የህግ ባለሞያዎች (የዐቃቤያን ህግ፣ የዳኞች እና የጠበቆች) የሞያ ሥነ-ምግባር (ክፍል 1)

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሥነ-ምግባር ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ማድረግ ወይም ያለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ባህሪያት ወይም ተግባራት መገለጫ ሲሆን ይህም በሥነ ምግባር ደንቦች ውስጥ ተካቶና ተዘርዝሮ ሊገኝ ይችላል። የሥነ-ምግባር ደንቦች በስራ ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በማኅበረሰብ ውስጥ፣ በሀይማት ተቋማት፣ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታዎች እና በመሳሰሉት ቦታዎች ይገኛሉ። የሞያ ሥነ-ምግባር ደንቦች ሰራተኞች ወይም ባለሞያዎች በስራ ቦታቸው ማክበር የሚጠበቅባቸውን መርሆች፣ ህጎች እና መመሪያዎች ስብስብ ነው። እያንዳንዱ ሞያ የየራሱ የሥነ-ምግባር ደንብ ሊኖረው የሚችል ቢሆንም ዓለም ዓቀፍ መርህን የተከተሉ ደንቦች ደግሞ ለሁሉም ሞያዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረጉ ይችላሉ። የሕግ ባለሞያዎች በተለያዩ ስራዎች ውስጥ ሊሳተፉ ሲችሉ ከነዚህም መካከል ዐቃቤ ሕግነት፣ ዳኝነት፣ ጥብቅና፣ የሕግ ጥናት እና ምርምር እና ሌሎችም ይገኙበታል። ታዲያ እነዚህን ስራዎች የሚሰሩ የሕግ ባለሞያዎች እንደስራዎቹ ባህሪ የተለያዩ የሥነ- ምግባር ግዴታዎች አሉባቸው።

በዚህ አጭር የንቃተ- ሕግ ጽሑፍ የሕግ ባለሞያዎች በተለይም ዐቃቤያን ሕግ፣ ዳኞች እና የፌደራል ፍርድ ቤት ጠበቆች ሊኖራቸው ስለሚገባ የሞያ ስነ-ምግባር የተለመዱ ብሔራዊ ልማዶችን እና ዓለም ዓቀፍ ህጎችን እንዲሁም የተለያዩ የሀገር ወስጥ ህጎችን መሠረት በማደረግ እንዳስሳለን።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተለመዱ የሕግ ባለሞያዎች የሞያ ሥነ-ምግባር ደንቦች

በአጠቃላይ የሞያ ሥነ-ምግባር ደንቦች ከሀገር ሀገር ሊለያዩ ቢችሉም በበርካታ ሀገራት ተቀባይነት ያገኙ እና በስራ ላይ የሚውሉ የዐቃቤያን ሕግ፣ የዳኞች እና ጠበቆች ሥነ-ምግባሮች አሉ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሕግ ባለሞያዎችን ሊገዙ የሚችሉ የተለያዩ የሥነ-ምግባር ደንቦች ወይም ስምምነቶች ያሉ ሲሆን ሀገራትም እነዚህን ደንቦች እንደ ሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ተግባራዊ ሲያደርጉ ይስተዋላል። በመቀጠል እነዚህን የሞያ ሥነ-ምግባር ደንቦች እንመለከታለን።

የዐቃቤያን ሕግ ሥነ-ምግባር

ዐቃብያነ ህጎች መንግሥትን በመወከል ክስ ማቅረብ እና የጥፋተኝነት ውሳኔዎችን ማሰጠት ብቻ ሳይሆን ፍትሕን የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው። በ1990 በወጣው የተባበሩት መንግስታት የዐቃብያነ-ሕግ ሚና መመሪያዎች እና የብሔራዊ የክስ ኮዶች ላይ እንደ ሰፈረው ይህን ሀላፊነታቸው በሚወጡበት ወቅት ሊከተሏቸው ከሚገቡ ሥነ-ምግባሮች መካከል፡-

  • ፍትሃዊነት/ Fairness/፡- ለተከሳሾች ትክክለኛ አያያዝ ማድረግ እና የተጎጂዎችን መብት መጠበቅ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ ወይም አድልዎ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል።
  • አለማዳላት/ Impartiality/፡-ጉዳዮችን መመርመር እና መወሰን ያለባቸው ከግል እምነት ወይም ውጫዊ ጫና ውጪ በመሆን ሕግን መሠረት በማድረግ መሆን አለበት።
  • ታማኝነት/ሀቀኝነት/ Integrity/፡-ማንኛውንም የጥቅም ግጭት ማስወደግ ያለባቸው ሲሆን አስገዳጅ ማስረጃዎችን ጨምሮ ማስረጃን በመግለጽ ረገድ ሐቀኝነትን መጠበቅ አለባቸው።
  • ሙያዊነት/Professionalism/፡- በህጋዊ አካሄዶች እና በሥነ-ምግባር ሀላፊነቶች ውስጥ ብቁ በመሆን ምስጢራዊነትን መጠበቅ እንዲሁም በማስተዋል እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
  • ተጠያቂነት/Accountability/፡-ለህጋዊ መስፈርቶች እና ለሥነ-ምግባር ቁጥጥር አካላት ተጠያቂ ናቸው።
  • ትብብር/Cooperation/፡-ከሕግ አስከባሪዎች፣ ተከላካይ ጠበቆች እና ከፍርድ ቤቶች ጋር በትብብር እና በአክብሮት መሥራት አለባቸው።

የዳኞች ሥነ-ምግባር

እ.ኤ.አ በ2002 የወጣው የባንጋሎር የዳኝነት ሥነ-ምግባር መርሆዎች በሰፊው የታወቀ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ሲሆን ዳኞች በሥነ ምግባር፣ በታማኝነት እና በገለልተኝነት ማገልገል እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ቁልፍ መርሆቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

  • ነጻነት/ Independence/፡- ዳኞች ከፖለቲካ ተጽእኖ፣ ከፓርቲዎች እና ከውጭ ጫናዎች ነጻ መሆን አለባቸው። በግላዊ ፍላጎቶች ወይም ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የለባቸውም።
  • አለማዳላት/Impartiality/ ፡- ጉዳዮችን በሕግ እና በማስረጃዎች ላይ ብቻ በመመስረት መወሰን አለባቸው።
  • ታማኝነት/ Integrity /፡- ዳኞች በታማኝነት መሥራት እና የዳኝነትን ክብር ማስጠበቅ ያለባቸው ሲሆን በሁሉም እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ያለአግባብ የሆኑ ተግባራትን ማስወገድ አለባቸው።
  • ጨዋነት/Propriety፡– ዳኞች የዳኞች የአኗኗር ዘይቤን መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን ከማኅበራዊ ጉዳዮች እራሳቸውን መገደብ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የፍትሕ አካላትን መልካም ስም ሊያበላሹ ከሚችሉ ተግባራት እራሳቸውን ማራቅ አለባቸው።
  • እኩልነት/Equality/፡- ሁሉንም ግለሰቦች እና ባለጉዳዮች ያለ አድልዎ እና በአክብሮት መያዝ አለባቸው።
  • ብቃት እና ትጋት/ Competence and Diligence/፡- ዳኞች ስራቸውን ብቃት ባለው የሕግ እውቀት እና በሕግ አግባብ ማከናወን አለባቸው።

የጠበቆች ሥነ-ምግባር

የዓለም ዓቀፍ የጠበቆች ማህበር የሥነ- ምግባር ደንብ /International Bar Association International Code of Ethics/ እንደሚያስቀምጠው ጠበቆች የተለያዩ የሥነ-ምግባር ግዴታዎች አሉባቸው። ከነዚህም ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የሙያቸውን ክብር መጠበቅ አለባቸው፤ ሙያዊ ተግባራቸውን ሲወጡ በነጻነት መሆን አለበት፤ የሙያ አጋሮቻቸውን በትህትና እና በፍትሃዊነት መያዝ አለባቸው፤ ሁል ጊዜ ለፍርድ ቤት ተገቢውን ክብር መስጠት አለባቸው፤ ከፍርድ ቤት ወጪ ያሉ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን ለደንበኞቻቸው ማሳወቅ አለባቸው፤ ጠበቆች በሙግት ውስጥ የጥቅም ግጭት ያለባቸው ፍላጎቶች በፍጹም መወከል የለባቸውም።

በኢትዮጵያ ደረጃ የተለመዱ የሕግ ባለሞያዎች የሞያ ሥነ-ምግባር ደንቦች

የዐቃቤያን ሕግ የሥነ-ምግባር ደንብ በኢትዮጵያ

የፌደራል የዐቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 443/2011 ዐቃቤያነ ሕግ ሊያከብሩ ስለሚገባው ስነ ምግባር ስለ ዐቃቤያነ ሕግ ግዴታ በሚደነግገው ክፍል ስር አካቶ ይገኛል። በዚሁ መሠረት ግዴታዎቹ የሚከተሉት ናቸው ፡-

  • ታማኝነት፡- በደንቡ እንቀፅ 69 እንደተደነገገው ዐቃብያነ ሕግ በሥራ ነጻነታቸው የተጣለባቸውን እምነት መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ መላ ጉልበቱን፣ ሀሳቡንና ችሎታውን በታማኝነት ለመንግሥትና ለሕዝብ አገልግሎት ጥቅም ማዋል አለበት፡፡
  • ስለ ዐቃቤ ሕግ ጠባይ ፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ የሕዝብን አክብሮትና እምነት እንዲያገኝ በመሥሪያ ቤቱም ሆነ ከመሥሪያ ቤቱ ውጭ በማናቸውም ጊዜ መልካም ጠባይና ሥነ ምግባር እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በማንኛውም ጊዜ የሙያውን ክብር ለማስጠበቅ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ መገኘት አለበት።
  • ታዛዥነት፡- ዐቃቤ ሕግ በደንቡ በተመለከቱት ሁኔታዎች ታዛዥ መሆን ይጠበቅበታል፣
  • ገለልተኝነት፡- ዐቃብያነ ሕግ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ወይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ ወይም በሥራቸው ላይ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን መግለጽ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ማሳየት የተከለከለ ነው፡፡ በማናቸውም ሁኔታ በሥራቸው ላይ የግል እምነታቸውን ወይም ሀይማኖታቸውን የሚያንጸባርቅ ተግባር መፈጸም የለባቸውም።
  • ዐቃቤ ሕግ ከሕዝብ ጋር ስላለው ግንኙነት፡- ዐቃቤ ሕግ ያለፍራቻ፤ ያለአድልኦ ወይም ያለምንም ጥላቻ በተለይም ከግለሰባዊና ከወገናዊ ጥቅም ወይም ከሕዝባዊና ከመገናኛ ብዙሃን ግፊት ተጽእኖ ሳያድርበት የሕዝብን ጥቅም ብቻ በማስቀደም ተግባሩን ማከናወን አለበት፡፡ ምን ጊዜም የሰዎችን ሰብዓዊ መብትና ክብር ማክበር፣ መጠበቅና መደገፍ አለበት፡፡
  • ምስጢር ስለመጠበቅ፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ መረጃው ተራ ወይም በሕዝብ ዘንድ የታወቀ ካልሆነ ወይም መደበኛ ሥራውን በሕጋዊ መንገድ ለመፈጸም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በሥራው አጋጣሚ ወይም ምክንያት ወይም በሌላ አኳኋን ያገኘውን መረጃ ለማናቸውም ሰው መግለጽ የለበትም፡፡
  • ገንዘብ ስለመበደር ፡-ለዐቃቤያን ሕግ አዘውትሮ ገንዘብ መበደር የተከለከለ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በሥራው ምክንያት ከሚያጋጥመው ባለጉዳይ ገንዘብ ለመበደር መሞከር ወይም መበደር ፍፁም ክልክል ነው::
  • ስጦታዎች፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ ከሥራው ጋር በተያያዘ ለሠጠው ወይም ወደፊት ስለሚሠጠው አገልግሎት ከማንኛውም ሰው ማናቸውም ዓይነት ዋጋ ያለውም ሆነ የሌለው ስጦታ መጠየቅ ወይም መቀበል የለበትም።
  • የጥቅም ግጭት፡- በመንግሥት ሥራና በግል ጉዳዮች ወይም ጥቅሞች መካከል ግጭት ሲኖር ወይም ሲፈጠር ይህንኑ ለቅርብ ኃላፊው ወዲያውኑ በማሳወቅ ጉዳዩ በሌላ ዐቃቤ ሕግ እንዲታይ ማመልከት አለበት፡፡
  • ስለ አለባበስ ፡- ዐቃቤ ሕግ በሥራ ላይ እያለ በሕግ የሚደነገገውን የአለባበስ ሥርዓት ማክበር እንዳለበት ደንቡ የሚደነግግ ሲሆን ይህንን መሠረት በማድረግ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤያን ሕግ አለባበስ እና ገፅታ መመሪያን ቁጥር 42/2017 ወጥቷል። መመሪያው ወንድ እና ሴት ዐቃቤያን ሕግ በስራ ቦታቸው ከአለባበስ እና ገፅታ አኳያ የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን በቀጣይ ክፍል ከዐቃቤያን ሕግ ስነ ምግባር እና አለባበስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በዝርዝር እንመለከታለን።

የዳኞች የሥነ-ምግባር ደንብ በኢትዮጵያ

በዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎች እንደተካተተው ሁሉ የኢትዮጵያ ዳኞች የነጻነት፣ የገለልተኝነት፣ የታማኝነት እና የተጠያቂነት መርሆዎችን ማክበር ይጠበቅባቸዋል። የፌደራል ዳኞች የሥነ-ምግባርና የዲስፕሊን ክስ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ቁጥር 1/2013 በምዕራፍ ሁለት ስር የሥነ ምግባር መርሆዎችና የዳኞች ተነጻጻሪ ግዴታዎች አካቶ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት ዳኞች የዳኝነት ሥራ ኃላፊነታቸውን ከማንኛውም አካል ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት ነጻ ማከናወን አለባቸው፡፡ ዳኞች የዳኝነት ሥልጣናቸውን ያለአድሎዎ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይጠቀማሉ፣ እንዲሁም ማናቸውም የዳኝነት ሥራቸው ሚዛናዊ መምሰሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የዳኝነት ተግባራቸውን፤ የዳኝነት ሥራቸው በሚፈለገው ደረጃና በዚህ ደንብ ውስጥ የተዘረዘሩት የሥነ-ምግባር መርሆዎችና የዳኝነት ተቋሙ በሚፈልጉት ደረጃ በተጣጣመና በጠንካራ የሞራል መርሆዎች፣ ተዓማኒነት እና ጨዋነት ያከናውናሉ፡፡ አንድን ጉዳይ ለመወሰን ያደረጉትን ክርክር እና በሥራቸው አጋጣሚ ያወቁትን ምስጢር ጨምሮ በዳኝነት ሥራቸው ያለባቸውን ምሥጢር የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። ለሥራ አፈጻጸም የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ማሟላትን፣ የሥራ ፖሊሲዎችን ማክበርን እና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እና/ወይም የሚሰሩባቸው ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች የሚያወጧቸውን የሥራ መመሪያዎች ማክበርን ጨምሮ ለዳኝነት ሥራቸው ቅድሚያ በመስጠት የዳኝነት ሙያ በሚጠይቀው ደረጃ ኃላፊነታቸውን በትጋት የመወጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ ዳኞች ክርክር በሚመሩበት ወቅት የችሎቱን ሥርዓት የማስጠበቅ፣ በዳኝነት ሥራ አመራር ተቀባይነት ያላቸውን ተግባሮች መፈጸም፣ ንቁ ሆኖ ጉዳዮችን መከታተል፣ ትዕግስተኛ፣ አክብሮት የሚቸራቸውና ሌሎችን የሚያከብሩ፣ ትሕትና የተላበሱ፣ ባለጉዳዮችን እና ሌሎች የፍርድ ሂደቱን የሚከታተሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያከብሩ፣ በቅንነትና በትሕትና የሚያስተናግዱ መሆን ያለባቸው ሲሆን ሌሎችም ይኸንኑ ሁኔታ እንዲከተሉ ማድረግ አለባቸው፡፡

ዳኞች በአደባባይ ሃሳባቸውን የመግለጽና የመደራጀት መብታቸውን ከዳኝነት ሥራቸው ጋር በተጣጣመ መልኩ የዳኝነት ነጻነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን በማይነካ ወይም የሚነካ በማይመስል ሁኔታ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ዳኞች የፍርድ ውሳኔ በሚሰጡበት ወይም በሥልጠና ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ካልሆነ በቀር የመንግሥትን ፖሊሲና በተወካዮች ምክር ቤትና በመንግሥት የሚወጡ ሕጎችን በአደባባይ በመንቀፍ ወይም በመደገፍ አስተያየት አይሰጡም፡፡ በክርክር ሂደት በመከባበር ላይ ተመስርቶ በሚፈጠር የሃሳብ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር፣ ዳኞች የሙያ ባልደረባ ዳኞችን ለብቻቸው በሚሆኑበት ጊዜ ወይም በአደባባይ ወይም ሌሎች ዳኞች ባሉበት አይተቹም ወይም ሃሳባቸውን አያጣጥሉም፡፡

  • ዳኞች ባለሃብት (ኢንቨስተር) መሆንና ሀብት መያዝ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዚህ ሥራ ውስጥ በዳይሬክተርነት፣ በአስተዳዳሪነት፣ በአማካሪነት፣ በአደራ ንብረት አስተዳዳሪነት ወይም በተቀጣሪ ሠራተኛነት ሊያገለግሉ አይችሉም፡፡ ዳኞች፣ በሰዎች መካከል ልዩነት ለመፍጠርና በማናቸውም ምክንያት ጥላቻን በማራመድ ዓላማ ወይም ጥላቻን በማራመድ ተግባር በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በእድሜ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበራዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ዓላማዎች በሚደራጁ ወይም በሚተገብሩ ማህበራት አባል አይሆኑም፡፡ ዳኞች ሌሎች ዳኞችን፣ ተከራካሪ ወገኖችን፣ ጠበቆችን፣ በክርክር ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችን፣ የፍርድ ቤት ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችን፣ እና ሌሎችን ክብራቸውን ሊጠብቁና በአክብሮት ሊይዙ ወይም ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡
  • ዳኞች ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠጥ ወይም በሕግ የተከለከለ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ መሆን የለባቸውም፣ እንዲሁም በአልኮል ወይም ሌላ በሕግ የተከለከለ አደንዛዥ ዕጽ ተጽዕኖ ሥር ሆነው ሥራቸውን በሚያከናውኑበት የሥራ ቦታ መታዬት የለባቸውም፡፡ ዳኞች በስራ ቦታ ጫት መቃም የለባቸዉም።
  • ዳኞች በፌደራል ሥነ-ምግባር ደንቡ የተከለከሉ ድርጊቶችን የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሊፈጽሙ አይችሉም፡፡ “የማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም” ማለት በዳኞች አስተያየቶችን እና ወይም ምስሎችን ወይም ቪዲዮችን መለጠፍ ወይም አስተያየቶችን፣ ወይም ምስሎችን ወይም ቪዲዮችን ወድጄዋለሁ/እደግፈዋለሁ ማለት ወይም ሌሎች ሰዎች የሚለጥፏቸውን ተመሳሳይ መልዕክቶች ለሌሎች ማጋራት ነው፡፡ ዳኞች እነዚህን እና ሌሎች በደንቡ የተካተቱ ግዴታዎችን ያላከበሩ እንደሆነ የሥነ-ምግባር ደንብ ጥሰት በመፈፀም ተጠያቂ ይሆናሉ።

የጠበቆች ሥነ-ምግባር ደንብ በኢትዮጵያ

በፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ 1249/2013 መሠረት ከጠበቆች ሞያዊ ግዴታ መካከል ስለታማኝነትና ለፍትሕ አጋር መሆን ይገኝበታል። በዚሁ መሠረት ማንኛውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት የጥብቅና አገልግሎት ሥራውን በታማኝነት የመሥራትና ለፍትሕ አጋር የመሆን ግዴታ አለበት፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት ያለበቂ ምክንያት ጉዳይን ያለማጓተት፣ ምስክሮችን በሐሰት ያለማደራጀት፣ ሀሰተኛ ማስረጃ ያለማቅረብ ወይም ያለማስቀረብ፣ ተዘጋጅቶ የመቅረብና ተገቢውን ክርክር የማድረግ፤ የሕግ መሠረት የሌለውንና የማያዋጣ ጉዳይን ያለመያዝ፤ የደንበኛውን ወይም ባለጉዳዩን ምስጢር ያለማውጣት እና ሌሎች መሰል የሥነ ምግባር ግዴታ አለበት፡፡ ከአዋጁ በተጨማሪ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 57/92 ጠበቆች ሊያከብሩ የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር የሥነ-ምግባር ደንቦችን ይዟል። ከእነሱም መከከል ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ አስፈላጊውን መረጃ ለደንበኛው መስጠት፣ ምስጢር መጠበቅ፣ የጥቅም ግጭት ያለባቸውን ጉዳዮች ያለመያዝ፣ ከደንበኛው ገንዘብ ያለመበደር እና ያለማበደር ይገኙበታል። በመሆኑም ጠበቆች ደንበኛቸውን በመወከል ሂደት የሥነ- ምግባር ደንቦችን በማክበር ለፍትሕ መስፈን ሚናቸው ሊወጡ ይገባል።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሥነ-ምግባር ለሰው ልጆች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ሲሆን ከሞያቸው ባህርይ አንፃር ደግሞ ልዩ ጥንቃቄ እና ትኩረት የሚፈልጉ የስራ መስኮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የሕግ ሞያ አንዱ ሲሆን የሕግ ባለሞያ ሆነው በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ የሕግ ባለሞያዎች የፍትሕ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የሥነ-ምግባር ደንቦችን ማክበር ይኖርባቸዋል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ