የቤተሰብ ሕግ ቤተሰብን ከመጠበቀ አንፃር ያለው ፋይዳ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ቤተሰብ የአንድ ሀገር ወይም ማኅበረሰብ መሠረት እንደመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ በሕግና እና ሥርዓት መመራት ይኖርበታል፡፡ የቤተሰብ መመስርቻ የሆነው ጋብቻ ከምስረታው ጀምሮ በቆይታው ጊዜ የሚፈጠሩት ግንኝነቶች እና ውጤቶች በሕጉ መሠረት ከለላ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ የቤተሰብን ምንነት፣ ቤተሰብ በሕግ የተሰጠውን ጥበቃ እና የቤተሰብ ሕግ ቤተሰብን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ያለውን ፋይዳ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የቤተሰብ ምንነት

አሁን በሥራ ላይ ባለው የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ውስጥ ቤተሰብ ለሚለው ቃል በቀጥታ ትርጉም አልተሰጠም፡፡ ሆኖም በተለያዩ ጽፎች ትርጉም ተሰጥቶት እንገኛለን፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ምርምር ማዕከል መዝገበ ቃላት (1993፣ ገጽ 242) ላይ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን ቤተሰብ፡-

  • የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሰዎች፣
  • በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች፣
  • የሚቀራረቡ፣ የሚተሳሰቡ፣ የሚዋደዱና እንደ ዘመድ የሚተያዩ ጓድኛሞችና አብሮ አደጎች በማለት ገልጾት ይገኛል፡፡

በዚህ መሠረት ቤተሰብ በጋብቻ፣ በደም ትስስር፣ በጉዲፈቻ… ወዘተ የተገኙና በአንድ ቤት (በአንድነት) የሚኖሩ ሰዎችን የሚያቅፍ የህብረተሰብ መነሻ ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቤተሰብ በሕግ የተሰጠው ጥበቃ

ቤተሰብ በተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሕጎችም ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡ ሀገራችን ተቀብላ የህጓ አካል ያደረገችው ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ /UDHR, 1948/ ቤተሰብ የአንድ ህብረተሰብ መሠረታዊና ተፈጥሯዊ መሠረት ስለሆነ በህብረተሰቡና በመንግሥት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል በማለት ገልጾት ይገኛል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 34 የጋብቻ፣ የግልና የቤተሰብ መብቶች በሚል ትኩረት በመስጠት አስቀምጧል፡፡ በዚህም በሕጉ ለተወሰነው የጋብቻ ዕድሜ የደረሱ ወንዶችና ሴቶች በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የማግባትና ቤተሰብ የመመስረት መብት እንዳላቸው እንዲሁም በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የተሻሻለው ፌደራል የቤተሰብ ሕግ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን ይህም የጋብቻ ምስረታን፣ ሕጋዊ ውጤትን፣ የጋብቻ መፍረስን፣ አባትነትን፣ ጉዲፈቻን፣ የቤተሰብ መደጋገፍ ግዴታን እና ፍቺ በሚኖርበት ጊዜም ከፍቺ በኋላ የልጆች አስተዳደግንና ቀለብን እንዲሁም ፍትሐዊ የንብረት ክፍፍልን ጭምር የሚደንግግ ሕግ ነው፡፡

የቤተሰብ ሕግ ለቤተሰብ ጥበቃ በማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ

የቤተሰብ ሕግ የማኅበረሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ ከመጠበቅ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፡- ይኸውም፡-

  • ጋብቻ በተጋቢዎች ሙሉና ነፃ ፈቃድ ላይ ብቻ እንዲመሠረት ማድረጉ፣
  • በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻ ዘመን እና በፍቺ ጊዜ የተጋቢዎችን የእኩልነት መብት ማስጠበቁ፣
  • ጋብቻ ከተፈፀመ በኋላ በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነትም (አብሮ መኖር፣ መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ እና ቤተሰብን በጋራ መምራት) ሆነ በንብረት ላይ (ንብረት ማፍራትና ማስተዳደር) እኩልነት እንዲኖር መደንገጉ፤
  • የልጆች ደኅንነት፣ አስተዳደግና አጠባበቅን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚጠይቁት መሠረት ለሕፃናት ደኅንነት ቅድሚያ መስጠቱ፣
  • ፍቺ በፍርድ ቤት ብቻ እንዲሆን ማድረጉ እና ፍቺ ከመወሰኑ በፊት ተጋቢዎች የማሰላሰያ ጊዜ እንዲኖራቸው ማድረጉ ቤተሰብን ለመጠበቅ ማስቻሉ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የቤተሰብ ሕግ ቤተሰብ ከምስረታው ጀምሮ በቆይታው ጊዜም ሆነ በሚፈርስበት ጊዜ እንዲሁም በቆይታው ጊዜ የሚኖሩ ልጆች የሚያድጉበትን ሁኔታ እና የተፈሩ ንብረቶች የሚተዳደሩበትን ሁኔታ በግልፅ በመደንገግ በቤተሰብ ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ