የሀገራችን ማኅበረሰብ ለሀይማኖቱና ለባህሉ ከፍተኛ ቦታ ሚሰጥ በመሆኑ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሲከሰቱ በስፋት ሲያወግዝ ይሰተዋላል፡፡ ከዚህ በመነሳትም በሀገራችን ህጎች በተለይም በወንጀል ህጉ ላይ ከመልካም ጠባይ ያፈነገጡ ተግባራት ሲከሰቱ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በወንጀል ህጉ ላይ የተደነገጉትን መልካም ጠባይን በመቃረን የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንመከታለን፡፡
የመልካም ጠባይ (Moral) ትርጉም
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሞራል ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን የተለያዩ ፃህፍትም በራሳቸው መንገድ ትርጉም ሰጥውበታል፡፡ ሞራል ማለት ከአንድ ባህል ወይም ሀያማኖታዊ ሥርአት ውስጥ ካለ ሥነምግባር የሚመነጭ የአንድን ሰው ባህሪ መለኪያ ነው፡፡ ሞራል በአንድ ማኅበረሰብ ወይም ባህል አማካኝነት የሚመነጭ ሥነ ምግባር ሆኖ ይህ ሥነ ምግባር በአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያለውና የሚተገበር ነው በሚል አብዛኛወቹ ፃህፍት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ በዚህ ትርጉም መሠረት በአንድ አካባቢ ወይም ሀገር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ አንድ ተግባር ለምሳሌ በአደባባይ ልብስ ሳይለብሱ ማለትም እራቁትን መሄድ ከሞራል ያፈነገጠ ወይም ከመልካም ጠባይ ተቃራኒ ተግባር እንደሆነ ተስማምተው ካወገዙት ይህን ድርጊት የፈፀመ ግለሰብ ከሞራል የፈነገጠ ድርጊት ፈፅሟል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ሞራል እንደየማህበረሰቡ ባህል ሊለያይ የሚችል ሲሆን ለአንዱ ሞራላዊ ድርጊት የሆነ ተግባር ለሌላው ደግሞ ከሞራል ያፈነገጠ ፍርጊት ሊሆን ይችላል፡፡
ሕግ ከማኅበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ የሚመነጭ በመሆኑ ሀገራት እንደየህዝባቸው ባህል ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ የሕግ ክልከላ ያደርጋሉ፡፡ በሀገራችንም በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጅል ሕግ ከማህበረሰባችን ባህልና እሴት አንፃር ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ እንደሆኑ የታመነባቸው ድርጊቶች በወንጀልነት ተደንግገው ሲፈፀሙ በፈፃሚው ላይ ሊከተለው የሚችለው የወንጀል ተጠያቂነት የተመለከተ ሲሆን እንደሚከተለው እንመልከታቸዋለን፡፡
ለመልካም ሥነ ምግባርና ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ የብልግናና አሳፋሪ ድርጊት
በአደባባ መፈፀም (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 639)
ማንም ሰው አስቦ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ ወይም በሕዝብ ፊት የግብረ ሥጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ሥነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ ፀያፍ ድርጊት የፈፀመ ወይም በአኳኋን ያሳየ አንደሆነ ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሽህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ሊቀጣ ይቀጣል፡፡ ከላይ የተቀመጠው ድርጊት አካለመጠን ባላደረሱ ልጆች ፊት ተፈፅሞ ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው አደባባይ ወይም በሕዝብ ፊት ወሲብ መፈፀምም ሆነ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ ተግባራትን መፈፀም ከሞራል ወይም ከሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ከመሆንም በላይ ከኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ውጭ በመሆኑ በወንጀል እንዲሚያስቀጣ ነው፡፡
ፀያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 640)
ፀያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን ማንም ሰው ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ በፅሁፎችን፣ ምስሎችን፣ ስዕላዊ መግለጫዎችን /ፖስተሮችን/፣ ፊልሞችን ወይም ሌሎችን ነሮችን ያዘጋጀ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ ሀገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ የተቀበለ፣ የያዘ፣ ለሕዝብ ያሳየ፣ ለሽያጭ ወይም ለኪራይ ያቀረበ፣ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከቦታ ቦታ ያዟዟረ ወይም እነዚህን ነገሮች የነገደ ወይም እነዚህ ነገሮች እንደምን እና ከማን ሊገኙ እንደሚችሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስታወቀ ወይም ያመለከተ እንደሆነ ነገሮቹ ተወርሰው ከመወገዳቸው በተጨማሪ ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
ወንጀል ፈፃሚው ይህንን ተግባር ሙያው አድርጎ የያዘው እንደሆነ፣ እነዚህን ነገሮች አስቦ አካላመጠን ላልደረሱ ልጆች ያሳየ፣ የሰጠ ወይም ያስረከበ እንደሆነ እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ ሲባል አካለመጠን ያልደረሱ ልጆች የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀሙ በማስመሰል ያሳየ ወይም ሀፍረተሥጋቸው እንታይ ያደረገ እንደሆነ ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እሥራት እና ከብር አስር ሺ በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል፡፡
ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ማሳየት (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 641)
ማንም ሰው ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን በትያትር፣ በሲኒማ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልሞች፣ በሬዲዮ፣ በቪድዮ፣ በቴሌቪዥን ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ እንዲተላለፍ ያደራጀ፣ ለሕዝብ ያሰማ ወይም እንዲታይ ያደረገ እንደሆነ ከላይ በአንቀጽ 640 በተመለከተው ቅጣት ልክ በእስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
ሆኖም ወሲብን ወይም ፍትወተ ስጋን ለመቀስቀስ ያልታሰቡ በባህሪቸው ሥነ ጥበባዊ፣ ሥነ ፅሁፋዊ ወይም ሳይንሳዊ የሆኑ ሥራዎች እንደፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ተደርገው እንደማይቆጠሩ በአንቀጽ 642 ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የወንጀል ህጉ አንቀጽ 641 ሆነ ተብሎ ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ሆኑ ነገሮችን ለማሰራጨት ታስቦ በሚዘጋጁ ነገሮች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ መግለጫዎችና ማስታወቂያዎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 643)
ማንም ሰው ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ሆኑ ወይም ከግብረ ገብ ውጪ የሆኑ ነገሮችን፣ ምርቶችን ወይም ሥራዎችን ለሕዝብ እይታ ካቀረበ ከአንድ ወር በማያንስ ቀላል እስራትና በመቀጮ የሚቀጣ ሲሆን እነዚህኑ ነገሮች ወዳልጠየቁ ወይም በነዚሁ ላይ የሙያ ዝንባሌ ወደሌላቸው ሰዎች በማናቸውም ዘዴ ከላከ በተበዳይ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአምስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም በቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሥራዎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 644)
ለጥቅም ወይም ስሜትን ለመቀስቀስ ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን የግብረ ሥራ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ከልክ በላይ ለመቀስቀስ፣ ለማበላሸት፣ ለማሳሳት ወይም አካላመጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የጭካኔ ወይም የገዳይነት ዝንባሌ ወይም ጸረ ማኅበራዊ የሆኑ ወይም ቤተሰባዊ ኑሮን የሚያናጉ ስሜቶችን ከመጠን በላይ ለማነሳሳት፣ ለመቀስቀስ ወይም ለማሳደር የሚችሉ ፅሁፎችን፣ ምስሎችን፣ ወይም ነገሮችን በንግድ ቤት መስኮት፣ በንግድ እቃ ማሳያ ቦታ ወይም ከውጪ ለሕዝብ ሊታይ በሚችል በማናቸውም ሌላ ሥፍራ በማስቀመጥ በቪዲዮ ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ እንዲታይ ማድረግ ወይም እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን ለአካለመጠን ላልደረሱ ልጆች እያወቁ ማቅረብ፣ ማዋስ፣ መስጠት ወይም መሸጥ የእቃው መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከስድስት ወር እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና በመቀጮ ሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡
ደንብ መተላለፍ (የወንጀል ህጉ አንቀጽ 845-847)
ከላይ የተመለከትናቸው የተከለከሉ ተግባራት እንዳሉ ሆነው በወንጀል ህጉ የደንብ መተላለፍ ክፍል ላይ ከአንቀጽ 845-847 ድረስ ባሉ ድንጋጌዎች ማንም ሰው በአደባባይ ወይም ሕዝብ በሚያየው ቦታ መልካም ሥነ ምግባርን ወይም መልካም ጠባይን የሚነካ ድርጊት አስቦ የፈፀመ እንደሆነ፣ መልካም ሥነ-ምግባርን ወይም መልካም ጠባይን በሚቃረን መንገድ ያልፈለገውን ሰው በድሪያ መልክ ያበሳጨው እንደሆነ፣ ተገቢ ባልሆነ ጥያቄ ሌላው ሰው ለሥነ-ምግባር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ወይም በህብረተሰቡ የተወገዙ ማናቸውንም አይነት የብልሹነት ድርጊት እንዲፈፅም የገፋፋ፣ በዝሙት ወይም በህብረተሰቡ በተወገዙ መሰል ድርጊቶች በመሰማራት የጎረቤቶቹን ወይም የአካባቢውን ነዋሪዎች ያወከ እንደሆነ እንዲሁም የብልግና ተግባርን ለማበረታታት ወይም የሌላውን ሰው ፍተወተ ስጋ ለማርካት ሲል ዝሙት የፈለገ ሰው በእንደዚህ አይነት ቦታ ራሱን ሊያስደስት ይችላል ብሎ በማናቸውም ዘዴ በይፋ ያስታወቀ እንደሆነ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱን ማዕከል አድረገው በተለያዩ መንገዶች ለወሲብ ተግባር ሰዎችን እናገናኛለን በማለት የሚያስተዋውቁ ግለሰቦች ድርጊቱ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን አውቀው ከድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
ሲጠቃለል ኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የዳበረ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ የሥነ ምግባር እሴት ያለው እንደመሆኑ እነዚህን እሴቶች አስጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ህብረተሰቡ ከላይ የጠቀስናቸው ከእሴቱ ወጣ ያሉ ተግባራት በወንጀል የሚያስጠይቁ እንደሆኑ በመረዳት ለህጉ ተፈፃሚነት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ