የነዳጅ ንግድና ስርጭት በኢትዮጵያ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በአሁኑ ወቅት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከግብርና እስከ አምራቹ ዘርፍ፣ ከትራንስፖርት እስከ መደበኛ የቤት ውስጥ የኃይል ፍጆታ ድረስ ነዳጅን የመጠቀም ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ያለበትን ሁኔታ መረዳት ይቻላል። በአንፃሩ የዘመኑ ቴክኖሎጂ እድገት በሚፈቅደው ልክ የኃይል አማራጮችን ለማስፋት በርካታ ጥረቶች ሲደረጉም እናስተውላለን። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአሁኑ ወቅት ለምሳሌ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣታቸውና በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ማሽኖችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችም ቢሆን በየጊዜው በሚያደርጓቸው ማሻሻያዎች ላይ የተሽከርካሪዎችን የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ ነው።

ይሁን እንጂ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ስለነዳጅ ሲነሳ ከኃይል ምንጭነትም አልፎ የአለም የፖለቲካ ስርዓት አሰላለፍ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ሀብት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፣ በዚህም ምክንያት ነዳጅ አምራች አገሮች ከሌሎች አገራት ጋር በሚኖራቸውን ግንኙነት ላይ ነዳጅ ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ መሳሪያ ሆኖ ተፅእኖ ሲፈጥር ይስተዋላል።

በጥቅሉ የነዳጅ ውጤቶች ከሚሰጡት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ፋይዳ አንጻር አቅርቦት፣ የክምችትና ስርጭት ሂደቱ የተለየ ክትትልና ጥብቅ የቁጥጥር ስርዓት የሚፈልግ ነው። በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ የሚፈጠር ክፍተት ከሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባሻገር ከጋዝ ተፈጥሯዊ ባህሪ የተነሳ በሰውና በእንስሳት ጤና፣ በንብረትና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ይህንን ልዩ ጥንቃቄ የሚሻ ወሳኝ የተፈጥሮ ምርት ግልፅ የሕግና የአስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶለት በጥንቃቄ ሊመራ ይገባል።

ከዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ በ1996 ዓ.ም ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን አቅርቦት ስራ ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 838/2016 ለ11 ዓመታት በስራ ላይ የነበረ ሲሆን በጥር 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ 1363/2017 በሚል አዲስ ሕግ ተተክቷል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በዚህ ሕግ የተሸፈኑ ጉዳዮችን በተለይም ህጋዊ የስርጭት ሂደት ምን መምሰል እንዳለበት፣ የአከፋፋዮችና የተጠቃሚዎች መብትና ግዴታ እንደዚሁም በህጉ የተቀመጡ ዝርዝር ክልከላዎችን መተላለፍ የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት በአጭሩ መዳሰስ ይሆናል።

ትርጉም

ከመደበኛው የቃል ፍች ስንነሳ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ነዳጅ የሚለው ቃል “ሞተርን ለማንቀሳቀስ የሚያገለግል በጋዝ ወይም በቤንዚን መልክ የሚገኝ የኃይል ምንጭ ነው” በሚል ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን። ከዚህ ትርጉም እንደምንረዳው አንድን ምርት ነዳጅ የሚያስብለው አብይ ጉዳይ ሞተርን የማንቀሳቀስ አቅም ያለው እንደሆነ ነው።

በሌላ በኩል በአዲሱ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ ቁጥር 1363/2017 አንቀጽ 2(1) መሠረት “የነዳጅ ውጤቶች” ማለት የተፈጥሮ ድፍድፍ ነዳጅን፣ ፔትሮሊየም ጋዝን፣ ባዮ ፊውልን ወይም ሲንተቲክ ነዳጅን ከማጣራት ወይም ከማቀናበር የተገኘ ንፁህ ወይም አግባብ ባለዉ መንገድ የተደባለቀ የነዳጅ ውጤት ሆኖ ቤንዚንን፣ ኬሮሲንን፣ ናፍጣን፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣን፣ የአውሮፕላን ነዳጅንና የመሳሰሉትን ያካትታል ሲል ተርጉሞታል። በዚህ ትርጉም መነሻነት በርካታ ቴክኒካዊ ሂደትን የሚያልፉ ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ነዳጅ አይነቶች እንዳሉ በመዘርዘር ቢያስቀምጥም ከፍ ብሎ በተመለከትነው ትርጓሜ መሠረት ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር ዓላማው ምን እንደሆነ ህጉ ክፍት አድርጎ የተወው መሆኑን እንረዳለን።

የነዳጅ ማደያዎች ግዴታ

በአዋጁ አንቀጽ 2 (10) መሠረት ነዳጅ ማደያ ማለት “የነዳጅ ውጤቶችን ከአከፋፋይ ገዝቶ ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች በችርቻሮ የሚሸጥ ሰው ነው” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። እነዚህ ማደያዎች በነዳጅ ስርጭት ሂደት ውስጥ ለመጨረሻው ተጠቃሚ በማድረስ በኩል የማይተካ ሚና ያላቸው አካላት ናቸው። በዚህ ምክንያት ማንኛውም ነዳጅ አዳይ ወይም የነዳጅ ማደያ የሚከተሉት ግዴታዎች አክብሮ መሥራት ይኖሩበታል፡-

  1. ለሚያቋቁመው ለእያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ በባለሥልጣኑ የሚጠየቁ መሥፈርቶችን አሟልቶ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የማግኘት፤
  2. የነዳጅ ውጤቶችን በችርቻሮ ለመሸጥ የሚጠቀምባቸውን መሳሪያዎች በየጊዜው የማስመርመር እና ሌሎች በዚህ አዋጅ መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ መመሪያ የሚወሰኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶ የመሥራት፤
  3. የሚመለከተው የመንግሥት አካል በአግባቡ የሚሠሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ የሰጠባቸውን የነዳጅ ውጤቶች መቅጃ መሳሪያዎች ልኬት ሊያዛባ ከሚችል ማናቸውም ድርጊት የመቆጠብ፤
  4. የነዳጅ ውጤቶችን ውል ከገባው አከፋፋይ ብቻ በመግዛትና በመረከብ ነዳጅ ማደያው ውስጥ እንዲራገፍ የማድረግ እና ስለተራገፈው ነዳጅ በጽሑፍ ወይም በሚዘረጋው የቴክኖሎጂ የአሠራር ሥርዓት መሠረት ለአጓጓዡ፣ ለአከፋፋዩ እና ለባለሥልጣኑ ወይም አግባብ ላለው አካል ተገቢውን መረጃ የመስጠት፤
  5. የነዳጅ ውጤቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ያለመቀላቀል፣ ጥራቱን ሊያጓድል ከሚችል ማናቸውም ድርጊት የመቆጠብ እና ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች በችርቻሮ የመሸጥ፤
  6. የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የነዳጅ ውጤቶች አግባብነት ያለው የመንግሥት አካል በወሰነው ዋጋ ብቻ የመሸጥ፤
  7. ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች ያልተቆራረጠ የሃያ አራት ሰዓት የሽያጭ አገልግሎት የመስጠት፤
  8. ነዳጅ በማደያ ውስጥ እያለ የሽያጭ አገልግሎት አለማቋረጥ፣
  9. ነዳጅ ውጤቶች ግብይት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ የመያዝና ሲጠየቅም ለባለሥልጣኑ ወይም አግባብ ላለው አካል የማቅረብ፤ እና.
  10. በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ መመሪያ የሚወሰኑ ሌሎች ተዛማጅ ግዴታዎችን የማክበር ግዴታን ያጠቃልላል፡፡ እና ባለስልጣኑ በሚያወጣቸው ልዩ ልዩ መመሪዎች የተካተቱ ዝርዝር ግዴታዎችንም ይጨምራል።

የነዳጅ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ግዴታ

በአዋጁ መሠረት የነዳጅ ተጠቃሚ የሚባለው ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶችን ከአከፋፋይ በጅምላ በመግዛት ለተፈቀደለት ፕሮጀክት ወይም የልማት ድርጅት ፍጆታ የሚያውል ሰው ነው። (አንቀጽ 2 (13) ፣በዚህ ሂደት ውስጥ ለምሳሌ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ውስጥ የነዳጅ ተጠቃሚ ተብለው በመመሪያ የተለዩ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጭ ተቋማት፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት እና የአቬሽን ባለሥልጣን ያሉትን ያካተተ ሆኖ የሚመራውም ነዳጅን ከኩባንያዎች በቀጥታ በመግዛት የሚጠቀሙ ተቋማት የፈቃድ አሰጣጥ በሚመለከት መመሪያ ቁጥር 905/2014 መሠረት ነው። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት በችርቻሮ ከሚያገኙት ከመጨረሻዎቹ ተጠቃሚዎች የተለዩ ሆነው የሚከተሉት ግዴታዎች ተጥለውባቸዋል።

  • በመመሪያ በሚወሰነው መሠረት የቀጥታ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያበቁ መስፈርቶችን በማሟላት ለባለሥልጣኑ ማመልከቻ አቅርቦ ፈቃድ የማግኘት፤
  • የተፈቀደለትን የነዳጅ ውጤቶች አይነት እና መጠን ከአከፋፋይ በመግዛት ለተፈቀደለት ፕሮጀክት ወይም የመንግሥት የልማት ድርጅት ዓላማ ብቻ የመጠቀም፤
  • የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች አጠቃቀም በተመለከተ መረጃ በመያዝ በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ መመሪያ በሚወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጽሑፍ ወይም በሚዘረጋ የቴክኖሎጂ የአሠራር ሥርዓት መሠረት ለባለሥልጣኑ ሪፖርት የማቅረብ፤
  • በማንኛውም ምክንያት የቀጥታ ተጠቃሚ መሆኑን ሲያቋርጥ ይህንኑ በጽሑፍ ወይም በሚዘረጋ የቴክኖሎጂ የአሠራር ሥርዓት መሠረት ወዲያውኑ ለባለሥልጣኑ እና የነዳጅ ውጤቶችን ሲያስረክበው ለነበረው አከፋፋይ የማሳወቅ እና የተሰጠውን ፈቃድ ለባለሥልጣኑ የመመለስ፤
  • በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ መመሪያ የሚወሰኑ ሌሎች ዝርዝር የአጠቃቀም ሁኔታዎችን የማክበር ግዴታ።

አስተዳደራዊ እርምጃዎች

በአዋጁ መሠረት የነዳጅ ግብይትን ሂደት በመምራት ረገድ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛው ሥልጣን ተሰጥቶታል። ከሚኒስቴሩ በተጨማሪ በተለይም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 2(20) እና 11 መሠረት የተቋቋመው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ሲሆን ባለስልጣኑ ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ ሰፋፊ ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል። በመሆኑም ይህ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት በአዋጁና አዋጁን ተከትሎ በሚወጡ ህጎች ላይ የተቀመጠውን አሠራር በሚጥሱ የትኞቹም ተዋናዮች ላይ በአንቀጽ 23 የተመለከቱትን ጨምሮ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ይወሰዳል። ከእነዚህም ውስጥ፣-

  • አዋጁን ወይም ሌሎች ህጎችን ተላልፎ በተገኘ ተዋናይ ላይ የተሰጠን የብቃት ማረጋገጫ ወይም የግንባታ ፈቃድ የመሰረዝ ወይም የማገድ፣
  • በዚህ አዋጅና በሌሎች ሕግች ስለመረጃ አያያዝ፣ወይም ስለሪፖርት አቀራረብ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን የተላለፈ ተዋናይን የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ካላስተካከለም ፈቃዱን የመሰረዝ ወይም የማገድ ውሳኔ ይሰጣል።
  • በአጠቃላይ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አለመውሰድ (ለነባር)፣ የሚጠበቅበትን ዴፖ ወይም ማደያ አለመገንባት፣ እና ሌሎች በመሪያ የተመላከቱ ግዴታዎችን አለመፈፀም ፈቃድ እስከማሰረዝ የሚያደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ምክንያቶች ናቸው።

ከዚህ ባለፈ በተለይም የነዳጅ ውጤቶች የሥርጭት፣ የርክክብና የሽያጭ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 904/2014 ላይ የነዳጅ ማደያዎች፣ ቦቴዎችና የትራንስፖርት አካላትና ሹፌሮች፣ የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችና ነዳጅ አዳዮች ላይ ከአሽከርካሪ ፈቃድ ማገድ እስከ የአከፋፋይነት ፈቃድ ስረዛ ድረስ የሚደርሱ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች በመመሪያው ተካተዋል።

የወንጀል ተጠያቂነት

በአዋጁ መሠረት የቁጥጥር ሥልጣን የተሰጠው አካል የሚወስዳቸው ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እርጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው የሚከተሉትን ክልከላዎች መተላለፍ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል፣ እነዚህም

  • የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርአት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ወይም በመመሪያ በተወሰነው መሠረት አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከብር ሶስት መቶ ሃምሳ ሽህ እስከ አምስት መቶ ሽህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • የነዳጅ ውጤቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ያቀረበ ማንኛውም ሰው ነዳጁ እንዲወገድ ተደርጎ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺ እስከ አምስት መቶ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የነዳጅ ውጤቶች መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጥ የተገኘ የግብይት ተዋናይ በመጀመሪያ ጥፋት ከብር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺ እስከ አምስትት መቶ ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፤ ድርጊቱን በተደጋጋሚ ከፈጸመ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር ሶስት መቶ ሺ እስከ አምስት መቶ ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • በሚመለከተው አካል የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሰረውን የቆረጠ ወይም ልኬቱን ያዛባ ማንኛውም ሰው ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺ እስከ አምስት መቶ ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • የካሊብሬሽን የምስክር ወረቀት ሳይዝ ወይም ካልብሬት የተደረገውን የነዳጅ ውጤቶች ልኬት በማዛባት የነዳጅ ውጤቶችን ሲያጓጉዝ ወይም ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የነዳጅ ውጤቶች ተወርሰው ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺ እስከ አምስት መቶ ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ሲያጓጉዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጪ ሲያራግፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ሲያጓጉዝ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዙት የነዳጅ ውጤቶች ተወርሰው ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር አራት መቶ ሺ እስከ ሰባት መቶ ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • አግባብ ካለው አካል የጽሑፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶቹን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከብር ሶስት መቶ ሽህ እስከ አምስት መቶ ሽህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
  • የባለስልጣኑን ወይም አግባብ ያለውን አካል የቁጥጥር ሂደት የተቃወመ፣ ያሰናከለ ወይም በማንኛውም መንገድ ተፅዕኖ ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከብር ሁለት መቶ ሽህ እስከ አምስት መቶ ሽህ ብር መቀጮ ይቀጣል።
  • በዚህ አንቀጽ የተመለከቱት ድርጊቶች የሕግ ሰውነት ባለው አካል የተፈፀሙ በሆነ ጊዜ ከብር ስድስት መቶ ሽህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር መቀጮ ይቀጣል።
  • የነዳጅ ግብይት የዲጂታል ስርዓት ግዴታን የጣሰ፣ ያጭበረበረ፣ ተግባራዊ ያላደረገ የግብይት ተዋናይ ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እስራትና እስከ ሶስት መቶ ሽህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
  • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2)፣(4)፣(5) እና (6) የተመለከቱትን ድርጊቶች ለሁለተኟ ጊዜ በመፈፀም ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ የግብይት ተዋናይ በዚህ አንቀጽ ከሚጣልበት ቅጣት በተጨማሪ ድርጅቱ ለአምስት ዓመት እንዲዘጋ ይደረጋል።

ማጠቃለያ

በአሁኑ ወቅት ነዳጅ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለ ምርት ነው። የተሳለጠ የነዳጅ ግብይት እንዲኖር ካስፈለገ በአስተዳደር አካላት ከሚወሰዱት ልዩ ልዩ እርምጃዎች በተጨማሪ የመጨረሻው ተጠቃሚን (End user) ጨምሮ ህብረተሰቡ ያሉትን የሕግ ማዕቀፎች ጠንቅቆ በማወቅ ኃላፊነቱን በንቃት ሊወጣ ይገባል።

በተያያዘም አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ከሕግ አንፃር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ካሻሻላቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል የተጠቃሚዎችንና የአከፋፋዮችን ግዴታ በዝርዝር ማስቀመጡ፣ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል እንዲሆን መፈቀድ፣ ራሱን በቻለ ተቋሚ የሚመራበትን ሁኔታ ማመቻቸቱና እስካሁን በመንግስታዊው የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ብቻ ተይዞ የነበረውን ነዳጅ ከውጭ ገዝቶ የማስገባት ስራ ሌሎች ኩባንዎችም ማከናወን እንዲችሉ