡትን መብቶች በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የተያዙ ሰዎች መብት
ማንም ሰው ነፃነቱ የተጠበቀ ሲሆን አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ የሚያዘው ወይም የነጻነት መብቱ የሚገደበው ወንጀል መፈፀሙን የሚያመለክት ማስረጃ ሲኖርና በሕግ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ሲሟላ ነው፡፡ በሕግ አግባብ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረና የተያዘ ሰው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግሥት እና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ በግልጽ የተቀመጡ እና ሊከበሩለት የሚገቡ መብቶች አሉት፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 19 መሠረት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተያዙ ሰዎች የተለያዩ መብቶች እንዳሏቸው ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የቀረበባቸውን ክስና ምክንያቶቹን በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ የመነገር መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም የተያዙ ሰዎች ያለመናገር መብት ያላቸው ሲሆን የሚሰጡት ቃልም በፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው፡፡ ይህ ማለት በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡
ሌላው የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ባይቀርቡ ወይም የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜ ገደቡ ፍርድ ቤት አቅርቦ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ የተያዙ ሰዎች የአካል ነፃነታቸውን (Habeas Corpus) እንዲያስከብርላቸው ለፍርድ ቤት የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ይህ የ48 ሰዓት ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ በተጨማሪም በህጉ በልዩ ሁኔታ በዋስትና መፈታት ካልተከለከለ በስተቀር የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በትኩረት መታየት ያለበት ጉዳይ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከራሱ ወይም ከሌላ ሶስተኛ ወገን መረጃ ለማግኘት ወይም እንዲናዘዙ ለማድረግ በአንድ ሰው ላይ ሆነ ብሎ የአካል ወይም የአእምሮ ስቃይ የሚያደርስ ድርጊት መፈፀም፣ እራሱ ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን ለፈፀመው ወይም ፈፅሟል ተብሎ የተጠረጠረበትን ድርጊት እንዲያምን ለማድረግ በማሰቃየት የሚፈፀም ማንኛውም ድርጊት የተከለከለ ነው፡፡ በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መሠረት በምንም አይነት ሁኔታ ማለትም የጦርነት ወይም የጦርነት ስጋት መኖር፣ የውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ለማስወገድ ወይም ሌላ የሕዝብ ደኅንነት እና ፀጥታ ለመጠበቅ በሚወሰድ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ ወቅት እንኳን ይህን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ መፈፀም የማይቻል ሲሆን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 93/4/ሐ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ክልከላ እንደማይሻር ተቀምጧል፡፡
የተከሰሱ ሰዎች መብት
የተከሰሱ ሰዎች በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20 ሥር የሚከተሉት መብቶች እንዳሏቸው ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የመቅረብ እና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት (የተከራካሪዎችን የግል ህይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እና የሀገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ሊታይ ይችላል)፣ በፍርድ ሂደት በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ በራሳቸው ጉዳይ በምስክርነት እንዲቀርቡ ያለመገደድ፣ የቀረበባቸውን ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ (የማስቀረብ) እና ምስክሮች እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ በተጨማሪም የተከሰሱ ሰዎች በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል (አቅም የሌላቸው እንደሆነ እና ይህም ፍትሕን የሚያጓድል ሲሆን ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው)፣ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ፣ ክርክሩ በማይረዱት ቋንቋ በሚካሄድበት ጊዜ በመንግሥት ወጪ እንዲተረጎምላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ተመልክቷል።
በወንጀል ተከሰው የሚቀርቡ ግለሰቦች ክርክራቸውን የሚያደርጉት ከመንግሥት ጋር በመሆኑ ሚዛናዊ የክርክር ሂደትን ለማስጠበቅ በህገ-መንግስቱ እና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ለተከሰሱ ሰዎች የተደነገጉ መብቶች በፍትሕ አካላት ማለትም በፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ እና ፍርድ ቤቶች በጥንቃቄ ሊተገበሩ ወይም ሊከበሩ የሚገቡ ናቸው፡፡
በጥበቃ ስር ያሉ እና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት
በፍርድ የታሰሩ ሰዎች (በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች) ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው እና ሰብዓዊ ክብር የተሞላ እንክብካቤ እና አያያዝ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 21 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት በቂና የተመጣጠነ ምግብ፣ የውሃና ንፅህና እንዲሁም የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በተጨማሪም ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሀይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሃኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና እንዲጎበኟቸው እድል የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
ማጠቃለያ
የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱ እና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች በሀገራችን እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች ያሏቸው ሲሆን ማንኛውም ሕግ አስከባሪ አካል እነዚህን መብቶች አውቆ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ እነዚህን መብቶች መጣስ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ