የስም አወጣጥና ለውጥ በኢትዮጵያ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ስም ሰዎችን ለመለየት የምንጠቀምበት ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡ በዚህም አንድን ሰው ከሌላ ሰው ለመለየት የሚያስችል ስያሜ ለሰዎች በመስጠት በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ- መንግሥት በአንቀጽ 36 (1) (ለ) ስም ማግኘት የሁሉም ሕፃናት መብት እንደ ሆነ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን (ICCPR,1966) አንቀጽ 24 (2) ላይ ሁሉም ሕፃናት እንደተወለዱ ወዲያውኑ እንዲመዘገቡ እና ስም እንዲወጣላቸው ደንግጎ ይገኛል፡፡

ከዚህ አንፃር የሀገራችንን ሕጎች ስንመለከት የፍትሐብሔር ሕጉ ስምን የሚያስተዳድሩ ውስን ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ እነሱም ከአንቀጽ 32 እስከ 46 ድረስ የተደነገጉት ናቸው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ማንኛውም ሰው የቤተ ዘመድ ስም፣ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የግል ስሞች እና የአባት ስም በዚሁ ቅደም ተከተል በሁሉም አስተዳደራዊ ሰነዶች ላይ እንዲሰፍር ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር እንደምናውቀው በእኛ አገር ተለምዷዊው የመዝገብ ስም አጠራር በቅድሚያ የሰውየው ስም በመቀጠል የአባት ስም እና በመጨረሻም የአያት ስምን የያዘ ነው። በዚህ አጭር ጽሁፍ በተለይም የተፈጥሮ ሰውን በሚመለከት ስም ምንድን ነው?፣ ስለ ስም አወጣጥ፣ ስም የማግኘት መብት (Right to Name)፣ ስለ ስም የመለወጥ ሂደትና በስም ያለአግባብ ስለ መጠቀም ወይም መገልገል የሚሉትን ነጥቦች የምንመለከት ይሆናል፡፡

ስም ምንድን ነው ?

የአውደ ጥበባዊ የሕግ መዝገበ ቃላት (2016፣ ገጽ 329) ስም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል መጠሪያ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ስም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ አንድን ሰው ከሌላ ሰው ለመለየት (Identification) እና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን (social Cohesion) ለማጠናከር የሚረዳ ነው፡፡ በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ- ብሔር ሕግ ቁጥር 32 መሠረት አንድ ሰው የቤተ-ዘመድ ስም፣ አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞችና የአባት ስም ይኖረዋል፡፡ በአስተዳደር ሰነድም በእነዚሁ ስሞች ይታወቃል በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህም ስም ምን እንደሆነና ምን ተግባር እንዳለው ህጉ በግልፅ ያመላከተው ጉዳይ የለም። ይልቁን በአንድ ሰው መደበኛ አጠራር ውስጥ የሚካተቱ የስም ዝርዝሮችን ብቻ ያመላከተ ነው።

ስም የማግኘት መብት (Right to Name)

የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ህጎች ውስጥ ልዩ ጥበቃ ከተሰጣቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ሕፃናት ዋነኞቹ ናቸው። ሕፃናት በወላጆቻው ወይም ወላጆች በማይኖሩበት ጊዜ በአሳዳጊዎቻቸው ስም እንዲወጣላቸው ጥበቃ የሚሰጥ መብት አላቸው። ሕፃናት እድሜያቸው 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ለራሳቸው ስም መስጠትም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ እንዳይወስኑ ሕግ ክልከላ የጣለባቸው በመሆኑ ሕጻናትን የመጠበቅ እና እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ወላጆች ወይም ሕጋዊ አሳዳጊዎች ላይ ነው። በመሆኑም ወላጆች/አሳዳጊዎች ለሕፃናት ስም የማውጣት የሕግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ለሕፃናት ከተሰጡ መብቶች አንዱ ስም የማግኘት መብት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 (1ለ) እና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 32)፡፡

ስለ ስም አወጣጥ

በፍትሐብሄር ሕግ አንድ የተፈጥሮ ሰው የቤተ-ዘመድ ስም፣ የግል ስም እና የአባት ስም እንደሚኖረው ከፍ ብሎ ተመላክቷል። ይሁን እንጅ የቤተ-ዘመድ ስምን በተመለከተ በተግባር የተሻረ (Disused) የሆነ የሕግ ክፍል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን የህፃን ልጅ ስም አወጣጥን ስንመለከት በፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር 33 መሠረት የአንድ ልጅ የግል ስም የሚመርጠው አባቱ ወይም አባቱ በሌለ ጊዜ የአባት ቤተ-ዘመዶች ሲሆኑ ሁለተኛ የግል ስሙን ደግሞ እናቱ ወይም እርሷ የሌለች ከሆነ የእናቱ ቤተ-ዘመዶች ሊያወጡለት ይችላሉ በሚል ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌም ቢሆን በተለይ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግሥት መፅደቅ በኋላ ተፈፃሚነት የሌለው የሕግ ክፍል ነው። (ህገ-መንግሥት አንቀጽ 9(1)፣ 35(2)) ከዚህ በመነሳት የቤተዘመድ ስምና ይህንን ስም አወጣጥ የሚመለከቱ የፍትሃብሄር ህጉ ክፍሎች ተፈፃሚነት የሌላቸው ህጎች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል።

ስለሆነም መሠረታዊ የልጆች አስተዳደግን ጨምሮ የቤተሰብ ኃላፊነትን በሚመለከት ባልና ሚስት የጋራ መብትና ኋላፊነት እንዳለባቸው በቤተሰብ ህጉና በህገ-መንግስቱ በግልፅ ተረጋግጧል። በመሆኑም የህፃን ልጅ ስምን የማውጣት መብትም ለባልና ሚስት በጋራ የተሰጠ መብት እንጂ በፍትሃብሄር ህጉ በተቀመጠው አግባብ የሚወጣ አይደለም። ይሁን እንጅ ባልና ሚስት በንግግር ስም የማውጣት መብትን በፈቃድ ለአንዱ በመስጠት ሌላኛው ያወጣው ስም መጠሪያ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ከሁለት አንዳቸው በሌሉ ወይም ባልታወቁ ጊዜ ልጁን በሞግዚትነት ይዞ የሚገኘው ወላጅ ስም ሊያወጣ ይችላል። በተግባርም የሚስተዋለው ይህ አሠራር ነው።

በሌላ በኩል ሁለቱም ወላጆቹ የማይታወቅ ልጅ የልደት የምስክር ወረቀት በሚሰጠው ጊዜ የተወለደበት አካባቢ ልማድ መሠረት በማድረግ በሚመለከተው የመንግሥት አካል የግል ስም እንዲኖረው ይደረጋል (ቁጥር 39)፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት ስም የወጣለት ልጅ ላይ የሞራል ወይም ግዙፍ ጥቅም አለኝ የሚል አካል በአምስት ዓመት ውስጥ ስሙ እንዲቀየር ለፍርድ ቤት በማመልከት ሊያስለውጥ የሚችልበት አግባብ መኖሩም በህጉ አንቀጽ 39(3) ስር ተደንግጓል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የጉዲፈቻ ልጅን ስም በሚመለከት ከዚህ ቀደም ስም የወጧለት ከነበር አንድ አዲስ የግል ስም በጉዲፈቻ ውሉ መሠረት ሊሰጠው እንደሚችልና የጉዲፈቻ አድራጊው የግል ስም የልጁ አባት ስም ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል። ህጉ በግልፅ ባያስቀምጠውም ከዚህ ቀደም ስም ያልወጣለት ህፃን በጉዲፈቻ በሚወሰድበት ጊዜም ቢሆን ጉዲፈቻ አድራጊው ለልጁ ስም የማውጣት መብት እንዳለው ከድንጋጌው አጠቃላይ ንባብ መረዳት ይቻላል።

ክልከላዎች

ሌላው ከፍ ብሎ እንደተጠቆመው በባልና ሚስቱ በጋራ ወይም በተናጠል በአንደኛው (በሌላኛው ፈቃድ) ለተወለደ ህፃን ስም የሚያወጡ ሲሆን ይህ የሚወጣው ስም ለማህበረረሰባዊ ደኅንነት ሲባል አንዳንድ ክልከላዎች ተጥለውበታል። በዚህ፣-

የመጀመሪያው ከቤተሰብ አባላት ጋር ተመሳሳይ እንዳይሆን ህጉ ግልፅ ክልከላ አስቀምጧል። ማንኛውም ልጅ የአባቱ ወይም የእናቱ ወይም ደግሞ በህይወት ካሉት እህቶቹና ወንድሞቹ የአንደኛው የግል ስም ሊሰጠው አይችልም። የስም ተመሳሳይነት በአጋጠመ ጊዜም ከእነዚህ ሰዎች የሚለየው አንድ ሌላ የግል ስም ሊኖረው እንደሚገባ ህጉ ያስቀምጧል፡፡ በመሆኑም በተለይም በቅርብ ቤተሰቦች መካከል የስም መመሳሰል እንዳይኖር ህጉ በግልፅ ይከለክላል።

ሁለተኛው ክልከላ ደግሞ ስምን አስመልክቶ የሚደረግ ማንኛውም ውል በፍትሐ-ብሔር ሕግ ዋጋ የሌለው እንደሆነ የተመላከተው ነው። በዚህም መሠረት ይህን ካደረግክልኝ በዚህ ስም ድጋሜ አልጠራም፣ ወይንም ከዛሬ ጀምሮ በስሜ ላልጠራ… ወዘተ የሚል ይዘት ያላቸው ውሎች ህጋዊ ውጤት የላቸው ስለመሆኑ በአንቀጽ 44(1) ሰፍሯል።

ከዚህ በተጨማሪም በሌላ ሰው ወይም በራስ ስም ያለአግባብ መገልገል የፍትሃብሄርና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያመጣ ተግባር እንደሆነ ተቀምጧል። (45-46) የመጀመሪያው የራስ ስምን ያለ አግባብ መጠቀም ሲሆን አንድ ሰው በስሙ ያለአግባብ ተጠቅሟል የሚባለው በስሙ ያለአግባብ መጠቀሙ የተፈፀመው በሞያ ሥራ ላይ (In the course of one’s profession) ሲሆን ወይም የሌላውን ሰው ጥቅም ለመጉዳት ተብሎ በዚያው ሰው ክብር ወይም ዝና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ወይም በሌላ ሰው ስም ተመሳሳይነት ተጠቅሞ ለሌላ ሰው ወይም ለራሱ ጥቅም ለማግኘት ወይም ሌላውን ሰው ለመጉዳት የተደረገ እንደሆነ ነው። በቀላል ምሳሌ አንድ ጌታቸው የሚባል ሰው ሌላ ታዋቂ፣ ባለሥልጣን ወይንም ባለሃብት ጌታቸው የሚባል ሰው ስለመኖሩ ቢያውቅና ምንም እንኳ በስም ተመሳሳይ ቢሆኑም ታዋቂው ጌታቸው እኔ ነኝ በሚል ማደናገር ጉዳት ቢያደርስ እንደማለት ነው።

በሌላ ሰው ስም ያለአግባብ መጠቀም፣ አንድ ሰው የሌላን ሰው ስም ባለስሙ የሞተ ወይም ስሙን ለመጠቀም ችሎታ ያጣ ቢሆንም እንኳ ያለተወላጆች ፈቃድ የሌላን ሰው ስም መጠቀም አይቻልም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የጉዳት ካሳው እንዳለ ሆኖ ስም በማጥፋት የወንጀል ተጠያቂነትንም ያስከትላል።

ስለ ስም መለወጥ

አንድ ጊዜ የወጣ የግል ስም በበቂ ምክንያት በፍርድ ቤት ሊቀየር ይችላል፡፡ በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ-ብሔር ሕግ ላይ በቂ ምክንያት ሲገኝ ማንኛውም ሰው የግል ስምን በፍርድ ቤት ውሳኔ ሊለወጥለት እንደሚችል ተደንግጓል (ቁጥር 42 እና 43)፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሰው ስሙን መቀየር የሚችለው በፍርድ ቤት ብቻ እንደሆነና በራሱ ፍላጎት ብቻ ስሙን ለመለወጥ እንደማይችልም ተደንግጓል፡፡ ስምን መለወጥ የሚቻለው በቂ ምክንያት መኖሩን ለፍርድ ቤት በማስረዳት ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤት ስም በሚለውጥበት ጊዜ አስፈላጊ የሆኑትን ማስረጃዎች በማስቀረብ እና ማስታወቂያ በማውጣት መወሰን ይችላል፡፡ ፍርድ ቤት ስም የመለወጥ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ በመጠሪያ ስም፣ በአባት ስምና በአያት ስም መካከል ልዩነት መኖሩን ወይም በሶስቱ ስሞች መካከል ተመሳሳይነት አለመኖሩ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ መጠሪያ ስሙን በሚመለከት ሕጉ እንደ ሁለቱ ሌሎች ስሞች ጥብቅ ላይሆን ይችላል፡፡ የአባትና የአያትን ስም በሚመለከት ግን የሌላ ሰው ስሞች ስለሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለዚህ በስሞቹ መለወጥ ምክንያት የሦስተኛ ወገኖች መብት መነካት የለበትም (ቁጥር 42 (2))፡፡ በዚህ ድርጊት የተነሳ የሦስተኛ ወገኖችን መብት የሚነካ ከሆነ ከፍ ብሎ እንደተመላከተው ሦስተኛ ወገኖች ግዙፍ ወይም የሕሊና ጉዳት የደረሰባቸው ወይም የሚደርስባቸው መሆኑን በማስረዳት ስሞች እንዳይለወጡ መቃዎም ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል አንድ ሰው የግል ስሙን ስንት ጊዜ ሊቀይር ይችላል የሚለው በግልፅ ያልተቀመጠ ሲሆን ፍርድ ቤቶች ከሕጉ እና ሰዎችን አንዱን ከአንዱ ለይቶ ማወቅ ከሚቻልበት ዓላማ አንፃር እንዲሁም ስምን ፍርድ ቤት በሚቀበለው በበቂ ምክንያት ብቻ መቀየር ያለበት ከመሆኑ አንፃር በተግባር ደጋግሞ ስም መቀየር የሚፈቀድ አይመስልም፡፡ ከአንድ በላይ ስም ያላቸው ሰዎች ስም መለወጥ ከፈለጉ በፍርድ ቤት የስም ለውጥ ይደረግልኝ አቤቱታና ማስረጃ በማቅረብ ማስቀየር ይችላሉ፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ስም የአንድ ሰው መጠሪያ ሆኖ በመለያነት ያገለግላል፡፡ ይሁን እንጂ ስም ከግለሰብ መጠሪያነት ያለፈ ጠቀሜታ ያለው ነገር በመሆኑ የሕግ ጥበቃ ተሰጥቶታል። በኢፌዲሪ የቤተሰብ ሕግና ህገ-መንግሥት መሠረት ለልጅ ስም የማውጣት የባልና ሚስት የጋራ መብት ስለመሆኑ ተመላክቷል። በአገራችን ስምን በተመለከተ በ1952 ዓ.ም የወጣው የፍትሐ-ብሔር ሕግ በሦስት ማዕዘናት ከፍሎ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ከሦስቱ የስም አይነቶች አንዱ የሆነው የቤተ-ዘመድ ስም በእኛ አገር ጥቅም ላይ አልዋለም። በሌላ በኩል አንድ ጊዜ የወጣን ስም ያለፈቃድ መለወጥ፣ በሌላ ስም መጠራት ከፍትሃብሄር ተጠያቂነት ጀምሮ በወንጀል ኋላፊነት የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 811 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ በፍርድ ቤት የስም ለውጥ ይደረግልኝ አቤቱታ በማቅረብ ስም መለወጥ የሚቻል መሆኑን እንዲሁ በህጉ የተፈቀደ ተግባር መሆኑን ህብረተሰባችን ሊገነዘብ ይገባል፡፡