አባትነት የሚረጋገጥባቸው መንገዶች በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ልጆች ወላጆቻቸውን የማወቅና ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው የማደግ መብት እንዳላቸው በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 7 እና በገራችን ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 36 ላይ በግልፅ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ ወላጆችን በተለመከተ በእናትነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በጣም አናሳ ቢሆኑም አባትነትን አስመልክቶ ግን ብዙ አከራካሪና እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የሚደርሱ ጉዳዮች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አባትነት የሚረጋገጥባቸውን መንገዶች እንዳስሳለን፡፡

የአባትነት ምንነት

የደስታ ተክለወልድ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አባትነትን “አባት መሆን” ሲል የተረጎመው ሲሆን “አባት” ማለት ደግሞ ወላጅ፣ አስገኚ፣ አሳዳጊ፣ ሞግዚት፣… የንጀራ አባት፣ የእናት ባል” የሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የተፈጥሮ አባትነትን የሚዳስስ በመሆኑ “ወላጅ” የሚለው ትርጉም የተሻለ ተስማሚ ሲሆን ይኸው መዝገበ ቃላት ወላጅነት የሚለውን ቃል “ወላድነት፣ ወላጅ፣ ወላድ መኾን፣ አባትነት፣ እናትነት፣ ልጅን አስገኝነት” የሚል ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን፡፡

አባትነት የሚረጋገጥባቸው መንገዶች

የልጅ ወላጆች ማንነት መታወቅ ለልጅ አስተዳደግም ሆነ ቀጣይ ህይወት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ እንደተገለፀው የአንድ ልጅ እናትን ለማወቅ ሌሎች ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ልጁን ፀንሳና አምጣ የወለደችው ተፈጥሯዊ እናቱ እንደሆነች ግልፅ ነው፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕጋችንም በአንቀጽ 124 ላይ ይህን ያረጋግጣል፡፡ በልጅና በአባት መካከል ግን እንደዚህ ዓይነት ተፈጥሯዊ መስተጋብር ስለማይኖር የልጁን ትክክለኛ አባት መለየት አደጋች የሚሆንባቸው ሁኔታዎች የሚገጥሙ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕጉ ሦስት አባትነትን የማረጋገጫ መንገዶችን ደንግጓል፡፡ እነዚህም በሕግ ግምት አባትነትን ማረጋገጥ፣ ልጅነትን በመቀበል አባትነትን ማረጋገጥ እና በፍርድ ቤት ውሳኔ አባትነትን ማወቅ የሚሉ ናቸው (የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 125)፡፡

በሕግ ግምት አባትነትን ስለማረጋገጥ

የሕግ ግምት ማለት አንድ ሕግ በአንድ ጉዳይ ላይ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ የሁኔታዎቹ መሟላት የአንድን ነገር መኖር ወይም አለመኖር ያረጋግጣል ሲል ድምዳሜ ላይ የሚደርስበት መንገድ ነው፡፡ አባትነትን አስመልክቶ ሕጉ መሠረት የሚያደርገው ልጁ በሚፀነስበት ወይም በሚወለድበት ጊዜ በእናትየዋና በአንድ ወንድ መካከል በሕግ የታወቀ ግንኙነት መኖርን በማረጋገጥ ነዉ፡፡ ይህም ልጁ ሲፀነስ ወይም ሲወለድ ከልጁ እናት ጋር በጋብቻ የነበረ ባል ወይም ጋብቻ ሳይፈጽም እንደ ባልና ሚስት አብሯት የነበረው ወንድ የልጁ አባት ነዉ ብሎ ሕጉ ግምት ይወስዳል፡፡ በመሆኑም በልደት ምስክር ወረቀት አባቱ ሌላ ነው ተብሎ ቢፃፍ ወይም አባቱ ሌላ ሰው መሆኑን የሚያመላክት ቢሆንም እንኳን የልደት ምስክር ወረቀቱ እርማት ይደረግበታል እንጂ የሕግ ግምቱን አያስቀርም (አንቀጽ 126 እና 130)፡፡

ከጊዜ አቆጣጠር ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለውን ክርክር ለማስቀረት ሕጉ ቁርጥ ያለ ጊዜን አስቀምጧል፡፡ በዚህም ልጁ ጋብቻ በተፈፀመ ወይም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ከጀመሩ በ180 ቀናት በኋላ ወይም ጋብቻው ከፈረሰ ወይም እንደ ባልና ሚስት መኖሩ ካበቃ ከ300 ቀናት ውስጥ የተወለደ ከሆነ ልጁ በጋብቻ ውስጥ ወይም እንደ ባልና ሚስት አብሮ በመኖር ውስጥ እንደተፀነሰ እንደሚቆጠር በአንቀጽ 128 እና 130 ተደንግጓል፡፡

ልጅነትን በመቀበል አባትነትን ማረጋገጥ

ከላይ በተገለፀው አግባብ በሕግ ግምት አባትነትን ማረጋገጥ ያልተቻለ ከሆነ በመቀበል አባትነት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ይህም አባትየው ልጄ ነው ሲል በመቀበሉ ምክንያት አባትነት ሊረጋገጥ እንደሚችል በአንቀጽ 131 ላይ ተደንግጓል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ አንድ ሰው አንድን የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ የእርሱ ልጅ መሆኑን አምኖ በመቀበል ቃሉን የሰጠ እንደሆነ በአንቀጽ 132 መሠረት የልጁ አባት ይባላል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለዉ ልጁ የተፀነሰዉ ወይም የተወለደው እናት ከአንድ ወንድ ጋር ጋብቻ ወይም ያለጋብቻ በአብሮ መኖር ሥርዓት ሳትመሰርት ልጅ ስትወለድ ነው፡፡ ምክንያቱም በመቀበል አባትነት ሊረጋገጥ የሚችለው በሕጉ ግምት መሠረት አባትነትን ማረጋገጥ ሳይቻል ሲቀር ስለመሆኑ በሕጉ የተቀመጠ በመሆኑ ጋብቻ ወይም ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ሁኔታ ካለ አባትነትን በተመለከተ የሕጉ ግምት ቅድሚያ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

አባትየው መቀበሉን የሚገልጽበት ፎርም ወይም ሥርዓት በክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ በሚሰጠዉ ቃል ወይም በጽሑፍ በሚያደርገዉ ኑዛዜ ወይም በሌላ በማናቸዉም ሥልጣን በተሰጠዉ ባለሥልጣን በተረጋገጠ ሠነድ አማካኝነት ነዉ (አንቀጽ 133)፡፡ በመርህ ደረጃ አባትነትን የመቀበል ቃሉን መስጠት ያለበት አካለ መጠን ያልደረሰ ቢሆንም እንኳን አባት ብቻ ነዉ፡፡ ነገር ግን ቃሉን በፍርድ ቤት የፀደቀ ልዩ ዉክልና ስኖር ብቻ ሌላ ሰዉ መስጠት እንደሚችል በአንቀጽ 134 ተደንግጓል፡፡ አባትየዉ ሞቶ ከሆነ ወይም ፈቃዱን ለመስጠት የማይችል በሆነ ጊዜ አንቀጽ 135 መሠረት ከአባትየዉ ወላጆች አንዱ በእርሱ ስም ልጁን ሊቀበል ይችላል፡፡

አባት ነኝ ባዩ ቃሉን በሚገባው ሥርዓት መሠረት ቢሰጥም እንኳን የልጁ እናት የተቀባዩን አባትነት ካላመነች የተሰጠው ቃል በሕግ ፊት ዉጤት የለውም፡፡ ይህን ማረጋገጫ ሳትሰጥ እናት ሞታ ወይም ፈቃድ መስጠት የማትችል ከሆነች ከእናት ወላጆች በአንዱ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የእናት ወላጆች የሌሉ ከሆነ ወደላይ የሚቆጠር ሌላ ወላጅ ወይም በፍርድ ቤት በተከለከለው ሰው አሳዳሪ ሊሰጥ እንደሚችል በአንቀጽ136 ተደንግጓል፡፡ አባት ነኝ ባዩ መቀበሉን የሰጠው ልጁ ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላ ከሆነ መቀበሉ ውጤት የሚኖረው ልጁ አባትነቱን ሲቀበል ብቻ ነው (አንቀጽ137)፡፡ በሁለቱም (በእናት ወይም በልጅ) የሚሰጠው ማረጋገጫ አባትነቱን መቀበሉን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ በ1 ወር ጊዜ ወስጥ ክርክር ካላነሱ አባት ነኝ ያለዉን ሰው አምነው እንደተቀበሉ ይቆጠራል (አንቀጽ 138)፡፡

በመርህ ደረጃ ልጅነትን መቀበል የሚቻለው ልጁ በሕይወት እያለ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ልጁ ሌላ ወደ ታች የሚቆጠር ልጅ ተክቶ ከሞተ ብቻ የሞተዉን ልጅ ልጅነትን መቀበል ይቻላል (አንቀጽ 139)፡፡ ይህ የሚያሳየው ሕጉ አባትነት መቀበልን ያመቻቸው ለልጅ ጥቅም ሲባል እንጂ ለወላጅ አባት ጥቅም አለመሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም ለአንድ ልጅ አባት ሊሆን የሚችለው አንድ ሰው ብቻ በመሆኑ ቀደም ብሎ አንድ ሰው ልጅነትን የመቀበል ቃል ሰጥቶ እያለ እና ቃሉም ካልተሻረ ወይም ካልፈረሰ በስተቀር ሌላ ሰው ልጄ ነው ሲል የሚሰጠዉ ቃል ተቀባይነት እንደማይኖረው ከአንቀጽ 142 መረዳት ይቻላል፡፡

ቃልን ስለመሻር እና ስለማፍረስ

አንድ ሰው የልጅ አባት መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ልጄ ነው ሲል የሰጠዉን ቃል መሻር አይችልም፡፡ ነገር ግን ቃሉን የሰጠዉ አካለ መጠን ያልደረሰዉ ልጅ ሲሆንና እሱን ተክቶ አስቀድሞ አሳዳሪዉ ስምምነቱን ካልሰጠ አባት ነኝ ያለው አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ አካለ መጠን ከመድረሱ በፊትእና ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ድረስ ቃሉን ሊሽር ይችላል፡፡ በዚህም ሁኔታ የመሻር መብቱ አካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ ብቻ ስለሆነ የልጁ ሕጋዊ ወኪሎችም ሆኑ ወራሾች ሊሽሩ አይችሉም (አንቀጽ 140)፡፡

በሌላ በኩል ልጅነትን ለመቀበል የተነገረው ቃል በኃይል የተሰጠ መሆኑን ማስረዳት ከቻለ አባትነቱን የተቀበለው ሰው የሰጠው ቃል እንዲፈርስ ማድረግ ይችላል፡፡ እንዲሁም ተቀባዩ ልጁ ከእርሱ ሊፀነስ የማይቻል መሆኑን በማያሻማ አኳኋን ካላረጋገጠ በቀር የመቀበሉ ድርጊት በስህተት ወይም በማታለል የተደረገ ነዉ በማለት ሊፈርስ እንደማችል በአንቀጽ 141 ተመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤት ውሳኔ አባትነትን ማረጋገጥ

ከዚህ በላይ በተገለፁት ሁኔታዎች ማለትም በሕግ ግምትና ልጅነትን በመቀበል አባትነት ሊረጋገጥ እንደሚችል አይተናል፡፡ በሕግ የታወቀ ግንኝነት ሳይኖር የሚወለድ ልጅ አባት ነኝ ባይ ሰው በፈቃዱ ካልተቀበለ ልጁ አባት የሚያጣበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነዉ፡፡ በመሆኑም በመካድ ወይም ባለመቀበል አባትነትን ለሚያጡ ልጆች በፍርድ ቤት በሚሠጥ ዉሳኔ አባት እንድያገኙ የሚያስችል ሦስተኛ አማራጭ እንዳለ በሕጉ ተቀምጧል (አንቀጽ 125፣ 143 እና ተከታዮቹ)፡፡

በአንቀጽ 143 መሠረት አባትነትን በፍ/ቤት ዉሳኔ ለማረጋገጥ የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው ፡-

  • ልጁ በተፀነሰበት ጊዜ በእናቲቱ ላይ የመደፈር ወይም የመጠለፍ ተግባር የተፈጸመባት ሲሆን፣
  • ሆነ ተብሎ በተደረገ የተንኮል ድርጊት፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ አገባሻለሁ በማለት የተስፋ ቃል በመስጠት ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገድ ልጁ በተፀነሰበት ጊዜ በእናቲቱ ላይ የማሳት ተግባር የተፈጸመባት ሲሆን፣
  • አባት ነው በተባለው ሰው የተጻፈና በማያሻማ ሁኔታ አባትነቱን የሚያረጋግጡ ደብዳቤዎች ወይም ሌሎች ጽሑፎች ሲኖሩ፣
  • በሕግ የታወቀ ግንኙነት ሳይኖራቸዉ የልጁ እናትና አባት የተባለው ሰው በሕግ በተመለከተዉ የእርግዝና ጊዜ ቀጣይነት ባለዉ ሁኔታ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብረው የኖሩ እንደሆነ፣
  • አባት ነው የተባለው ሰው ልጁን በመንከባከብ፣ በማስተማር ወይም በማሳደጉ ላይ እንደአባት በመሆን የተሳተፈ እንደሆነ ነዉ፡፡

ከእነዚህ ከአምስቱ ሁኔታዎች በእንዱ ምክንያት ልጅ ተፀንሶ ወይም ተወልዶ ከሆነ በድርጊቱ ላይ ተሳታፊ የነበረዉ ወንድ አባት ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ይወሰናል፡፡

ማጠቃለያ

ልጆች አባታቸውን አውቀው በአካልም ሆነ በስነ ልቦና በአግባቡ ታንፀው ማደግ እንዲችሉ ሕጉ አባትነትን የማረጋገጫ መንገዶችን ያስቀመጠ ሲሆን ህብረተሰቡ በዚህ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ለልጆች መብት መከበር የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ