መገናኛ ብዙኃን ዘርፈ ብዙ መረጃዎችን ለሕዝብ የሚያቀርቡ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡ ለሕዝብ ከሚያቀርቧቸው መረጃዎች መካከል የፍርድ ቤት ክርክሮችን የተመለከቱ መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በሕግ መሠረት እንይገለፁ ከተከለከሉ ወይም የፍርድ ቤት ነጻነትን የሚጋፉ ካልሆነ በቀር የሚሰጡ ውሳኔዎች፣ ትእዛዞች እንዲሁም ሌሎች ሂደቶች ለሕዝብ ግልፅ በመሆናቸው መገናኛ ብዙህን መረጃዎቹን ለሕዝብ ያደርሳሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃን እነዚህ ግልፅ የሆኑ የችሎት ሥራዎች እና የክርክር ሂደቶች ሲዘግቡ ግን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የመገናኛ ብዙኃን ምንነት፣ መገናኛ ብዙኃን በችሎት ዘገባ ጊዜ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች እና የሥነ ምግባር ሁኔታዎች ይዳሰሳሉ፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምንነት
በመገናኛ ብዙኃን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 2(1) መሠረት መገናኛ ብዙኃን ማለት በየጊዜው የሚወጣ ህትመትን የብሮድካስት አገልግሎትን እና የበይነመረብ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የዜና እና የፕሮግራም አገልግሎት ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ አካላት ሲሆኑ ይህም መፃሕፍትን፣ ማኅበራዊ መገኛኛ ብዙኃንን፣ ጦማሮችን እና በየጊዜው የሚወጣ ህትመት አካል ያልሆኑ ፎቶ፣ ስዕልና ካርቱን ሳይጨምር የዜና አገልግሎት ድርጅቶችን የሚያካትት ነው፡፡
በችሎት ዘገባ ወቅት ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
የተከሳሽን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት ማክበር
ማንኛዉም ተከሳሽ የጥፋተኝነት ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ከወንጀል ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳለው በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 20/3/ ስር ተመላክቷል፡፡ ምክንያቱም ከክርክር በኋላ ተከሳሹ ነፃ ሆኖ ሊገኝም ስለሚችል ነው፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኖች የችሎት ዘገባዎችን ሲሰሩ የጥፋተኝት ፍርድ ያልተሰጠበትን ተከሳሽ ጥፋተኛ አድርጎ ከመዘገብ መቆጠብ አለባቸው፡፡
ሚዛናዊ መሆን
መገናኛ ብዙኃን በክርክር ላይ ባለ እና ውሳኔ ባልተሰጠው ጉዳይ ላይ አንዱ ወገን አሸናፊ በሚያስመስል መልኩ ወይም ለአንዱ ተከራካሪ ወገን በማዳላት ሚዛናዊ ባልሆነ አግባብ መዘገብ የለባቸውም፡፡ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎችና ትንተናዎች ፍርድ ቤት አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት በሚገባው ጉዳይ ከፍርድ ቤቱ አስቀድሞ ውሳኔ መስጠት በሚመስል መልኩ የሚቀርቡ መሆን የለባቸውም፡፡
የምስክሮች ከጥቃት የመጠበቅ መብት
ማንኛውም ምስክር ለፍትሕ እርዳት የመስጠት ህጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ ጥቆማ ወይም ምስክርነት በመስጠቱ ምክንያት በምስክሮችና በቤተሰቦቻቸው ህይወት ወይም ንብረት ላይ አደጋ የሚፈጠር ከሆነ የምስክሮች ማንነት፣ አድራሻ፣ ንብረት እንዳይገለፅ በማድረግ የሕግ ጥብቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በመሆኑም መሰል ሁኔታዎች ሲኖሩ የምስክሮች ህይወት ወይም ንብረት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በችሎት የተገኙ ምስክሮችን ማንነት በመገናኛ ብዙኃን ከመግለፅና በዘገባ ዉስጥ ከማካተት መቆጠብ ይገባል፡፡
የጉዳዩን ፍሬ ነገር እንዳይዛባ መጠንቀቅ
መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ሲሰሩ በችሎት ሂደት የነበረውን ሁኔታ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ በመዘገብ የጉዳዩ ፍሬ ነገሮች እንዳይዘቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ሕግ የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ ዘገባዎች የተዛቡ እንዳይሆኑ ከሕግ ባለሞያ ማብራሪያ በመጠየቅ ቢሰሩ ተሻለ ይሆናል፡፡
ችሎት ማክበር
ችሎት የራሱ ሥነ ሥርአት አለው፡፡ ማንኛውም በችሎት የሚገኝ ሰው ይህን የችሎት ሥርአት ማክበር ያለበት በመሆኑ ዘጋቢዎች ዘገባ ለመሥራት በችሎት ሲገኙ የፍርድ ቤትን የችሎት ሥነ ሥርአት ጠንቅቆ ማወቅ እና ችሎት ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
የግል ህይወት መብትን ማክበር
የግል ህይወት መከበር በህገ መንግስቱ አንቀጽ 26 መሠረት በሕግ ጥበቃ የተደረገለት ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ይህም መብት የአንድ ሰው የግል ሕይወት፣ ሰዉነት፣ ንብረት እንዲሁም የሚፃፃፋቸው ድብዳቤዎች የተጠበቁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህ መብት ለሀገር ሰላም፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ለሕዝብ ጤና እና ሞራል ሲባል በልዩ ሁኔታ በሕግ መሠረት ብቻ ሊገደብ የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚሰሩ ዘገባዎች የተከራካሪ ወገኖችንም ሆነ የማንኛውንም ዜጋ የግል ነጻነትና መብት የሚጋፉ መሆን የለባቸውም፡፡
ሥነ ምግባር
እያንዳንዱ ሙያ የሚጠይቀው የራሱ የሆነ ሥነ ምግባር አለ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያ መሆንም የሚጠይቀው የራሱ የሆነ የሙያ ሥነ ምግባር አለው፡፡ ለአብነትም ከአድሎ የፀዳ እና የተለያዩ ሀሳቦችን በእኩል የሚያስተናግድ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የችሎት ዘገባ የሚሰራ ባለሞያ የሙያ ሥነ ምግባሩን በጥብቅ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡
ማጠቃለያ
መገናኛ ብዙኃን የችሎት ዘገባዎችን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችን ለዜጎች በሚያደርሱበት ወቅት ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ ምግባር ደንቦችን ማክበር ይገባቸዋል፡፡ በተለይ ችሎት ውስጥ መረጃ ሲሰበሱቡም ሆነ ሲዘግቡ በፍርድ ቤት የተቀመጡ የችሎት መመሪያዎችንና የችሎት ሥነ ሥርአት በጥንቃቄ ሊያከብሩ የሚገባ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሕዝብ የሚደርሱ ዘገባዎች የተከራካሪ ወገኖችን መብትና ነጻነትን የሚያከብሩ፣ የምስክሮችን ደኅንነት የሚያስጠብቁ እንዲሁም የፍርድ ቤትን ነጻነት የማይጋፉ መሆን ይገባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ