የህይወት መድን ውል በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሰዎች በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው የተለያዩ ህጋዊ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያቸው ሞትን ጨምሮ ሌሎች አካላዊ ጉዳቶች እና ህመሞችን ማስተናገዳቸዉ ተፈጥሯዊ ሃቅ ነው፡፡ ስለሆነም ሰዎቸ ሊገጥሟቸው ከሚችሏቸው የአደጋ ውጤቶች ለመቋቋም እና ለማካካስ እንዲሁም ለጥገኞቻቸው እና ለባለመብቶቻቸው ጥቅም ሲባል የህይወት መድን ውል መግባታቸው መልካም የመፍትሄ እርምጃ እንደሆነ ይጠበቃል፡፡ በዓለማችን ኢንሹራንስ ሽፋን የሚገባበት ዋናው ዓላማ ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለማካካስ እና በሕይወት ሕልፈት፥ በእድሜ መግፋት ምክንያት የሚደርስን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቋቋም ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የሕይወት መድን ምንነት፥ዓይነቶች፥ የሚይዛቸው ፍሬነገሮች እና ልዩ ባህርያት የሚዳሰሱ ይሆናል።

የህይወት መድን ምንነት

ታዋቂዉ የሕግ መዝገበ ቃላት ብላክስ ሎው በ9ኛ እትሙ (እ.ኤ.አ 2009) የህይወት መድንን እንዲህ ሲል ይተረጉመዋል፡፡ “Life insurance is an agreement between an insurance company and the policy holder to pay a specified amount to a designated beneficiary on the insured’s death or at the end of a definite or indefinite time.” ይህን ወደ አማርኛ ስንመልሰው የህይወት መድን ማለት በኢንሹራንስ ኩባንያ እና በፖሊሲው ባለቤት መካከል የተወሰነ መጠን ለተመደበው ተጠቃሚ በመድን ገቢው ሞት ወይም በተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ መጨረሻ ላይ ለመክፈል የሚደረግ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በሃገራችን በ1952 ዓ.ም በወጣው የንግድ ሕግ ቁጥር 691 እንዲህ ሲል ይተረጉመዋል፤ “የህይወት ኢንሹራንስ ማለት ባለኢንሹራንሱ አንድ ጊዜ ወይም ከአንድ ጊዜ በበለጠ ስለ ኢንሹራንሱ የሚከፍለዉን ገንዘብ ተቀብሎ በተዋዋዩ ወይም ኢንሹራንስ በተገባበት ሶስተኛ ወገን ህይወት ወይም ሞት ጋራ የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎች በደረሱ ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ለተዋዋዩ ወይም ለተጠቃሚው ለመክፈል የሚዋዋለው ውል ነዉ፡፡

በሌላ በኩል በመድን ስራ አዋጅ ቁጥር 746/2012 አንቀጽ 2(23) መሠረት የህይወት መድን ማለት መድን ሰጪው አረቦን በመቀበል የመድን ገቢው በህይወት የመኖር ወይም ሞት ላይ ተመስርቶ በተፈፀመ ዉል ለመድን ገቢዉ ወይም ለሌላ ተጠቃሚ አስቀድሞ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል የሚገባዉ የመድን ዉል ዓይነት እንደሆነ ትርጓሜ ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡

በአጠቃላይ የህይወት መድን ውል በመድን ሰጪው እና በመድን ገቢው መካከል የሚደረግ ስምምነት ሲሆን ይህ ስምምነትም በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 1678 የተደነገጉ መሠረታዊ የውል ሕግ መርሆችን ማለትም የተዋዋዮች ችሎታ፣ ስምምነቱ ጉድለት የሌለበት መሆን፣ ውሉ የሚቻል እና ህጋዊ መሆን፣ የውሉ አጻጻፍ/ፎርም/ አስፈላጊዉን ፎርማሊቲ ያሟላ መሆን እንዳለበት መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በንግድ ሕግ ቁጥር 694 ስር እንደተደነገገዉ ችሎታ በሌለዉ ሰው ስም የተደረገ ኢንሹራንስ ማለትም ችሎታ በሌለው ሰው ስም በወኪሉ ወይም በራሱ ችሎታ በሌለው ሰው የተፈረመ ኢንሹራንስ ፍርስ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

የህይወት መድን ውል የሚይዛቸው ፍሬነገሮች

  1. ስለ ህይወት ኢንሹራንስ የተደረገለት ሰው የግል ስም፣ የቤተዘመድ ስምና የተወለደበት ቀን
  2. ተጠቃሚው ተለይቶ የታወቀ እንደሆነ የተጠቃሚው ቤተዘመድ ስምና የግል ስም
  3. የተስማሙበት ገንዘብ እንዲከፈል የሚደረግበት ሁኔታ
  4. ቅናሽ የሚደረግበትና መልሶ የሚገዛበት ሁኔታ በኢንሹራንስ ፖሊሲ ውስጥ በትክክል መገለፅ እንዳለበት በቀድሞው ማለትም በአዋጅ ቁጥር 166/1952 በወጣው የንግድ ሕግ አንቀጽ 695 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የሕይወት መድን ውል አይነቶች

የሕይወት መድን ውል/policy/ በተገባለት የመድን ሽፋን ይዘት መሠረት በሶስት አይነት ምድቦች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።

  1. ኢንዶውመንት የሕይወት መድን /Endowment Life Insurance/:-ይህ የሕይወት መድን መድን በተገባለት ተጠቃሚ በሕይወት መኖር ላይ የተመሰረተ ሲሆን መድን ገቢዉ በውሉ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በሕይወት ካለ ይከፈለዋል የሚል በመድን ገቢው እና በመድን ሰጪዉ መካከል ባለ የዉል(ፖሊሲ) ይዘት ላይ የተመረኮዘ ነዉ። የንግድ ሕጉ በቁጥር 692(1) በሚከተለዉ መልኩ ተደንግጓል። የሕይወት ኢንሹራንስ(መድን) የሚዋዋለዉ መድን ሰጪ፣ ኢንሹራንስ የገባው ሰው በኢንሹራንስ ውል ዉስጥ በተወሰነ ጊዜ በሕይወት ያለ እንደሆነ የተወሰነ ዋና ገንዘብ በሕይወት እስካለ ድረስ ወይም በየጊዜዉ የሚከፈል ገንዘብ ለመክፈል እንደሆነ ተቀምጧል። ስለሆነም ይህ የመድን ዓይነት መድንን ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንትንም የሚያሳድግ ሲሆን ቁጣባን ያበረታታል። የኢንዶዉመንት መድን ትልቁ ጥቅም በፖሊሲዉ ዘመን በሕይወት እስከቆየ ድረስ መክፈያ ጊዜዉ/maturity date/ የደረሰዉን ቁጠባ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለምሳሌ ብድር ጋር የሚከፈል ይሆናል( የመድን ስራ አዋጅ ቁጥር 746/2012 አንቀጽ 46)።
  2. የዕድሜ ልክ የሕይወት መድን/Whole-life Insurance/:-ይህ የሕይወት መድን ፖሊሲዉ ሽፋን የሚሰጠዉ መድን ገቢዉ በፖሊሲዉ ዘመን ሲሞት ከመድን ገቢዉ መብት ላላቸዉ ወይም በፖሊሲዉ ለተጠቀሱ ተጠቃሚዎች የሚከፈል ነዉ። የንግድ ህጉ በቁጥር 692/2/ እንዲህ ሲል አስቀምጦት እናገኛለን። ኢንሹራንስ/መድን/ ሰጪዉ የተዋዋለዉ ኢንሹራንስ ስለገባዉ ሰዉ ሞት የሆነ እንደሆነ ኢንሹራንስ ከገባዉ ሰዉ መብት ላላቸዉ ወይም በኢንሹራንስ/መድን/ ዉል ዉስጥ ለተጠቀሰዉ ተጠቃሚ የተወሰነ ዋና ገንዘብ ወይም በሕይወት እስካለ ድረስ በየጊዜዉ የሚከፈል ገንዘብ ኢንሹራንስ የገባዉ ሰዉ በሞተ ጊዜ ለመክፈል ነዉ።
  3. ጥምር የሕይወት መድን/Combined Life Insurance/:- ይህ የሕይወት መድን ውል ከላይ የተጠቀሱት ውሎች ጥምር ሲሆን በንግድ ሕግ ቁጥር 692/3/ መሠረት እንዲህ ተደንግጎ ይገኛል። መድን ሰጪው ከላይ በቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሱትን የክፍያ አማራጮችን ለመክፈል የተስማማ እንደሆነ የተጣመረ የመድን ውል መዋዋል እንደሚችል ደንግጎ እናገኛለን።

በዚህ መሠረት መድን ገቢው ከመድን ሰጪው ጋር የሚዋዋለው በተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ውስጥ በሕይወት ኖሬ ከተገኘሁ የፖሊሲው ገንዘብ ለራሴ ይከፈለኝ ፣ ነገር ግን ያ የተባለው ቀን ከመድረሱ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየሁ እንደሆነ በውሉ ላይ ለተጠቀሰው ተጠቃሚ የፖሊሲው ገንዘብ ይከፈል የሚል ይዘት ይኖረዋል፡፡

አሁን ላይ ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ በሀገራችን ያሉ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትኩረታቸዉ በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት በተለይም በተሽከርካሪ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሽፋን መስጠት ሲሆን ለሕይወት መድን በተገቢ ትኩረት ሽፋን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

የሕይወት መድን ውል ልዩ ባህርያት

የሕይወት መድን ከሌሎች የመድን ውሎች ልዩ የሚያደርገዉ ባህርያት አሉት። እነዚህም፤

  1. መድን የሚገባበት ጉዳይ/Object of the Insurance Policy/፦ በሌሎች የመድን ዉሎች ሽፋን የሚሰጠዉ ለንብረት ወይም እቃ ሲሆን በሕይወት መድን ውል/ፖሊሲ/ ሽፋን የሚሰጠዉ የሰዉ ሕይወት ነዉ።
  2. የደርጊቱ እርግጠኝነት፦ በንብረት ወይም እቃ ላይ የሚገባ የመድን ውልን በተመለከተ ንብረቱ ላይ ጉዳት ላይደርስ ስለሚችል ሊደርስ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሰረተ ሲሆን በሕይወት መድን ውል ግን የሰዉ ልጅ ሞት አይቀሬነት የታመነ ሲሆን መቼ እንደሚከሰት ብቻ ነው ማወቅ የማይቻለው። ይህ ሁኔታ በዕድሜ ልክ የሕይወት መድን በግልፅ የታወቀ ሲሆን በኢንዶውመንት የሕይወት መድንም ቢሆን አስቀድሞ የተወሰነ ጊዜ በስምምነቱ ቢካተትም እንኳን የሞት አይቀሬነት የታመነ ነዉ።
  3. የውል ዘመን፦ ከሌሎች የመድን ውሎች በተለየ መልኩ የሕይወት መድን ውል ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ መሆኑ ሌላው ልዩ መገለጫው ነው።
  4. የሰው ሕይወት በገንዘብ የማይተመን መሆኑ፦ በንብረት ላይ የሚገባ መድን ንብረቱ ላይ ጉዳት ቢደርስ ጉዳቱን ሊያካክስ የሚችል ገንዘብ ወይም ምትክ በመስጠት ተጎጂውን ወደነበረበት የመመለስ ዉጤት ሲኖረው የሕይወት መድን ኢንሹራንስ ግን የሰው ልጅ ሕይወት በገንዘብ የማይተመን ከመሆኑም ባሻገር ዓላማው ለሟች ጥገኞች ወይም ባለመብቶች በሟች ሞት ምክንያት ሊደርስባቸው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቋቋም እንዲያስችላቸው ማድረግ ነዉ።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የሕይወት መድን፥ መድን ገቢዎች ለመድን ሰጭው የአረቦን/Premium/ ክፍያ በመፈፀም ሊደርስ የሚችለዉን አደጋ ለማካካስ ወይም ለጥገኞች እና ለባለመብቶች ለማስተላለፍ የሚደረግ ውል መሆኑን መረዳት ይቻላል። በዚህም ውል መድን ሰጭው ኃላፊነት የሚወስድለት አደጋ ተለይቶ የታወቀና ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች የተስማሙበትና የግራ ቀኙን መብትና ግዴታ የሚዘረዝሩ ይዘቶች እንደሚካተቱበት መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም የሕይወት መድን ሞት አይቀሬ መሆኑን በመገመት በሕይወት እስካለ ድረስ መድን ገቢ ለመድን ሰጭዉ የአረቦን ክፍያ በመክፈል በሞት ጊዜ ለሚያጋጥም ጉዳት ለመድን ገቢ ጥገኞችና ባለመብቶች ኃላፊነትን ወደ መድን ሰጭ የሚያስተላልፉበት ስልት እና በሞት ምክንያት ጥገኞችና ባለመብቶች ላይ የሚደርስን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መቋቋሚያ መሆኑን በመገንዘብ ሰዎች የሕይወት መድን ውል ሊገቡ ይገባል እንላለን።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት