የንግድ ምልክት ጥበቃ ህግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

የንግድ ምልክት የአእምሯዊ ንብረት አካል ከሆነው ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ዘርፍ የሚካተት ነው፡፡ አእምሯዊ ንብረት የፈጠራ ሥራዎችን ለሚያመነጩ ባለመብቶች እንደማንኛውም ቁሳዊ ንብረት ሁሉ የሚሰጡ የባለቤትነት መብቶች ናቸው፡፡ ለዚህ በዋናነት እንደ ምክንያት የሚቀርበው እነዚህን ስራዎችን ለማመንጨት የፈጠራ ባለመብቶች እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን መስዋእት በማድረግ ከብዙ ድካም በኋላ ያገኟቸው የፈጠራ ውጤቶች በመሆናቸው ነው፡፡

የአእምሯዊ ንብረት መብቶች የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ የሚጠበቁበትን አሠራር ማበጀትን ያስፈልጋል፡፡ በዚህም በሀገራችን የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ አግኝቶ በመተግባር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሑፍም ስለንግድ ምልክት ምንነት፣ አስፈላጊነትና ህጉ በያዛቸው የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው፡፡

የንግድ ምልክት ምንነት

የንግድ ምልክት ማለት አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርትና አገልግሎት እንዲለይ ለማስቻል በንግድ ምልክት ባለቤቶች ለምርታቸውና ለአገልግሎታቸው መለያ እንዲሆን ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ ምልክት ነው፡፡ የንግድ ምልክት ሸማቹ ህብረተሰብ የሚፈልገውን ምርትና አገልግሎት በቀላሉ ለይቶ እንዲገዛ ከማስቻሉም በላይ በሚገዛው ምርትና አገልግሎት ጥራት ላይ በመተማመን ፍላጎቱን እንዲያሟላ የሚያደርግ ነው፡፡ በጠቅላላ አነጋገር የንግድ ምልክት የቀዳሚነት/originality/ አርማ ነው፡፡

በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/1998 ላይም ትርጉም የተቀመጠለት ሲሆን የአንድን ሰው/ድርጅት ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች/ድርጅቶች ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ማለት ነው ይላል፡፡ ምልክቱም ቃላቶችን፣ ንድፎችን፣ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለሞችን፣ የእቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርጽ ወይም የእነዚሁኑ ቅንጅት ሊይዝ ይችላል፡፡ የንግድ ምልክት ከንግድ ስም የሚለይ ሲሆን የንግድ ስም የአንድ ድርጅት የህጋዊ ሰውነት መለያ ሲሆን ንግድ ምልክት ግን የአንድን ሰው/ድርጅት እቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች/ድርጅቶች እቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ነው፡፡

የንግድ ምልክት ጥበቃ አስፈላጊነት

የንግድ ምልክት ጥበቃ ማድረግ የሚያስፈልገው፡-

እቃ በማምረት እና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት በመስጠት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን መልካም ስምና ዝና ለመጠበቅ በተመሳሳይ እቃዎችና አገልግሎቶች መካከል መሳከርን በማስወገድ ሸማቾች የሚፈልጉትን ምርት ወይም አገልግሎት በግልፅ ለመለየት እንዲሁም በብሔራዊና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ምቹ የንግድ ውድድር በመፍጠር የንግዱን ማኅበረሰብ መልካም ስምና ዝና በመጠበቅ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማገዝ ነው፡፡

ስለዚህ ተጠቃሚዎች የሚፈልጓቸውን ምርቶችና አገልግሎቶችን መለየት የሚያስችላቸው የንግድ ምልክቶች ጥበቃና የመብት ማስከበር ሥርአቶች ከሌሉ ተመሳስለው በሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች መታለልና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡ በመሆኑም የንግድ ምልክት ምርቶችን በመሸመቱ ሂደት በምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ያለምንም ግራ መጋባት/መሳከር/ ግብይቱን ማከናወን ያስችላቸዋል፡፡

የንግድ ምልክት ምዝገባ

ሰዎች ምርታቸው ጥራት ኖሮት እንዲታወቅና ስምና ዝናቸው ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም ተመሳስሎ የተሰራ ምርት ወደ ገበያ ገብቶ ተጠቃሚውን እንዳያወናብድ፣ አምራቹ ላይም ኪሳራ እንዳያደርስ የምርታቸውን ምልክት በማስመዝገብ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማድረግ አለባቸው፡፡

ለምዝገባ ብቁ ስለሆኑ የንግድ ምልክቶች፡-

በንግድ ምልክትነት ምዝገባ የሚቀርቡ ምልክቶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ንግድ ምልክቶች ከአንድ ቃል ወይም የቃላት ውህደት፣ ፊደሎችና ቁጥሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ስእሎች፣ ባለ ሶስት ዳይሜንሽን ምልክቶች ለምሳሌ፡ የምርቶች ቅርፅ ወይም አስተሻሸግና የመሳሰሉት እንደንግድ ምልክት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

በአዋጁ አገላለፅም ማንኛውም የንግድ ምልክት የአንድን ሰው/ድርጅት ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች/ድርጅቶች ምርቶች ወይም አገልግሎቶች በግልፅ ለመለየት የሚያስችል ከሆነ ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ሆኖም፡-

  • አንድ ሊመዘገብ የሚችል የንግድ ምልክት የምልክቱን ልዩ ባህርይ የሚቀንስ ወይም የሌላ ሰውን መብት የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ ጥበቃ ሊደረግላቸው የማይችሉ ክፍሎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ “ሀ ሻይ” የሚል አንድ ንግድ ምልክት ለ“ሻይ” ምርት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ነገር ግን “ሻይ” የሚለው መጠሪያ ሻይ ቅጠል አምራቾች በሙሉ የሚጠቀሙበት ቃል ስለሆነ አመልካቹ ብቸኛ መብት የሌለው መሆኑን በጽሑፍ ማረጋገጥ አለበት፡፡
  • የንግድ ምልክት በጥቁርና ነጭ ወይም በማንኛውም አይነት ቀለም ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ነገር ግን በጥቁርና ነጭ ቀለም የተመዘገበ ንግድ ምልክት በማናቸውም የቀለም ቅንጅት ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን የንግድ ምልክቱ የተመዘገበው ከሁለቱ ቀለሞች ውጭ በሆነ ቀለም ከሆነ ጥበቃ የሚደረግለት በተመዘገበው የቀለም ቅንጅት ብቻ ይሆናል፡፡

ለምዝገባ ብቁ ስለማይሆኑ የንግድ ምልክቶች፡-

  • የእቃዎችን ወይም የአገልግሎቶችን ዓይነት፣ ጥራት፣ ብዛት፣ ጠቀሜታ፣ ዋጋ፣ እቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ የመነጩበትን ቦታ፣ የተመረቱበትን ወይም የሚቀርቡበትን ጊዜ፣ ሌሎች የእቃዎቹን ወይም የአገልግሎቶችን ባህሪ ብቻ የሚያንፀባርቁ ምልክቶችን ወይም መለያዎችን የያዘ የንግድ ምልክት
  • እቃዎቹ ወይም አገልግሎቶች የመነጩበትን ቦታ ወይም የእቃዎችን አይነትና ባህርይ በተመለከተ ህዝቡን ወይም የንግዱን ማኅበረሰብ ሊያሳስት የሚችል ንግድ ምልክት
  • በንግድ እንቅስቃሴ ወይም በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና በጋራ መግባቢያነት የሚያገለግሉ ቃላቶች/ምልክቶች
  • ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ሳይገኝ ወታደራዊ አርማ፣ የክብር አርማ፣ ሰንደቅ ዓላማ ወይም በአህፅሮተ ቃል የተፃፈ የታዋቂ ድርጅቶች ስም ወይም ሌላ ተመሳሳይ መለያዎች
  • የሕዝብን ሰላም ወይም ሥነ ምግባር የሚፃረር የንግድ ምልክት
  • ድምፅ ወይም ሽታን የያዘ የንግድ ምልክት እንዲሁም
  • ያለ ግለሰቡ ፈቃድ የአንድን በህይወት ያለ ግለሰብ ሙሉ ስም በንግድ ምልክትነት ማስመዝገብ አይቻልም፡፡

የንግድ ምልክት ምዝገባ የሚያስገኘው መብት

የንግድ ምልክት መብት ሰዎች ምርቶቻቸውንና አገልገሎታቸውን ሚዛናዊ በሆነ አግባብ እንዲያቀርቡ በማድረግና በብሔራዊና ዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተሳለጠ የንግድ ሥርአት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አስተዋፅኦው የላቀ ነው፡፡ ለባለመብቱ ምርቶቹ ወይም አገልግሎቶቹ በተጠቃሚዎች እንዲለዩለት ወይም እንዲታወቁለት ያደርጋል፡፡ የንግድ ምልክት ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድሮችን በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፣ አስመስሎ የሚሰሩና ለገቢያ የሚቀርቡ ስራዎችን ለመዋጋት አይነተኛ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡

በሌላ በኩል የንግድ ምልክት ባለቤቱን በማስተዋወቅ እውቅናና የገንዘብ ትርፍን ያስገኛል፤ ይኸውም የንግድ ምልክቶች በራሳቸው ዋጋ ያላቸው በመሆኑ ክፍያን መሠረት አድርጎ ሶስተኛ ወገን እንዲጠቀምበት የመፍቀድ መብትን ይሰጣል፡፡

አንድን የንግድ ምልክት ሳያስመዘግቡ መጠቀም በምልክቱ ላይ በሚኖሩ የይገባኛል ክርክሮች ላይ በቀላሉ ውሳኔ ለመስጠት ከማስቸገሩ በላይ መብትን ለማስከበር ሰፊ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ይጠይቃል፡፡

በአዋጁ እንደተቀመጠው የተመዘገበ ንግድ ምልክት ከሆነ ግን ለባለመብቱ፡-

  • የምዝገባ ሰርተፍኬቱ ለሚነሱ ክርክሮች በቂ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል
  • ምልክቱ ከተመዘገበበት እቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር አያይዞ የመጠቀም፣ ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት የመፍቀድ፣ የማከራየትና መብትን ለማስተላለፍ
  • ሌሎች ሰዎች በንግድ ምልክቱ እንዳይጠቀሙ የመከላከል፣ በተለይም በተመሳሳይ ምልክቶች ተመሳሳይ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በጉሙሩክ በኩል እገዳ እንዲደረግ ለመጠየቅ እንዲሁም
  • ምልክቱ በሌሎች ሀገሮች በቀላሉ ለማስመዝገብ ያስችለዋል፡፡

የንግድ ምልክት ጥበቃ ጊዜ

በአዋጁ መሠረት አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት በየሰባት አመቱ እድሳት የሚደረግለት ሲሆን በታደሰ ቁጥር የጥበቃ ጊዜውም እየተራዘመ ይሄዳል፡፡

የንግድ ምልክት የሚታደስባቸው ሁኔታዎች፡-

  • የቆይታ ጊዜው ካለቀ ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ያለቅጣት
  • የሶስት ወራት ጊዜ ካለፈ በደንቡ የተወሰነውን ክፍያ በመክፈል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ በቅጣት
  • በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ያልታደሰ ንግድ ምልክት እንደተተወ ተቆጥሮ መብቱ ይሰረዛል፡፡ ከተሰረዘ በኋላ ግን ማንኛውም ሰው የቀድሞ ባለቤት የነበረውን ጨምሮ እንደገና በንግድ ምልክት ባለቤትነት ማስመዝገብ ይችላል፡፡

የንግድ ምልክት መብት ጥበቃ ተፈፃሚነት

የንግድ ምልክት መብት ገሰሳን ለመከላከል አዋጁ በጊዜያዊነት የሚሰጡ እርምጃዎች፣ የፍትሐብሔር መፍትሄዎችና የወንጀል ቅጣቶችን ደንግጓል፡፡ ባለመብቱ በማስረጃ የተደገፈ ክስ ሲያቀርብ ሥልጣን የተሰጠው ፍ/ቤት፡-

  • ፈጣንና ጊዜያዊ እርምጃ ማለትም እግድና የመሳሰሉትን እርምጃዎች ሊወስድ ይችላል
  • በፍትሐብሔርና ወንጀል ሥነ ሥርአት ህጎች መሠረት ፍተሻ እንዲካሄድና እቃዎች እንዲያዙ ሊያዝ ይችላል
  • ተከሳሹ የመብት መጣሱን ድርጊት እንዲያቆም የማዘዝና በባለመብቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ መወሰን ይችላል፡፡

የወንጀል ቅጣትን በተመለከተ የወንጀል ሕግ የበለጠ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር በዚህ አዋጅ ጥበቃ ያገኘ መብትን ሆነ ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ5 ዓመት በማያንስ እና ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ሕግ የበለጠ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ጥበቃ ያገኘ መብትን በጎላ ቸልተኝነት የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ1 ዓመት በማያንስ እና ከ5 ዓመት በማበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡

በወንጀል ህጉ ላይም የንግድ ምልክት መብትን ለመጠበቅ በአንቀጽ 720 ስር የተደነገገ ሲሆን ይህን መብት የሚጥስ ማንኛውም ሰው ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ አዋጁ በግልጽ ያላስቀመጠው ነገር ግን በወንጀል ህጉ በግልጽ የተደነገገው ሌላው ጉዳይ ተመሳስሎ የተሰራ ወይም የተቀዳ የንግድ ምልክት ያለበትን ምርት ያከፋፈለ፣ የሸጠ ወይም የመሳሰሉትን ተግባራት የፈፀመ ሰው በተመሳሳይ የእስራት ቅጣት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ይህ ወንጀል የተፈፀመው በቸልተኝነት ከሆነ ከአምስት ዓመት በማበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ማንም ሰው የሚጠቀምበትን የንግድ ምልክት በህጉ መሠረት በማስዝገብ ጥበቃ ማግኘት የሚችል ሲሆን አከፋፋዮችም የሚሸጡን እቃ ምንነትና ምንጩን አጣርቶ የንግድ ምልክት ባለቤቱን መብት በማክበር ሸማቹንም ተመሳስለው ከሚሰሩና ጥራት ከጎደላቸው ምርቶች ሊታደጉ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ