ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት

ማውጫ

Share this Article

በዚህ አጭር ጽሁፍ የሕግ ጥበቃ (ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት) ምንነት፣ ጥበቃ የተደረገላቸው መስኮች እና የሕግ ጥበቃው ስለሚነሳበት እንዲሁም የሕግ ጥበቃ ያላቸው ሰዎች በወንጀል ሲጠረጠሩ ስለሚያዙበት እና ስለሚከሰሱበት ህጋዊ ሁኔታ ምብራሪያ ይቀርባል

ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት /Legal Immunity/ ምንነት

ለሕዝብ እና ሀገር ጥቅም ሲባል ለተወሰኑ ሰዎች የሚሰጥ በሁኔታ ላይ የተመረኮዘ የሕግ ጥበቃ ሲሆን ይሄንን መብት የተጎናጸፉ ሰዎች በሕግ የተደነገጉ ሁኔታዎችን እስካልተላለፉ ድረስ ወይም ከለላው እስካልተነሳ ድረስ ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት አላቸው፡፡ ይህ ልዩ መብት ወይም (Privilege) ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን የሚሰጥበት ዓላማ ይህ መብት ወይም ጥበቃ የሚሰጣቸው ሰዎች ባላቸው ኃላፊነት እና ተግባር ምክንያት ስራቸውን በሚያደናቅፍ መልኩ በየምክንያቱ የማሰርና የመክሰስ ተግባር እንዳይኖር በማድረግ የሚያከናውኑትን ተግባር እና የሚወከሉትን ኃላፊነት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ልዩ መብት ጥፋት ወይም ወንጀል ለመፈፀም ፈቃድ ለመስጠት ወይም ተጠያቂነትን ለማስቆም (impunity) እንዲኖር አይደለም፡፡ ልዩ መብቱ የሚሰጣቸው ሰዎች ይታመናሉ ሕግንም ያከብራሉ ከሚል እምነት ነው፡፡ ይህ ልዩ መብት የሚሰጠው በልዩ ሁኔታ እንደመሆኑ በጠባቡ የሚተረጎምና አስፈላጊ መሆኑ በታመነ ጊዜ ብቻ በአዋጅ የሚሰጥ መሆኑ ሌላው ባህሪው ነው፡፡ ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች ጥፋት ወይም ከባድ ወንጀል ፈፅመው ሲገኙ ግን ይህን ሁኔታ በምርመራ ክፍሉ በቂ ጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን ከለላውን በሚከታተለው አካል የጥርጣሬው ትክክለኛነት ተረጋግጦ በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል፡፡

ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት ያላቸው አካላት

የምክር ቤት አባላት

ምክር ቤት ማለት የሕግ አውጪው የመንግሥት አካል ሲሆን አንዳንድ አገራት ባለ አንድ ምክር ቤት (unicameral) ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ባለ ሁለት ምክር ቤት (bicameral) የሆኑ አሉ፡፡ ስያሜውን ስናይ በኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ አገራት የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት እያሉ የሚገልጹት ሲሆን በእንግሊዘኛ አጠራሩ house of lord and house of common ይባላል፡፡

ያለ መከሰስ መብት ብዙውን ጊዜ ለነዚሁ ለሕዝብ እንደራሴዎች የተሰጠ መብት ሲሆን አባላቱ የወከላቸውን ሕዝብ ሃሳብ እና ፍላጎት በነጻነት እንዲገልጹ እና በውጤታማነት መወከል እንዲችሉ ለማስቻል ያለመ መብት ነው፡፡ በአሜሪካ እና እንግሊዝ የምክር ቤት አባላት በምክር ቤቱ ለሚያደርጉት ንግግር በፍትሐብሄር ኃላፊነት የማይጠየቁ ሲሆን አይታሰሩም፡፡ ነገር ግን ወንጀል ከፈጸሙ የሚጠየቁበት (የሚከሰሱበት) አግባብ አለ፡፡ በሌላ በኩል በፈረንሳይ እና ሌሎች አውሮፓ አገራት ሕግ አውጪ የሆነው ምክር ቤት ሳይፈቅድ አባላትን ማሰር የተከለከለ ነው፡፡

በአገራችን የስርአተ መንግሥት አወቃቀር መሠረት በፌደራል እና በክልል ደረጃ የሕግ አውጪ አካላት ያሉ ሲሆን በፌደራል ደረጃ ሁለት ምክር ቤቶች አሉ፡፡ እነሱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲሆኑ ክልሎችም የየራሳቸው ምክር ቤቶች አላቸው፡፡ እነዚህ የምክር ቤት አባላት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 4 እና በአንቀጽ 63 መሠረት የሁሉም ሕዝብ ተወካይ ናቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ማንኛውም የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፣ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም በወ/መ/ስ/ስ/ሕግ አንቀጽ 19 እና 20 መሠረት እጅ ከፈንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም በወንጀልም አይከሰስም፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው በአገራችን ያለመያዝ እና ያለ መከሰስ መብት ለሁሉም ሰው የተሰጠ ሳይሆን ለምክር ቤት አባለት የተሰጠ ልዩ ጥበቃ ነው፡፡ ሆኖም ፍጹም መብት ግን አይደለም ምክንቱም በሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ መብት ስለሆነ። ስለዚህ የምክር ቤት አባላት አባል የሆኑበት ምክር ቤት ሲፈቅድ ወይም የምክር ቤቱ ፈቃድ ሳያስፈልግ ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ከተያዙ የሚያዙበት እና የሚከሰሱበት የሕግ አሠራር ያለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በክልሎች ህገ-መንግስታት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995(እንደተሻሻለው) አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር መሠረት የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮቹ ምክር ቤት አባላት ከላይ በተገለጸው መልኩ ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሲሆን ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ከተያዙ ግን የሚያዙበት ሁኔታ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ለሌላ ወንጀል ጉዳይ ግን የምክር ቤቶቹ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ከባድ ወንጀል ምንድን ነው ለሚለው የአገራችንን የወንጀል ሕግ ማየት የሚስፈልግ ሲሆን ህጉ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ ሆኖም የወንጀል ህጉ አንቀጽ 106 እና 108 ባስቀመጡት አግባብ ቀላል እስራት እና ጽኑ አስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎችን እንደየሁኔታው ከባድ ወንጀልን ለመለየት በመስፈርትነት መጠቀም ይቻላል፡፡

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ

በአለምአቀፍ ሕግ መሠረት የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የላካቸውን አገር እና አለምአቀፍ ድርጅት ወክለው ባሉበት አገር ፍርድ ቤት በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ያለመከሰስ መብት አላቸው፡፡ ይህ ያለመከሰስ መብት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በመኖሪያቸው እና በቢሮዎቻቸው ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴም የሚሰጥ መብት/የሕግ ጥበቃ ነው፡፡ ይህ ጥበቃ ሀገራችንም ፈርማ ባፀደቀችው የ1961 የቬና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ስምምነት መሠረት የሚሰጥ ሲሆን ለውጭ አገራት አምባሳደሮች፣ ቆንስላዎች እና የኢምባሲቸው ሰራተኞች የሚሰራ ነው፡፡ እንዲሁም ለአለምአቀፍ ድርጅት ዳይሬክተሮች እና ሰራተኞች ከስራቸው ጋር በተገናኘ ሀገራችን በፈረመችው የመቀመጫ ሀገር ስምምነት(host country agreement) የሚሰጥ የሕግ ጥበቃ ሲሆን ሆኖም ይህ ያለመከሰስ መብት ፍጹም አይደለም፡፡ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ የላካቸውን አገር ወይም አለምአቀፍ ድርጅት የበላይ ሀላፊ ያለመከሰስ መብቱን እንዲያነሳ በመጠየቅ ሲነሳ መያዝ እና መጠየቅ የሚቻል ሲሆን ይሄንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ተጠርጣሪውን ከአገር እንዲወጣ ማድረግ (persona non grata) የአንድ አገር ሉዓላዊ ሥልጣን ነው፡፡

ዳኞች

በፌደራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ማንኛውም ዳኛ ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፈንጅ ካልተያዘ ወይም በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያለመከሰስ መብቱ ካልተነሳ በስተቀር ሊያዝ፣ ሊታሰር እና ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡ ይህ ሕግ ዳኞች በህገመንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 ላይ የተደነገገውን ዳኞች ከማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ሌላ አካል ነጻ ሆነው በሕግ ብቻ እየተመሩ የዳኝነት አገልግሎትን ማከናወን እንዳለባቸው የተደነገገውን ለማስፈጸም የወጣ ሕግ ነው፡፡ በዚህም ዳኞች በሚወስኑት ውሳኔ ፍትሕን ለማስፈን ከየትኛውም አካል መያዝ፣ እስር እና ክስ ሳይደርስባቸው ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ለማስቻል ሲሆን በዚህም ፍትሕ ፈላጊው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ የሕግ ጥበቃ ፍጹም እና ዳኞችም እንደፈለጉት እንዲሰሩ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ዳኞች ከላይ ባነሳነው የወንጀል ሕግ እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነሥርዓት ሕግ መሠረት ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ከተያዙ ቀጥታ የሚያዙበት፣ የሚታሰሩበት እና የሚከሰሱበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ከባድ ወንጀል ባይሆንም ወንጀል ከፈጸሙ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተደርጎ ተይዘው ክስም የሚቀርብባቸው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች

በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት አገራዊ ምክክሩን እንዲያመቻች በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋመ ህጋዊ ሰውነት ያለው አገራዊ ተቋም ሲሆን ይሄንኑ ኮሚሽን እንዲመሩ በኮሚሸነርነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየሙ 11 ኮሚሽነሮች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 15(1(ሀ) መሠረት እነዚህ ኮሚሽነሮች ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሲሆን በዚሁ መሠረት ያለመከሰስ መብታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተነሳ ወይም ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ካልተያዙ በስተቀር በኮሚሽነርነት በሚያገለግሉበት ወቅት ያለመከሰስ መብት አላቸው፡፡ እነዚህ ኮሚሽነሮች ከባድ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን ስራቸውም ከማንም አካል ተጽእኖ ነጻ ሆኖ መከናወን እንዲችል የዚህ አይነቱ ጥበቃ በሕግ ተድርጎላቸው ይገኛል፡፡

የምርጫ ስራ አመራር ቦርድ አባላት

በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ ጊዜ የሚያገለግሉ 5 አባላት ያሉት ስራ አመራር ቦርድ ያለው ሲሆን በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት የስራ አመራር ቦርድ አባላት ኃላፊነት ላይ አስካሉ ድረስ ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ካልተያዙ በስተቀር ያለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ያለመያዝ እና በወንጀል ያለመከሰስ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት ስራ አመራሩ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ያለ ተጽኖ በነጻነት አንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ የተደነገገ ነው፡፡ ይሄም መብት ጊዜአዊ ሲሆን አባለቱ ሀላፊነታቸውን ሲለቁ ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ሲያነሳ የሚያበቃ ነው፡፡

ለምርጫ የተመዘገቡ እጩዎች

በአትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 42 መሠረት የግልም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ተወዳዳሪ /እጩ ተመራጭ/ የሆኑ ሰዎች ከተመዘገቡበት ቀን አንስቶ ምርጫው አልቆ ውጤቱ እስኪገለጽ ድረስ በወንጀል ተጠርጥረው ያለመያዝ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ከባድ ወንጀል ፈጽመው እጅ ከፈንጅ ከተያዙ ተይዘው ሊከሰሱ ይችላሉ፡፡ የፈጸሙት ወንጀል እጅ ከፈንጅ ባይሆንም የሕግ እርምጃ የሚወሰድባቸው ምርጫው አልቆ ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡ ተጠርጣሪው በምርጫው ያሸነፈ ከሆነ በዚሁ ሕግ መሠረት ሊያዝ እና ሊታሰር የሚችለው ያለመከሰስ መብቱ በተወከለበት ምክር ቤት ከተነሳ በኋላ ነው፡፡ የዚህ ከለላ ዋነኛ አለማ የምርጫ ውድድሩን ፍትሀዊ ለማድረግ እና ተወዳዳሪዎች ያለምንም እስር እና ክስ እና ሌሎች እንቅፋቶች የሚወክሉትን መራጭ የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ እና ፍላጎት እንዲገልጹ ወይም እንዲያራምዱ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ከለላውን ሽፋን በማድረግ ወንጀል ከፈጸሙ ከላይ በተገለጸው አግባብ ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/2002 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) በአንቀጽ 35 መሠረት የኮሚሽኑ ከፍተኛ ሀላፊዎች እና መርማሪዎች ያለመከሰስ መብታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተነሳ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ ካልተያዙ በስተቀር አይከሰሱም፡፡ እነዚህ የስራ ሃላፊዎችም በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነሮች እና የልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ የተሾሙ ኮሚሽነሮችን ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም በአዋጅ ቁጥር 210/2002 አንቀጽ 2(10) እና አንቀት 35 መሠረት በዋና ኮሚሽነሩ የተሰየሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎችም የዚህ መብት ተጠቃሚ ናቸው፡፡

በጥቅሉ ያለመያዝ እና ያለመከሰስ መብት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስቀር ሳይሆን ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች ካለባቸው የስራ ኃላፊነት ባህሪ አንጻር ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው ታስቦ የተደነገገ ሲሆን ወንጀል ከፈጸሙ ግን ይህ ከለላ በህጋዊ ሂደት ተነስቶ የሚጠየቁ መሆኑን እና የሕግ የበላይነት በማንኛውም ሰው በእኩልነት የሚረጋገጥ እና የሚፈጸም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በንቃት ሕግ: ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ