የሙስና ወንጀል ምንነትና ልዩ ባህሪያት

ማውጫ

Share this Article

በሀገራችን በፍትሕ ስርዓት ከሚታወቀው የሕግ አይነት አንዱ የወንጀል ሕግ ነዉ፡፡ የተለየዩ ድርጊቶችን በሕግ ወንጀል በማድረግ ልዬ ልዬ የወንጀል ህጎች ያሉ ሲሆን ለምሳሌ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ፤ የጸረ ሽብር ሕግ ፤ የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሕግ፤የሙስና ወንጀሎች ሕግ እና ሌሎች ህጎች ይገኛሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አጠቃላይ ወንጀል ምንነትና የሙስና ልዬ ባህርን የሚመለከተ ነው፡፡ ስለሆነም ወንጀል ማለት ምን ማለት ነዉ? የሙስና ወንጀል ትርጉሙ ምንድነው? የሙስና ወንጀል ከሌላው ወንጀል አንጻር ልዩ ባህራያት ምን እንደሆነ ለመዳሰስ ተሞክሯል ፡፡

የወንጀል ትርጉም

አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት በወንጀል ህጉ በተጠቀሰው መሠረት ሶስት ፍሬ ነገሮች መሟላት አለበት፡፡ አንደኛው ፍሬ ነገር (element) በሕግ የተከለከለ ድርጊት መሆን አለበት፡፡ ድርጊቱ በሕግ እንዲያደርግ ወይም እንዳያደርግ የሚገልጽና ይህንን ግዴታ የተላለፈ ሰው ላይ ቅጣት የሚጥል መሆን አለበት፡፡ በ1996ዓ.ም የወጣ የወንጀል ሀግ አንቀጽ 2 ስለ ህጋዊነት መርህ ሲገልጽ፣ የወንጀል ሕግ ስለ ልዬ ልዬ ወንጀሎችና በወንጀል አድራጊዎች ላይ ስለሚፈፀሙት ቅጣቶችና ጥንቃቄ እርምጃዎች በዝርዝር እንደሚደነግግ ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ሊቆጥረዉ እና ቅጣት ሊወስንበት አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቱ በሕግ ከተደነገጉት በቀር ሌሎች ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊወስን አይችልም በማለት ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው የፈጸመዉ ድርጊት በሕግ የተከለከለ ካልሆነና የተከለከለ ሆኖም ቅጣትን የማይወስን ከሆነ የወንጀል ድርጊት አይሆንም፡፡

ሁለተኛዉ ፍሬ ነገር በሕግ የተከለከለ ድርጊትን መፈጸምን የሚመለከት ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ሕግ አንቀጽ 23 ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገዉን ድርጊት መፈጸም ወንጀል ነዉ ይላል፡፡ በህጉ መሠረት ድርጊት ማለት በሕግ የተከለከለዉን ማድረግ ወይም በሕግ የታዘዘዉን አለማድረግ ነዉ፡፡ ሶስተኛ ፍሬ ነገር የሀሳብ ክፍል ወይም ሞራላዊ ፍሬ ነገር የሚመለከት ነዉ፡፡በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(2) ላይ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለዉ ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተሟልተዉ ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ሲባል የወንጀል ድርጊት የተባለዉን ድርጊት አድራጊዉ ሆን ብለዉ አስበዉ ዉይም በቸልተንነት ስለመፈጸሙ የሚመለከት ሲሆን ይህም የሚረጋገጠዉ ከተፈጸመዉ ግዙፋዊ ድርጊት አፈጻጸምን በማመዛዘን ነዉ፡፡ በመሆኑም ወንጀል ድርጊት የሚባለዉ ድርጊትን የሚከለክል ሕግ፣ በሕግ የተከለከለ ድርጊት መፈጸምንና በህጉ በተጠቀሰዉ የሀሳብ ክፍል አይነት አስበዉ ወይም በቸልተኝነት የተፈጸመ ሲሆን ነው፡፡

የሙስና ወንጀል

የሙስና ወንጀል ትርጉም በሙስና ወንጀሎች ሕግ ላይ በግልጽ ትርጉም አልተሠጠም፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው በ2007ዓ.ም የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 2 ስር የተመለከተዉን የሙስና ባህርይ የሚያሟላ ወንጀል በፈጸመ ጊዜ ለወንጀሉ የተደነገጉ የቅጣት ድንጋገዎች ይፈጽመብታል ይላል፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለመግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጠዉ ኃላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባዉን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባዉን እንዲያደርግ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ ወይም የጠየቀ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት የተሰጠዉን ሥልጣን ወይም የሕዝብ አደራ ያላአግባብ የተገለገለ እንደሆነ፤ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ለመንግስተ ወይም ለህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፣ያቀረበ፣የሰጠ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንደሆነ፤ ወይም በአግባቡ ለተፈጸመ ወይም በአግባቡ ለወደፊት ለሚፈጸም የመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም የመንግሰት ልማት ድርጅት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ስራ የማይገባ ጥቅም ለማንኛውም ሰዉ የሰጠ ወይም ከማንኛዉም የመንግሥት ወይም ህዝባዉ ድርጅት ሠራተኛ የተቀበለ እንደሆነ በሙስና ወንጀል ፈጻሚነት ተጠያቂ ይሆናል በማለት ይገልጻል (በአዋጁ አንቀጽ 4(2))፡፡

ሙስና ወንጀልን በተመለከተ በቀጥታ ትርጉም የሚያስቀምጥ ሳይሆን ምን አይነት ድርጊት ሲፈጸም በሙስና ወንጀል ሊያስቀጣ እንደሚችል የሚገልጹ ናቸዉ፡፡

ሆኖም ሙስና ከሌሎች ወንጀሎች የራሱ የሆነ ልዬ ባህርይ ያለዉ በመሆኑ በአዋጅ የተለያዬ ድርጊቶችን የሙስና ወንጀል በማድረግ በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የተሻሻለዉ የጸረ-ሙስና ልዬ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(1)(1) የሙስና ወንጀል ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተሰጠዉ ትርጓሜ እንደሚኖር ይገልጻል፡፡ የመስና ወንጀሎች ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ የሚፈጸም ወንጀል ነዉ፡፡

የሙስና ወንጀሎች ልዬ ባህሪያት

  1. ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በተመለከተ በሙስና ወንጀል ፈጻሚነት የሚጠየቁት የመንግሥት መስሪያ ቤት ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅት እና የህዝባዊ ድርጅት ስራ ጋር በተያያዘ በህጉ የተጠቀሱ ድርጊቶችን በመተላለፍ የሚፈጽም የመንግሰት ሠራተኛ ወይም ኃላፊ ወይም ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተያያዘ የህጉ ድንጋጌ የተላለፈ ማንኛዉም ግለሰብ የሚመለከተ ነዉ፡፡ ህዝባዊ ድርጅት ሲባል በማንኛዉ አግባብ ከአባላት ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለህዝባዊ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ሌላ ሀብትን የሚያስተዳድር አካልንና አግባብነት ያለዉን ኩባኒያ የግል ዘርፍ የሚያካትት ሲሆን፤ የሃይማኖት ድርጅትን፣የፖለቲካ ፓርቲን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅትን እና እድርንና ተመሳሳይ ባህላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ይዘት ያለዉ ማህበርን አያካትትም፡፡
  2. ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም ጉዳት ለማድረስ በማስብ የሚፈጸም መሆኑ፤ የሙስና ወንጀሎች ሕግን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአብዛሃኛዉ የማይገባ ጥቅም ለማገኘት ወይም ለማስገኘት የሚፈጸሙ ናቸዉ፡፡ የማይገባ ጥቅም ማለት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ወይም አግባብ ባለሆነ መንገድ የተገኘ ጥቅም ማለት ነዉ (በአዋጁ አንቀጽ 2(14))፡፡

ጥቅም በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ2(13)

  • 1ኛ. በገንዘብ ወይም በማናቸዉም ዋጋ ባለዉ መያዣ ወይም በሌላ ንብረት ወይም በንብረት ላይ ያለን ጥቅም (መብት)፤
  • 2ኛ. ማንኛዉንም ሹሜት፣ ቅጥር፣ ወይም ዉል
  • 3ኛ. ብድርን፣ግዴታን ወይም ማናቸውንም ዕዳ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈልን፣ማስቀረትን፤ ማወራረድን፤ወይም ከእነዚህ ነገሮች ነጻ ማድረግን፤
  • 4ኛ. ከተመሰረተ ወይም ካልተመሰረተ የአስተዳደር፣ የፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ክስ ወይም ካስከተለዉ ወይም ከሚያስከትለዉ ማናቸዉም ቅጣት ወይም የችሎታ ማጣት በማዳን ወይም ይህን በመሰለ ዘዴ የሚደረግን አገልግሎት ወይም ውለታ፤
  • 5ኛ. ማናቸውንም መብት ወይም ግዴታ መፈጸምን ወይም ከመፈጸም መታቀብን፤
  • 6ኛ. ከተጠቀሱት ዉጭ በገንዘብ የማይተመን ማናቸውንም ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት፤ እና ከተጠቀሱት ጥቅሞች አንዱን ማቅረብን፣ ጥቅሙ የሚገኝበትን መንገድ ማመቻቸትን ወይም ይህንኑ በሚመለከት የተስፋ ቃል መግባትን ወይም መቀበልን ያካትታል፡፡

የሶስተኛ ወገን ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማስብ መሆኑ

የሙስና ወንጀል የሚፈጸመዉ ጥቅም ለማገኘት ወይም ለማስገኘት ብቻ ሳይሆን በሚሰራበት የመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም ህዝባዊ ድርጅትን ጥቅም ወይም መብት ወይም የሌላ ግለሰብ ጥቅም ወይም መብት ላይ ህጉን በመተላለፍ ጉዳት ካደረሰ ጥቅም ባያገኝም በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ጥቅም የማግኘት ወይም ጉዳት የማድረስ ሀሳብ በሕግ ግምት የሚወሰድ ስለመሆኑ

ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር የሙስና ወንጀሎቹ የተፈጸሙት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም ሌላዉን ሰው ለመጉዳት መሆኑ በተደነገገ ጊዜ በድንጋገዉ የተመለከተው ግዙፋዊ ፍሬ ነገር መፈጸሙ ከተረጋገጠ ድርግቱ የተፈጸመው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም ሦስተኛ ወገንን መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት እንደሆነ ይገመታል፡፡ በህጉ መሠረት ክስ የቀረበበት ሰዉ የሙስና ወንጀል በመተላለፍ የፈጸመው ግዙፋዊ ነገር ወይም ድርጊቱ ከተረጋገጠ፤ ያደረሰዉ ጉዳት ወይም ያገኘዉ ጥቅም አስበዉ እንደሆነ ህጉ ግምት ይወስዳል፡፡ ሆኖም በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው በሌላ ማስረጃ የቀረበበት ክስ ማስተባበል ይችላል፡፡

በሕግ አግባቡ ለተሰራዉ ስራ ጥቅም መቀበል ወይም መስጠት በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ሌላ ልዬ ባህረይ ነዉ፡፡

ማንኛዉ የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በሕግ የተጣለበት ግዴታ ከመፈጸሙ በፊት ይሁን ከፈጸመ በኃላ ጥቅም ያገኘ እንደሆነ በህጉ የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ያስጠይቃል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ግታዉን ለተወጣዉ ሠራተኛ ጥቅም የሰጠ ማንኛዉ ግለሰብ በሙስና ወንጀል ያስቀጣል፡፡

በሙስና ወንጀል ልዬ በሚያደርገዉ ተጎጂ መንግሰት ወይም ህብረተሰቡ መሆኑ ወይም የአክሲዮ ባለቤቶች መሆናቸዉ ነዉ፡፡

ምንም እንኳን ጉቦ መስጠት አይነት ጉዳይ የግለሰብ ተጎጂ ሊኖር የሚችል ቢሆንም በሙስና ወንጀል ቀጥታ ተጎጂ የሚሆነዉ አብዛሃኛዉ ማህበረሰቡ ነዉ፡፡

ሙስና ዉስብስብ ከሚያደርጉት አንዱ ቀጥተኛ ተጎጂ ግለሰብ ባለመኖሩ ምርመራ፤ ክስ እና የፍርድ ሂደት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ሌላዉ ጥቅም ሰጪ ይሁን ጥቅም ተቀባይ በስምምነት የሚፈጽሙ በመሆኑ የምርመራ ሆነ የክስ ሂደት አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ህብረተሰቡ የሙስና ድርጊት ሁሉም ህብረተሰብ የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ሙስና በመዋጋት ሁሉም የድርሻዉን መወጣት አለበት፡፡

በአጠቃላይ ወንጀል ለማለት ድርጊትን የሚከለክል ሕግ፣ የተለከለ ድርጊት መጸምንና በሕግ የተከለከለ ድርጊት የፈጸመበት የሀሳብ ክፍልን በአንድነት ተሟልቶ ሲገኝ ስለመሆኑ ተገልጸል፡፡ የሙስና ወንጀል በሙስና ወንጀል ህጉ የሚከለከሉ ተግባራት የገለጸ ሲሆን የሀሳብ ክፍል በተመከለተ በሕግ ግምት የሚወሰድ ነዉ፡፡ የተከለከሉ ተግባራት በህጉ ከተደነገጉት መካከል ሥልጣን አለአግባብ መገልገል፤ የመንግሥት ስራ በማይመች አኳኃን መምራት፤ ጉቦ መስጠት ወይም መቀበል እና ሎሎች ይገኛሉ፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ