የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ የሚቀርብ ክስ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ፍትሕ የማግኘት መብት በሀገራችን እውቅና የተሰጠው መብት ሲሆን ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37(1) ተደንግጓል፡፡ የወንጀል ጉዳዮች በዐቃቤ ሕግ በኩል ክርክር የሚደረግባቸው ሲሆን በፍትሐብሔር ግን ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቅርቦ ክርክር ማድረግ መብቴ ተነካ የሚለው ሰው ኃላፊነት ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ሰው የዳኝነት መክፈል የሚጠበቅበት ከመሆኑ አንፃር ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች ገንዘብ በማጣት ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዳይጓደል ህጉ መፍትሄ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የዳኝነት ሳይከፈል ክስ የሚቀርብበትን የሕግ ሂደት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ የሚቀርብ ክስ ምንነት

ዳኝነት ሳይከፈል በነፃ የሚቀርብ ክስ የገንዘብ አቅም በማጣት ምክንያት የዳኝነት መክፈል የማይችሉ ሰዎች ይህንን የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረብ የዳኝነት ሳይከፍሉ በደሀ ደንብ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት ሥርአት ነው፡፡

የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ የሚቀርብ ክስ አቀራረብ

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ክስ ተገቢው የዳኝነት ክፍያ ካልተከፈለበት በስተቀር በፍርድ ቤት ተቀባይነት እንደማይኖረው የፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 215 ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የዳኝነት መክፈል የማይችል ሰው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 467 መሠረት የዳኝነት ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ሳይከፍል በነፃ በድሀ ደንብ ፋይል ከፍቶ ክስ ማቅረብ እንዲፈቀድለት ማመልከት ይችላል፡፡ ማመልከቻው ሲቀርብ በቃለ ማህላ የተደገፈ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማመልከቻው መቅረብ ያለበት ዋናውን ክስ ለሚያየው ፍርድ ቤት ሲሆን የክሱ አቤቱታ አብሮ መቅረብ አለበት፡፡

የፍርድ ቤት ሥልጣን

ማመልከቻው የቀረበለት ፍርድ ቤት ስለአመልካች የሀብት ሁኔታና ስለማመልከቻው ተገቢነት አስፈላጊ ማስረጃ ለማግኘት አመልካችን ወይም ወኪሉን አስቀርቦ ሊጠይቅ የሚችል ሲሆን ማመልከቻው የቀረበው በወኪል ከሆነም አመልካቹ እራሱ እንዲቀርብ አልያም በሚገኝበት ቦታ በተተኪ ዳኛ እንዲመረመር ማዘዝ ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዚህ መልኩ በሚያደርገው ምርመራ ማመልከቻው የሚነቀፍበት ምክንያት ካላገኘ አመልካቹ ድሀ ስለመሆኑ እንዲሁም ሀብት አለው የሚሉ ሌሎች ወገኖች ካሉ ቀርበው እንዲያስረዱ በማድረግ የግራ ቀኙን ማስረጃ እና ክርክር የሚሰማ ይሆናል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜም ማስረጃ ከመስማቱ ከ10 ቀናት በፊት ሌላኛው ተከራካሪ ጉዳዩን እንዲያውቅ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባደረገው ምርመራ የዳኝነት ሳይከፈል ክስ ለማቅረብ የቀረበውን ማመልከቻ የሚቀበል ከሆነ በነፃ እንዲከራከር በመፍቀድ በተለመደው መደበኛ ሥነ ሥርአት መሠረት ክርክሩ ይቀጥላል፡፡

በአንፃሩ ፍርድ ቤቱ ባደረገው ምርመራ አመልካቹ ድሀ አለመሆኑ ከተረጋገጠ፣ በነፃ ለመክሰስ ያቀረበው ነገር የማያስከስስ ከሆነ፣ ክስ ከማቅረቡ ከሁለት ወር በፊት የነበረውን ንብረት ለሌላ ሰው አስተላልፎ እንደሆነ ወይም በማጭበርበር መንገድ ንብረቱን አዛውሮ ከሆነ ወይም የዳኘነት ላለመክፈል ዘዴ ፈጥሮ ከሆነ፣ ክርክር በሚያቅርብበት ንብረት ወይም መብት ውስጥ ሌላ ሶስተኛ ሰው እንዲጠቀም ወይም ማናቸውንም መብት እንዲያገኝ ተዋውሎ ወይም ተስማምቶ ከሆነ በድሀ ደንብ ማመልከቻው ተቀባይነት አይኖረውም (ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 470)፡፡

በነፃ ክስ የማቅረብ ፈቃድ የሚፀናበት ጊዜ

በነፃ እንዲታይ የሚሰጥ ፈቃድ የሚያገለግለው ለተሰጠበት ክርክር ብቻ ሲሆን ፈቃድ የተሰጠበት ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚያገኝ ይቆያል፡፡ በተጨማሪም በነፃ በተከፈተው ክስ ላይ ተከሳሽ የሆነው ሌላኛው ወገን ይግባኝ የሚያቀርብ እና የነፃ ፈቃድ ያገኘው ሰው መልስ ሰጪ የሚሆን ከሆነ የነፃ ፈቃዱ በይግባኝም የሚፀና ይሆናል፡፡ ሆኖም በተቃራኒው በመጀመሪያ ደረጃ በነፃ ክስ እንዲያቀርብ ፈቃድ የተሰጠው ሰው በተሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ የሚያቀርብ ከሆነ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በድጋሚ በነፃ ይግባኝ እንዲያቀርብ ማመልከቻ ካላቀረበ በስተቀር በቀደመው የነፃ ፈቃድ ሊገለገል አይችልም፡፡ (ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 474)

የማመልከቻ ውድቅ መሆን ውጤት

የዳኝነት ሳይከፍል ልከራከር የሚል የቀረበ ማመልከቻ ውድቅ የተደረገ ከሆነ ማመልከቻ አቅራቢው በዚያው ጉዳይ በድጋሚ በነፃ ልክራከል በሚል ማመልከቻ ማቅረብ እንደማይችል በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 477 ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በዚያው ጉዳይ ክስ የሚያቀርብ ከሆነ የሚጠበቅበትን የዳኝነት ክፍያ እንዲሁም የነፃ ዳኝነት እንዲፈቀድለት በጠየቀ ጊዜ ባለጋራው መቃወሚያ ለማቅረብ ያወጣውን ወጪና ኪሳራ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

የዳኝነት ሳይከፍል ክስ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት ሰው መብቱን የሚያጣበት ሁኔታ

በነፃ ለመከራከር ፈቃድ የተሰጠው ሰው ክርክሩ እንዲሰማ በተቀጠረው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ ከቀረ ወይም የማወክ፣ የማስቸገርና የተንኮለኛነት ጠባይ ካሳየ፣ ክርክሩ በሚቀጠልበት ጊዜ ሀብት ያለው መሆኑ የተገለፀበት አንደሆነና ፍርድ ቤቱም በነፃ ዳኝነት መጠቀም የማይገባው መሆኑን ከተረዳ እንዲሁም ለክርክሩ መነሻ በሆነው ሀብት ላይ ሌላ ሶስተኛ ወገን ጥቅም እንዲያገኝ ስምምነት አድርጎ ከሆነ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 475 መሠረት በነፃ እንዲከራከር የተሰጠውን መብት ያጣል፡፡

በነፃ እንዲከራከር የተፈቀደለት ሰው ሀብት ማግኘት የሚስከትለው ውጤት

የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ ክስ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት ሰው በክርክሩ ከረታ እና ሀብት ካገኘ ፍርድ አስፈፃሚው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 476 መሠረት ንብረቱን ለረቺው ከማስረከቡ በፊት ለዳኝነት ሊከፈል የሚገባውን ገንዘብ ተቀናሽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም በነፃ እንዲከራከር የተፈቀደለት ሰው በአስር ዓመት ግዜ ውስጥ ወይም ክርክሩ በሚቀጥልበት ጊዜ ሀብት ካገኘ ፈቃዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት በማሳወቅ የዳኝነቱን የመክፈል ግዴታ እንዳለበት በሥነ ሥርአት ህጉ ቁጥር 478 ሥር ተደንግጓል፡፡

ማጠቃለያ

የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ ክስ የሚቀርብበት ሥነ ሥርአት በገንዘብ እጦት ምክንያት ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን እንዳያጡ የተቀመጠ መፍትሄ በመሆኑ በገንዘብ እጦት ምክንያት የዳኝነት መክፈል የማይችሉ ሰዎች አስፈላጊውን ማስረጃ በማቅረብ ሊገለገሉበት ይችላሉ፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ