መግቢያ
አለማችንን እጅጉን እየፈተኗት ከሚገኙ ችግሮች መካከል አንዱ ህገ-ወጥ የአደንዛዥ እጾች ማለትም የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች ምርት፣ ዝውውር እና አጠቃቀም ነው። በእያንዳንዱ የአለማችን አገራት ላይ ለተለያዩ ወንጀሎች መስፋፋት እና ለማኅበረሰብ ሰላም፣ ጸጥታ እና ደኅንነት መደፍረስ ስጋት ከመሆን አልፈው ከፍተኛ የጤና፣ የኢኮኖሚዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ በህክምናው አለም ለሰው ልጅ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይታወቃል። በመሆኑም በእነዚህን መድኃኒቶች ምርት፣ ዝውውር እና አጠቃቀም ላይ ቁጥጥር በማድረግ፣ በሕግ እና በጥንቃቄ በመያዝ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ችግሮች መከላከል አስፈላጊ ነው።
የአደንዛዥ እጾች ምርት እና ዝውውር ከፍተኛ አቅም ባላቸው የወንጀል ቡድኖች እና ግለሰቦች የሚመራ ከፍተኛ የሰው ኃይል እና ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት፤ ድንበር ተሻጋሪ እና የተለያዩ አገራትን የሚነካ ነው። ስለሆነም ይህን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የአገራትን ትብብር፣ ቅንጅት እና አብሮ መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ አገራትም ይህንኑ በመገንዘብ በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት የተለያዩ ስምምነቶችን እና ህጎችን አጽድቀዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በ1961 የወጣው የናርኮቲክ መደኃኒቶችን ምርት፤ አጠቃቀም እና ስርጭትን ለመከላከል የተደረገው ስምምነት፤ በ1971 የወጣው የሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶችን ምርት ፤አጠቃቀም እና ስርጭቶችን ለመወሰን የተደረገው ስምምነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተባበሩት መንግስታት ስር የተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ፅህፈት ቤት (United Nations Office on Drugs and Crime (UNODC)) ህገ-ወጥ መድኃኒቶችን፣ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።
ኢትዮጵያ በአደንዛዥ እፆች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እና የሕግ ተጠያቂነትን ለማምጣት የሚያስችሉ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ ሀገራዊ ህጎችን አውጥታ በስራ ላይ አውላለች። ከእነዚህም ውስጥ በ1996 በወጣው የወንጀል ሕግ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶችን እና ህገ ወጥ የሆኑ አደንዛዥ እጾችን ያለፍቃድ ማምረት፣ መጠቀም፣ ማከማቸት እና ማዛወር ክልክል እንደሆነ እና በወንጀል እንደሚያስቀጣ ደንግጋለች። በተጨማሪም የምግብ እና መድኃኒት አስተዳዳር አዋጅ ቁጥር 1112/11 ላይ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃንቶችን ለማምረት፤ ለማዘዋወር፤ ለማከማቸት እና ለመጠቀም ከሚመለከተው ባለሥልጣን የተለየ ፍቃድ እንደሚያስፈልግ፤ በአዋጁ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እና ጥንቃቄዎችን የማያሞላ እና የሚጥስ አካል በወንጀል እንደሚቀጣ ደንግጋለች፡፡
በዚህ አጭር ትምህርታዊ ጽሑፍ አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ህጎች፣ የአደንዛዥ እጾች ምንነት፣ የአደንዛዥ እጽ አይነቶች፣ አደንዛዥ እፆች የሚያስከትሉት ጉዳቶች እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት ይዳሰሳል።
አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ህጎች
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አደንዛዥ ዕፆችን መቆጣጠርን በተመለከት ሶስት ዋና ዋና ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፤
1. የናርኮቲክ ንጥረ ነገር ነጠላ ኮንቬክሽን (the Single Convention on Narcotic Drugs of 1961 (as amended in 1972),
2. የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ኮንቬክሽን (the Convention on Psychotropic Substances of 1971), እና
3. በተባበሩት መንግስታት በህገ-ወጥ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ እፆች ላይ የተደረገ ኮንኔክሽን (the United Nations Convention against Illicit Traffic in Narcotic Drugs and Psychotropic Substances of 1988). ስምምነቶቹ እርስ በእርስ ተደጋጋፊ እና አንዱ እንዱ የሚያማሉ ናቸው (mutually supportive and complementary).
ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አብዘህኛው የአለም አገራት የአደንዛዥ እፆችን ጥፋት (offenses) በተለያዩ የወንጀል መለኪያ ቢሆንም በህጎቻቸው ውስጥ አካተው የሚገኙ ሲሆን ጥፋቶቹ የአቅርቦት (supply) እንደ እርሻ፣ ማምረት (በፋብሪካ) እና ማዘዋወር እንዲሁም የፍላጎት (demand) እንደ መጠቀም እና መያዝን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ህጎቹ ተለይተው ጎጂ ናቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ወይም አደንዛዥ ዕፆችን ማምረትን፣ ማዘዋወርን፣ መጠቀም እና መያዝን ወንጀል የሚያደርጉ ሲሆን አተገባበራቸው ከሀገር ሀገር የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁኑና ብሔራዊ ህጎቹ የዓለም ዓቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን መዋቅር የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡
የአደንዛዥ እጾች ምንነት
አደንዛዥ እፅ ማለት የሰውነትን ተግባር የሚጎዳ፣ በሕግ ቁጥጥር እና ክልከላ የሚደረግበት መድሀኒት ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1961 በተደረገው የናርኮቲክ መደኃኒቶች ኮንቬንሽን እና በ1971 በተደረገው የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ኮንቬንሽን ላይ የናርኮቲክ እና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶችን በመዘርዘር ያስቀመጠ ሲሆን እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
– ናርኮቲክ መድኃኒቶች:- ህመምን ማስታገስ ጨምሮ የሰውን ልጅ በቀላሉ ሱስ የሚያስይዙ፣ የሚያነቃቁ፣ የሚያደነዝዙ፣ የተለያዩ ተለዋዋጭ ስሜት ውስጥ የሚከቱ በተፈጥሮ የሚበቅሉ እጾች እና በፋብሪካ የተመረቱ መድኃኒቶች ናቸው፡፡
– ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች፡- የአዕምሮችንን ሁኔታ፣ ግንዛቤን፣ አስተሳሰብን፣ ስሜትን ባህሪ የሚቀይሩ በአጠቃላይ የአዕምሮን ጤንነት እና አሠራርን የሚያቃውሱ ንጥረ ነገሮች እና መድኃኒቶች ናቸው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳዳር አዋጅ ቁጥር 1112/11 አንቀጽ 2(11) እና 12 ለናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች ትርጉም የሰጠ ሲሆን ናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች ማለት በተባበሩት መንግሥታት በወጣው እና ኢትዮጵያ ባፀደቀችው የናርኮቲክ መድኃኒቶች እና የሳይኮትሮፒክ ንጥረ-ነገሮች ስምምነት መሠረት ቁጥጥር የሚደረግበት መድኃኒት ሆኖ በአስፈጻሚ አካሉ (አዋጁን እና አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ ህጎችን በፌደራል ደረጃ ለማስተዳደር በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የፌደራል መንግሥት አካል) እንደ ናርኮቲክ መድኃኒትነት የተመደበ መድኃኒትን እንደሚያጠቃልል ያስቀምጣል፡፡
የአደንዛዥ እጽ አይነቶች
በአለማችን ላይ በተፈጥሮ የሚበቅሉ አደንዛዥ እጾችን ጨምሮ በፋብሪካ የሚመረቱ መድኃኒቶች እና አደንዛዥ እጾች ያሉ ሲሆን በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ከሚታወቁ እና በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉ መካከል ካናቢስ (Cannabis)፣ ኮኬን (Cocaine)፣ ኦፒያም (Opium)፣ ሔሮየረን (Heroin)፣ ሞርፊን (morphine) እና ሌሎች መድኃኒቶች እና አደንዛዥ እጾችን ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አደንዛዥ እፆች የሚያስከትሏቸው ጉዳቶች
አደንዛዥ እጾች አላግባብ ጥቅም ላይ ከዋሉ በሰው ልጆች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትሉ ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ፡-
– በቤተሰብ እና ማኅበረሰብ ላይ የሚደርስ ጉዳት፡- በአደንዛዥ እፆች ሱስ ሳቢያ በሚከሰት የቤተሰብ መበተን ፤ በማኅበረሰብ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ቀውስን ይፈጠራል፡፡
– የጤና ጉዳት ፡- አደንዛዥ እጾች በሰው ጤና ላይ ሊያስከትሉ ከሚችሉት ችግሮች መካከል ድብርት፣ ጭንቀት፣ የአዕምሮ መታወክ፣ የክብደት መቀነስን ጨምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ የጤና ችግሮችን ያስከትላሉ፡፡
– ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ፡- በአደንዛዥ እጽ ሱስ የሚያዙ ሰዎች በአብዛኛው እድሜቸው ከ 18 -35 ዓመት የሚጠጉ አምራች የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ሲሆኑ በሱስ ምክንያት ስራ መሥራት እና ማምረት ስለማይችሉ እንዲሁም በተለያዩ የጤና እና የማኅበራዊ ችግሮች ስለሚጠቁ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት እንዲፈጠር እና ኢኮኖሚው በሙሉ ኃይል እንዳያመርት ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም አገራት ለአደንዛዥ እጽ ተጠቂዎች ህክምና እና የአደንዛዥ እጽ ምርት እና ዝውውርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ወጪን ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡
– በአከባቢ እና ተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ጉዳት ፡- የአደንዛዥ እጾችን ለማምረት በሚደረግ የደን ምንጣሮ እና በሚለቀቁ አደገኛ ኬሚካሎች ምክንያት በአከባቢ እና በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ብክለት እና ጉዳት ሊደርስ ይችላል።
– የወንጀል መስፋፋት፡- አደንዛዥ እጾች ለወንጀሎች መበራከት እና መስፋፋት እንዲሁም ለስላም እና ጸጥታ መደፍረስ ዋንኛ ምክንያቶች ሲሆኑ በወንጀለኞቹ ሊፈጸሙ ከሚችሉ ወንጀሎች መካከል ስርቆት፣ ዘረፋ፣ ሙስና እና ሌሎችም ወንጀሎች ይገኙበታል።
አደንዛዝ እፆች የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን ማምረትና በማሰራጨት የሚደረጉ ወንጀሎች ስር ተካቶ ይገኛል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 525 ላይ እንደተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮተክና ሣይኮትሮፒክ መድኃነቶችን ወይም እፆችን ማምረት፣ መሥራት፣ ማዘዋወር ወይም መጠቀም የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በድንጋጌው ስር የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡-
– ማንም ሰው ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው መርዛማ ነገሮችን ወይም ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶችን ወይም እፆችን ያበቀለ፣ ያመረተ፣ የሰራ፣ የለዋወጠ ወይም የፈበረከ፤ ንጥረ ነገሮቹን ይዞ የተገኘ፣ ወደ ሀገር ያስገባ፣ ወደ ውጪ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የደለለ፣ የገዛ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያሰራጨ፣ ያዘዋወረ፣ አሳልፎ የሰጠ ወይም ለሌላ ያስገኘ፤ ንጥረ ነገሮቹን ለመስሪያነት፣ ማቀነባበሪያነት፣ ማምረቻነት፣ መሸጫነት ወይም ማከፋፈያነት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነበትን ቤቱን፣ ግቢውን ወይም ቦታውን የሰጠ፣ ያከራየ ወይም የፈቀደ ከአምስት ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከአንድ መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ (አንቀጽ 525/1)
– ቅጣቱን የሚያከብዱ ሁኔታዎች በአንቀጽ 525/2 ስር የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም፡-
– ወንጀሉ የተፈፀመው ለዚሁ ንግድ ወይም በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ወንጀል ለመፈፀም በተደራጀ የቡድን ወይም የማህበር አባል በሆነ ወይም ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ሙያው አድርጎ በያዘ ሰው እንደሆነ ፤
– ጥፋተኛው የተከለከለውን ህገ ወጥ ነገር ወይም ለዚሁ ዓይነት ነገር መጠቀሚያ ቦታ እያወቀ የሰጠው ወይም የፈቀደው በአፍቅሮ ንዋይ፣ በወራዳነት ወይም አግባብ በሌለው ሌላ ዓላማ እንደሆነ፤ ወይም ተጠቃሚው ህፃን፣ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወጣት ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ወይም የእፅ ሱስ ያለበት እንደሆነ፤
– ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈፀመው ሕፃናትን ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ሰውን ለወንጀል ድርጊቱ አፈፃፀም መጠቀሚያነት በማድረግ እንደሆነ፤
– ወንጀሉ የተፈፀመው በማረሚያ ቤት፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ፣ ሕፃናት ወይም ወጣት ተማሪዎች ለትምህርት፣ ለስፖርት ወይም ለሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሚጠቀሙበት ቦታ እንደሆነ ወይም
– ወንጀለኛው ከዚህ ቀደም በፈፀመው ተመሳሳይ ወንጀል ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት የነበረ እንደሆነ ከአሥር ዓመት በማይንስ ፅኑ እስራት እና ከሁለት መቶ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
– ማንም ሰው ለራሱ ወይም ሌላ ሰው በግል እንዲጠቀምበት በማሰብ፣ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ያበቀለ፣ የገዛ፣ የተቀበለ፣ የሠራ፣ ይዞ የተገኘ፣ የሸጠ፣ የሰጠ ወይም ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ ያለሕክምና ፈቃድ ወይም በማናቸውም ሌላ ህገ ወጥ መንገድ የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ እንደሆነ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከ50 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል። (አንቀጽ 525/4)
– ናርኮተክ ወይም ሳይኮትሮፒክ ነገሮችን ለሕገወጥ ዓላማ ለማዋል በማሰብ የሕክምና ባለሞያውን በማጭበርበር የመድሃኒት ማዘዣ እንዲሰጠው ያደረገ ወይም በሕጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ያገኘውን ማዘዣ ላልተፈቀደለት ሦሥተኛ ወገን ያስተላለፈ ሰው ወይም የእነዚህን ነገሮች ማዘዣ አስቦ በሕገ ወጥ መንገድ የፃፈ የህክምና ባለሙያ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል። (አንቀጽ 525/4)
በሌላ በኩል የምግብ እና መድኃኒት አስተዳዳር አዋጅ ቁጥር 1112/11 ናርኮቲክ መድኃኒት፣ ሳይኮትሮፒክ መድኃኒ ለማምረት፣ ለማስመጣት ወይም ለመላክ ከአስፈጻሚ አካሉ ልዩ ፈቃድ ማግኘት እንደሚያስፈልግ በአንቀጽ 31፣ የናርኮቲክና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒት አስተዛዘዝ ሥርዓት እና ስለማደል በአንቀጽ 32 እና 33 ስር በዝርዝር ደንግጎ ይገኛል።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶች እንደሆኑ እና እነዚህን ንጥረ ነገሮች ከሕግ አግባብ ውጪ ማምረት፣ መሥራት፣ ማዘዋወር ወይም መጠቀም እና ሌሎች በወንጀል ህጉ የተጠቀሱ ተግባራትን መፈፀም የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከተል መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ህብረተሰቡ አደንዛዥ ዕፆችን የተመለከቱ ክልከላዎችን ባለመተላለፍ እራሱን ከሕግ ተጠያቂነት እና ንጥረ ነገሮቹ ከሚያስከትሉት የስነ ልቦና፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ጉዳት ሊጠብቅ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ