የኢትዮጵያ የቤተሰብ ፍትሕ መምሪያ ይፋ ሆነ

The Ethiopian Family Justice Manual was unveiled

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ፍትሕ መምሪያ (Ethiopian Family Justice Guideline) የማብሰሪያ መርሃ ግብር በፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣የዳኝነት አካላት አመራሮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተካሄደ። መምሪያው የቤተሰብ ጉዳዮችን በቀላል፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ማኀበረሰብ ተኮር በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያግዝ እና በተለይም በማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ ማዕከላት የሚሰጠውን የፍትሕ አገልግሎት ይበልጥ ወጥና ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጀ አስገዳጅ ያልሆነ የአሠራር መምሪያ ነው።

በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ወቅት እንደተገለጸው፣ የመምሪያው ዋና ዓላማ የፍትሕ ተደራሽነትን በማሻሻል የሕብረተሰቡን የፍትሕ ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ እና ለዜጎች ቅርብ፣ ምቹና ተደራሽ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ሥራ ማጠናከር ነው። የቤተሰብ ፍትሕ መምሪያው በቤተሰብ መካከል ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጋር ተያይዘው የሚነሱ የቀለብ፣ የልጆች አስተዳደግና የጥበቃ ጉዳዮች፣ የንብረት አስተዳደር፣ የፍቺ እና የንብረት ክፍፍል ጉዳዮችን በተቻለ መጠን ቀላል፣ ፈጣንና ተገቢ በሆነ አሠራር ለመፍታት የሚያግዙ አማራጮችን ያመላክታል። መምሪያው በአዲስ አበባ፣ በአማራ እና በሲዳማ ክልሎች የተገኙ የተግባር ልምድና ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከአካባቢያዊ እውነታዎች ጋር የሚጣጣሙ እና በተግባር ሊውሉ የሚችሉ የጉዳይ መፍቻ አማራጮችን ያካተተ ነው።

የቤተሰብ ፍትሕ ጉዳዮች ከሰዎች ሕይወት፣ ስሜትና ክብር ጋር በቀጥታ የተያያዙ በመሆናቸው መምሪያው የሰው ልጅን ክብር፣ ስሜትና ባህል በማክበር ሰው ተኮር የፍትሕ አገልግሎት እንዲሰጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በተለይም የሕፃናትና የሴቶች መብትና ደህንነት፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችና በማኅበረሰቡ የተገለሉ ቡድኖች ፍትሕ የማግኘት እድል በልዩ ጥንቃቄ እንዲጠበቅ የሚያስችሉ መርሆዎችንና አሠራሮችን አካቷል።

ፍትሕ ሚኒስቴር የቤተሰብ ፍትሕ መምሪያውን ከ The Hague Institute for Innovation of Law (HiiL) እና Destiny Ethiopia ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል። በሂደቱም አካባቢያዊ እውነታዎችንና የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ሥርዓትን ከአለም አቀፍ ልምድና በተግባር ከተፈተኑ የቤተሰብ ፍትሕ አሠራሮች ጋር በማጣመር ተዘጋጅቷል። በዚህም መሠረት መምሪያው በተለይ ለሕፃናት፣ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋት ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። የኢትዮጵያ የቤተሰብ ፍትሕ መምሪያ በአገሪቱ እየተቋቋሙ ባሉና በቀጣይነት በሚደራጁ የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ ማዕከላት የሚሰጡ የቤተሰብ ፍትሕ አገልግሎቶችን ይበልጥ ወጥ፣ ጥራት ያለው፣ ተደራሽና ተጠቃሚ ተኮር ለማድረግ አስተዋጾው የጎላ ነው ተብሏል።

ፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ አገልግሎትን ለዜጎች ይበልጥ ቅርብ፣ ምቹ፣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ ማዕከላትን እያቋቋመ ይገኛል።

Tagged Under: act • decree • destiny ethiopia • directive • ethiopian family law • family • federal institute of justice and law • federal justice and law institute • fundamental law • guide • guideline • hague • hiil • innovation • institute • itu • Justice • justice and law institute • law • legislation • line • manual • Policy • proclamation • Regulation • rule • statute • the hague institute for innovation of law • un • vat
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች