መግቢያ
በሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለውጥ ዉስጥ በርካታ ኩነቶች ይከሰታሉ፡፡ የሰላም ጊዜ፤ የጦርነት ጊዜ፤ የድህነትና የብልጽግና ዘመን፤ ሁሉን ዓቀፍ እድገት፤ ሁሉን አቀፍ ውድቀት፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት በአንጻሩ የሰዎች የበላይነት የነገሰበት፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፤ ሰላምና መረጋጋት፤ በዜጎች መካከል መፈቃቀር እንዲሁም አለመግባበቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የገሃዱ ዓለም እውነታዎች ናቸው፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የትኛውም የሀገር መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የመንግሥትን እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፤ እውነተኛ ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡ በሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሂደት ውስጥ አንድ በኩል አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ በአንጻሩ ሰላማዊ የሆኑ ዜጎች የጥፋት ሰላባ ሆነው ፍትሕ ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡
በሰላም ይሁን በጦርነት ጊዜ አላግባብ ሰብዓዊ መብታቸውን የተገፈፉ፤ ፍትሕ ያጡ፤ የአካል እና የሞራል ውድቀት የደረሳባቸው ዜጎች የሽግግር ፍትሕ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታታ በርካታ ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን በመቅረጽ ተግበራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመዘረጋት እና ተግባረዊ ለማድረገ ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ስለሆነም በዚህ ጽሁፍ ስጠቅላላ የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሃሳብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡
የሽግግር ፍትሕ ምንነት
የሽግግር ፍትሕ ማለት፡- በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና ወይም የፍትሕ እጦት ነዉ፡፡ የዚህ የሰላም እጦት መነሻ ምክንያቱ በእርስ በእርስ ግጭት፤ በውስጥና የዉጭ ጦርነት ወይም ሀገር ሰላም በነበረችበት ወቅትም ቢሆን የተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ጥቃቶች ናቸው፡፡ የሽግግር ፍትሕ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች በተሟላ መልኩ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ነው። በዋናነት ሙሉ ፍትሕ የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋት፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት፤ ማህበረሰቡ ተመልሶ ወደቀደመ የፍትሕ እጦት ሁኔታው ውሰጥ እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ የሰላም እና እርቅ ስርዓቶችን መዘርጋት ነው፡፡
የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት
በአንድ ሀገር ውስጥ ውስብስብ በደሎች ይፈጸማሉ፡፡ በመደበኛዉ የሕግ ሂደት አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ የተላለፉ ቅጣቶች ቀጣይነት ያለዉ ሰላም እና እውነተኛ ፍትሕን ለማምጣት በቂ አይደሉም፡፡ የተለያየ ሀገራት ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት በመደበኛው ወንጀል ክስ አማካኝነት የአጥፊዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ላይ በማተኮራቸው ተጎጆዎችን በፍትሕ አለመፈወሳቸው እንዲሁም ተጎጂዎችን እና ማህበረሰቡን ለማከም በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው እንደ ክፍተት የታየ እውነት ነዉ፡፡
ስለሆነም ሌሎች አማራጮችን ማፈላለጉ የህበረተሰቡን መሠረታዊ የፍትሕ ጥያቄ ሊመለስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርተይድ ሥርዓት ማብቂያ በኋላ /post-apartheid transitional justice/፤ በዳይና ተበዳይ ተቀራርበዉ በመነጋገር እርቀ ሰላም ያወረዱበትና ዘላቂ ሰላም የተገኘበት፤ እንዲሁም በሴራሊዮን፤ በላይቤሪያ፤ በኬኒያ በተደረገዉ የሽግግር ፍትሕ በርካታ ጠቀሜታዎች መገኘታቸዉን መረዳት ይቻላልል፡፡ ለሆነም አጠቃላይ አስፈላጊነቱ ሲታይ
- የቆዩ የመንግስታዊ ጭቆና፤ አድሏዊነት፤ በደሎች እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት በነበሩባቸው ሀገራት ሁሉንም አጥፊዎች ለፍርድ ማቅረብ የማይቻል በመሆኑ የተወሰኑትን ዋና ዋና ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚቀጣ የፍትሕ ሂደት በማስፈለጉ፤
- የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ እና ቀጣይነት ላይ ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት መሆኑ፡
- በጥፋተኞች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ዘላቂ ሰላም እና እርቅ በመፍጠር ረገድ ተገቢ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑ፤
- ከረጅም ጊዜ በፊት የነበሩ እና አሁን ላይ እተፈጸሙ ያሉ በርከት ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ትኩረት በመስጠት አጥፊዎቸን ለሕግ በማቅረብ መጠየቅ እንዲችሉ ማድረጉ፤
- የሽግግር ፍትሕ ስልትን ተጠቅሞ ተጠያቂነትን ከማስፈን በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ እውነት የሚጣራበት፤ ለሕዝብ ግልጽ የሚሆንበት እና ዘላቂ እርቀ ሰላም የሚረጋግጥበት መሆኑ፤
- ወንጀል ለተፈጸመባቸው ተጎጂዎች የካሳ ስርዓት በመዘርጋት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ፤
- ከሽግግር ፍትሕ ጋር አብሮ የዘመነ እና ይህን አስተሳሰብ የሚሸከም የተቋማትና የሰዉ ኃይል ለውጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤
- በእውነት፡ በፍትሕ፡ በሰላም እና በእርቀ ሰላም ላይ በመመስረት ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማደስ እና የተቀራረብ ሀገራዊ እሳቢዎችን ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ ወዘተ የሚጠቀሱ ነጥቦች ናቸው
የሽግግር ፍትሕ ተግዳሮቶች
- ተጠያቁነትን በተመለከተ ከየትኛዉ ጊዜ ጀምሮ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምርመራና ክስ ይጀመር የሚለው ሀሳብ ላይ ወጥ የሆነ የግዜ ገደብ ማስቀመጥ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ፤
- የወንጀል ምርመራ ራቅ ካለ ጊዜ የሚጀመር ከሆነ የይርጋ ጊዜ የሚገድበው በመሆኑና በዚህም ምክንያት አላግባብ ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚያስመልጥ መሆኑ፤
- የወንጀል ምርመራ ከቅርብ ጊዜ የሚጀመር ከሆነ የሽግግር ፍትሕ ሁሉን አካታችና የእኩልነት መርህ የሚጻረር ሲሆን የተወሰነ አካል ብቻ የሚያስጠይቅ መሆኑ፤
- የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ያደረገ ቢሆኑም ነገር ማካተት ያለበት ዓለም ዓቀፍ ይዘት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ወይስ ሁሉንም ዓይነት ወንጀሎች የሚለው ሀሳብ በተለያዩ ምሁራን እና የህብረተሰበ ክፍሎች ወጥ የሆነ የሚያግባባ ሀሳብ ላይ አለመደረሱ፤
- የሽግግር ፍትሕ ሊያስፈጽሙ የሚችሉ ተቋማት ሲቋቋሙ የገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ
- ተቋማዊ ማሻሻያ ሲደረግ ጊዜ የሚወስድና ወጭ የሚጠይቅ መሆኑ ወዘተ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ሊመራባቸው የሚገቡ መርሆች
የተሳከ የሽግግር ፍትሕ ለማሳካት ከበርካታ መርሆች ዉስጥ የሚከተሉት መሠረታዊ ነጥቦች ናቸወ፡፡ እነርሱም ሀገራዊ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፡ ሀገራዊ እሳቤዎች ላይ በተቀራረበ ሀሳብ መግባባት፤ ተገላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቃቶች ላይ ቅድሚያ የሚሰጠ ሲሆን እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፤ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞች እና ወጣቶችን፤ የተገፉ፡ የተገለሉና ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ልዩ ሁኔታና ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱም የሕዝብ ተሳትፎን ያረጋገጥ፡ በነጻነት፡ በገለልተኝነት፡ በብቃት፡ በአካታችነት እንዲሁም ቅንጅታዊ አሠራር ላይ የተመሠረት መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት መርህ የሚደጋገፉ እና የሚመጋገቡ ስልቶች እንደሆኑ በመገንዘብ ተግባሪዊ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህን መርሆች ተከትሎ ለመተግበር ጠንካራ መንግሥት እና ተቋማት እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተገቢዉን ክስ በማቅረብና በማስቀጣት፡ ሁለንተናዉ የሆነ እርቅን በማጠከር፡ ምሕረትን በመስጠት፤ እውነትን በማፈላለግ፤ ማካካሻን በመስጠት፡ተቋማዊ ማሻሻያን እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው ጉዳዮችን በአንድነትና በተመጋጋቢነት ያካተተ ሁለንተናዊ አካሄድ ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ለተጀመረዉ የሽግግር ፍትሕ የፖለሲ አማራጭ ስኬታማነት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ