የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግ በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው፣ ኢኮኖሚያው፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች ጥቅሞቻቸውም እንዲጠበቁላቸው ይፈልጋሉ፣ ጥረትም ያደርጋሉ፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ከሚያግዟቸው ነገሮች መካከል በሀገራችን ህገመንግሥት እንዲሁም ሀገራችን ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ውስጥ የተካተተው የመደራጀት መብት አንዱ ነው፡፡ የዚህ የመደራጀት መብት መገለጫ ከሆኑት አደረጃጀቶች መካከል ዋነኞቹ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምንነት እና የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን በተመለከተ በሀገራችን ያለውን የሕግ ማዕቀፍ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምንነት

በሀገራችን በሥራ ላይ ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በአንቀጽ 2(1) ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማለት ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፍቃደኝነት የሚመሠረት፣ የመንግሥት አካል ያልሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገነ፣ እና ህጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ አካል ሲሆን የሙያ ማህበራትን፣ የብዙሀን ማህበራት እና የድርጅቶች ህብረቶችን ይጨምራል በሚል ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ እነዚህ ድርጅቶ ሀገር በቀል ወይም የውጪ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሀገር በቀል ድርጅቶች የሚባሉት በኢትዮጵያ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ ህጋዊ ስራ ለመሥራት በአዋጁ መሠረት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን፣ በኢትዮጵያ ነዋሪ በሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በሁለቱም የሚመሠረት ድርጅት ሲሆኑ በማህበር፣ በቦርድ መር ድርጅት፣ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት እና የበጎ አድራጎት ድርጅት በሚሉ አምስት አይነት አደረጃጀቶች ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ የውጭ ድርጅት ደግሞ በውጭ ሀገር ሕግ መሠረት የተቋቋመና በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሆነ ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አመሰራረት

አዋጁ የሲቭል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሲመሰረቱ መከተል ያለባቸውን መርሆዎች ያተቀመጠ ሲሆን አነዚህ መርሆችም፤-

  • ድርጅቶቹ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊቋቋሙ መቻላቸው
  • በድርጅቶቹ ውስጥ አባል ለመሆን ፍቃደኝነት የግድ ሲሆን ከድርጅቱ በፈለገው ሰዓት መውጣት መቻል
  • አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት በማድረግ የአባላት መቀበያ መስፈርቶችን መወሰን መቻል
  • ማንኛውም ሰው መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ የድርጅቶቹ አባል መሆን መቻል
  • እያንዳንዱ አባል እኩል ድምጽ ያለው መሆን
  • ድረጅቶች ለአባላት ትርፍ በማሰብ ሊቋቋሙ የማይችሉ መሆን
  • የድርጅቱ አመሰራረትና ውስጣዊ አሠራር ዴሞክራሳዊ መርሆዎችን የተከተለ፤ ከአድሎአዊነት የጸዳ፤ ነፃና ገለልተኛ መሆን
  • ድርጅቶቹ የሚመሩት በመተዳደሪያ ደንብ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ሙሉ ተሳትፎ በተመረጡ ሰዎች መሆን፤
  • ድርጅቱ በመተዳደሪያ ደንቡ ካልሆነ በስተቀር አባላትን ሊቀበልና ሊያሰናብት አለመቻል

ሲሆኑ እነዚህ መርሆዎች ለሁሉም ሲቪል ድርጅቶች ምስረታ ተፈፃሚ የሚሆኑ ናቸው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ

ማንኛውም የሲቪል ማበረሰብ ድርጅት የፌደራል መስሪያ ቤት በሆነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መመዝገብ እንዳለብት በአስገዳጅነት ተደንግጓል፡፡ ሀገር በቀል ድርጅቶች ለመመዝገብ በድርጅቱ መስራቾች ሰብሳቢ የተፈረመ ማመልከቻ መቅረብ ያለበት ሲሆን ይህም

  • የመስራቾችን ስም፣ አድራሻና ዜግነት የያዘ የምስረታ ቃለ-ጉባኤ
  • የመስራቾች መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ኮፒ፤
  • የድርጅቱ ስም እንዲሁም አርማ ካለው አርማውን፤
  • የድርጅቱ ዓላማና ሊሰራ ያሰበበት የስራ ዘርፍ፤
  • ሊሰራ ያሰበበትን ቦታ፤
  • በመስራቾች የጸደቀ መተዳደሪያ ደንብ፤
  • የድርጅቱን አድራሻ አካቶ መቅረብ አለበት፡፡

በውጭ ሀገር የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን ደግሞ በኢትዮጵያ ለመመዝገብ ከላይ ለሀገር በቀል ሲቪል ድርጅቶች ከሚጠየቁት በተጨማሪ

  • ድርጅቱ መቋቋሙን የሚያሳይ ከተቋቋመበት አገር የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ ሰነድ፤
  • ሥልጣን ያለው የድርጅቱ አካል ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ ያሳለፈው በአግባቡ የተረጋገጠ ውሳኔ፤
  • በአገር ውስጥ ተወካዩ የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ የውክልና ሥልጣን፤ ከተቋቋመበት ሀገር ሥልጣን ባለው አካል የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ፤
  • ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚተገበር የስራ እቅድ ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ቅደመ ሁኔታዎች አሟልቶ የቀረበ ሀገር በቀል ድርጅት ማመልከቻውን ለኤጀንሲው ባቀረበ በ30 ቀናት ውስጥ፣ የውጭ ድርጅት ከሆነ ደግሞ የምዝገባ ማመልከቻውን ከስራ እቅድ ጋር ባቀረበ በ45 ቀናት ውስጥ በኤጀንሲው ተመዝግቦ የምስክር ወረቀት ማግኘት ይችላል፡፡ ኤጀንሲው በዚህ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ በአዋጁ አንቀጽ 57(5) መሠረት ድርጅቱን ላለመመዝገብ በቂ ምክንያት እንደሌለው የሚያስቆጥርበት ይሆናል፡፡ የምዝገባ ማመልከቻ አስገብቶ በተባለው ቀን ውስጥ የምስክር ወረቀት ያልተሰጠው ድርጅትም በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለኤጀንሲው ቦርድ ማቀረብ የሚችል ሲሆን ቦርዱ በ60 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በቦርዱ ውሳኔ ቅሬታ ያለው አመልካች ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው፡፡

ምዝገባ ውድቅ የሚሆንበት ሁኔታ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድረጅት ከላይ የተገለፁ ምዝገባ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ይዞ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ ካቀረበ በኋላ ኤጀንሲው ከሚከተሉት ምክንያቶች አንዱ መኖሩን ካረጋገጠ በአዋጁ አንቀጽ 59 መሠረት ድርጅቱ ያቀረበውን የምዝገባ ጥያቄ ውድቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እነዚህም ምክንያቶች

  • የቀረበው ማመልከቻ ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የማያሟላ ሆኖ ሲገኝና ይህንንም እንዲያስተካክል የአመልካቹ ተወካይ ተጠይቆ ለማስተካከል ካልቻለ፤
  • የድርጅቱ ዓላማ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተመለከተው የሥራ ዝርዝር ለሕግ ወይም ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ ከሆነ፤
  • ድርጅቱ የሚመዘገብበት ሥም ወይም ዓርማ፣ ከሌላ ድርጅት ወይም ከማንኛውም ሌላ ተቋም ሥም ጋር የሚመሳሰል ከሆነ ወይም ሕግን ወይም የሕዝብን ሞራል የሚቃረን ከሆነ፤
  • ድርጅቱ ለምዝገባ ያቀረበው ሰነድ በሐሰት የተዘጋጀ ወይም የተጭበረበረ ከሆነ ናቸው፡፡

ከነዚህ ከላይ በግልጽ ከተመለከቱት ምክንያቶች ውጪ ኤጀንሲው በአሠራርም ይሁን መመሪያ በማውጣት የምዝገባ ጥያቄን ሊከለክል የማይችል ሲሆን ኤጀንሲው የቀረበውን ማመልከቻ ሲመረምር ተቀባይነት የሌለው ሆኖ ካገኘው በ30 ቀናት ውስጥ የጎደለውን ነገር አሟልቶ እንዲያቀርብ የምዝገባ ጥያቄ ላቀረበው ድርጅት በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የጎደለውን ነገር አስተካክሎ እንዲቀርብ በጽሁፍ የተሰጠው ድርጅት በተባለው ቀን ውስጥ ለኤጀንሲው ካላቀረበ ምዝገባው ውድቅ ይሆናል፡፡ ምዝገባው ውድቅ የተደረገበት ድርጅትም ቅሬታ ካለው በ30 ቀናት ውስጥ ለቦርዱ ቅሬታውን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ቦርዱ ቅሬታው በቀረበለት በ60 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በቦርዱ ውሳኔ ቅሬታ የተሰማው ድርጅት ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ በመሥራቾቹ አማካኝነት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

በሌላ በኩል አንድ ድርጅት በማታለል ወይም በማጭበርበር የምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቶ ከሆነ ይህ ማጭበርበር በኤጀንሲው ሲረጋገጥ ቦርዱ ድርጅቱ እንዲፈርስ ሊወስን የሚችል ሲሆን በተሰጠ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ድርጅት የቦርዱ ውሳኔ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኙን በመሥራቾቹ አማካኝነት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።

ማጠቃለያ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አደራጃጀት ህገመንግስታዊ የሆነው የመጀራጀት መብት ከሚገለፅባቸው ሁኔታዎች አንዱ ሲሆን በዚህ መልኩ መደራጀት የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ድርጅቶቹ የሚገዙበትን የሕግ ማዕቀፍ ማወቁ መብትና ግዴታውን ተረድቶ ሥራውን ለማከናወን የሚጠቅመው በመሆኑ በህጉ ዙሪያ ግንዛቤውን ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ