የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት አሰጣጥ በኢትዮጵያ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ሰዎች በእለት ከእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው መደበኛ የሆኑ ስራዎቻቸውን ከመሥራት እና ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ባሻገር የላቀ አፈጻጸም እና ስኬትን የሚጎናፀፉት ቀላል አይደሉም። የላቀ አፈጻጸም ሲባል በሀገር ደረጃ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ወይም የላቀ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ ወይም አለምአቀፋዊ የሆነ ሳይንሳዊ ወይም ኪነ ጥበባዊ አበርክቶን ያካትታል። በኢትዮጵያ የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ ግለሰቦች ሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ሲበረከትላቸው ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በመከላከያ እና በፖሊስ አገልግሎት ዙሪያ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት እየተተገበረ ይገኛል። ሆኖም ግን ከመከላከያ እና ፖሊስ ውጭ ያሉ የሽልማት ስርዓቶች በተበታተነ መልኩ ሲካሄዱ መቆየታቸው ወጥ በሆነ ሕግ መመራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ራሱን የቻለ ሕግ እንዲወጣ አስገድዷል። ይህ አስገዳጅነትም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 71(5) እና 74(10) የሚመነጭ ሲሆን ኒሻንና ሽልማት በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት እንደሚሰጥ ተመላክቷል። በዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መነሻነት የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት አዋጅ ቁጥር 1325/2017 ተደንግጎ ወጥቷል። በዚህ አጭር ጽሁፍ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ምንነት፣ የተፈጻሚነት ወሰን፣ የአሰጣጥ ሂደቶች፣ የሚያስገኘዉ ጥቅም፣ በማንና ለማን እንደሚሰጥ፣ ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት መልሶ ስለመውሰድ፣ ያለአግባብ መጠቀም ስለሚያስከትለው ተጠያቂነት አጠር ባለመልኩ የሚዳሰስ ይሆናል።

የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ምንነት

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት(1993) ሜዳይ(ሜዳልያ) ማለት ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከነሃስ የተሰራ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ወይም ውድድሮች ብልጫ ላሳዩ ወይም ጥሩ ለሰሩ ሰዎች ከመንግሥት፣ ከድርጅት የሚሰጥ ሽልማት ወይም ኒሻን እንደሆነ ይተረጉመዋል። ይህ መዝገበ ቃላት ኒሻን(ሊሻን) ማለት ከብር ወይም ከወርቅ የሚሰራና በደረት ላይ የሚደረግ ለአገር፣ ለወገን አኩሪ ስራ ለሰራ ሰዉ በሽልማት መልክ የሚሰጥ የክብር ወይም የታላቅ ስራ ምልክት እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን።

ኒሻኖች በአብዛኛዎቹ ሀገራት ለሀገር መሪዎችና በተመሳሳይ ደረጃ ለሚገኙ ግለሰቦች የሚበረከት ሽልማት እንደሆነ በሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት አሰጣጥ አዋጅ ማብራሪያ ላይ ተመላክቷል።

የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት አዋጅ ቁጥር 1325/2017 ስለሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ምንነት በትርጉም ክፍሉ በአንቀጽ 2((1)፣ (2)፣ (3)) እንደ ቅደም ተከተላቸው ያካተተ ሲሆን ይኸውም፡-

ሜዳይ ማለት ሳንቲም በሚመስል ብረት ላይ ክብሩን የሚመጥን ጌጥ በመቅረጽ ወይም በማተም፣ የማዕረግ አርማ በማድረግ ወይም ቃላትን፣ ድርጊትን ወይም ኩነትን በሚገልጽ መልኩ በመቅረጽ በስራ ፈጠራ፣ በሳይንስና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በስነ ጥበብ፣ በስፖርት፣ በመንግሥት ስራ ወይም በተለያዩ ዘርፎች የላቀ ወይም አርአያነት ያለው ስራ ለሰራ ሰው የሚሰጥ እውቅናና ስጦታ ነው በሚል ትርጉም ሰጥቶታል። ይህ ትርጓሜ ከላይ ከተቀመጠው የመዝገበ ቃላት ትርጓሜ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ኒሻን ማለት ሳንቲም በሚመስል ብረት ላይ ክብሩን የሚመጥን ጌጥ በመቅረጽ ወይም በማተም፣ የማዕረግ አርማ በማድረግ ወይም ቃላትን፣ ድርጊትን ወይም ኩነትን በሚገልጽ መልኩ በመቅረጽ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች በኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ አህጉር ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ እውቅናና ስጦታ ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ይህ ትርጓሜ ከላይ በመዝገበ ቃላቱ ከተሰጠው ትርጉም ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ሽልማት ማለት ሜዳይ ወይም ኒሻን ከሚያሸልሙ ሁኔታዎች ውጭ ሽልማቱን በሚሰጠው መስሪያ ቤት የስራ ዘርፍ ከፍተኛ እና የሚያስመሰግን ስራ ለሰሩ የመንግሥት ሰራተኞች፣ የመንግሥት ሠራተኛ ላልሆኑ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ዘርፉን በሚመራ መስሪያ ቤት በዓይነት፣ በገንዘብ ወይም በሌላ አግባብ ባለው መልኩ የሚሰጥ እውቅና ወይም ስጦታ ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል።

የተፈጻሚነት ወሰን

አዋጁ የተፈጻሚነት ወሰኑን በተመለከተ ከወታደራዊ ወይም ከፖሊስ አገልግሎት ዉጭ በሆኑ በአዋጁ መሠረት ለሽልማት የሚያበቃ ተግባር በፈጸሙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የዉጭ ሀገር ሰዎች ወይም ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖረዉ በአንቀጽ 3 ስር አስቀምጧል። ይህ የሆነበት ምክንያት በመከላከያ ሰራዊት አዋጅ እና በፌዴራል ፖሊስ መተዳደሪያ ደንብ የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ስርዓት በሕግ ተካተው ስለሚገኙ ነው።

የሜዳይ ዓይነቶች እና የሚያስገኙት መብት

አዋጁ በአንቀጽ 4 ስር ሶስት የሜዳይ ዓይነቶችን የደነገገ ሲሆን እነዚህም፡-

  • ብሔራዊ የላቀ የፈጠራ ስራ ሜዳይ፤
  • ብሔራዊ የህዳሴ ሜዳይ፤
  • ብሔራዊ የላቀ ሲቪል አገልግሎት ሜዳይ ናቸዉ።

ብሔራዊ የላቀ የፈጠራ ስራ ሜዳይ፡- ይህ ሜዳይ የሚሰጠው በማናቸውም ዓይነት የፈጠራ ስራ በኢትዮጵያ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች እጅግ የላቀ የህብረተሰቡን ችግር የፈታ ወይም ሊፈታ የሚችል የፈጠራ ስራ የሰራ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት ስለመሆኑ በአንቀጽ 5 ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን።

ብሔራዊ የህዳሴ ሜዳይ፡- ይህ ሜዳይ የሚሰጠዉ በሳይንስና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በስነ ጥበብ፣ በስፖርት ወይም በተለያዩ ዘርፎች ለሀገር፣ ለሕዝብ ወይም በአጠቃላይ ለሰው ልጆች እጅግ የላቀ ስራ ለሰራ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት ነው ሲል የአዋጁ አንቀጽ 6 ደንግጎ እናገኛለን።

ብሔራዊ የላቀ ሲቪል አገልግሎት ሜዳይ፡- ይህ ሜዳይ የሚሰጠዉ በተመደበበት የመንግሥት ስራ ስራው የሚጠይቀውን ዲሲፕሊን ጠብቆ በታታሪነትና በታማኝነት በማገልገል ለሀገርና ሕዝብ የላቀ ስራ ለሰራ የመንግሥት ሠራተኛ ነዉ በማለት በአዋጁ አንቀጽ 7 ስር ተደንግጎ እናገኛለን።

ሜዳይ ተሸላሚዎች ስለሚኖራቸዉ ልዩ መብቶች

ከላይ የተጠቀሱትን ሜዳዮች የተሸለመ ግለሰብ ወይም ቡድን የሚከተሉት ልዩ መብቶችን እንደሚጎናጸፍ በአዋጁ አንቀጽ 8 ስር የተደነገገ ሲሆን እነርሱም፡-

  • ተሸላሚዉ ደሞዝ ካለው የደሞዙ ሃያ አምስት በመቶ (25%) ወይም ጡረተኛ ከሆነ የደሞዙ አርባ በመቶ (40%) ይጨመርለታል፤
  • ተሸላሚዉ ደሞዝ ወይም ጡረታ ከሌለዉ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን የገንዘብ መጠን በስጦታነት ይሰጠዋል፤
  • በመንግሥት የትምህርት ተቋሞች ቅድሚያ የትምህርት እድል ይሰጠዋል፤
  • በመንግሥት የጤና ተቋማት ነጻ የህክምና አገልግሎት ያገኛል፤
  • በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተፈረመ መታወቂያ እና ሰርተፊኬት ይሰጠዋል፤
  • በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ቅድሚያ/በቅጥር ወይም በአገልግሎት/ ይሰጠዋል።

የኒሻን ዓይነቶች እና የሚያስገኙት መብት

በአዋጁ አንቀጽ 9 ስር ስለኒሻን ዓይነቶች የተደነገገ ሲሆን እነዚህም፡-

  • የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን እና
  • የአፍሪካ ታላቅ ክብር ኒሻን ናቸዉ።

የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን፡- በኢትዮጵያ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች ለሀገር እና ሕዝብ እጅግ የላቀ ችግር ፈቺ ስራ ስራ ላበረከተ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት፤ ወይም ለኢትዮጵያ ልዩ ድጋፍ ላደረገ ሀገር ወይም መሪ እንደሚሰጥ በአዋጁ አንቀጽ 10 ስር ተደንግጎ ይገኛል።

የአፍሪካ ታላቅ ክብር ኒሻን፡- ለአፍሪካ አህጉር በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዘርፎች አህጉራዊ ችግር ፈቺ ስራ ላበረከተ ወይም በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል መልካም ወዳጅነት እና ዘላቂ ትስስር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከተ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት እንደሚሰጥ በአዋጁ አንቀጽ 11 ስር ተደንግጎ ይገኛል።

የኒሻን ተሸላሚ ስለሚኖረዉ ልዩ መብት

በአዋጁ አንቀጽ 12 ስር የኒሻን ተሸላሚ ልዩ መብቶች የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡-

  • ብሔራዊ በዓላት አከባበር ስነ-ስርዓት በሚከበርበት ቀንና ስፍራ በሚዘጅለት ቦታ ይቀመጣል፤
  • በስሙ መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ሕንጻ ወይም ተመሳሳይ ተቋም ይሰየምለታል፤
  • በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተፈረመ መታወቂያ እና ሰርተፊኬት ይሰጠዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ኒሻን ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሆነ የሚከተሉት ልዩ መብቶች ይኖሩታል። እነሱም፡-

  • ተሸላሚው ደሞዝ ካለው የደሞዙ ሃያ አምስት በመቶ (25%) ወይም ጡረተኛ ከሆነ የጡረታ አበሉ አርባ በመቶ (40%) ይጨመርለታል፤
  • ተሸላሚው ደሞዝ ወይም ጡረታ ከሌለው ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን የገንዘብ መጠን በስጦታነት ይሰጠዋል፤
  • በመንግሥት የትምህርት ተቋሞች ቅድሚያ የትምህርት እድል ይሰጠዋል፤
  • በመንግሥት የጤና ተቋማት ነጻ የህክምና አገልግሎት ያገኛል፤
  • በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ቅድሚያ/በቅጥር ወይም በአገልግሎት/ ይሰጠዋል።

ስለሜዳይ ወይም ኒሻን አሰጣጥ ስርዓት

በአዋጁ መሠረት ሜዳይ ወይም ኒሻን ለመሸለም ብቁ የሆነ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሽልማቱ በፕሬዝዳንት ይበረከትለታል(አንቀጽ 15(1))። ይህ እንዳለ ሆኖ የሜዳይ ወይም ኒሻን ሽልማት እንደሁኔታው ፕሬዝዳንቱ በወከለው ሰው ሊሰጥ ይችላል(አንቀጽ 15(2))። ሜዳይ እና ኒሻን የማዘጋጀት ሥልጣን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 23(7) ስር ተደንግጎ ይገኛል።

የሜዳይ፣ ኒሻን አደራረግን/wearing/ በተመለከተ አዋጁ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መመሪያ እንዲያወጣ ሥልጣን የሰጠ ስለመሆኑ በአንቀጽ 23(10) ስር ተደንግጎ እናገኛለን። ከዚህ በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 20/1/ የተቋቋመው ብሔራዊ የሜዳይ እና ኒሻን ሽልማት ኮሚቴ የሜዳይ እና ኒሻን ሽልማት የሚገባቸውን እጩዎች የመመልመል፣ የመመርመርና ውሳኔ የመስጠት፣ ይገባቸዋል የሚል ውሳኔ ከሆነ ከነምክንያቱ የውሳኔ ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማቅረብ ኃላፊነት በአዋጁ አንቀጽ 23 መሠረት ተሰጥቶታል።

ስለዘርፍ ሽልማቶች እና ሽልማት አሰጣጥ ስርዓት

ብሔራዊ የሜዳይ እና ኒሻን ሽልማት ኮሚቴ የተለያዩ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና የአስተዳደር ዘርፎችን እና ሞያዎችን የተመለከቱ ሽልማቶችን ዘርፉን በሚመራው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የውሳኔ ሀሳብ ሲያቀርብለት መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ሲል በአንቀጽ 16(1) ስር ተቀምጧል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የሚበረከት ሽልማት እንደዘርፎቹ ዓይነት ዘርፎቹን በሚመሩ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ ይሆናል በማለት በአንቀጽ 16(2) ስር ተደንግጎ እናገኛለን።

ለሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት የሚያበቃ ተግባር ፈጽሞ ስለሞተ ሰው

በአዋጁ መሠረት ለሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት የሚያበቃ ተግባር ፈጽሞ ለሞተ ሰው አግባብነት ያለው ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት እንደሚዘጋጅ እና በስሙ እንደሚመዘገብ አንቀጽ 24(1) ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን የሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት አሰጣጡን በተመለከተ ከአንቀጽ 24((2)-(6)) እንደቅደም ተከተላቸው የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም፡-

  • ለሟቹ ተሸላሚ ታላቅ ልጅ ወይም በልጆቹ እድሜ ቅደም ተከተል መሠረት የሚሰጥ ይሆናል፣
  • ሟቹ ተሸላሚ ልጅ ከሌለው ለባለቤቱ፣ ባለቤት ከሌለው አግባብ ባለው የውርስ ሕግ መሠረት ለውርስ ባለመብቱ ሽልማቱ ይሰጣል፣
  • የሟቹ ተሸላሚ ልጆች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ከሆነ አግባብነት ባለው ሕግ የልጆቹ ሞግዚት ወይም አሳዳጊ የሆነ ሰው ሽልማቱን ይረከባል፣
  • ሟቹ ተሸላሚ የጡረታ አበል ካለው አግባብነት ባለው ሕግ የጡረታ አበል ተጠቃሚ ለሆነ ሰው የጡረታ አበል ጭማሪ ይደረግለታል፣
  • ሟቹ ተሸላሚ የጡረታ አበል ከሌለው ለልጆቹ፣ ልጅ ከሌለው ለሚስቱ፣ ሚስት ከሌለው አግባብነት ባለው ሕግ ለወራሾች ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን የገንዘብ መጠን በስጦታነት ይሰጣል።

ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማትን መልሶ ስለመውሰድ

አዋጁ ሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማትን ተሸላሚው ስለሚመልስበት ሁኔታ በአንቀጽ 25(1)(ሀ) እና (ለ) ስር ደንግጎ የሚገኝ ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎችም፡-

  • አግባብነት ባለው ሕግ የሚኖረው ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ ሜዳዩ፣ ኒሻኑ ወይም ሽልማቱ በተሳሳተ ወይም በተጭበረበረ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ከሆነ፣
  • ተሸላሚው አግባብነት ባለዉ ሕግ ከባድ ወንጀል ፈጽሞ ጥፋተኛ ከተባለ፣

ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው አግባብ ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማቱን የሚመልስ ሰው በአዋጁ መሠረት ያገኛቸው ልዩ መብቶች ቀሪ እንደሚሆኑ በአንቀጽ 25(2) ስር ተደንግጎ እናገኛለን።

ቅጣት

ማንኛውም ሰው አግባብነት ካለው አካል ፍቃድ ሳያገኝ በአዋጁ የተደነገጉትን ሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ያዘጋጀ ወይም ወደ ሐሰት የለወጠ እንደሆነ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም ከአስር ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ በሁለቱም እንደሚቀጣ በአንቀጽ 27(1) ተደንግጓል ። ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው ሳይፈቀድለት ኒሻን አድርጎ ከተገኘ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በአንቀጽ 27(2) ተደንግጓል።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት አዋጁ የወጣው ከአዋጁ መውጣት በፊት የነበረውን ወጥ ያልሆነ የሽልማት ስርዓት ወጥ በሆነ ሕግ የተደገፈ ስርዓት መተካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሲሆን ሀገራዊ ወጥ የሆነ የሽልማት ስርዓት መዘርጋት ሀገራዊ የስራ ፈጠራ፣ መነሳሳት እና ትጋትን የሚያበረታታ ከመሆኑም ባሻገር ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እድገት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለሆነም አዋጁ ጠቅለል ባለ መልኩ ሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ስለሚሰጥበት፣ ስለሚያጎናጽፈው ልዩ መብት፣ እንደገና ስለሚወሰድበት/ቀሪ ስለሚሆንበት/ ሁኔታ፣ ያለፍቃድ የሚያዘጋጅ እና የሚያደርግ አካል የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል የደነገገ መሆኑን በመገንዘብ በተለያዩ ዘርፎች የላቀ አበርክቶ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች አዋጁንና እሱን መሠረት በማድረግ በሚወጡ መመሪያዎች አማካኝነት የሽልማት ስርዓቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ሊሰመርበት ይገባል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ