በባለዕዳዎች መካከል ስላለው የማይከፋፈል አንድነት

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሰዎች ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ የተለያዩ ውሎችን ይፈፅማሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ብድር አንዱ ሲሆን ሰዎች ይበደራሉ፣ ያበድራሉ፣ በተናጥል ወይም በጋራ ኃላፊነት ወይም የእዳ ውል ይፈፅማሉ፡፡ በዚህ ግዴታ ባለገንዘብ የሆነው ወገን በስምምነቱ መሠረት ብድሩ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት የሚኖረው ሲሆን ባለዕዳው ደግሞ በውሉ መሠረት የተበደረውን ገንዘብ የመመለስ ግዴታ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ባለእዳዎች ብዙ በሆኑ ጊዜ በባለዕዳዎች መካከል ስለሚኖረው የማይከፋፈል አንድነት ኃላፊነት እንዳስሳለን፡፡

እዳን በማይከፋፈል አንድነት መከፈል ምንነት

እዳ ማለት ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆኑ ሰዎች በሚያደረጉት የውል ስምምነት መሠረት አንዱ ተወዋይ ወገን/ባለገንዘብ/ ለሌላኛው ተዋዋይ ወገን/ባለእዳ/ ላበደረው ገንዘብ ተመልሶ የሚከፈል ገንዘብ ወይም ጥቅም ነው፡፡ እዳን በማይከፋፈል አንድነት መከፈል ሲባል ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ባለእዳዎች በአንድነት ለተበደሩት እዳ ሳይከፋፈሉ በጋራ ለባለገንዘቡ የሚከፍሉት ገንዘብ ወይም በሌላ ሁኔታ የተገባ እዳ ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1749 ገንዘብን የሚመለከት እዳ ከሆነ እዳው የሚከፈለው በሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ነው፡፡ አንድ ባለእዳ ወይም ተበዳሪ ከዋናው እደው በተጨማሪ ወጪ እና ወለድ ሊከፍል ይችላል፡፡ ይህም በአበዳሪ እና በተበዳሪ ስምምነት ላይ የተወሰነ ይሆናል፡፡ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ህጋዊ ወለድ በዓመት በመቶ ዘጠኝ ሂሳብ ይከፍላል ይህም 9 ፐርሰንት ሲሆን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1751 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

እዳን በማይከፋፈል አንድነት ስለሚከፈልበት ሁኔታ

በሕግ ፊት የሚፀና ውል ለማድረግ ተዋዋይ ወገኖች በሕግ ችሎታ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህም 18 ዓመት የሞላው/የሞላት፣ በተዋዋይ ነፃ ፍቃድ የተፈጸመ፤ በሕግ (ፎርም) ተለይተው የተቀመጡ አስገዳጅ ፎርም እንዲሁም የውሉ ዓላማ እና ህጋዊ ይዘቱ ይህም የሚቻል፣ ህጋዊና ሞራላዊ ጉዳት የማያስከትል መሆን እንዳለበት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1678 ስር ተደንግጓል፡፡ እነዚህ አስገዳጅ የውል ፍሬ ነገሮች ካልተሟሉ በስተቀረ የተቀመጠ የውል ግዴታ ወይም ዕዳ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ ህገ ወጥ በሆነ የውል ስምምነት የተገባ እዳን ባለዕዳዎች መቃወም ይችላሉ፡፡ የጋራ ባለዕዳዎች እዳቸውን የሚከፍሉበትን ሁኔታ የውል ስምምነት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተቃራኒ የሆነ የውል ስምምነት ከሌለ ወይም በሕግ ላይ የተገለጹ ልዩ ድንጋጌዎች ከሌሉ ባለዕዳዎች እዳቸውን በማይከፋፈል አንድነት እንዲከፍሉ ይገደዳሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1896)፡፡ ይሁን እንጂ የገንዘብ ባለመብቱ ከቡዙ ባለእዳዎች ውስጥ እንዱን ወይም ሁሉንም ለማስከፈል ይችላል፡፡ ነገር ግን እዳው በሙሉ ተጠናቆ እስካላለቀ ድረስ እያንዳንዱ ባለእዳ ኃላፊነት አለበት (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1897)፡፡ የገንዘብ ባለመብቱ ባለእዳዎችን ነጣጥሎ መክሰስ ይችላል፡፡ በአንዱ ባለእዳ ላይ ብቻ ክስ ማቅረቡ በሌላ ጊዜ በሌላኛው ባለእዳ ላይ ክስ እንዳያቀርብ አይከለክለውም፡፡ በተመሳሳይ በአንዱ ባለእዳ ላይ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ በሌሎቹም ላይ እንደተሰጠ ይቆጠራል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1899)፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሊያየው በሚችልበት ሁኔታ ወይም ሊረዱት በሚችሉበት አግባብ ማስጠንቀቂያውን መስጠት ወይም መለጠፍ ያስፈልጋል፡፡

እዳን መከፈልን ስለመቃወም

እዳ ለመክፈልም ሆነ ላለመክፈል የውል መሠረታዊ ፍሬ ነገሮች አስቀድሞ መሟላት አለባቸው፡፡ እነዚህ ፍሬ ነገሮች ካልተሟሉ የተቀመጠ የውል ግዴታ ወይም ዕዳ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ባለእዳዎች የሚከፍሉት እዳ በሕግ በተከለከለ ዓላማና ሞራላዊ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን ይህን አይነቱን ግዴታ ላለመወጣት መቃወም ይቻላል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1900)፡፡ ለምሳሌ የእዳ ውል ለመዋዋል ችሎታው ከሌለው ሰው ጋር ተፈጽሞ ከሆነ የዚህ የውል ስምምነት ጉድለት አለብኝ የሚለው አካል ጥያቄውን በማንሳት እዳውን መቃወም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ባለእዳዎች በሙሉ ወይም በከፊል የተከፈለ እዳ ካለ በክርክር ወቅት እንደመቃወሚያ ሊያነሱት ይችላሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1901)፡፡ የእዳ ማስከፈል የይርጋ ጊዜ ካለፈ ማስከፈል እንደማይቻል ጭምር በህጉ ተደንግጎ ይገኛል ፡፡ በፍትሐብሔር ቁጥር 1845 በሌላ በሕግ በግልጽ ካልተቀመጠ በቀር በውል ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ወይም ውል እንዲፈርስ የሚጠየቅ የይርጋ ጊዜ አስር ዓመት ነው፡፡ የይርጋ ጊዜ የሚጀምረው ዉሉ መፈጸም ከነበረበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ የይርጋ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ሊቛረጥ ይችላል፡፡ ይህም ባለእዳው እዳውን ሲያምን፣ ከወለዱ ወይም ከእዳው ከፊል ከሰጠ ወይም መያዧ ወይም ዋስ የሰጠ እንደሆነ፣ ባለገንዘቡ መበት እንዳለው ለፍርድ ቤት አስታውቆ ክስ አቅርቦ ለባለእዳው ያሳወቀ ከሆነ የይርጋ ጊዜ ይቐረጣል (በፍትሐብሔር ቁጥር 1851) ፡፡

እዳን ቀሪ ስለማድረግና ስለመተካት

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1826 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት ግዴታ ቀሪ የሚሆነው ሁለቱ ወገኖች ባለእዳ እና ባለገንዘብ በጉዳዩ ላይ አዲስ ግዴታ በምክንያቱ ወይም በውሉ ላይ ለመተካት ሲስማሙ ነው፡፡ የመተካካት ሂደት በግልጽ ስምምነት ከሌለ በቀር በመጀመሪያዉ ግዴታ ውስጥ የነበሩ ዋስተናዎች፣ ወለዶች፣ ቅድሚያ መያዧዎች ወደ መተካካቱ አይተላለፉም፡፡ በሌላ በኩል ከባለዕዳዎች መካከል ለአንዱ ባለእዳ እዳው ቀሪ ከተደረገለት ለሌሎቹም የጋራ ባለእዳዎች ቀሪ ይሆንላቸዋል ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ባለእዳዎች ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት ቀሪ የተደረገለት ባለእዳ መጨረሻ ይከፍለው ከነበረው የእዳ መጠን ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይ ለአንዱ ባለእዳ ቀሪ የተደረገለት ገንዘብ ለሌሎቹም ቀሪ እንደሚሆነው ሁሉ የቀድሞ እዳን በሌላ የተመተካት ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ ለሌሎቹም ተፈጻሚ እንደሚሆን በፍ/ሕግ ቁጥር 1901 እና 1902 ሥር ተመላክቷል::

እዳን ስለማቻቻልና መዳረግ

መቻቻል ማለት ሁለት ሰዎች አንዱ በአንዱ ላይ ባለእዳ ሆኖ ሲገኝ እዳቸውን በማቻቻል የሚያስቀሩት ስምምነት ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1832)፡፡ እዳዎች የሚቻቻሉት የመክፍያ ጊዘያቸው በደረሱ እዳዎች መካከል ብቻ ነው፡፡ ከባለእዳዎች መካከል ገንዘብ ጠያቂው ላይ የሚከፈል ገንዘብ ካለው እዚያው እንዲቻቻልለት መጠየቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን የመቻቻል ሥነ ሥርዓት የእዳው አይነት ልዩ በመሆኑ ለባለገንዘቡ በእጁ የሚከፈል ሲሆን ለባለ እዳው እና ለቤተሰቡ ደሞዝ እና ለቀለብ አስፈላጊ ለሆኑ ንብረቶች፣ ለመንግሥት መስሪያ ቤት የሚከፈል ገንዘብ፣ ባለቤቱ አላግባብ እንዲመለስለት የቀረበበት እንዲሁም በአደራ የተሰጠውን እቃ እንዲመለስለት ጥያቄ የቀረበባቸውን ንብረቶች ለማማቻቻይ አይቀርቡም (የፍ/ሕግ ቁጥር 1833)፡፡

የአንድነት ባለዕዳ የሆነው ሰው ለባለ ገንዘቡ በከፈለው ልክ ተዳራጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ተደራጊ የሆነው ባለእዳ የሚጠቅሙትን መረጃዎች ሁሉ ከባለገንዘቡ የመቀበል መብት አለው (የፍ/ሕግ ቁጥር 1904 እና 1909)፡፡ ባለገንዘቡ የአንደነት ባለእዳውን በከፈለው ልክ ተገቢውን አገልግሎት በይሰጠው ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ ድርጎ ወይም ተደራጊ በለእዳ በከፈለው እዳ ልክ የባለገንዘቡ የመብት ጠያቂነት ልክ ተደራጊ ሆኖ ይወስዳል፡፡

በአንድ የውል ስምምነት በጋራ ለተገባ እዳ ባለእዳዎች የአንድነት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከባለእዳዎች አንዱ ለከፈለው እዳ ወይም ላቻቻለው የገንዘብ መጠን የሌሎች ባለእዳዎች እዳ ቀሪ ያደርግላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ክፍያውን የፈጸመው ባለእዳ አስፈላጊ መረጃዎችን ከባለገንዘቡ የማግኘት ልዩ መብት ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ባለእዳዎች በይርጋ ምክንያት ለተቋረጠ እንዲሁም በውል ስምምነት ጉድለት መሠረት ያለባቸውን እዳ አላግባብ ላለመክፈል ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡

ማጠቃለያ

በጠቅላላው በህጋዊ መንገድ ለተገባ ማንኛውም ግዴታ ባለእዳዎች ለባለገንዘቡ በአንድነት እዳቸውን የመክፈል ህጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ እዳን በጊዜው አለመክፈል ከባለገንዘቡ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ከማሻከሩም በላይ ለተጨማሪ ወለድ እና ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡ በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ