የሴቶች መብት በኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ

ማውጫ

Share this Article

ሴቶች በሁሉም ማኅበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት እየተደረገባቸው እና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው መቆየታቸውን ከታሪክ መመልከት እንችላለን፡፡እነዚህን የመብት አለመከበር እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶችን ለማስወገድ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና አገር አቀፍ ህጎች በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ውለው ይገኛሉ፡፡ለሁሉም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እውቅናን ከሰጡት እንደ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መገለጫ(UDHR)፣ ዓለምአቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(ICCPR)፣ዓለምአቀፍ የኢኮኖሚ፣ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት(ICESCR)፣እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ለሴቶች መብት ልዩ ትኩረት ያደረጉት የሴቶች የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(CPRW)፣በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ መግለጫ(Declaration on Elimination All Forms of Discrimination Against Women)የመሳሳሉ ሰነዶች ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡ አለምአቀፍ ስምምነቶች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም የሴቶች መብት ከኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ እውቅና ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ እንዲሁም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9/4 መሠረት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል ይሆናሉ በማለት የደነገገ በመሆኑ በስምምነቶቹ የተዘረዘሩትን የሴቶች መብት የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት በመንግሥት ላይ ወድቋል ማለት ነው፡፡

መንግሥት የሴቶችን መብት ለማክበር እና ለማስከበር ከሚወስዳቸው መሠረታዊ እርምጃዎች መካከል ለመብቶቹ በቂ የሕግ ማዕቀፍ መስጠት ይገኝበታል፡፡በዚሁ መሠረት ለሴቶች መብት ሰፊ ሽፋን ከሰጡ ህጎች የተሻሻለው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የቤተሰብ ሕግ ተጠቃሽ ነው፡፡በክልሎችም እንደ ክልሎቹ ማኅበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ የቤተሰብ ሕግ አውጥተው እየተገበሩ ይገኛል፡፡ በዚህ አጭር ንቃተ ሕግ ጽሑፍ በተሻሻለው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የቤተሰብ ሕግ በጋብቻ አፈፃፀም፣በጋብቻ ዘመን እና በፍቺ ጊዜ የሚኖሩ የሴቶች የእኩልነት መብቶች፣ የጋራ ንብረትን የማስተዳደር መብት፣ቀለብ የማግኘትና የመስጠት መብት እና እንደባልና ሚስት አብሮ በመኖር ወቅት የሚኖሩ መብቶች ይዳሰሳሉ፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡ ድንጋጌዎችን ከመመልከታችን በፊት የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ በሆነው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግሥት ስለሴቶች መብት የተደነገገውን ድንጋጌ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 35 ስር ሴቶች ህገ መንግስቱ በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ እና በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው፣ በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው፣ከጎጂ ባሕል ተፅዕኖ የመላቀቀ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር እንዳለበት፣የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደሞዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት እንዳላቸው፣በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በፕሮጀክቶች ዝግጅትና አፈፃፀም በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሀሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው፣ ንብረት የማፍራት፣የማስተዳደር፣የመቆጣጠር፣የመጠቀምና የማስተላለፍ በተላይ መሬት በመጠቀም ፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው፣የቅጥር የስራ እድገት፣የእኩል ክፍያና ጡረታን የማስተላለፍ እኩል መብት እንዳላቸው እና በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት፣መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት እንዳላቸው ተገንግጎ ይገኛል፡፡

የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ ስንመለከት በጋብቻ ወቅት ሁለቱም ተጋቢዎች ጋብቻን ለመመስረት ነፃ ፍቃዳቸውን መስጠት እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ይህም መመዘኛ መሠረታዊ እና ጋብቻን በሕግ ፊት እንዲፀና የሚያደርግ ነው፡፡ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት በአብዛህኛም የሀገሪቱ የገጠር ክፍል ጋብቻ የሚፈፀመው በተጋቢዎች ነፃ ፍቃድ ሳይሆን በቤተሰብ በተዘጋጀ ጋብቻ(arranged marriage) ሲሆን ሴቶች ከማይፈልጉት ሰው ጋር እንዲኖሩ የሚያስገድድ በመሆኑ ነው፡፡በተጨማሪም የተጋቢዎች የጋብቻ እድሜ ለሁለቱም እኩል 18 ዓመት መሆኑ ተጋቢዎች የኑሮ ጫናን በእኩል ኃላፊነት እንዲጋሩ የሚያስችላቸው ነው፡፡ ሌላው በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 49/1 ስር እንደተደነገገው ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣መተጋገዝ እና መደጋገፍ አለባቸው፡፡ ይህም ሴቶች ተገቢውን ክብር የማግኘት መብት እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡

ቤተሰብ አመራርን በተመለከተ ባልና ሚስት እኩል መብት እንዳላቸው እና በማናቸውም ረገድ የቤተሰቡን ደኅንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ልጆቻቸውን በመልካም ስነ ምግባር እንዲታነፁ፣ተገቢውን ትምህርት እንዲቀስሙና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ መተባበር እንዳለባቸው በአንቀጽ 50 ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ይህም በቀድሞው የፍትሐ ብሄር ሕግ የቤተሰብ አስተዳደሩን ለባል ሰጥቶ የነበረውን ያሻሻለ ሕግ ሲሆን ሴቶች ከጋብቻ በፊት ያገኙትን የግል ንብረታቸውን፣በጋብቻ ውስጥ ያፈሩተን የጋራ ንብረታቸውን እንዲሁም ልጆቻቸውን የማስተዳደር መብት አላቸው፡፡ባልና ሚስት እያንዳንዳቸው ገቢያቸውን በየራሳቸው ቢቀበሉም እንደኛው ተጋቢ ሲጠይቅ ሌላኛው ተጋቢ ያገኘውን የገቢ መጠን የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ይህም የሚያመለክተው ሴቶች የባሎቻቸውን ገቢ የማወቅ መብት እንዳላቸው ነው፡፡እንዲሁም ሴቶች በጋብቻ ውስጥ እያሉ በቀጥታ በስጋ ወይም በጋብቻ ለሚዛመዷቸው ዘመዶቻቸው ማለትም ከጋብቻ በፊት ለነበራቸው ልጃቸው፣ለእናት፣ለአባት፣ለአያት፣ለእህት ወይም ለወንድማቸው የቤተሰብ ህጉ የሚያስቀምጠውን መስፈርት በመከተል ቀለብ የመስጠት መብት ያላቸው ሲሆን ከባላቸው ቀለብ የማግኘት መብትም አላቸው (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 እና 49)፡፡

በሌላ በኩል ሴቶች በፍቺ ወቅት ከጋራ ንብረታቸው እኩል የመካፈል መብት እንዳላቸው የሚያመለክተው በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንቀፅ 90 ስር የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡በመሰረቱ በፍቺ ጊዜ ባልና ሚስት የየግል ሀብታቸውን መልሰው መውሰድ የሚችሉ እንዲሁም ንብረታቸውን በስምምነት መካፈል የሚቻል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ለሁለቱም እኩል የሚካፈል ይሆናል፡፡የንብረት ክፍፍሉም በአይነት ወይም በገንዘብ ሊደረግ የሚችል ሲሆን በአይነት ክፍፍሉ ሲገረግ ለእያንዳንዱ ተጋቢ ይበልጥ ጠቃሚነት ያላቸው ንብረቶች እንዲያገኝ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ሴቶች በፍቺ ወቅት በንብረት ረገድ እኩል የተጠቃሚነት መብት አላቸው፡፡ በተጨማሪም ፍቺ ሲወሰን የልጆች አጠባበቅና አያያዝን የሚመለከት ውሳኔ ፍርድ ቤት እንደሚሰጥ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 113 ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡በዚሁ መሠረት ልጆች ከማን ጋር ሊኖሩ እንደሚገባ፣ስለትምህርታቸው እና ስለጤናቸው አጠባበቅ፣ስለቀለባቸውና ባጠቃላይ ስለአኗኗራቸው እንዲሁም ወላጆችና ልጆቻቸው ለመጠየቅ ስላላቸው መብት ይወስናል፡፡ውሳኔውንም በሚወሰንበት ጊዜ ከሚያገናዝባቸው ጉዳዮች የልጆቻቸውን ዕድሜ፣ጥቅማቸውንና ፍላጎታቸው የሚጠበቅበት ሁኔታ ይገኝበታል፡፡ስለሆነም ለምሳሌ ልጃቸው በጣም ህፃን በመሆኑ የእናቱ እንክብካቤ ይበልጥ የሚያስፈልገው ከሆነ ሴቷ ህፃኑን/ኗን የማሳደግ መብት እንዲሰጣት ለፍርድ ቤት ልታመለክት ትችላልች፡፡በመጨረሻም ከጋብቻ ውጪ እንደባልና ሚስት የሚሩ ሴቶች በቤተሰብ ህጉ የተከበረላቸውን መብት ከማየታችን በፊት ከጋብቻ ውጪ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በህጉ የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብረው ኖሩ ለማለት ወንድየውና ሴትየዋ የሚያሳዩት ሁኔታ በሕግ እንደተጋቡ ሰዎች ዓይነት መሆኑ እና ቤተዘመዶቻቸው እና ማህበረሰቡ እንደተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ብለው ሲገምቷቸው መሆኑ አስፈላጊና በቂ ነው የሚል ነው፡፡

በዚህ ግንኙነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የንብረት አስተዳደራቸውን አስመልክቶ የሚያደርጉት ውል እንደተጠበቀ ሆኖ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ከሶስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ በግንኙነቱ ውስጥ እያሉ ያፈራቸው ንብረቶች የጋራ ሀብታቸው ይሆናሉ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 102 )፡፡ ይህ በህጉ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በአብዛህኛው ማኅበረሰብ የሶሰት ዓመት ሳይሆን ሶስት ወራት እንደሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ ተይዞ እንመለከታለን፡፡ ከላይ ከተጠቀው የሕግ ድንጋጌ የምንገነዘበው ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብረው የኖሩ ሴቶች ግንኙነቱን ባቋረጡ ጊዜ(ግንኙነቱን ለማቋረጥ የፍቺ ሂደትን መከተል አይኖርባቸውም) በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከተፈራው ንብረት እኩል የመካፈል መብት እንዳላቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ጋብቻን በተመለከት በቤተሰብ ህጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎች እንደየአግባብነታቸው ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው በሚኖሩ ሰዎች ላይ ተፈፃሚ ስለሚሆኑ(የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንቀፅ 114) ሴቶች በነዚህ የሕግ ድንጋጌዎች እውቅና ከተሰጣቸው መብቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡