የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተሽከርካሪ አደጋ በእጅጉ እየበዛ እና ከፍተኛ የሆነ ሞት፣ አካል ገዳት እና የንብረት ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ ከአደጋው አስከፊነትና ከሰብዓዊነት አንፃር የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ጉዳት አድራሹ በመሰወሩ ምክንያት ላይታወቅ የሚችልበት እድል ከመኖሩም በላይ ቢታወቅም እንኳን በወቅቱ ወጪውን ለመሸፈን የሚያስችል አቅም የሌለው የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህም ተጎጂዎችን ለተጨማሪ ጉዳትና እንግልት ሊዳርግ ይችላል፡፡

ይህንን ችግር ለማቃለል የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አስገዳጅ በሆነ መልኩ በሕግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ የሚገኝ ሕግ ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ የሕጉን ይዘት እንዳስሳለን፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ምንነት

መድን ወይም ኢንሹራንስ ስለሚለው ቃል ከተለያየ አቅጣጫ በማየት ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ ከግለሰቦች መነሻ ነጥብ ተነስቶ የሚሰጠው ትርጉም የመጀመሪያው ሲሆን እሱም “አንድ ሰው በንብረቱ፣ በህይወቱ ወይም በአካሉ ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊያጋጥም በሚችል አደጋ ምክንያት የሚደርስ በገንዘብ የሚለካ ጉዳትን ለኢንሹራንስ ድርጅት ማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡” ሁለተኛው መነሻ ነጥብ ከኢንሹራንስ ሰጪው ድርጅት በመነሳት ሲሆን “ኢንሹራንስ ሰጪው በአደጋ ምክንያት የሚያጋጥምን ኪሳራ ለተመሳሳይ አይነት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚያከፋፍልበት መንገድ ወይም ዘዴ ነው፡፡”

በሀገራችንም በነባሩ የንግድ ሕግ አንቀጽ 654(1) ላይ “የኢንሹራስ ውል ፖሊሲ ማለት ኢንሹራንስ ሰጪ የሚባለው በአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ነው፡፡” በማለት ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡ ይህ የጠቅላላው የመድን ውል ትርጓሜ ሲሆን የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድንን በተመለከተ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 799/2005 አንቀጽ 2(እና (10) ስር ከተሰጡት ትርጉሞች ተነስተን መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህም መሠረት “የመድን [ውል] ማለት የመድን ገቢው ተሸከርካሪ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው የሞት አደጋ፣ የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ኪሳራ ካሳ ለመክፈል እና የአስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት ክፍያን ለመፈፀም መድን ሰጪው ውለታ የሚገባበት ሰነድ ነው” ይላል፡፡ ሦስተኛ ወገን ማለት ደግሞ “በመድን [ውሉ] መሠረት ኃላፊነት ያስከተለ የተሽከርካሪ አደጋ በደረሰ ጊዜ ከመድን ገቢው፣ ከመድን ገቢው ቤተሰብ፣ ከአሽከርካሪው ወይም ከመድን ገቢው ተቀጣሪ ሠራተኛ በስተቀር የመድን [ውሉ] ተፈፃሚነት የሚመለከተው ማንኛውም ሌላ ሰው ነው” ይላል፡፡ በመሆኑም የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ማለት የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት ሰው ሊያገኘው የሚገባ ካሳ ወይም የሕክምና ወጪ ሽፋን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አስፈላጊነት

የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 እንሊወጣ ያስፈለገበት አራት ምክንያቶች በመግቢያው ላይ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህም በተሽከርካሪ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጨመረ መምጣቱ፣ በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሣራ ማኅበራዊ ችግር እያስከተለ ያለ መሆኑ፣ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ማመቻቸት እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን እዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ መድን ወይም ኢንሹራንስ እጅግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጠቀሜታዎቹ ውስጥ አንደኛው በአንድ ሰው ላይ የሚደርስን ፍትሐብሔራዊ ተጠያቂነትን፣ የንብረት ጉዳትን፣ በሞት ወይም የአካል ጉዳት ምክንያት የሚደርስን የኢኮኖሚያዊ ኪሳራን በካሳ መልክ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ስለሚከፍለው በተቻለ መጠን ጉዳት አድራሽ ወይም ጉዳት የደረሰበት ሰው የከፋ ኪሳራና ምስቅልቅል ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡

የሕጉ ተፈፃሚነት ወሰን

ህጉ ከብስክሌትና ከአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ (ዊልቼር) በስተቀር በመንገድ ላይ በሚሄድ በኤሌክትሪክ ወይም በመካኒካ ኃይል በሚሰራ ባለሞተር ተሽከርካሪ፣ ግማሽ ተሳቢ ወይም ተሳቢ ላይ ሁሉ ተፈፃሚ እንደሚሆን ከአዋጁ አንቀጽ 2(5) እና ከአንቀጽ 3 ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት ከባጃጅ እንስቶ ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎች ሁሉ ይህን የመድን የምስክር ወረቀት ሳይዙ መንቀሳቀስ አይችሉም። በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ እንደተገለፀው ማንኛውም ሰው ተሽከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ የፀና የመድን ሽፋን ሳይኖረው ተሽከርካሪውን በመንገድ ላይ መንዳት፣ መጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲነዳ ወይም እንዲጠቀም ማድረግ ወይም መፍቀድ እንደማይችል ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ምስክር ወረቀት ካልያዙ ሽፋኑ እንደሌላቸው ተቆጥሮ ተሽከርካሪዎቹ በፖሊስ ተይዘው ይቆያሉ። ተሽከርካሪው የመድን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው ወይም በወቅቱ የታደሰ ካልሆነ መድህን ለተሽከርካሪው የመግባት ግዴታ ያለበት ሰው አዋጁን እንደጣሰ ተቆጥሮ በሕግ እንደሚጠየቅ በአዋጁ አንቀጽ 13 ላይ ተደንግጓል። ለተሽከራካሪው የሦስተኛ ወገን መድን የመግባት ግዴታ ያለበት የተሽከርካሪው ባለቤት፣ ተሽከርካሪው ላይ በኪራይ ወይም በውክልና መብት አግኝቶ የሚጠቀም ሰው ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙበት መፍቀድ የሚችል ማንኛውም ሰው ነው፡፡

የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚሸፍነው ጉዳት

በአዋጁ አንቀጽ 4(2) ላይ በተገለፀው መሠረት የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ፖሊሲ መድን የተገባለት ተሽከርካሪ ለሚያደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሳራ መከፈል የሚገባውን ካሳና አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡

ነገር ግን በመድን ገቢው ወይም ቤተሰብ (የትዳር ጓደኛ፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት ወይም የሚያስተዳድረው ማንኛውም ሰው) ላይ የሚደርስ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ጉዳት፣ በመድን ገቢው ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው በሥራው ላይ እያለ በሚደርስ የግጭት አደጋ ወይም የሞት ወይም የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ጉዳት፣ መድን በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ የሚደርስ አደጋ፣ መድን በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ በኪራይ ወይም በክፍያ በሚጓጓዝ ንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት እና ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጪ የደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ተከትሎ የመጣ ኃላፊነትን የማይሸፍን መሆኑን እና ካሳ እንደማይከፈለው ከአዋጁ አንቀጽ 7 እንረዳለን፡፡ በሌሎች ሕጎች ግን ጉዳት አድራሹን ወይም ተሽከርካሪው የመድህን ሽፋን ካለው መድህን የሰጠውን ኩባንያ ካሳ የመጠየቅ መብታቸው እንደተጠበቀ ነው።

የካሳው መጠን

በአዋጁ አንቀጽ 16 መሠረት በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ መድን ፖሊሲ ለደረሰ ጉዳት የሚሸፍነው የካሳ መጠን የሞት አደጋ ከብር 5 ሺ ያላነሰና ብር 40 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ፣ በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ ለአካል ጉዳት ከብር 40 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ኪሳራ ከብር 100 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ የሚከፈል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሕግ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው ጉዳት አድራሹን ወይም በሕግ ኃላፊነት ያለበትን ሰው በፍ/ቤት ተገቢነት ባለው ሌላ ሕግ መሠረት ከሶ ካሳ መጠየቅ ይችላል፡፡

በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ የመድን ዋስትና የአሽከርካሪውን እድሜ፣ የአካል ወይም የአእምሮ ሁኔታ፣ የተሽከርካሪውን ሁኔታ፣ የፈረስ ጉልበት ወይም የሲሊንደር ችሎታ ወይም ዋጋ፣ የሚይዘው ሰው ብዛት፣ የሚጭነውን እቃ ክብደት፣ አካላዊ ባህሪ ወይም ልዩ መሳሪያ፣ ተሽከርካሪው አገልግሎት ላይ የሚውልበትን ጊዜ ወይም አካባቢ ካሳ እንዳይከፈል ገደብ ሊያስደርጉ አይችሉም።

እንዲሁም እንደ ሌሎች የመድን ዋስትናዎች በመድን ውሉ በተስማማነው መሠረት አይደለም በሚል የመድን ኩባንያው ወይም ሌላ አካል ካሳው እንዳይከፈል መቃወም ወይም መከልከል አይችልም። የመድን ፈንድ ኤጀንሲው ጉዳት አድራሹ ተሽከርካሪ ካልታወቀ ወይም የመድህን ሽፋን ከሌለው በተሽከርካሪው ለደረሰ የሞት ወይም የአካል ጉዳት ከላይ የጠቀስነውን የካሳ መጠን ይከፍላል። የአስቸኳይ ህክምና ወጪንም ይሸፍናል፡፡

አስቸኳይ የህክምና እርዳታ

ማንኛውም ሰው በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ከደረሰበት ከአደጋው ቦታ፣ ወደ ህክምና በሚጓጓዝበት ወቅትና በድንገተኛ ክፍል እስከ ብር 2 ሺህ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የማግኘት መብት አለው፡፡ ማንኛውም የጤና ተቋም ይህን አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ክፍያ ሳይጠይቅ የመስጠት ግዴታ አለበት። ክፍያውን አገልግሎቱን ከሰጠ በኋላ ከመድን ኩባንያው ወይም ከመድህን ፈንድ ኤጀንሲው የሚጠይቅ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 27(3) እና (4) ላይ ተገልጿል።

የመድን ምስክር ወረቀት እና ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ

የመድን ምስክር ወረቀት ማለት የተሽከርካሪው ባለንብረት ወይም ህጋዊ ግዴታ ያለበት ሰው ተሸከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ በአዋጁ መሠረት መድን የገባለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ነው፡፡ መድን ሰጪ ድርጅት ከመድን ገቢው ጋር የመድን ሽፋን ለመስጠት ከተስማሙ የመድን ፖሊሲውን (የመድን ስምምነት ውላቸውን) ለመድን ገቢው ይሰጠዋል፡፡ ከመድን ፖሊሲው በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 9(1) እና 12(1) ላይ እንደተገለፀው የመድን ምስክር ወረቀት እና የመድን ተለጣፊ ምልክት ለመድን ገቢው አብሮ መስጠት እንዳለበት ሕጉ በመድን ድርጅቱ ላይ ግዴታ ጥሎበታል፡፡

ይህ በአዋጁ አንቀጽ 9 መሠረት የተሰጠ የመድን ምስክር ወረቀት ከተሰጠበት ቀን አንስቶ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚፀና ነው፡፡ የመድን ሽፋን ውሉ ሲቋረጥ ወይም የውል ዘመኑ ሲያልቅ መድን ገቢው የመድን ምስክር ወረቀቱንና የመድን ተለጣፊውን ወዲያውኑ ለመድን ሰጪው ድርጅት መመለስ አለበት፡፡

የመድን ፈንድ

የመድን ፈንድ ማለት ቋሚ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ በኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ልዩ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ተቀማጭ እንዲሆን በአዋጁ የተቋቋመ ቋሚ የገንዘብ ምንጭ ነው፡፡ የፈንዱ የገንዘብ ምንጭ ከፈንዱ ተመን የሚሰበሰብ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወሰን ሌላ ተጨማሪ ገቢ ነው፡፡ ይህን ፈንድ የሚስተዳደረው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በተቋቋመው የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ሲሆን የፌደራል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ስያሜው የመንገድ ደኅንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት በሚል ተቀይሯል፡፡

የፈንዱ ዓላማ መድን ባልተገባለት ወይም ባልታወቀ ተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሰው አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ እንዲከፈለው ማድረግ እና ለሞተ ሰው ቤተሰብ አባላት ካሳ እንዲከፈል ማድረግ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 20(2) ላይ እንደተገለፀው ከፈንዱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚከፍለው የካሳ ክፍያ መጠን መድን የተገባለት ተሽከርካሪ አደጋ ባደረሰ ጊዜ በሚከፈለው የካሳ መጠን ልክ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

የመድን ፈንድ አገልግሎቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት በሕጉ የተቀመጠውን የጉዳት ካሳ መጠን ከከፈለ በኋላ ይህን የከፈለውን ክፍያ ለጉዳቱ በኃላፊነት ተጠያቂ ከሆነው ሰው ላይ የማስመለስ መብት እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 20(3) ተደንግጎል፡፡

ተጠያቂነት

የተሽከርካሪ የሶስተኛ ወገን ሕግን አለማክበር የማስተካከያ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ከማስከተሉም በተጨማሪ ክልከላዎችን ተላልፎ መገኘት ከብር 3 ሺ እስ ብር 5 ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከ1 ዓመት እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 30 ተደንግጓል፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ችግር በተወሰነ መልኩ እንዲቋቋሙ እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ለማስቻል ተግባራዊ የተደረገ ሕግ ነው፡፡ ስለሆነም ሕብረተሰቡም የተሽከርካሪ አደጋ እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋ ከደረሰ ግን በጠቀስናቸው መብቶች መጠቀም የሚችል መሆኑን መገንዘብ እንዳለበት መጠቆም እንወዳለን፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ