የማስታወቂያ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በዓለም እንዲሁም በሀገራችን እየተስፋፋ የመጣው የዲጂታል ኮሚውንኬሽን ቴክኖሎጂ ሰዎች የሚሰሩትን ምርትም ሆነ አገልግሎት ለሌሎች ሰዎች ተደራሽ ለማድረግና ለማስተዋወቅ እጅግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ አሁን አሁን መደበኛ በሚባሉት የሚዲያ ማስራጫዎችና ከዚህ ቀደም ከተለመዱት የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች በተጨማሪ የኢንተርኔት ድረ ገፅ (ቲክቶክና ፌስቡክ በመሳሰሉት የማኅበራዊ ሚዲያዎች) ዋነኛ የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ መሆን ጀምረዋል፡፡ የማስታወቂያ ሕግን አለማወቅ እና በሂደቱም የሚፈፀሙ የሕግ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንደሚያስከትሉ ተገንዝቦ ዘርፉ የሚፈልገውን ተገቢውን እውቀት እና የሚገዛበትን የሕግ ማዕቀፍ ጠንቅቆ ማወቁ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሚመጣብን ተጠያቂነት ሊታደገን ስለሚችል ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባናል፡፡ የማስታወቂያ ስራዎች የሚመሩበት ዋነኛው የሕግ ክፍል የሚገኘው በአዋጅ ቁጥር 759/2004 በተደነገገው አግባብ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የማስታወቂያ ምንነት እና ዓላማ፣ በማስታወቂያ ስራ ለመሰማራት ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች፣ የማስታወቂያዎች ይዘትና አቀራረብ፣ ክልከላና ገደብ የተደረገባቸው የማስታወቂያ ዓይነቶች እና የሕግ ተጠያቂነት የሚሉትን ጉዳዮች በአጭሩ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

የማስታወቂያ ምንነት እና ዓላማ

ማስታወቂያ ማለት አንድን ምርት፣ አገልግሎት፣ ክስተት ወይም ሀሳብ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ እና ፍላጎት ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ነው። ይህም በተለያዩ መንገዶች ሊከናወን ይችላል:: ለምሳሌ፡- በህትመት ሚዲያ (ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ እና ብሮሸሮች)፤ በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ (ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ እና ኢንተርኔት)፤ በማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ሌሎችም)፤ በውጭ ማስታወቂያዎች (ቢልቦርዶች፣ ፖስተሮች እና ሌሎችም) እና በቀጥታ ግንኙነት (ስልክ፣ ኢሜይል፣ እና ፊት ለፊት ውይይት) መንገዶች የማስታወቂያ ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 2/1/ ድንጋጌ መሠረት ማስታወቂያ ማለት የምርት ወይም የአገልግሎት ሽያጭ እንዲስፋፋ ወይም ስም፣ አርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም ዓላማ እንዲተዋወቅ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት የሚሰራጭ የንግድ ማስታወቂያ ሲሆን የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያንና የግል ማስታወቂያን ይጨምራል፡፡ በሕጉ መሠረት የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች የሚባሉት ደግሞ፡- መገናኛ ብዙሃንን፣ የውጭ ማስታወቂያን፣ የቴሌኮምን፣ የፖስታ፣ የኢንተርኔት ድረ ገፅ እና የፋክስ አገልግሎቶችን፣ ሲኒማን፣ ፊልምን፣ ቪዲዮን እና መሰል የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድን እንደሚጨምር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የማስታወቂያ ዓላማ ሰዎችን ስለ አንድ ነገር ማሳወቅ፣ ፍላጎት መፍጠር፣ እና ሽያጭ ማሳደግ ነው። ውጤታማ ማስታወቂያ ግልጽ፣ አጭር፣ እና ትኩረት የሚስብ መሆን አለበት።

በማስታወቂያ ስራ ለመሰማራት ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች

በማስታወቂያ ስራ ላይ ሊሰማሩ የሚችሉ ሰዎችን በተመለከተ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት የሚገባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የመጀመርያው ቅድመ-ሁኔታ ዜግነት ነው፡፡ የማስታወቂያ አዋጁ በአንቀጽ 4(1) እና (2) ስር በግልጽ እንዳስቀመጠው በማስታወቂያ ስራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ጠያቂው ግለሰብ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ መሆን ያለበት ሲሆን ፍቃድ ጠያቂው ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተቋቋመና በካፒታሉ ውስጥ የውጭ አገር ዜጋ ድርሻ የሌለበት የንግድ ማኅበር መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ ሀገር ዜግነት የተሰጣቸው በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጪ አገር ዜጋ በማስታወቂያ ስራ ላይ የመሰማራት መብት ያላቸው መሆኑን ከአዋጁ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ይሁንና ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻውን የማስታወቂያ ወኪል ወይም አስነጋሪ ለመሆን ያስችላል ማለት ግን አይደለም፡፡ ይልቁንም በማስታወቂያ ስራ ላይ ለመሰማራት አግባብ ካለው የመንግሥት አካል ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ በአዋጁ አንቀጽ 5 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ማንኛውም ማስታወቂያ አሰራጭ ማስታወቂያ በማዘጋጀት ሥራ ላይ ለመሰማራት አግባብ ካለው የመንግሥት አካል የማስታወቂያ ሥራ ፈቃድ ማውጣት አለበት፡፡ ይሄም ማለት አሁን አሁን በስፋት እየተለመደ የመጣው በኢንተርኔት ድረ ገፅ እና እንደ ቲክቶክና ፌስቡክ ባሉ መሰል የማስራጫ መንገዶች ላይ ማስታወቂያዎችን በክፍያ እንደሚሰሩ በመግለፅ ብዙ ተከታይ ባላቸው የማኅበራዊ ድህረ ገፆቻቸው ላይ አድራሻ በማስቀመጥና የቪዲዮ፣ የፊልም ወይም የሲኒማን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከሚመለከተው አካል ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ስራ ፍቃድ ሳይወስዱ የማስታወቂያ ስራዎችን መሥራት የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል የሚያስገነዝብ ነው፡፡ የማስታወቂያ ፍቃድን በተመለከተ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ምርቱ፣ አገልግሎቱ ወይም ሌላ መልዕክት እንዲተዋወቅለት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የማስታወቂያ ሥራ ፈቃድ ማውጣት ሳያስፈልገው የራሱን ማስታወቂያ አዘጋጅቶ ማሰራጨት ወይም ማስታወቂያውን አዘጋጅቶ በማስታወቂያ አሰራጭ አማካኝነት እንዲሰራጭለት ማድረግ ይችላል፡፡

የማስታወቂያዎች ይዘትና አቀራረብ

በአዋጁ አንቀጽ 6 መሠረት የማስታወቂያዎች ይዘትና አቀራረብ ተከታዮቹን ነጥቦች ከግምት ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ እነሱም፡-

  • ማንኛውንም ሕግ ወይም መልካም ሥነ-ምግባር የማይፃረር፣ አሳሳች ወይም ተገቢ ካልሆነ አገላለጽ ነፃ የሆነ፣ የሕብረተሰቡን ማኅበራዊና ባህላዊ እሴት የሚያከብርና የሸማቹን ሕጋዊ ጥቅም የማይጎዳ፣ የሚተዋወቀውን ምርት ወይም አገልግሎት እውነተኛ ባህሪ፣ ጥቅም፣ ጥራትና ሌላ መሰል መረጃዎችን የሚገልጽ፣ የሌሎችን ሰዎች ምርት ወይም አገልግሎት የማያንቋሽሽ እና የአገርን ክብርና ጥቅም የሚጠብቅ እንዲሁም የሙያ ሥነ-ምግባርን የሚያከብር ይዘትና አቀራረብ ያለው መሆን አለበት፡፡
  • በተጨማሪም ከይዘት አንፃር በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ከሌሎች ፕሮግራሞች የተለየ መሆኑ በግልፅ በሚታወቅ መልኩ እና በዜና መልክ ባልተዘጋጀ መልኩ መቅረብ ያለበት ሲሆን፡፡ በተጨማሪም የማስታወቂያ ወኪል የአንድን ሰው ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት የሚያስተዋውቅ የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጅቶ ባሰራጨ በሦስት ወራት ውስጥ የሌላ ሰውን ተመሳሳይ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት በተመሳሳይ የማስታወቂያ ተዋናይ ምስል ወይም ድምፅ አዘጋጅቶ ማሰራጨት የለበትም::
  • ክልከላ የተደረገባቸው ማስታወቂያዎች

የሚከተሉትን ማስታወቂያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማንኛውም የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡-

  • አግባብ ባለው የመንግሥት አካል በአደንዛዥ እፅነት የተመደበን ማንኛውንም እፅ የሚመለከት ማስታወቂያ፤ ያለሕክምና ትእዛዝ የማይሰጥ ወይም በጥቅም ላይ የማይውል መድሀኒትን ወይም የሕክምና መገልገያን ተጠቃሚው በቀጥታ እንዲጠቀም የሚገፋፋ ማስታወቂያ፤ ናርኮቲክ መድሐኒትን ወይም ሳይኮቴራፒክ ንጥረ ነገርን የሚመለከት ማስታወቂያ፤ የጦር መሳሪያ ማስታወቂያ፤ የቁማር ማስታወቂያ፤የሕገ ወጥ ምርት ወይም አገልግሎት ማስታወቂያ፤ የአራጣ አበዳሪ ማስታወቂያ፤ የጥንቆላ ማስታወቂያ፤ የሲጋራ ወይም የሌሎች የትምባሆ ውጤቶች ማስታወቂያ፤ የፖለቲካ ግብ ያለው ማስታወቂያ(ነገር ግን አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የምርጫ እጩ ተወዳዳሪ በምርጫ ወቅት የሚያሰራጨውን የምርጫ ውድድር ማስታወቂያ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቱ የሚያሰራጨውን የአድራሻ ለውጥ፣ የስብሰባ ጥሪ እና መሰል ማስታወቂያዎችን የሚከለክል አይደለም።)እና ሌሎች በሕግ የተከለከሉ ማስታወቂያዎች፡፡
  • ገደብ የተደረገባቸው ማስታወቂያዎች
  • የአልኮል መጠኑ ከ12 በመቶ በላይ የሆነ ማንኛውንም መጠጥ የሚመለከት ማስታወቂያ ከውጭ ማስታወቂያ እና እለታዊና ሳምንታዊ ካልሆነ ጋዜጣ እና መጽሔት በስተቀር በሌሎች የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች (ማለትም በብሮድካስት አገልግሎት፣ በስልክ አገልግሎት ወይም በፖስታ አገልግሎት የማስራጫ መንገዶች) አማካኝነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡ ሌላው እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው የአልኮል መጠኑ ከ12 በመቶ በላይ የሆነን መጠጥ በውጭ ማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ ለምሳሌ፡- በሕንጻ ወይም በማናቸውም ስትራክቸር ወይም በትራንስፖርት ተሽከርካሪ ላይ በሚፃፍ ወይም በሚለጠፍ፣ በተንጠልጣይ ነገር፣ በፖስተር፣ በስቲከር፣ በብሮሸር፣ ሊፍሌት ወይም በራሪ ወረቀት በመጠቀም ማሰራጨት ቢቻልም በሌላ በኩል ደግሞ እንደ የኤሌክትሮኒክ ስክሪን፣ በድምፅ ማጉያ፣ የድምፅ ካሴት ወይም በሌላ በምስልና በድምፅ በሚሰራጭ የውጭ ማስታወቂያ መንገዶች ማሰራጨት አይቻልም፡፡ ሌላው ማንኛውም የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ የአልኮል መጠጡን መውሰድ ለጤና ተስማሚ እንደሆነ፣ ግላዊ ወይም ማኅበራዊ ስኬትን እንደሚያስከትል፣ የተሻለ ሥነ ልቦናዊ ወይም አካላዊ ብቃት እንደሚያስገኝ ወይም ፈዋሽ እንደሆነ የሚገልጽ ወይም በተደጋጋሚ ወይም ከልክ በላይ እንዲጠጣ የሚገፋፋ፤ ከአልኮል ሱስ መጠበቅን የሚያጣጥል ወይም የሚቃወም፣ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ወይም አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን የማስታወቂያው ተዋናይ አድርጎ የሚጠቀም፤ ወይም ሌላ መሰል መልእክት የሚያስተላልፍ መሆን የለበትም፡፡ በተጨማሪም የአልኮል መጠጥ የውጭ ማስታወቂያ ከልጆች መዋያ ማዕከል፣ ከትምህርት ቤት፣ ከህክምና ወይም ታሪካዊ ተቋም፣ ከሲኒማ ቤት፣ ከቲያትር ቤት ወይም ከስታዲየም በመቶ ሜትር ራዲየስ ውስጥ እንዲቀመጥ መደረግ የለበትም፡፡

የሕግ ተጠያቂነት

የማስታወቂያ ስራ ሊከተለው የሚገባ ሕግና ስርዓት ያለው እንደመሆኑ ሕግና ስርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ የማስታወቂያ ስራ ላይ መሰማራትም ሆነ ማሰራጨት አስተዳደራዊ፣ ፍትሀ ብሔራዊና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ከወንጀል አንፃር ሊኖር የሚችለውን የሕግ ተጠያቂነት ሁኔታ እንደሚከተለው ተዳሷል፡-

  • በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 34/1/ሀ/ መሠረት አንድ ሰው በአዋጁ አንቀጽ 5/1/ እና/2/ መሠረት በማስታወቂያ ስራ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ፍቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኝ በማስታወቂያ ስራ ላይ የተሰማራ እንደሆነ በንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ አንቀጽ 49/2/ መሠረት ለስራው የሚጠቀምበት መሳሪያ መወረስን ጨምሮ ከብር 150ሺ እስከ 300ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ7ዓመት እስከ 15ዓመት በሚደርስ የፅኑ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡
  • ከይዘትና ስርጭት አንፃር በመገናኛ ብዙሀን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ከሌሎች ፕሮግራሞች የተለየ መሆኑ በግልፅ በሚታወቅ መልኩ እና በዜና መልክ ባልተዘጋጀ መልኩ መቅረብ ያለበት መሆኑን፣ የማስታወቂያ ወኪል የአንድን ሰው ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት የሚያስተዋውቅ የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጅቶ ባሰራጨ በሦስት ወራት ውስጥ የሌላ ሰውን ተመሳሳይ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት በተመሳሳይ የማስታወቂያ ተዋናይ ምስል ወይም ድምፅ አዘጋጅቶ ማሰራጨት የለበትም በማለት በአዋጁ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ (2)(3) እና(4) የተደነገጉትን መተላለፍ፣ በአዋጁ አንቀጽ 26(3) ስር 12 በመቶ በላይ የአልኮል መጠን ያላቸውን መጠጦች የማስታወቂያ ስርጭት በተመለከተ የተቀመጡ ገደቦችን መተላለፍ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 34/1/ለ/ መሠረት ከብር 10ሺ በማያንስና ከብር 100ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግገዋል፡፡
  • በአዋጁ አንቀጽ 6/1/ ስር የተዘረዘሩት የማስታወቂያ ይዘት የተመለከቱ ክልከላዎችን መተላለፍ፣ ሕግን ወይም መልካም ስነምግባርን የሚፃረሩ እንዲሁም አሳሳች ወይም ተገቢ ያልሆኑ ማስታወቂያዎች ተብለው በህጉ የተደነገጉትን ማስታወቂያዎች ሰርቶ ማሰራጨት፣ በአዋጁ አንቀጽ 26(1)፣(2) እና (4) የተጠቀሱትን ክልከላዎች በመተላለፍ የአልኮል ይዘታቸው ከ12 በመቶ በላይ የሆኑ መጠጦችን ከተፈቀደው የማስታወቂያ መንገድና ቦታ ውጭ ማስተዋወቅ ከ20ሺ ብር በማያንስና ከብር 150ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
  • በአዋጁ አንቀጽ 25/1/ ስር የተመለከቱትን በሕግ ክልከላ የተደረገባቸውን ማስታወቂያዎች ማሰራጨት ደግሞ ከ30ሺ ብር በማያንስና ከብር 250ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
  • በአዋጁ አንቀጽ 34/2/ መሠረት ከፍ ሲል ከተመለከተው የገንዘብ መቀጮ በተጨማሪ ጥፋተኛ የሆነው ሰው ከሕገ ወጥ ማስታወቂያ ሥራው ያገኘው ገቢ ይወረሳል፡፡

ከቅጣት ጋር በተያያዘ ሌላው ከግንዛቤ ልናስገባው የሚገባው ጉዳይ በአዋጁ ላይ በዝርዝር የተጠቀሱት ሌሎች ሁኔታዎች ማለትም የተለየ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ስለሚያስፈልገው ማስታወቂያ፣ አካለመጠን ያልደረሰ ልጅን ስለሚመለከት ማስታወቂያ፣ ስለጸረ አረም ወይም ጸረ ተባይ በተመለከተ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ወዘተ በተመለከተ የተጠቀሱ ዝርዝር ሁኔታዎችን አለማሟላት በአዋጁ አንቀጽ 34 መሠረት የሚያስቀጡ መሆናቸውን መገንዘብ የሚገባ ሲሆን፡፡ በተጨማሪም ከፍ ሲል ያየናቸው በአዋጁ ላይ ተጠቅሰው የሚገኙት ቅጣቶች ተፈፃሚ የሚሆኑት ድርጎቶቹ በሌላ ሕግ የበለጠ የማያስቀጡ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ድርጊቱ በሌላ ሕግ በአዋጁ ከተገለፀው የቅጣት መጠን በላይ የሚያስቀጣ በሆነ ጊዜ ለጉዳዩ የምንጠቀመው የበለጠ የሚያስቀጣውን ሕግ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 8(12) መሠረት በትክክለኛ ዋጋው እየተሸጠ ያለን ምርት ወይም አገልግሎት በነጻ እየተሰጠ ወይም በቅናሽ እየተሸጠ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ ማስታወቂያ አሳሳች ወይም ተገቢ ያልሆነ ይዘት ወይም አቀራረብ እንዳለው ማስታወቂያ ይቆጠራል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 34(1)(ሐ) መሠረት ደግሞ መሰል አሳሳች ይዘት ያለው ማስታወቂያ ማሰራጨት ከ20ሺ ብር በማያንስና ከብር 150ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የንግድ ስራ እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 22(4)(5) መሠረት የንግድ እቃዎችንና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ፣ ስለዋጋ ቅናሽ አሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ መስተላለፍ በአዋጁ አንቀጽ43/3/ ተጠቃሎ ሲታይ ስለ ዋጋ ቅናሽ አሰተኛ ወይም የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፍ(ማስተዋወቅ) የአመታዊ ሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እና ከ1 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ ይሄም ከፍ ሲል በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 34/1/ሐ/ ከተጠቀሰው የቅጣት መጠን ከፍ የሚል በመሆኑ መሰል የዋጋ ቅናሽን በተመለከተ የሚቀርቡ ሀሰተኛ ማስታወቂያዎች ሲሰሩ ክስ ሊቀርብ የሚገባው በንግድ ስራና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ መሠረት ሊሆን እንደሚገባ መረዳት ያስችላል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ከፍ ሲል አጠር ባለ መልኩ ለማቅረብ ከተሞከረው ጽሁፍ መረዳት እንደሚቻለው የማስታወቂያ ስራዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ የሕግ ሁኔታዎች እንዳሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ እየተስፋፋ ከመጣው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት አንፃር ዜጎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በማስታወቂያ ስራዎች ውስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ እየሰፋ በመምጣቱ በዚሁ የስራ መስክ የሚሰማሩ ሰዎች ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ የማስታወቂያ ስራ ሕጎች ላይ በንባብም ሆነ በሌላ መልኩ እራሳቸውን በማብቃት ስራውን ተከትሎ ሊመጡ ከሚችሉ የሕግ ተጠያቂነቶች ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡