መግቢያ
ኃላፊነት ከውል ወይም ከሕግ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ከውል የሚመነጭ ኃላፊነት ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው መሠረት መፈፀም ሳይችሉ ሲቀሩ ውሉን ያልፈፀመው አካል ለተጎዳው ሊከፍለው የሚገባው ካሳ ወይም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ የሚኖርበት ኃላፊነት ሲሆን ከሕግ የሚመነጭ ኃላፊነት ደግሞ በሕግ የተቀመጡ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት እነዛ ሁኔታዎች በሚጣሱበት ጊዜ ሕጉ በተለያዩ አካላት ላይ የሚጥለው ኃላፊነት ነው፡፡
ከሕግ የሚመነጩ ኃላፊነቶችን የወንጀል ኃላፊነት (ተጠያቂነት) እና የፍትሐብሔር ኃላፊነት ብለን በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የወንጀል ኃላፊነት የሚኖረው ሕገ-ወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገውን ድርጊት በመፈፀም ሲሆን የፍትሐብሔር ኃላፊነት የሚፈጠረው ደግሞ በተለያየ ምክንያት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት (ኪሳራ) የደረሰ እንደሆነ ነው፡፡ ፍትሐብሔራዊ ኃላፊነት ውልን መሠረት አድርጎ የሚኖር ኃላፊነት እና ከውል ውጪ በሚኖር ግንኙነት የሚፈጠር ኃላፊነት ተብሎ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከውል ውጪ የሚከሰት ኃላፊነት ምንነት እና ከውል ውጪ ኃላፊነት ምንጮችን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የከውል ውጪ ኃላፊነት ምንነት
ከውል ውጪ የሚደርስ ኃላፊነት የፍትሐብሔር ኃላፊነት አንድ አካል ሲሆን እውቁ የብክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላት የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቶታል፡- “tort is a civil wrong, other than breach of contract, for which a remedy may be obtained, usu. in the form of damages; a breach of a duty that the law imposes on persons who stand in a particular relation to one another.” ወደ አማርኛ ስንመልሰው “ከውል ውጪ ኃላፊነት ማለት ውልን መሠረት ያላደረገ ፍትሐብሔራዊ ተጠያቂነት ሲሆን ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ወይም የጣሱ ሰዎች በካሳ መልክ ሊከፍሉት የሚገባ ግዴታ ነው” እንደ ማለት ነው፡፡
አንድን ሰው በከውል ውጭ ኃላፊነት ተጠያቂ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው አራት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህም ድርጊት/ግድፈት፣ ጉዳት፣ የምክንያትና የውጤት ግንኙነት እና የደረሰው ጉዳት በሕግ እውቅና የተሰጠው መሆን ናቸው፡፡ ድርጊት ወይም ግድፈት ሲባል አንድ ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት ባደረገው ድርጊት ወይም ግድፈት በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ማድረስን ይመለከታል፡፡ ጉዳት ደግሞ በድርጊቱ ወይም በግድፈቱ ምክንያት የሚከሰት ውጤት ሲሆን ይህ ውጤት ደግሞ በሕግ የተጠበቀ መብትን የሚጥስ ሆኖ ሲገኝ መመዘኛውን ያሟላል ማለት ነው፡፡ የምክንያትና የውጤት ግንኙነት መኖር ሲባልም ደግሞ ደረሰ በተባለው ጉዳት እና በምክንያቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወይም ጉዳቱ በማን እና በምን ምክንያት እንደተከሰተ የሚያሳይ ነው፡፡
በከውል ውጭ የሚኖር ኃላፊነት ኃላፊነት ምንጮች
ሕጉ መሠረት ሶስት ዓይነት በከውል ውጭ የሚኖር ኃላፊነት ኃላፊነት ምንጮች አሉ፡፡ እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን፡፡
በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፊነት (Liability for Fault)
የመጀመሪያው የኃላፊነት ምንጭ በራስ ጥፋት በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ማድረስ (Liability for Fault) ነው፡፡ ይህ ጥፋት በቸልተኝነት ወይም ታስቦ ሊፈፀም ይችላል፡፡ እንዲሁም አንድ ጥፋት በማድረግ ወይም ባለማድረግ ሊፈፀም ይችላል፡፡ እነዚህ ኃላፊነትን የሚያስከትሉ ጥፋቶች በፍትሐብሔር ህጉ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን ማንም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት ድርጊቶችን በመፈፀም ወይም ባለመፈፀም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ጉዳት የደረሰበትን ተጎጂ የመካስ የሕግ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
ጥፋትን መሠረት ያደረገ ኃላፊነት የተለመደና የታወቀ የኃላፊነት ዓይነት ነው፡፡ ይህም ማለት ማንም ሰው ባጠፋው ጥፋት መሠረት በሌሎች ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ቢያደርስ ያንን ጉዳት የመካስ ግዴታ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ጥፋት ማለት ህሊናን ወይም መልካም ጠባይን መሠረት በማድረግ የሚገባን ነገር አለመሥራት፣ መሥራት የማይገባን ነገር ደግሞ መሥራት ሲሆን ህሊናን ወይም መልካም ጠባይን የምንለካው ደግሞ ትክክለኛ አእምሮ ያለው ሰው መመዘኛን መሠረት በማድረግ ነው (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2030)፡፡ በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፊነት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ይኸውም
በሞያ ሥራ ላይ የሚደረግ ጥፋት፡- ይህ የጥፋት ዓይነት በሞያተኛ የሚፈፀም የጥፋት ዓይነት ነው፡፡ አንድ ሞያ የራሱ የሆኑ ደንቦች ወይም አሰራሮች አሉት፡፡ እነዚህ ደንቦች በፅሑፍ የተቀመጡ ወይም ያልተፃፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህን የሞያ ደንቦች አክብሮ ባለመሥራት የሚከሰቱ ጉዳቶች ኃላፊነትን ያስከትላሉ (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2031 እና 2035)፡፡
በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም፡- ማንኛውም ሰው የተሰጠውን ሥልጣን ያለአግባብ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም የሠራበት እንደሆነ እና በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኃላፊነትን ያስከትላል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2033)፡፡
ሕግን ስለመጣስ፡- ይህም ማለት በሕግ እንዲደረግ የታዘዘን ነገር ባለማደረግ ወይም እንዳይደረግ የተከለከለን ተግባር በማድረግ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ኃላፊነትን ያስከትላል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2035)፡፡
የበላይ ትእዛዝ፡-በበላይ ኃላፊ ትእዛዝ ስር ያሉ ሰዎች የበላያቸውን ትእዛዝ ሲተገብሩ ኃላፊነትን በማያስከትልባቸው መልኩ መሆን ይገባል፡፡ የዚህ ድንጋጌ አጠቃላይ ይዘት ሲታይ በመርህ ደረጃ በበላይ ኃላፊ ቀጥተኛ ትእዛዝ ስር ሆኖ የተፈፀመ ጥፋት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑን በተለይም የበላይ ኃላፊው ትእዛዙን የመስጠት ችሎታ የሌለው ከሆነና ትእዛዙ የአመፅ ጠባይ (ሕገ-ወጥ) ካለው ወይም ተገቢነት የሌለው (አስወቃሽ) ከሆነ አድራጊው ጥፋት እንዳደረገ ተወስዶ ለድርጊቱ ኃላፊ ይሆናል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2036)፡፡
ሰውነትን ስለመጉዳት፡- ማንም ሰው አስቦ ያለግለሰቡ ፈቃድ የሌላ ሰውን አካል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነካ እንደሆነ በጥፋተኝነት ተቆጥሮ የፍትሐብሔር ኃላፊነት ይኖርበታል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2038)፡፡ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ መንካት የሚፈቀድባቸውና አድራጊውም ጥፋተኛ ተብሎ ኃላፊነት የማይጣልበት ጊዜ አለ (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2039)፡፡
ነጻነትን ስለመንካት፡- ከግለሰቡ ፈቃድ ውጭ የሌላውን ሰው ነጻነት የሚጋፋ ተግባር መፈፀም ጥፋት በመሆኑ ኃላፊነትን የሚያስከትል ተግባር ነው (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2040)፡፡ ነጻነት መንካት ሲባል በሕግ ከተፈቀደው ውጪ በሰውነቱ ላይ ጉዳት ቢያደርስም ባያደርስም የሰውዬውን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቱን ማገድ ወይም አንዳች አደጋ እንደሚደርስበት በመዛት የግዴታ ስራ እንዲሰራ የማስገደድ ተግባርን ያጠቃልላል፡፡ (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2041-2043)፡፡
ስምን ስለማጥፋት፡- አንድ ሰው በንግግሮቹ፣ በፅሑፎቹ ወይም በሌላ ዓይነት አድራጎቶቹ በሕይወት ያለን ሰው ስም ያጠፋ እንደሆነ በፍትሐብሔር ኃላፊነትን ያስከትልበታል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2044)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በሕይወት የሌለ ሰው ስም ማጥፋት በወንጀል ሊያስቀጣ የሚችል ተግባር መሆኑ፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 607 ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የስም ማጥፋት ተግባር ቢፈፀምም አድራጊው የሚከተሉትን ሁኔታዎች ማስረዳት ከቻለ ከኃላፊነት ነፃ ይሆናል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2046)፡- ድርጊቱ የተፈፀመው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንደሆነ፣ የተገለፀው የስም ማጥፋት ሀሳብ ሐሰት መሆኑን ሳያውቅ ያደረገው ከሆነ (እውነት ነው ብሎ በማመን የተፈፀመ)፣ ጉዳዩ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠና ተበዳዩን ለመጉዳት ያልተደረገ ከሆነ፣ ስም ማጥፋቱ የተደረገው በምክር ቤት (በፓርላማ) ክርክር፣ በፍርድ ቤት ክርክር ጊዜ ሆኖ ተበዳዩን ለመጉዳት ያልተደረገ ከሆነ፣ በጋዜጣ ታትሞ የተወራ ከሆነ አጥፊው በተለይ ተበዳዩን ለመጉዳት አስቦ ያላደረገው ከሆነ፣ ከፍ ባለ ቸልተኛነት ያልተደረገ ከሆነ፣ በተበዳዩ ጠያቂነት አጥፊው መልሶ ይቅርታ ከጠየቀ ናቸው፡፡
ጥፋት ሳይኖር ኃላፊነት (Strict Liability)
ሁለተኛው የኃላፊነት ምንጭ ምንም ጥፋት ሳይኖር ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት በመውሰድ የሚከሰት (Strict Liability) ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ኃላፊነት ሕጉ አንድ ሰው ምንም ጥፋት ባይኖርበትም እንኳን ለደረሰው ጉዳት ካሳ የሚከፍልበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
የፍትሐብሔር ሕግ በቁጥር 2027/2/ አንድ ሰው ጥፋት ባልሆነ ሥራ በህጉ እንደተመለከተው በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ሥራ ከሰራ ወይም በእጁ የያዘው ነገር በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ኃላፊ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በአጠቃላይ አንድ ሰው በሚፈፅመው ድርጊት ምክንያት የሚመጣ ኃላፊነት እና በንብረት ባለቤትነት ወይም ባለይዞታነት ምክንያት ንብረቱ ጉዳት ሲያደርስ የሚመጣ ኃላፊነት በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡
በተፈፀመ ድርጊት ምክንያት የሚመጣ ኃላፊነት፡-
አስፈላጊ ሁኔታ፡- የሚባለው የራስን ወይም ሊከላከሉለት የሚገባን የሌላውን ሰው ህጋዊ መብት ሊደርስ ከሚችል ከፍተኛ አደጋ ለማዳን በሌላ ሰው ህጋዊ መብት ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ማድረስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ በሚፈፀም ድርጊት በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረስ ኃላፊነትን ያስከትላል(ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2066)፡፡
በሰው አካል ላይ ጉዳት ማድረስ፡- የፍትሐብሔር ህጉ በቁጥር 2067(1) ስር እንደሚያስቀምጠው ማንም ሰው በሰራው ሥራ ወይም በድርጊቱ በሌላ ሰው አካል ላይ ጉዳት ካደረሰ ድርጊቱ ጥፋት ባይሆንም እንኳን ላደረሰው ጉዳት የፍትሐብሔር ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱት ያደረሰው ሥራ በሕግ የተፈቀደ ወይም የታዘዘ ከሆነ፣ ጉዳቱ የደረሰው ራስን ለመከላከል በተፈፀመ ድርጊት ወይም በተጎጂው ጥፋት ማለትም የጉዳቱ ምክንያት ተጎጂው ብቻ ከሆነ እና የጉዳት አድራሹ አስተዋፅኦ ከሌለ ጉዳት አድራሹ ምንም አይነት ተጠያቂነት አይኖርበትም (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2067(2))፡፡
አደገኛ ሥራ፡- ጥፋት ባይሆኑም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ኃላፊነትን የሚያስከትሉ ናቸው ተብለው በአደገኛነት የተፈረጁ አራት የሥራ ዘርፎች አሉ (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2069)፡፡ እነዚህም፡- የሚፈነዱ ወይም መርዝ የሚሆኑ ቅመማትን በሥራ ላይ ማዋል፣ ከፍተኛ ጉልበት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት፣ የመሬትን የተፈጥሮ መልክ መለወጥ፣ አደገኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ሥራ ማካሄድ ናቸው፡፡ እነዚህን አደገኛ ሥራዎች መሥራት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ አደገኛ በመሆናቸው ብቻ ሊከለከሉ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከሥራዎቹ ባህሪ አንፃር ለሕብረተሰቡ ክፍተኛ የአደጋ ስጋት በመሆናቸው ከሚያደርሱት ኪሳራ ለመጠበቅ ከለላ መስጠት ስለሚያስፈልግ በእነዚህ ሥራዎች ምክንያት በሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ከደረሰ የሥራው ባለቤት ጥፋት ባይኖርበትም ለተጎጂው የመካስ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
በንብረት ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት
እንስሳት፣ ህንፃዎች፣ ማሽኖች እና ሞተር ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የተመረቱ/የተሰሩ/ ዕቃዎች ጉዳት ያደረሱ እንደሆነ የንብረቶቹ ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን ኃላፊነት ያስከትላል፡፡
እንስሳት ለሚያደርሱት ጉዳት ኃላፊነት፡- አንድ እንስሳ ለሚያርሰው ጉዳት ኃላፊነት የሚወስዱት እንደሁኔታው የእንስሳው ባለቤት ወይም የእንስሳው ጠባቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጉዳት ያደረሰ እንስሳ ባለቤት ምንም እንኳን ለጉዳቱ መድረስ የእርሱ ጥፋት ባይኖርበትም ጉዳት ያደረሰው እንስሳ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነትን ይወስዳል፡፡ እንስሳን ለግል ጥቅሙ ከባለቤቱ በተውሶም ሆነ በኪራይ የተረከበ እንስሳውን ለመጠበቅ ወይም ለመቀለብ ወይም ለሌላ የግል ጉዳይ የተረከበ ሰውም በእጁ በነበረበት ጊዜ ጉዳት ቢያደርስ ጠባቂው ኃላፊነቱን ይወስዳል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2072)፡፡
በህንፃ ለሚደርስ ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት፡- ህንፃው በመፍረስ ወይም በመደርመስ በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ቢያደርስ ያደርሳል ተብሎ ያልታሰበም ሆነ አልሆነ የህንፃው ባለቤት ወይም ባለይዞታ ጥፋት ያለበት መሆኑን ማስረዳት ሳያፈስልግ ተጠያቂ ይሆናል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2077)፡፡ ከሕንፃዎች ጋር በተያያዘ ኃላፊነትን የሚያስከትለው በመፍረስ ብቻ ለሚደርስ ጉዳት ሳይሆን ከሕንፃው ላይ በሚወድቁ ዕቃዎችም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ኃላፊነት የሚወስደው የግድ የሕንፃው ባለቤት ሳይሆን በሕንፃው የሚኖረው ሰው ይሆናል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2080)፡፡
በመኪናና ሞተር ተሸከርካሪዎች ለሚደርስ ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት፡- መኪናዎች እና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ባለቤቱ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይህ መኪና ወይም ሞተር ተሽከርካሪ ጉዳት ያደረሰው ይህንኑ ለማንቀሳቀስ ወይም ለመንዳት ባልተፈቀደለት ሰው ምክንያት ቢሆንም እንኳን ባለቤቱ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ነገር ግን አደጋው በደረሰ ጊዜ ተሸከርካሪው የተሰረቀ መሆኑን ማረጋገጥ ከተቻለ ባለቤቱ ኃላፊነት አይኖርበትም (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2081)፡፡
በሌላ በኩል አንድ ሰው መኪናውን ወይም ባለሞተር ተሸከርካሪውን ለግል ጥቅሙ ሊገለገልበት ከባለቤቱ የወሰደ እንደሆነ ይህ መኪና ወይም ተሽከርካሪ በእጁ በነበረበት ወቅት ላደረሰው ጉዳት ኃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ነገር ግን መኪናውን ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪውን ለማንቀሳቀስ ወይም ለመንዳት የተቀጠረ ሠራተኛ ጉዳቱ የደረሰው በራሱ ጥፋት ካልሆነ በቀር ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ስለሆነም የተሽከርካሪው ባለቤት የቀጠረው ሠራተኛ ንብረቱን በሚያንቀሳቅስበት ወቅት አደጋ አድርሶ ጉዳት ቢያደርስ ኃላፊነቱን የሚወስደው ባለቤቱ ይሆናል፡፡ ይህ ባለቤት ከኃላፊነት ሊያመልጥ የሚችለው የደረሰው ጉዳት በሠራተኛው ጥፋት መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሠራተኛው ኃላፊነት ይኖርበታል (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2082)፡፡
በተሰሩ እቃዎች ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት
አንድ ሰው ምርት አምርቶ ትርፍ ለማግኘት ለገበያ ቢያቀርብ እና ይህ ምርት በአግባቡ በተጠቀመው ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆን የፍትሐብሔር ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ተጎጂ ዕቃውን ሲገዛ በልማድ እንደሚደረገው ተገቢውን ምርመራ ወይም ፍተሻ አድርጎ መሆን የገዛ እና ተጎጂ ጉዳት የደረሰበት ዕቃውን በሚገባ ወይም ለተሰራበት ዓላማ በተገቢው ሁኔታ ተጠቅሞበት መሆን አለበት፡፡
ለሌሎች ኃላፊ ስለመሆን (Vicarious Liability) ((ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2124-2136))
ሦስተኛው የኃላፊነት ምንጭ ሌላ ሰው ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊነት በመውሰድ የሚከሰት (Vicarious Liability) ነው፡፡ የዚህ ኃላፊነት መሰረቱ የጉዳት አድራሹ እና ኃላፊነትን የሚሸከመው ሰው ህጋዊ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅና በቤተሰቡ ወይም በልጁ ጠባቂ ወይም አሳዳጊ መካከል፣ በአሰሪ እና ሠራተኛ መካከል፣ በደራሲ እና አሳታሚ መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ያካትታል፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ህጋዊ ግንኙነት ውስጥ አንድ ሰው በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት ሲያደርስ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነትን የሚወስደው ጉዳት አድራሹ ሳይሆን ሕጉ ኃላፊ የሚያደርገው ሰው ነው፡፡
በዚህ የኃላፊነት አይነት አካለ መጠን ላላደረሰ ልጅ ወላጆች፣ ለሰራተኞች አሰሪዎች እና ለደራሲያን ደግሞ አሳታሚዎች ሀላፊዎች ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኃላፊነት የሚወስዱት አካላት የመቆጣጠር ችሎታና አቅም ስላላቸው፣ የድርጊቱ መንስኤ እነሱ ስለሆኑ፣ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው ስለሆኑ የሚሉት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ማጠቃለያ
ሰዎች በተለያየ ምክንያት በሌሎች ላይ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ ወይም ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርሱ ከውል ውጪ በሚደርስ ኃላፊነት ሕግ መሠረት ጉዳት ያደረሱበትን አካል ለጉዳቱ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ከውል ውጪ የሚደርስ ኃላፊነት የፍትሐብሔራዊ ኃላፊነት አንድ ዘርፍ ሲሆን ዋነኛ ዓላማውም የተጎዳን አካል በሕግ አግባብ ካሳ እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ