በጋብቻ ውስጥ የግልና የጋራ ንብረት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቤተሰብ ህግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተጠበቀ የተረጋጋ ቤተሰብ ብሎም ዜጋ መፍጠር የሚቻለው ጤናማ የጋብቻ ህይወት ሲመሠረት መሆኑ እሙን ነው። ከዚህም አንፃር ጋብቻ በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው የተከበረ ማኅበራዊ ተቋም ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ በልዩ ልዩ መንገዶች ይመሰረታል። በዚህም በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ከአንቀጽ 2 እስከ 4 በተጠቀሱት ድንጋጌዎች ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በኃይማኖት እና በባሕል ሥርዓት መሠረት ሊፈጸም ይችላል፡፡

ከተጠቀሱት የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቶች ውስጥ በአንደኛው ስነ-ስርዓት ጋብቻ የተፈጸመ እንደሆነ በጥንዶቹ መካከል ቢያንስ ሶስት ያህል በሕግ እውቅና የተሰጣቸው የትዳር ግንኙነት ውጤቶች ይመሰረታሉ። እነዚህም ግላዊ ግንኙነትን የሚመለከት ግዴታ (የመረዳዳት ግዴታ) ፣ ንብረትን የሚመለከት ግዴታ እንዲሁም ቀለብ የመስፈር ግዴታዎች ናቸው።

ጥንዶቹ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት የጋብቻ መፈጸሚያ መንገዶች ውስጥ በአንዱ ጋብቻ ቢፈጽሙ የጋብቻ ውጤትን መሠረት በማድረግ በሕግ የጋራ እና የግል ንብረቶቻቸው ላይ የሚኖረው ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በጋብቻ ውስጥ ንብረትን አስመልክቶ የሚኖርን ህጋዊ ግንኙነት በተለይም የግል ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉና የጋራ የሚሆኑ ንብረቶችን ህጋዊ የአስተዳደር ሁኔታ ለመዳሰስ ተሞክሯል።

በጋብቻ ውስጥ የጋራ ንብረት ምንነት

ከፍ ብሎ እንደተጠቆመው ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሕግና በሞራል ጥምረት አንድ የሚሆኑበት ብሎም ቀሪ ህይወታቸውን እርስ በእርስ በመደጋገፍ የሚኖሩበት ስርዓት ነው፣ የጋብቻ መመስረት ከሚፈጥራቸው ህጋዊ ግንኙነቶች ውስጥ ደግሞ ንብረትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው። ከዚህ በመነሳት የኢፌዲሪ የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 42 ላይ በመርህ ደረጃ ተጋቢዎች ንብረታቸውን በተመለከተ ስለሚያስከትለው ውጤት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ዕለት በውል መወሰን እንደሚችሉ በግልፅ ይደነግጋል።

በተያያዘ በአንቀጽ 43(1) እና (2) መሠረት በሕግ የተከለከለ ሰው የጋብቻ ውል ለመዋዋል የሕግ ችሎታ ያለው ሲሆን ይህም ውል እርስ እራሱ ሊፈጽመውና በፍርድ ቤት ሊጸድቅ ይገባል፡፡ የጋብቻ ውል በጽሑፍ መደረግና በአራት ምስክሮች (በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን ሁለት) ሆነው ሊፈርሙበት ይገባል፡፡ የባልና ሚስት የጋራ ሀብትን በተመለከተ በአንቀጽ 43 አገላለፅ ውል ያልተደረገ እንደሆነ ወይም የተደረገው ውል በሕግ ፊት የማይፀና አንደሆነ በህጉ የተቀመጠው እንደሚከተለው ነው።

በአንቀጽ 62(1) ስር በተደነገገው መሠረት ባልና ሚስቱ ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 62(2) እንደተጠቀሰው በአንቀጽ 58(2) መሠረት የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት ነው ካልተባለ በስተቀር ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ በግብይት የሚያገኙት ንብረት ሁሉ የጋራ ሀብታቸው ይሆናል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 62(3) በስጦታ ውል ወይም በኑዛዜው ቃል በሌላ አኳኋን ካልተመለከተ በስተቀር በስጦታ ወይም በኑዛዜ ለተጋቢዎቹ የተሰጧቸው ንብረቶች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አከራካሪ በሆኑ ንብረቶች ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎችን ለማየት ያህል፡-

ሀ. ከጋብቻ በፊት የግል ምሪት በነበረ ቦታ ላይ የተሰራ መኖሪያ ቤት ፡-

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 14479 በቅጽ 4፣ በመ/ቁ 26130 በቅጽ 6 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ቤት የተሰራበት ቦታ አንደኛው ወገን ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት በመንግሥት ተመርቶ ያገኘው ሲሆንና በዚሁ ቦታ ላይ ባልና ሚስቱ በጋብቻ ውስጥ ቤት ቢሰሩ ቤቱ በጋብቻ ውስጥ ስለተሰራ የጋራ ሀብት ነው ይዞታው ግን ከጋብቻ በፊት ስለተመራ የግል ነው ሊባል አይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይልቁንም ቤቱ እና ቤቱ የተሰራበት ቦታ ለየብቻ ለያይቶ መመልከት ተገቢ ስለማይሆን ቤቱም ሆነ ይዞታው የጋራ ሀብት ነው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ለ. የኮንዶሚኒየም ቤት

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 74451 በቅጽ 14 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት የኮንዶሚኒየም ቤት የተገኘው በጋብቻ ጊዜ ከሆነ በአንደኛው ተጋቢ ስም የተገኘው የኮንዶሚኒየም ቤት ቅድመ ክፍያ በጋብቻ ወቅት ካፈሩት የጋራ ንብረት የተከፈለ ከሆነ፣ ቤቱን ለማሳመርና የቤቱን ፓርትሽን ለመሥራት በጋብቻ ውስጥ ያፈሩትን ገንዘብ ከተጠቀሙ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም የኮንዶሚኒየም ቤቱ እና ያለበት ዕዳ እንደማንኛውም ንብረት የጋራ ስለሚሆን ከተስማሙ በስምምነት መስማማት ካልቻሉ ተሸጦ ዕዳው ተከፍሎ ቀሪውን ባልና ሚስቱ ሊካፈሉ ይገባል እንጂ አንደኛው ከፍሎ ያስቀር ማለት የተጋቢዎቹን የእኩልነት መብት የሚጥስ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።

በተጨማሪም በቅጽ 10 በመ/ቁ 51893 በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት ለኮንዶሚኒየም ቤት አንደኛው ተጋቢ ከማግባቱ በፊት ተመዝግቦ እጣው በጋብቻ ጊዜ የወጣ ከሆነ እና የቤቱ ባለቤት የሚያደርጋቸው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ እያሉ ከተፈጸመ የኮንዶሚኒየም ቤቱ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 62(2) መሠረት በጋብቻ ጊዜ በግብይት የተገኘ ሊባል የሚችል ስለሆነ የጋራ ሀብት ነው በሚል ወስኗል፡፡

በጋብቻ ውስጥ ስለግል ንብረት

በሕግ በጸና የጋብቻ ግንኙነት ውስጥ መግባት በጠባብ ሁኔታም ቢሆን የግል ንብረት ከማፍራት አይከለክልም። በዚህም ምክንያት በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 57 መሠረት ባልና ሚስት ጋብቻ በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ

• በውርስ ወይም

• በስጦታ

• በግል ንብረት ለውጥ የተገኘና

በየግላቸው ያገኟው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ሆነው ይቆጠራሉ በማለት ያስቀምጣል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው ጋብቻ በሚፈጽምበት ጊዜ በግል የነበረው ንብረት ከጋብቻ በኋላም የግል ሆኖ እንደሚቀጥልና ጋብቻ ከፈጸመ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ የሚያገኛቸውን ንብረቶች በጋብቻ ውስጥ የግል ሆነው እንደሚቀጥሉ በመርህ ደረጃ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና በጋብቻ ውስጥ በእነዚህ ንብረቶች አማካኝነት የሚገኝ ገቢ ከፍ ብሎ በአንቀጽ 62 ስር በተመለከተው አግባብ የጋራ ሀብት ይሆናል። ሌላው በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 58(1) መሠረት ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በሆነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሽጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ይባልልኝ ብሎ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ያጸደቀው እንደሆነ የግል ሀብቱ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በፍቺ ጊዜ ወይም ጋብቻቸው በሚፈርስበት ጊዜ ባልና ሚስቱ የግል ሀብት መሆኑን በማስረዳት የግል ንብረታቸውን መልሶ የመውሰድ መብት ይኖራቸዋል።

የንብረት አስተዳደርን በሚመለከት ፡-

አንቀጽ 59(1) እንደሚያስቀምጠው በመርህ ደረጃ እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን ራሱ የማስተዳደርና ገቢውንም ለመሰብሰብ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በአንቀጽ 59(2) እንደተመላከተው የግል ሀብቱ ላይ በነጻነት የማዘዝ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ነገር ግን ይህ ቢኖርም በአንቀጽ 60 (1) መሠረት ባልና ሚስት አንደኛው የሌላውን ተጋቢ የግል ሀብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት እና እንደ አስፈላጊነቱ እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ህጋዊ የውክልና ሥልጣን አሰጣጥ ሂደትን የሚከተል አሠራር ይሆናል።

ማጠቃለያ

በጋብቻ ውስጥ ንብረትን በተመለከተ ቀዳሚው ነገር ባልና ሚስቱ የጋብቻ ውል እንዲያደርጉ በህጉ የሚጠበቅ ሲሆን ውል ካልፈጸሙ ወይም የፈጸሙት የጋብቻ ውል በሕግ ፊት የማይጸና እንደሆነ በትዳር ውስጥ የሚያፈሯቸው ንብረቶች የግል ወይም የጋራ ናቸው ለማለት የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎችና የሰበር ውሳኔን መሠረት በማድረግ ይሆናል።

በተያያዘ አንድ ጊዜ በሕግ ፊት የሚፀና ትዳር ከተፈፀመ በኋላ በትዳር ውስጥ የሚፈራ ንብረት በአንቀጽ 57 የተቀመጠውን ሁኔታ የሚያሟላ ካልሆነ በቀር የጋራ ንብረት ተደርጎ የሕግ ግምት እንደሚወሰድ የህጉ አንቀጽ 63 በግልፅ ይደነግጋል። በተጨማሪም በዚህ ዙሪያ ያለው አሠራርና የተሰጡ ውሳኔዎች ይህንን ያሳያሉ። በመሆኑም ተጋቢዎች አንድም የንብረት አስተዳደርን አስመልክቶ ግልፅ የውል ግንኙነት በማድረግ ካልሆነም የግል ንብረትን ተገቢውን የፍርድ ቤት ሂደት ጠብቆ በግል ባለቤትነት በማስመዝገብ ካላስፈላጊ የንብረት ክርክር መዳን ይቻላል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ