የሰንደቅ ዓላማ ሕግ በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ቀደም ሲል የወጡ ሰንደቅ ዓላማን የሚመለከቱ የተለያዩ ሕጎች ተደንግገዉ ይገኛሉ፡፡ ስለ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 1 እና 2 የተደነገገ ሲሆን ይህን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ተከትለው ቀደም ሲል የወጡ እና በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ የየራሳቸውን ድንጋጌዎች አስፍረዋል፡፡ አሁን ያለው የፌዴራል መንግሥት ቅርፅ የሪፐብሊኩ እና የክልሎች ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲኖሩ የሚፈቅድ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የሰንደቅ ዓላማን ምንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ እንዲሁም ሰንደቅ አለማ ጋር ተያይዞ የተከለከሉ ተግባራት እና ቅጣት የሚሉትን እንመለከታለን፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ምንነት

በሀገራችን የሚገኙ አብዛኞቹ መዝገበ ቃላቶች ተመሳሳይ ትርጉም ሰጥተውት የሚገኝ ሲሆን

ሰንደቅ፡ ማለት “ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር፣ ሕዝብ “ማለት ሲሆን

ዓላማ፡ “ምልክት፣ የህዝቦች የማንነት መለያ” ማለት ነው፡፡ ይህም ሰንደቅ ዓላማ “የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነጻነት፣ እድገትና ማህበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡” የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ከምልክትነት ከፍ ያለ ነው፡፡ ዜጎች ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆሙ ቁጥር ልዩ ስሜት ውስጥ የሚገቡት በሀገርና በሕዝብ ፊት እንደቆሙ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

  • ለሀገራችን ነጻነት የተፋለሙ የጦር ጀግኖቻችን
  • ሀገራችንን የወከሉ አትሌቶች በዓለም አደባባይ

የሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት የሕዝብና የሀገር ክብር፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ከፍ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የሕዝብ ያለፈ ታሪክ፣ ወቅታዊ ገጽታና የወደፊት ዓላማ ነፀብራቅም ነው፡፡

ለሀገርና ለሕዝብ የጠለቀ ፍቅር፣ ክብርና ቁርጠኝነት ያለው ዜጋ የተግባር ልዕልና የሚገለጠውም ሰንደቅ ዓላማውን በሰቀለበት ማማ ከፍታ ነው፡፡ በተቃራኒው የሰንደቅ ዓላማ መውረድ/መረገጥ የሀገርና የሕዝብ ሽንፈት ወይም ውርደት ምልክት ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ምልክት (መገለጫ) ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የህዝቦች ባህል፣ እምነትና መገለጫ እንዲሆን ተደገርጎ የሚቀረጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፣ የኢንባሲና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሀገሮች ውክልና የሚገለፀው በሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መግለጫ ነው፡፡

ታሪካዊ አመጣጥ

ሰዎች ከ4000 ዓመታት በፊት ጀምረው የሚገልፃቸውን ምልክት ይጠቀሙ ነበር፡፡ በጥንታዊ ግሪክ ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ፣ ጀግንነት ሲፈፅሙ እና ዘመቻ በሚመሩበት ጊዜ በወቅቱ የብረት ቁራጭ በምልክትነት ያስቀምጡ ነበር፡፡ 2000 ዓመታት በኋላ ከብረት ምልክትነት ቀስ በቀስ ወደ ጨርቅ ባንዲራዎች መጡ፡፡ ከ15ኛው ክ/ዘመን የአውሮፓ ሀገራት ዓለም አቀፍ ዳሰሳ በየሃገራቸው መርከቦች ይህንን ምልክት በመጠቀም በመካከላቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ያለ መግባባቶች ለማስወገድ ተጠቅመውበታል፡፡ ቅኝ ገዢዎች፤ በአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና ኤስያ ነባር ህዝቦችን በስነልቦናም ጭምር የገዢዎቻቸውን አስተሳሰብ እንዲሸከሙ አድርገውበታል፡፡ የሀገሮች መለያ ምልክት (የብሔራዊ ማንነት መገለጫ) እስከ መሆን ደርሷል፡፡ አሁን ላይ ሃገሮች በተለይ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ስምምነት አባልነት ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን የሃገራቸው ፖለቲካዊና ማሕበራዊ መገለጫ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ በጠቅላላው

ሰንደቅ ዓላማ የሀገሩና የህዝቡ እኩልነትና አንድነት መገለጫ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ሕዝብና መንግሥት እንደ ሕዝብና መንግሥት ስለ መኖራቸው፡፡

ብሔራዊ ዓርማ ህዝቦች የሚኖራቸው አጠቃላይ ፍልስፍና፣ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ ምን እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ከ195 (ዩኤን) ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል የ64 ሃገራት ሃይማኖታዊ ምልክትን እንደ ብሔራዊ አርማ አካተዋል፡፡ 48% የክርስትና ሃይማኖት፣ 33% ደግሞ የእስልምና ሃይማኖትን የሚወክል ዓርማን ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በኤስያ ከሚገኙ ሌሎች ቡድሂዝምን የመሳሰሉ እምነቶች ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎች ሀገራት ለነፃነታቸው ከከፈሉት መስዋእትነት ጋር የሚገናኙ አርማዎችን ይጠቀማሉ፡፡

ብሔራዊ ዓርማ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር መገለጫ ማህተም አድርገውም ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ዓርማውን ህጋዊ ለሆኑ ሰነዶች ሁሉ ጥቅም ላይ ያውሏቸዋል፡፡

ሌሎች ሀገራት ደግሞ ሰንደቅ ዓላማውንና ብሔራዊ ዓርማውን ነጣጥለው ይጠቀማሉ፡፡

ለምሳሌ፡- የአውስትራሊያ ሰንደቅ ዓላማ አምስት ኮከብ ያለው እና በቀይና ነጭ የተደበላለቀ መስቀል በጥቁር ሰማያዊ መደብ ላይ ያረፈ ነው፡፡ በሀገሪቱ ብሔራዊ ሰነዶች ላይ የሚጠቀሙት ዓርማ ግን የካንጋሮና በሀገራቸው ብቻ የምትገኘውን ከንጋሮ ምስል ነው፡፡

የሩስያ ሰንደቅ ዓላማም በተመሳሳይ ሰንደቅ ዓላማቸው ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ ቀለም ያለው ሲሆን ብሔራዊ ዓርማቸው (National emblem) ደግሞ ሁለት ራስ ያለው ንስር፤ ይህም የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ዓርማ ከሰንደቅ ዓላማቸው የተለየ መሆኑን ያሳያል፡፡

አሜሪካም እንደ አውስትራሊያና ሩስያ ሁሉ ብሔራዊ ዓርማዋ እና ሰንደቅ ዓላማዋ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካንን ወክለው በሚዘጋጁ ሀገራዊ ከሰንደቅ ዓላማው ጋር በመደረብ ሲጠቀሙበት ሰነዶች ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ ዓርማ ይታያል፡፡

ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ በኢትዮጵያ

ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ታሪክ አለው፡፡ ነገስታት የራሳቸውን ምልክት እያተሙበትም ቢሆን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማቱን ጠብቆ ብዙ ዘመናትን ቆይቷል፡፡

“የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ” አሁን ባለው ቅርፅ ስራ ላይ የዋለው በ1880ዎቹ መጨረሻ ላይ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

– በ1898 ዓ.ም በተሰጠ ትርጉም

  • አረንጓዴ —› የተስፋ፣
  • ቢጫ ——› የብርሃን፣
  • ቀይ ——-› የመስዋዕትነት ምልክት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ጊዜ መንፈሳዊ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እየታከለበት ከዘመን ዘመን ተሻግሯል፡፡

አራት መአዘኑ ሰንደቅ ዓላማ ከመጽናቱ በፊት ሶስት እርስ በእርስ ባልተያያዙ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡

  • ከ1889-1967 ሰንደቅ ዐላማው ከይሁዳ አንበሳ ዓርማ ጋር፡፡ (ይህ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ራስ ተፈሪያውያን በብዛት ይጠቀሙበታል፡፡)
  • ከ1967-1979 እ.ኤ.አ እና ከ1983-1987 ሰንደቅ ዓላማው ያለምንም ተጨማሪ ዓርማ፡፡
  • ከ1975-1987 የደርግን ዓርማ ይዞ ከልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ ጎን ለጎን (በጣም አልፎ አልፎ) ፡፡
  • ከ1987-1991 የኢህዴሪ ሰንደቅ ዓላማ
  • ከ1988 ጀምሮ – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ

የአድዋ ድል በሰንደቅ ዓላማችን ስር ተንበርክከን ለህዝባችንና ለሀገራችን ክብር ለመዋደቃችን ዐብይ አብነት ነው፡፡ ዛሬ ድህነት መዋጋት የነጻነትና የሰንደቅ ዓላማ ትግል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ብዝሃነትን ያስተናገደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ አንድና የተዋሀደ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብን መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ለመፍጠር ሰንደቅ ዓላማችን የሚኖረው በአንድ የማስተባበርና የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን የመገንባት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ሠንደቅ ዓላማ ሀገርና ሕዝብን በአንድ ጥቅም ዙሪያ የሚያሰባስብ ምልክት ነው፡፡ ልዩ ልዩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች ሳይቀር ለአንድ ዓላማ የሚወክል የጋራ መንፈስ ነው፡፡

የ.ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ አርማ ሕጋዊ ትርጉም

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ (3) “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀል ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡” ብሔራዊ ዓርማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል፡፡ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ በአዋጅ ቁጥር 654/2001 ዓ.ም አንቀጽ (5)፣ ሰንደቅ ዓላማው የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍላጎትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸው መገለጫ ምልክታቸው ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል፤ አንቀጽ 6(1)፤ ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ዓርማው በሰንደቅ ዓላማው መካከል ላይ የሚያርፈው የክቡ ዙርያ የአረንጋዴውንና የቀዩን ቀለም ቁመት አጋማሽ አካል ይሆናል፡፡ እነዚህ ቀለማት አግድም የተዋቀሩና እኩል ስፋት የሚኖራቸው ሆኖ የሰንደቅ ዓላማው ወርድ የቁመቱን እጥፍ ይሆናል (አንቀጽ 6(2)፡፡ አንቀጽ 6/4/ሀ ሰንደቅ ዓላማው ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረ ኮከብ የሚኖረው ሲሆን ቀጥታና እኩል በሆኑ መስመሮች መተላለፊያ ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ጨረር ይኖረዋል፡፡

የ.ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማቱ ትርጉም

  • አረንጓዴው፡- የስራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት (አንቀጽ 7/1/)
  • ቢጫው፡- የተስፋ፣ የፍትሕና የእኩልነት ምልክት (አንቀጽ 7/2/)
  • ቀዩ ፡- ለነጻነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋእትነትና የጀግንነት ምልክት (አንቀጽ 7/3/) ነው፡፡

የ.ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብሔራዊ ዓርማ ትርጉም

ዓርማው ብዝሀነትን በአግባቡና በብቃት በማስተናገድ፣ የግለሰብ ነፃነቶችና መብቶችን በአግባቡ በማክበርና ለቡድን መብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገንባት ነው፡፡ አስተማማኝ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፤ የኢፌዴሪ መንግሥት ከማናቸውም ሃይማኖታዊ ምልክቶች ወይም እምነቶች ጋር የማይያያዝ ወይም የማይወግን መሆኑን ያመለክታል፣ ተቻችሎና ተከባብሮ በነጻነት የመኖር ተስፋቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡

  • ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች፡- የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶች እኩልነትን (አንቀጽ 8/2/)፣
  • ቀጥታና እኩል ከሆኑ መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት፣
  • ቢጫ ጨረር በመፈቃቀድ አንድነት ለመሰረቱት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ይጠቁማል፡፡ (አንቀጽ 8/3/)
  • ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ ተገቢውን ሕጋዊ ክብር ስለ መስጠት

የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ እና ለብሔራዊ ዓርማው በአዋጅ ቁ. 654/2001 ተገቢ ክብር መስጠት እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡

የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በየቀኑ ከጧት 12፡00-ምሽት 12፡00 ሠዓት ሰንደቅ ዓላማውን ይሰቅላሉ፡፡

ሲሰቀልና ሲወርድ ዜጎች ተገቢውን ክብር የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡

የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ አባል ክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ ከመጣ በስተቀኝ በኩል ይሆናል፡፡ ሁለት ከሆኑ ከፍ ብሎ ከመሀል፣ ሁሉም ከሆኑ የክልሎቹ በፊደል ቅደም ተከተል የክልሎቹ ሰንደቅ ዓላማዎች በክልሎቹ ስያሜና በአማርኛ ፊደል ተራ መሠረት ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡

የሀገር መሪዎች ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሠንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል፤ የአስክሬን ሳጥኑ በሰንደቅ ዓላማ ይሸፈናል፡፡

የሰንደቅ ዓላማውን ክብር መጠበቅ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ማክበር ነው፡፡

ብሔራዊ ዓርማውን ማክበር የዜጎችን እኩልነትና በመከባበር አብሮ ለመኖር የገቡትን ቃልኪዳን ማክበርም ነው፡፡

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 863 /2006 መሠረት ጥቅምት አንደናኛ ሳምንት ዕለተ ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃል መነሻነት ተከብሮ ይዉላል፡፡ በዚህ መሠረትም ዘንድሮ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የተከለከሉ ተግባራት

በዚህ አዋጅ ቁጥር 23 መሠረት ከዚህ በታች የተመለኩትን ተግባራት መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡

  • ሰንደቅ ዓለማውን በዚህ አዋጅ በተደነገገው መሠረት ዓርማውን ሳያካትቱ መጠቀም፤
  • ሰንደቅ ዓላማው ላይ ቃላቶችን መፃፍ ሌሎች ምልክቶችን ወይም ስዕሎችን ለጥፎ መገልገል፤
  • ያረጁ፣ የተበላሹ፣ ቀለማቸው የደበዘዘና የተቀደዱ ሰንደቅ ዓላማዎችን መጠቀም ወይም መገልገል፤
  • ሰንደቅ ዓላማው በወጣበት ሰንደቅ (ምሰሶ) ላይ ማስታወቂያ መለጠፍ፣ ያለአግባብ ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎችን ወይም አርማዎችን ጨምሮ ማውለብለብ ወይም መገልገል፤
  • ሕዝብ በተሰበሰበት ቦታ ሰንደቅ ዓላማውን በጽሁፍ ወይም በቃላት፣በድርጊት ወይም በሌላ በማንኛውም አኳኋ መድፈር ወይም ማዋረድ ወይም ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ፤
  • የሰንደቅ ዓላማውን ቀለማት ቅደም ተከተል እንዲሁም የብሔራዊ ዓርማውን መጠን ሳይጠብቁ ማዘጋጀትና መገልገል፤
  • ሰንደቅ ዓላማውን በዚህ አዋጅ ከተጠቀሰው የማውረጃ ጊዜ በላይ ማቆየት፤
  • በስብሰባ ወይም በማናቸውም መሰል ክንውኖች ሰንደቅ ዓላማውን የጠረጴዛ መሸፈኛ ማድረግ፤
  • ሰንደቅ ዓላማን የህንፃ ወይም የሌሎች ቁሶች መሸፈኛ ማድረግ፤
  • ሰንደቅ ዓላማውን በማነኛውም ንግድ መስተወቂያነት መጠቀም፤
  • ሰንደቅ ዓላማው በሚሰቀልበትና በሚወርድበት ጊዜ ተገቢውን ክብር አለመስጠት፡፡

ቅጣት

በአዋጁ አንቀጽ 23 ከንዑስ አንቀጽ 2 እስከ 11 ድረስ ተመለከቱትን የተከለከሉ ተግባራት በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ እስከ ሶስት ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ እስከ አምስት ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በአዋጁ የተመለከተውን ጥፋት የፈፀመው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ከሆነ የገንዘብ ቅጣቱ ከሁለት እጥፍ ያላነሰ ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 244 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ማንኛውም ሰው በተንኮል፣ በንቀት ወይም ይህን በመሳሰለ በማናቸውም ሀሳብ በግልጽ የታወቀውን አንድ የአገር ምልክት ማለትም የፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ወይም ዓርማን እንዲሁም የክልላዊ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማን ወይም ዓርማን በአዳባባይ የቀደደ፣ የቃጠለ፣ ያጠፋ፣ የደፈረ፣ ያበላሸ፣ የሰደበ ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የዋረደ እንደሆነ ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡

ማጠቃለያ

ሰንደቅ ዓላመችን ለሉዓላዊነታችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ በተቻለን መጠን ሁሉ ልናከብረው እና ከፍ እንዲል ለመድረግ የየበኩላችን ድርሻ ልንወጣ ይገባል፡፡ በጥረታቸው፣ ባላባቸውና በደማቸው ሰንደቅ ዓለማችን ከፍ ያደረጉ የሀገር ባለውለታወችንም ማክበር አለበን፡፡ በተጨማሪም በሕገ-መንግስቱ፣ በሰንደቅ ዓላማ አዋጁም ሆነ በመንኛውም ሕግ ሰለ ሰንደቅ ዓላማ የተደነገጉ ሕጎችን በማክበርና በማስከበር የበኩላችን ድረሻ መወጣት ተገቢነት ያለው ነው፡፡ እንዲሁም የተከለከሉ ተግባራትን ባለመፈፀም ከተጠያቂነት መጠበቅ አለብን እንላለን፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ