የወንዝ ዳር ልማትና የአከባቢ ጥበቃ የህግ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከታደለችው ሰፊና ብዙ አይነት መልካአምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ የተነሳ የተለያዩ እንስሳት እንዲሰፍሩባት፣የተለያዩ እፅዋት እንዲበቅሉባት የሚያስችል ሥርዓተ-ምኅዳር ባለቤት ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከከተሞች መስፋፋት፣ ከሕዝብ ብዛት መጨመር እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች ከሚከሰቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጋር በተያያዘ በተለያዩ መንገዶች ተጠብቀው በቆዩ ለአካባቢያዊ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባላቸው የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። ከእነዚህ ለጉዳት ከተጋለጡ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ደግሞ የውሃ ሀብት ተጠቃሽ ነው። መንግሥት እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ የውሃ፣ የአፈር እና የደን ሀብትን የመጠበቅና የአየር ንብረት እንዳይዛባ የማድረግ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ሰፋፊ እና የሀገሪቱን ዜጎች በነቂስ የሚያሳትፉ መጠነ ሰፊ ተግባሮችን እንደ አንድ ዋነኛ የሀገሪቱ አጀንዳ ይዞ ለአፈፃፀሙ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። ይሄም ለጉዳዩ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው። ከዚህም ባሻገር በቅርብ ጊዜያት በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ የመልካም አስተዳደርና የከተማ ገጽታ ማሻሻያ አካል ሆነው ብቅ ብለዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከውበት እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር ከሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ህጎች ጋር በእጅጉ የሚጣጣሙ ናቸው። ይህ ጽሁፍ የሀገራችንን የአካባቢ ጥበቃ የሕግ ማዕቀፎች በጠቅላላው፣ የወንዝ ዳር የኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ሕግ ተፈፃሚነት የሚያበረክተውን አዎንታዊ ተፅዕኖ እና የወንዞች ዳርቻ ብክለት የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2016 እና ሌሎች ህጎች አንፃር ይዳስሳል።

የአካባቢ ጥበቃ የሕግ ማዕቀፎች በጠቅላላው

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 545/2016 አንቀጽ 2(2) መሠረት “የአካባቢ ጥበቃ ” ማለት የሰው ልጅን ጨምሮ የማንኛውም አካል ሕይወት እና እድገት የሚወስኑ የመሬት፣ የውሃ፣ የአየር፣ የአየር ንብረት ሥርዓት የመሳሰሉት ሌሎች የአካባቢ ሀብቶች፣ ክስተቶችና ሁኔታዎች በመጠበቅ የአሁኑን ትውልድ ፍላጎት የማርካቱ ሂደት የመጪውን ትውልድ ዕድል ሳያሰናክል እንዲሟላ ማስቻል ነው። ከዚህ ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው የአሁኑ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም የመጪውን ትውልድ በተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ዕሳቤ መተግበር የሚረዱ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች በተግባር ላይ ውለዋል።

የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ አንፃር ሀገራችን የተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ህጎችን በማውጣት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማፅደቅ ወደ ትግበራ ገብታለች። በዚህ ረገድ ከተዘጋጁት የሕግ ማዕቀፎች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መቋቋሚያ አዋጅ፣ የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር፣ የአከባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ፣ የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ቁጥጥር አዋጅ፣ የደን ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም አዋጅ፣ በቅርቡ የፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017፣ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀት መጠን መቀነስን የሚመለከተው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ማፅደቂያ አዋጅ፣ የአደገኛ ዝቃጮች ድንበር ዘለል ዝውውርንና አወጋገድን ለመቆጣጠር የወጣው የባዜል ኮንቬንሽን ማፅደቂያ አዋጅ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2016፣ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ እና መሰል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከአካባቢ ጥበቃ ረገድ ሚና ያላቸውን የሕግ ማዕቀፎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

በ1995 የወጣው የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህገ-መንግሥት ለአካባቢ ደኅንነት እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን በአንቀጽ 44 (1) ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው እንዲሁም በአንቀጽ 92 መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢውን ደኅንነት ያገናዘበ እንዲሆን እና የሕዝብን የአካባቢ ደኅንነት የሚመለከት ፖሊሲ እና ፕሮግራም በሚነደፍበት እና ስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በህገ-መንግስቱ ተቀምጧል፡፡

ሌላኛው ከአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የሚነሳው አዋጅ ቁጥር 300/1995 ሲሆን ከጠቅላላው የአዋጁ ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው በአካባቢ ወይም በሰው ደኅንነት ወይም ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ በካይ ነገሮችን ወደ አካባቢ መልቀቅን ይከለክላል። በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጁ መሠረት ማንኛውም ሰው የአካባቢ ግምገማ ተጽዕኖ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም ከሚመለከተው የክልል አካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ይሁንታ ሳያገኝ መከናወን እንደሌለበት፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት በፕሮጀክቱ ባለቤት ወጪ መከናወን እንዳለበት እና ባለስልጣኑም ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

የወንዝ ዳር የኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ህጎች ሊያበረክት የሚችላቸው በጎ ተፅዕኖች

የአከባቢ ብክለት ቁጥጥር ህጎችን ዓላማ ያሳካል

ከአከባቢ ብክለት ቁጥጥር ጋር በተገናኘ በተለያየ መልኩ ከወጡ ህጎች ለአብነት ያህል የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 300/1995 ብንመለከት የቆሻሻ አወጋገድን፤ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓቶችን እና የውሃ አካላትን ብክለት መቆጣጠርን አስመልክቶ ግልጽ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። የኮሪደር ልማቱ ከወንዙ ዳር የሚገኙ ቤቶችንና ድርጅቶችን ከህጋዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት ጋር በማገናኘት እንዲሁም የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ማስወገጃ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የአዋጁን ዓላማዎች በተግባር እንዲውሉ ያደርጋል። የወንዞች ንፅህና ሲጠበቅ የመጠጥ ውሃ ምንጮች ጥራት ይጠበቃል፣ የውሃ ወለድ በሽታዎች ስርጭት ይቀንሳል እንዲሁም ለሰው ልጆችም ሆነ ለእንስሳት ጤናማ የመኖሪያ አካባቢ ይፈጠራል።

የህገ-ወጥ ቆሻሻ አወጋገድን ማስቀረት

የኮሪደር ልማቱ የውሃ ዳርቻዎችን ለአገልግሎት ክፍት ሲያደርግና የሕዝብ ክትትል ሲኖርበት ሰዎች ቆሻሻን ወደ ወንዝ የመድፋት ልምዳቸው ይቀንሳል። ይህ ደግሞ እንደ ደንብ ቁጥር 180/2016 በመሳሰሉ የሕግ ማዕቀፎች በሕግ የተከለከለውን የውሃ ብክለት በተግባር እንዲወገድ ያግዛል።

የዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ድጋፍ

የወንዝ ዳር ኮሪደር ልማት የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚያስችሉ እፅዋትን በመትከል፣ የግንባታ መዋቅሮችን በማበጀት እና የውሃ ፍሰትን በማስተካከል ይረዳል። ይህ በረጅም ጊዜ ለአፈርና ውሃ ሀብት ዘላቂ አስተዳደር ወሳኝ ነው። የአፈር መሸርሸርን መቆጣጠር የመሬት ጥራት እንዲጠበቅ ከማድረጉም በላይ፣ የወንዙን የውሃ ፍሰት መደበኛነት እንዲያገኝ ያግዛል ይህም የመሬት ይዞታ ህጎችን በተዘዋዋሪ ይደግፋል።

በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የሕዝብ ተሳትፎን ማሳደግ

የአካባቢ ተፅዕኖ ምዘና ሕግ ህዝቡ በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ በሚያሳድሩ ፕሮጀክቶች ላይ ሃሳቡን የመስጠት መብት እንዳለው ይደነግጋል። የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ ለሕዝብ ክፍት በመሆኑ፣ ሰዎች የወንዞችን ውበትና ሥነ-ምህዳራዊ ፋይዳ በአካል እንዲያዩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያዳብራል።

የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2016

የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀጽ 94 መሠረት አድርጎ ነው። የደንቡ ተፈፃሚነትም በአስተዳደሩ አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ በሚገኙ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች እና በወንዝና በወንዝ ዳርቻ እና በአካባቢው ደኅንነት ላይ ብክለትና አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በሚያስከትል ማንኛውም ሰው ላይ እንደሆነ በደንቡ አንቀጽ 3 ስር ሰፍሯል።

ደንቡ “የወንዝ ዳርቻ” ማለት ለወንዝ ዳርቻ መጠበቂያ ቢያንስ ከወንዙ ጠርዝ ግራና ቀኝ ዝቅተኛው 30 ሜትር ሆኖ እንደአካባቢው ሁኔታ አስተዳደሩ በሚወስነው መሠረት ስፋቱ ሊጨምር የሚችል ሲሆን ለማንኛውም ዓይነት ግንባታ ወይም አገልግሎት እንዲውል የማይፈቀድ ቦታ እና በወንዙ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሥፍራን እንደሚያጠቃልል ይደነግጋል። በደንቡ ትርጉም ከተሰጠባቸው ቃላት መካከል “የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር ልማት” የሚለው የሚገኝበት ሲሆን ትርጉሙም ከወንዙ ተፋሰስ መነሻ ጀምሮ የሥነ-ምህዳር ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ መዝናኛ ቦታዎችን እና ተያያዥ አገልግሎቶችን ከወንዙ ኩታ-ገጠም የሆኑ አካባቢዎች ማልማት ሆኖ ወሰኑና የመሬት አጠቃቀሙ በጥናት የሚወሰን መሆኑን ደንግጓል።

የተከለከሉ ተግባራት እና የሚያስከትሉት አስተዳደራዊ ቅጣት

በደንቡ አንቀጽ 7 መሠረት ወንዝና በወንዝ ዳርቻ ላይ የሚከተሉትን ተግባራት መፈጸም የተከለከለ ነው ፡-

  • ከጤና ተቋማት፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከነዳጅ ማደያ፣ ከጋራዦች እና ከመኪና ማጠቢያዎች የሚወጡ የተለያዩ በካይ ኬሚካል ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በወንዝና ወንዙ ዳርቻ ላይ ማከማቸት ወይም መጣል ወይም መልቀቅ ሲሆን ይሄን ተላልፎ የተገኘ ሰው 400 ሺህ ብር ይቀጣል።
  • ከመኖሪያ ቤት፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና አምራች ድርጅቶች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች፣ የጠርሙስ ስብርባሪ፣ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ጣሳዎች፣ ፕላስቲክና የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ ያገለገሉ የተሸከርካሪ ጎማዎች፣ የሞተ እንስሳት አካል፤ በድን፤ አጥንት፤ ጸጉር፤ ቆዳ፤ የግንባታና የህንፃ ፍርስራሾች፣ ደረቅ ቆሻሻ እና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸው በካዮች ወደ ወንዝና በወንዝ ዳርቻ መድፋት ወይም መጣል የተከለከለ ሲሆን ይሄን ተላልፎ በተገኘ ግለሰብ ላይ 20,000 ብር፣ የተላለፈው ድርጅት በሚሆን ጊዜ 100,000 ብር ያስቀጣል።
  • ከመኖሪያ ቤት የሽንት ቤት ወይም ማንኛውም ያልተጣራ ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ ወይም መስመሩን አገናኝቶ ወንዙን መበከል ክልክል ሲሆን ይሄንን የተላለፈ ግለሰብ ላይ 150 ሺህ ብር፣ ድርጅት ሲሆን 300 ሺህ ብር ያስቀጣል።
  • ማንኛውንም ሰው ፈቃድ ሳይሰጠው የታከመ ፍሳሽን ወደ ወንዝ መልቀቅ የተከለከለ ሲሆን ይሄንን በሚተላለፉ ግለሰቦች ላይ 15 ሺህ ብር፣ እንዲሁም ድርጅቶች ደግሞ 40 ሺህ ብር ያስቀጣል።
  • ፍሳሽን ወደ ወንዝ ለመልቀቅ ፈቃድ ተሰጥቶት ቁጥጥር ሲደረግ የፍሳሽ የጥራት ደረጃዎች ሳያሟላ እና የተከለከሉ ይዘቶች የያዙ ፍሳሾች መልቀቅ፤ መልቀቅ የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ እንደየሁኔታው ከ20ሺ ብር እስከ 400 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት ይጣላል።
  • ማንኛውም በካይ ፍሳሽ ከተፈቀደው የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ወይም የፍሳሽ መስመሩን ወደ ወንዝ ወይም የፍሳሽ መስመሩን ከጎርፍ መውረጃ ቦይ ጋር በማገናኘት ወደ ወንዝና ወንዝ ዳርቻ እንዲፈስ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፈው የሚገኙ ግለሰቦች 50 ሺህ ብር፣ ድርጅቶች ደግሞ 400 ሺህ ብር ይቀጣሉ።
  • ኬሚካል ነክ ፍሳሾችን ተገቢውን የማከሚያ ዘዴ ሳይጠቀሙና ባለሥልጣኑ ወይም አግባብ ያለው አካል ሳያረጋግጥ ወደ ወንዝና ወንዝ ዳርቻ መድፋት ወይም መልቀቅ የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፈው የሚገኙ ግለሰቦች 50ሺ ብር፣ ድርጅቶች ደግሞ 300 ሺህ ብር ይቀጣሉ።
  • ከአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማንኛውንም ያልታከመ ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ በመልቀቅ ወይም መስመሩን በማገናኘት መበከል የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፎ የተገኘ 300 ሺህ ብር ይቀጣል።
  • የሽንት ቤት ፍሳሽ የማስወገድ ፈቃድ ወስዶም ሆነ ፈቃድ ሳይወስድ የሚሰራ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በሚያስወግድበት ጊዜ ቀጥታ ወደ ወንዝ መድፋት ወይም መቀላቀል የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፎ የተገኘ 1 ሚሊዮን ብር ይቀጣል።
  • በባህሪው አደገኛነት ያለው ደረቅም ሆነ ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መጣል ወይም እንዲጣል በማድረግ መበከል የተከለከለ ሲሆን ይሄንን ተላልፈው የሚገኙ ግለሰቦች 500 ሺህ ብር፣ ድርጅቶች ደግሞ 1 ሚሊዮን ብር ይቀጣሉ።
  • በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ መፀዳዳት ክልክል ሲሆን ተላልፎ የተገኘ በ2 ሺህ ብር ይቀጣል።
  • የፍሳሽ ማጣሪያ ሳይኖረው በወንዝ ዳርቻ እና አካባቢ ላይ የተሽከርካሪ እጥበት ማከናወን የተከለከለ ሲሆን ይህንን የተላለፈ በ400 ሺህ ብር ይቀጣል።
  • በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ እንስሳት ማሰማራት ወይም እንዲገቡ ማድረግ ወይም ከተፈቀደ መግቢያና መውጫ ውጭ ተሽከርካሪ ማሽከርከር የተከለከለ ሲሆን ይህንን ተላለፎ የተገኘ በ30 ሺህ ብር ይቀጣል።
  • በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ውስጥ ከተፈቀደው የመዝናኛ፣ መናፈሻና፣ ፓርክ እና ሌሎች ለወንዝ ዳርቻው ልማት አስፈላጊ ከሆነ ግንባታ ውጪ የፕላስቲክ ቤት ወይም ማንኛውም ዓይነት ግንባታ መገንባት የተከለከ ሲሆን ይህንኑ መተላለፍ በ200 ሺህ ብር ያስቀጣል።

አስተዳደራዊ ቅጣት የተጣለበት ማንኛውም ሰው የተሰጠውን አስተዳደራዊ ቅጣት ማስታወቂያ ወረቀት በመያዝ ወዲያውኑ ጥፋቱ በተፈፀመበት አካባቢ በሚገኘው የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ቀርቦ ወይም በኤሌክትሮኒክስ መክፈያ ዘዴ በሦስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣቱን ገቢ በማድረግ ቅጣቱን መፈጸም የሚኖርበት ሲሆን ቅጣቱ በተጠቀሰው ጊዜ ያልተከፈለ እንደሆነ የቅጣት መጠኑ እጥፍ ይሆናል (አንቀጽ 17(4) እና (7)።

ሌላው በወንጀል ሕግ እና በሌሎች ሕጎች የተመለከተው ቅጣት እንደተጠበቀ ሆኖ እንደአግባብነቱ ባለሥልጣኑ ወይም የከተማው አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ይህንን ደንብ በተላለፈ ማንኛውንም ሰው ላይ እንደ ጥፋቱ ሁኔታ ድርጊቱን የማስቆም፣ የማዘጋት፣ የማሸግ፣ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ የማድረግ፣ የንግድ ሥራ ፈቃድ ወይም የግንባታ ፈቃድ እንዲሰረዝ የማድረግ፣ የውሃ አቅርቦት እንዲቋረጥ ሥልጣን ላላቸው ተቋማት በጽሁፍ የማሳወቅ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል (አንቀጽ 17(1)(ሀ)።

በደንቡ አንቀጽ 18 መሠረት ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ክልከላዎች በመተላለፍ አስተዳደራዊ ቅጣት የተወሰነበትን ቅጣት ከፈጸመበት ቀን ጀምሮ በድጋሚ ተመሳሳይ ጥፋት የፈፀመ ማንኛውም ሰው ከፍ ሲል የተጠቀሰውን የቅጣት መጠን በእጥፍ ይከፍላል። ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ክልከላዎች የሚተላለፉ ሰዎች በሚያጋጥሙ ጊዜ ማንኛውም ሰው የወንዝ ወይም በወንዝ ዳርቻ ብክለት አድርሷል ወይም ሊደርስ ይችላል የሚል ጥቆማ ወይም አቤቱታ ለከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በአካል በማቅረብ፣ በጽሁፍ፣ በስልክ እንዲሁም በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎች ማቅረብ የሚችል መሆኑ በደንቡ አንቀጽ 15 ስር ተገልጿል።

የወንጀል ተጠያቂነት

ከፍ ሲል የተጠቀሰው ደንብ በአዲስ አበባ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ለሚከሰቱ ብክለቶች የተቀመጠውን የአስተዳደራዊ ቅጣት ሁኔታ የሚያመለክት ሲሆን፤ ነገር ግን ወንዞችን መበከል ከሚያስከትለው አስተዳደራዊ ቅጣት ባሻገር የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ የሕግ ማዕቀፎች አንዱ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995 ነው። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 16 መሠረት አንድ ሰው አዋጁን ወይም በስሩ የሚወጡ ደንቦችን በመተላለፍ በካይን ወደ አካባቢ(የውሃ አካላትን ጨምሮ) በመልቀቅ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ከ1 ሺህ ብር በማያንስ እና ከ5 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከ1 ዓመት በማያንስና ከ10 ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።

ጥፋቱን የፈፀመው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ከሆነ ከ5 ሺህ ብር በማያንስና ከ25 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን የስራ ኃላፊውም ከ5 ዓመት በማያንስና ከ10ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም ከ5 ሺህ ብር በማያንስና ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል። በሌላ በኩል የወንጀል ህጉን አንቀጽ 517 የተመለከትን እንደሆነ ማንም ሰው አስቦ ለሰው ወይም ለእንስሳ የሚያገለግለውን የመጠጥ ውሃ ለጤና ጎጂ በሆኑ ነገሮች የበከለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ እና እንደ ጉዳቱ መጠን በመቀጮ ወይም ከ1ወር በማያንስ ቀላል እስራት፣ ወይም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከ7 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል። ወንጀሉ የተፈፀመው የውሃ ጉድጓዶችን፣ ማጠራቀሚያዎችን ምንጮችን፣ የውሃ ኩሬዎችን፣ ወንዞችን ወይም ሀይቆችን አስቦ በመመረዝ እንደሆነ ቅጣቱ ከ15 ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት ይሆናል። ይሄም ከፍ ሲል በአዋጅ ቁጥር 300/1995 አንቀጽ 16 ከተቀመጠው የቅጣት መጠን ከፍ የሚል በመሆኑ ተመሳሳይ ለሆነ ድርጊት በአፈፃፀም ረገድ ጥፋተኞች ላይ ሊተገበር የሚገባው የወንጀል ህጉ የቅጣት መጠን ይሆናል፤ (የአዋጅ ቁ 300/1995 አንቀጽ 12(3)። ሌላው ከፍ ሲል በወንጀል ህጉ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት የተፈፀመው በቸልተኛነት ከሆነ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።

ወንዞችን መበከል ከፍ ሲል በዝርዝር ከተቀመጡት የአስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶች ባሻገር የድርጊቱን ፈፃሚዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍሉ የሚያስችል ከውል ውጪ ኃላፊነት የሚመነጭ የፍትሐብሄር ተጠያቂነትም የሚያስከትል መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።

ማጠቃለያ

አሁን ላይ በስፋት ወደ ልማት ኮሪደርነት እየተቀየሩ የሚገኙት ወንዞች ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለማኅበረሰብ ጤንነት፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ከሚያስገኙት በጎ ፋይዳ ባሻገር ለከተሞች የሚሰጠው ውበትና መልካም ገፅታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዜጎችን የሚጠቅሙ ስራዎች በመሆናቸው ሁሉም ዜጋ ሊንከባከባቸውና ሊጠብቃቸው ይገባል። ከዚህ ባሻገር በእነዚህ የሀገር ሀብቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚኖሩ ጊዜ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ