ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One Man Company) በኢ.ፌ.ድ.ሪ የንግድ ህግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 ሥራ ላይ የዋለው የኢፌድሪ ንግድ ሕግ ለውጥ ካመጣባቸው የህጉ ክፍል መካከል የንግድ ማህበርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ህጉ በቀድሞ የንግድ ሕግ ውስጥ ከተካተቱት ስድስት የንግድ ማህበራት አይነቶች መካከል ተራ የሽርክና ማህብር በመባል የሚታወቀው ከሕጉ እንዲወጣ ያደረገ ሲሆን በምትኩ ሁለት አዳዲስ የንግድ ማህበር ዓይነቶችን ማለትም ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር /Limited Liability Partnership/ እና ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት (One Man Company) አካቶ በጠቅላላ ሰባት የንግድ ማህበር አይነቶችን አካቷል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት (One Man Company) ባህርያትና ተያያዥ ጉዳዮችን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One Man Company) ምንነት

በንግድ ህጉ አንቀጽ 534 መሠረት ባለ አንድ አባል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማለት አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት የተቋቋመ የንግድ ማህበር ሲሆን ማህበሩ ከአባሉ የተለየና የተነጠለ የራሱ የሕግ ሰውነት ያለው ነው፡፡

የማህበሩ አመሰራረት

ከላይ እንደተመለከተው ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመሰረተው አንድ ሰው በሚሰጠው መግለጫ መሠረት ሲሆን አባሉ የሚሰጠው መግለጫ ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት መደረግና መግልጫውም በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የሚቀርበው መግለጫው

  • ማህበሩ አንድ አባል ብቻ ያለው መሆኑን
  • የአባሉን ስም፣ ዜግነትና አድራሻ
  • አባሉ የሞተ፣ የጠፋ ወይም በፍርድ የተከለከለ እንደሆነ ስለ ወራሾቹ ወይም ስለ አባሉ ሆኖ ሕጋዊ ተግባራትን እንዲፈፅም የታጨው የንብረት ጠባቂ ሰው ስም
  • ዕጩ ንብረት ጠባቂው ፍቃደኛ ሆኖ ኃላፊነቱን የተቀበለ መሆኑን
  • የማህበሩን ስም፣ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ቅርንጫፎች ካሉትም መሥሪያ ቤቶቹን
  • የማህበሩን የንግድ ዓላማ
  • የማህበሩ ዋና ገንዘብ መጠንና በሙሉ የተከፈለ መሆኑን የሚያሳይ መግለጫ
  • በዓይነት የተከፈለ መዋጮ ካለ ግምቱን
  • የሥራ አስኪያጁን ስምና ሥልጣን
  • ካለ ኦዲተሩን
  • ማህበሩ የሚቆይበትን ጊዜ
  • ማህበሩ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት የሚያስታውቅበትን መንገድና ጊዜ እንዲሁም፤ ሌሎች በሕግ ወይም በአባሉ እንዲካተቱ የተወሰኑ ጉዳዮችን ማካተት አለበት፡፡

እንደሌሎች ማህበሮች ሁሉ ባለ አንድ አባል ኃለፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር የሚቋቋመው በመመስረቻ ጽሑፍ ሲሆን ማህበሩን ለመመስረት የሚቀርበው ዝቅተኛ ዋና ገንዘብ ከብር 15,000 (አሥራ አምስት ሺ) ማነስ የለበትም፡፡ በዚሁ መሠረት ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላ ድረስ ግለሰብ ነጋዴ የንግድ ሥራውን ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርነት መለወጥ የሚችል ሲሆን ሆኖም ግለሰብ ነጋዴው ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከመመሥረቱ በፊት ለገባበት ዕዳ ሁሉ ከማህበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ኃላፊ ይሆናል፡፡

ሌላው የምስረታው ቅድመ ሁኔታ የሆነው የእጩ ንብረት ጠባቂን የተመለከተ ሲሆን እጩ ንብረት ጠባቂው እጩነቱን የተቀበለ መሆኑ ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት መረጋገጥ እንዳለበት በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 ተመልክቷል፡፡ በዚህም ዕጩ ንብረት ጠባቂው ዕጩነቱን የተቀበለ መሆኑን ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት ካላረጋገጠ በስተቀር ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊመሠረት አይችልም፡፡ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለተለያዩ ባለ አንድ አባል ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማህበራት የንብረት ጠባቂ ሆኖ መመረጥ አይችልም፡፡

የማህበሩ አመራር (Governance)

በንግድ ህጉ አንቀጽ 541 መሠረት ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲኖረው ሕጉ የሚያስገድድ ሲሆን አባሉ ራሱ ወይም ሌላ ሰው የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁም አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ያለው ሥልጣን እና ተጠያቂነት ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም በህጉ አንቀጽ 542 መሠረት የማህበሩ አባል የአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባላት ጠቅላላ ጉባዔ ያለውን ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ አባሉ በጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣኑ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ቃለ-ጉባዔ ውሳኔው በተሰጠ ከሦስት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ የማህበሩ ማህደር ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ በማህበሩ ምሥረታ ጊዜ በተሰጠ መግለጫ ውስጥ የተካተቱትን ነገሮች የሚለውጥ ማንኛውም ውሳኔ ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የአባሉ ውሳኔዎች የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ያላሟሉ ቢሆኑ እንኳን በሕግ ፊት የፀኑ ሲሆኑ ጉድለቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አባሉና ማህበሩ በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

የተጠያቂነት ሥርዓት

ከተጠያቂነት አንፃር አባሉ ወይም መስራቹ የራሱን መዋጮ ሙሉ በሙሉ እስከከፈለ ድረስ ከማህበሩ ላይ ለሚፈለግ ዕዳ በግሉ ተጠያቂ እንደማይሆን በህጉ አንቀጽ 534(3) ላይ ተደንግጓል፡፡ የማህበሩ ባህርይ ኃላፊነቱ የተወሰነ እንደመሆኑ ማለትም የሚመጣ ተጠያቂነት በማህበሩ ሀብት ላይ ብቻ የተገደበ በመሆኑ አባሉ ኃላፊነቱን ከተወጣ ማለትም መዋጮውን ሙሉ በሙሉ እና በወቅቱ እሰከከፈለ ድረስ ኃላፊነት የለበትም ማለት ነው፡፡

ሆኖም በመርህ ደረጃ አባሉ መዋጮውን በወቅቱ ከከፈለ ለሚመጣው ተጠያቂነት በግሉ ኃላፊነት የለበትም ቢባልም ተጠያቂ የሚሆንባቸው ልዩ ሁኔታዎች ግን አሉ፡፡ ይህም በህጉ አንቀጽ 543 የተመለከተ ሲሆን አባሉ ወይም በማህበሩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ያለው ሌላ ሰው

  • ማህበሩን ወይም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ጉዳት ላይ የሚጥል ህገ-ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ ከፈፀመ
  • የባለ አንድ አባል ማህበር ንብረትን ከራሱ ንብረት ጋር ከቀላቀለ
  • የባለ አንድ አባል ማህበርን እና የራሱን ማንነት ካልነጣጠለ
  • ስለ ማህበሩ የፋይናንስ አቋም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ካወጣ
  • ያለ ተመጣጣኝ ክፍያ የማህበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገኞች የግል ጥቅም ካዋለ
  • በሕግ ሊከፈል ከሚችለው በላይ የትርፍ ክፍያ ከፈፀመ ወይም
  • ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ከፈፀመ ከማህበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ እንደሚሆን በግልፅ ደንግጓል፡፡

የማህበሩ መፍረስ እና የሚያስከትለው ውጤት

ማህበሩ በንግድ ሕጉ ጠቅላላ ክፍል በአንቀጽ 181 የተመለከቱ ለማህበራት መፍረሻ ምክንያቶች እንደአግባብነታቸው በሚያገጥሙበት ጊዜ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ይኸውም

  • ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ መፈፀም ሳይችል ሲቀር
  • የማህበሩ የቆይታ ጊዜ ሲጠናቀቅ
  • አባሉ ማህበሩ እንዲፈርስ ሲወስን
  • ፍርድ ቤት ማህበሩ እንዲፈርስ ሲወስን
  • የማህበሩ መክሰር በፍርድ ቤት ሲወሰን ናቸው፡፡

ማህበሩ በሚፈርስበት ጊዜ አባሉ መደበኛ የሂሳብ ማጣራት ሂደትን በመከተል ሂሳብ እንዲጣራ ማድረግ ይችላል፡፡ በአንፃሩ አባሉ መደበኛ የሂሳብ ማጣራት ሂደት መከተል ካልፈለገ እና ያለበትን ዕዳ በሙሉ የከፈለ ከሆነ የማህበሩ ሀብት ሳይጣራ ባለበት ሁኔታ በጠቅላላው ለአባሉ እንደሚተላለፍ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 544 መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም በዚህ መልኩ ሂሳቡ ሳይጣራ ወደ አባሉ ከተላለፈ በኋላ ገንዘብ ጠያቂዎች የቀረቡ እንደሆነ አባሉ በግሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አባሉን ተጠያቂ ለማድረግ የሚቀርብ ክስ ገንዘብ ጠያቂው የማህበሩን መፍረስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ሲሆን የማህበሩ ሀብት ለአባሉ ከተላለፈ ከአሥር ዓመት በኋላ ግን ምንም ዓይነት ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡

ማጠቃለያ

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One Man Company) በንግድ ህጉ እውቅና የተሰጠው የንግድ ማህበር ሲሆን በዚህ መልኩ ንግድ ማከናወን የሚፈልጉ ዜጎች በህጉ የተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ማህበሩን በመመስረት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ንግድ የሚሰሩ ነጋዴዎች ወደ ማህበር በመለወጥ የንግድ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚችሉ ከህጉ መረዳት ይቻላል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ