በውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ወይም የግልግል ዳኝነት ውሳኔ የሚፈፀምበት ሁኔታ

ማውጫ

Share this Article

የሰው ልጆች መስተጋብር በተለይ በአሁኑ የዓለም ሁኔታ በሀገራት ድንበር የተገደበ አይደለም፡፡ በዚህ መስተጋብር መካከል ወደ ፍርድ ቤት ወይም ወደ ሌሎች አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች የሚሄዱ እና አፈፃፀማቸው በተለያዩ ሀገራት የሚሆኑ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ መሰል የውጭ ሀገር ፍርዶችን የማስፈፀም ጉዳይ የዓለም አቀፍ የግለሰቦች ሕግ (private international law) አካል ሲሆን ሀገራት የውጭ ሀገር ፍርድ ለማስፈፀም እንዲረዳቸው የሕግ ማዕቀፍ ያዘጋጃሉ፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሀገራት ሁለት ውይም ከሁለት በላይ ባሉ ሀገራት በሚደረግ የዓለም አቀፍ ስምምነት የውጭ ሀገር ፍርድን ያስፈፅማሉ፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ በውጭ ሀገር የተሰጡ ፍርዶች እና በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በሀገራችን የሚኖረውን የአፈፃፀም ሥርዓት እንመለከታለን፡፡

በውጭ ሀገር የተሠጡ ፍርዶች ምንነት

የውጭ ሀገር ፍርድ ማለት በውጭ ሀገር መንግሥት ፍርድ ቤት የተሰጠ ፍርድ ማለት እንደሆነ እና የውጭ ሀገር ፍርድ ቤት ማለት ደግሞ ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጭ የሚገኝ በሀገሩ ሕግ መሠረት የተቋቋመ የማናቸውም ሀገር ፍርድ ቤት እንደሆነ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀጽ 3 ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በተጨማሪም የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ዓ.ም አንቀጽ 2(በውጭ ሀገር ለተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ትርጉም የሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ባፀደቃቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት በውጭ ሀገር እንደተሰጠ የሚቆጠር የግልግል ውሳኔን ወይም የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫ በውሳኔው ውስጥ ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ መሆኑ የተገለፀበት ውሳኔ እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

በውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ እንዲፈፀም የሚቀርብበት ሥርዓት

በዓለም አቀፍ ስምምነት በተለየ እንዲፈፀም የሚያደርግ ልዩ ሕግ ከሌለ በስተቀር ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ የተሠጠ ፍርድ፣ ውሳኔ ወይም ብይን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀመው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ መሠረት እንደሚሆን በሥነ ሥርአት ህጉ አንቀጽ 456 ተመላክቷል፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀጽ 456(2) መሠረት የውጭ ሀገር ፍርድ የሚፈፀመው እንዲፈፀም ማመልከቻ ከቀረበ ብቻ ነው፡፡ በፌ.ዴ.ራ.ል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ዓ.ም መሠረት የውጭ ሀገር ፍርድ ማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ ማመልከቻው መቅረብ ያለበት ለዚሁ ፍርድ ቤት ነው፡፡

ይህ ማመልከቻ ሲቀርብም

  • የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ ትክክለኛነት የተረጋገጠበት የፍርድ ግልባጭ
  • ፍርዱ በተሰጠበት ሀገር ፍርዱ የመጨረሻ እና መፈፀም የሚገባው መሆኑን የሚያረጋግጥ በፈረደው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይም ሬጅስትራል የተፈረመ የምስክር ጽሑፍ በአባሪነት አብሮ መቅረብ አለበት፡፡

የውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ እንዲፈፀም ማመልከቻ የቀረበለት ፍርድ ቤት ባለእዳው ቀርቦ አስተያየቱን እንዲገልፅ መብት መስጠት ያለበት ሲሆን ለዚህም ቀነ ቀጠሮ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ጉዳይ ለማጣራት ተከራካሪ ወገኖችን አስቀርቦ ክርክራቸውን መስማት አስፈላጊ ነው ብሎ ካላመነ በስተቀር ውሳኔ የሚሰጠው በቀረበለት ማመልከቻ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የውጭ ሀገር ፍርድ የሚፈፅመው ፍርድ ቤት በማናቸውም ግዜ የሚያጠራጥር ሁኔታ ያጋጠመ እንደሆነ አጠራጣሪ የሆነው ጉዳይ እስኪጣራ ድረስ በአንቀጽ 459(3) መሠረት የውጭ ሀገር ፍርድ አፈፃፀም ውሳኔን ሊያግደው ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ተቀብሎ ፍርዱን ለማስፈፀም ከወሰነ አፈፃፀሙ የሚመራው በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰጠ ፍርድ በሚፈፀምበት ሥርአት እንደሚሆን በሥነ ሥርአት ህጉ አንቀጽ 460(3) ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ሲወስን ስለወጪ እና ኪሳራ አከፋፈል አብሮ መወሰን አለበት፡፡

በውጭ ሀገር የተሠጠ ፍርድ ወይም ብይን የማስፈፀም ቅድመ ሁኔታዎች

በውጪ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ይፈፀም ዘንድ ሥነ ሥርአት ህጉ በአንቀጽ 458 ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎቹም መሟላት አለባቸው፡፡ ይኸውም

  • እንዲፈፀም የተጠየቀውን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ የተሰጠን ፍርድ የሚፈፅም መሆኑ መረጋገጥ
  • ፍርዱ የተሰጠው በሕግ በተቋቋመ ፍርድ ቤት መሆን
  • ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት የፍርድ ባለእዳው መቃወሚያውን እና መከራከሪያውን ለማሰማት መብት ተሰጥቶት የነበረ መሆኑ መረጋገጥ
  • የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ የመጨረሻ እና ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ መታወቅ(የመጨረሻ ፍርድ የሚባለው በይግባኝ የሚታይበትን ሂደት በሙሉ የጨረሰ እና እንደገና የማይታይ ሲሆን ነው፡፡)
  • የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ ለሕዝብ ሞራል (public moral) እና ፀጥታ (public order) ተቃራኒ ያልሆነ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

የሕዝብ ሞራል ሲባል የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ በሀገራችን ህብረተሰብ ዘንድ በጠቅላላው ተቀባይነት ያለው ወይም ለባህል ተቃራኒ ያልሆነ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሕግ ተቀባይነት የሌላቸው የኮንትራት(የውል ጋብቻ) ወይም ተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሌላ ሀገር ቢከናወን እና ከዚህ ጋር በተያያዘ በተነሳ ክርክር አፈፃፀሙ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ ለሕግ እና ለሞራል ተቃራኒ በመሆኑ ኢትዮጵያ ማመልከቻውን ተቀብላ አታስፈፅምም፡፡

እነዚህን በህጉ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች የማያሟላ የውጪ ሀገር ፍርድ በኢትዮጵያ ሊፈፀም አይችልም፡፡

በተመሳሳይ በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን በሀገራችን የሚፈፀመው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ አንቀጽ 461 የተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟላ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም፡-

  • በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀጽ 458(ሀ) መሠረት የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይኑ የተሰጠበት ሀገር በኢትዮጵያ የሚሰጥን ብይን የሚፈፀም የሆነ እንደሆነ
  • ብይኑ የተሰጠው ተከራካሪዎቹ ወገኖች ለግልግል ወይም ለሽምግልና ዳኞች ጉባኤ ባቀረቡት ስምምነት መሠረት ወይም ብይን የተሰጠበት ሀገር ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የሆነ እንደሆነ
  • ተከራካሪ ወገኖች የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኞችን ለመምረጥ የእኩልነት መብት ተሰጥቷቸው እንደሆነ ወይም በክርክር ላይ ማስረጃቸውን ለማቅረብ እና ክርክራቸውንም ቀርቦ ለመስማት የእኩልነት መብት አግኝተው እንደሆነ
  • የግልግሉ ወይም የሽምግልናው ዳኝነት ጉባኤ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተቋቁሞ ከሆነ
  • ብይኑ የተሰጠበት ጉዳይ በኢትዮጵያም ሕግ በግልግል ወይም በሽምግልና ዳኝነት ሊታይ የሚችል እንደሆነና የፍርዱም አፈፃፀም የህዝቡን ሞራል እና ፀጥታ የማይቃረን እንደሆነ
  • የተሰጠው ብይን የኢትዮጵያ ሕግ በሚያዘው እና በሚፈቅደው ሁኔታ ሊፈፀም የሚችል እንደሆነ ነው፡፡

በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 461 ስር የተጠቀሱትን ካላሟላ በስተቀር ሊፈፀም አይችልም፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሠራር ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 53 ጭምር የተመለከቱ ናቸው፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ በውጭ ሀገር ለተሰጠ ፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉ ድንጋጌዎች ሁሉ በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን ላይም በተመሳሳይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ በውጭ ሀገር የተሰጠን ፍርድ እና የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ውሳኔ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ለማስፈፀም በህጉ የተደነገጉት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡

በመሆኑም በውጪ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ወይም የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ውሳኔ ማስፈፀም የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በቅድሚያ ቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

በንቃተ ሕግትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ