መግቢያ
ባንኮች፣ የብድር ፣ቁጠባ እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ሳይቋቋሙ በፊት ማህበረሰቡ ባለው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ በወለድ ብድር አገልግሎት ይጠቀምበት ነበር፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ወለድና የወለድ ወለድ ምንነት እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
ትርጓሜ
በመደበኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ ወለድ ማለት አንድ ገንዘብ ያበደረ ሰው ተበዳሪው ብድሩን በመጠቀሙ ላበዳሪው ወገን በበኩሉ የሚከፍለው ወይም አንድ የባንክ ደንበኛ ያለውን ገንዘብ በአንድ ባንክ ገንዘብ ተቀማጭ ሲያደርግ በመቶኛ የሚታሰብ ገንዘብን የሚመለከት ወይም ተበዳሪ የወሰደውን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፈል የገንዘብ መጠን ነው፡፡ በተጨማሪም ወለድ በስምምነት ወይም ያለስምምነት ማለትም በሕግ አግባብ ሲወሰንና ሊከፈል ይችላል፡፡ የወለድ ወለድ ማለት በሚከፈል ወለድ ላይ በስምምነቱ ወይም በሕግ መሠረት ወለዱን በወቅቱ ያልከፈለ ወገን በወለዱ ላይ የሚከፍለው ተጨማሪ የወለድ ወለድ እንደመቀጫ ያለ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ወለድን በተመለከተ የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1751 ህጋዊ ወለድ (Legal Rate of Interest) ማለት በውል ያልተወሰነ ወለድ (ጥቅም) ከፋይ የሆነ ሰው በዓመት በመቶ ዘጠኝ (9%) ሂሳብ ይከፍላል በማለት በትርጓሜ መልክ ደንግጓል፡፡ ስለዚህ ህጋዊ ወለድ ማለት በዓመት በመቶ ዘጠኝ የሚከፈልበት ገንዘብ ማለት ነው፡፡
ወለድ ከፍትሐብሔር ሕግ አንፃር
የገንዘብ እዳ መክፈያ ግዜ ካለፈ ምንም እንኳን በውላቸው አነስተኛ ወለድ ለመክፈል የተስማሙ ቢሆንም እንኳን በፍትሀብሔር ሕግ ቁጥር 1803 መሠረት ወደ ህጋዊ ዘጠኝ በመቶ እንደሚከፈል ይደረጋል ሲል ይደነግጋል፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2478 ድንጋጌ ህጋዊ ወለድን ላለመክፈል ሊስማሙ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ደግሞ የብድር ውል ሲዋዋሉ ውላቸው ያለወለድ ወይም በወለድ እንዲሆን ለማድረግ መብት እንዳላቸው ያሳያል፡፡ ተዋዋዮቹ በመካከላቸው የሚያደርጉት ውል ከሕግና ከሞራል የማይቃረንና የሚፈፀም ወይም የሚቻል ከሆነ በመካከላቸው እንደ ሕግ ሆኖ እንደሚያገለግል ከፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 1731 ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ የፍትሐብሄር ህጉ ቁጥር 2479(1) የብድር ውል ተዋዋይ ወገኖች ተበዳሪው ሊከፍለው የሚገባው የወለድ መጠን በወር ወይም በቀን ሳይሆን በዓመት ከአስራ ሁለት በመቶ (12%) በላይ ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡
ስለውል አለለመፈፀም ስናነሳ የፍትሐብሄር የውል ሕግ ክፍል ቁጥር 1803 (2) ላይ የገንዘብ ዕዳን በማሳለፍ ስለሚከፈል ወለድ በተመለከተ “በውለታው ውስጥ የበለጠ ወለድ የታሰበ እንደሆነ በዚሁ በከፍተኛው ወለድ መታሰቡ ይቀጥላል” በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይኸውም በውሉ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ሳይከፈል በቀረ የገንዘብ ዕዳ ላይ የሚታሰበውን የወለድ ምጣኔ ተዋዋዮቹ የተስማሙበት መጠን እንደሆነ የሚደነግግ ነው፡፡ ስለዚህም ዳኞች የውሉን ሁኔታ በማየት ትርጓሜ የሚሰጡበትና ከውሉ በተቃራኒ ወለዱን የሚቀንሱበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ 81857 ቅፅ 14 ላይ በቀን ጥር 13/2005 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም የፍትሐ ብሄር/ቁጥር 1803 (2)ን በማጣቀስ የሰጠው ውሳኔ አመልካች ለተጠሪ በውላቸው መሠረት በዋናው ገንዘብ ላይ የ14% ወለድ እንዲታሰብ መወሰኑ የድንጋጌ ትርጉም የሚያጠናክር ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ማናቸውም ውሎች ከብድር ውል በስተቀር ተዋዋይ ወገኖች እስከፈለጉት የወለድ መጠን ድረስ መዋዋል እንደሚችሉ ነው፡፡ የብድር ውልን በተመለከተ ግን ተበዳሪው ወለድ እንዲከፍል የውል ቃል ከሌለ በቀር ላበዳሪው ወለድ መክፈል እንደሌለበት የፍ/ህ/ቁጥር 2479 ያስረዳል፡፡ ይህ ማለት ግን ባለእዳው ግዴታውን ባለመወጣቱና በውላቸው ላይ ወለድ ባይታሰብ እንኳን በፍርድ ቤት ለሚቀርብበት ክስ ሀላፊ ሲሆን በከሳሽ የሚጠየቀውንና በፍርድ ቤት የሚወሰነውን ህጋዊውን ወለድ ያስቀራል ማለት አይደለም፡፡
ህገወጥ ወለድን አስመልክቶ የወንጀል ህጉ እይታ
ከፍትሐብሄር ኃላፊነት ባሻገር መነሳት ያለበት ጉዳይ የአራጣ ጉዳይ ነው፡፡ አራጣን በተመለከተ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የህሊናን ወይም የሰውን ችግር መሠረት በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስር በአንቀጽ 712 መሠረት ከብድር ውል ጋር የሚያያዝ ሲሆን ድንጋጌውም ፡-
- ማንም ሰው የተበዳዩን ችግረኛነት፣ የበታችነት ወይም የገንዘብ ችግሩን ወይም መንፈሰ ደካማነቱን ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌላው መሆኑን መሠረት በማድረግ
- በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረ እንደሆነ ወይም
- ካበደረው ገንዘብ ጋር በግልፅ ተመጣጣኝነት የሌለውን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ያደረገው ወይም ቃል ያስገባው እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
- ማንም ሰው በተመሳሳይ በአራጣ ላይ የተመሰረተ መብት የተቀበለ፣ በመከላከያነት የተጠቀመበት ወይም ለሌላ ሰው ያስተላለፈ እንደሆነ እንዲሁ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል ሲል የደነገገ ሲሆን የዚህ ድንጋጌ ቅድመ ሁኔታዎችም፡-
- የተበዳዩን ችግረኛነት፣ የበታችነቱን፣ ወይም የገንዘብ ችግሩን፣ ወይም መንፈሰ ደካማነቱን፣ ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑን መሠረት በማድረግ በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረው እንደሆነ ነው፡፡
ስለዚህ አራጣ ማለት ህጉ ከፈቀደው የብድር ወለድ መጠን በላይ ተዋውሎ ማበደር ማለት ነው፡፡ ህጉ የፈቀደው የብድር ውል ወለድ መጠን በዓመት 12% ድረስ ብቻ ነው፡፡
ባንኮች የፍትሐብሔር ህጉ ላይ ካለው 12% በላይ ወለድ ብድር ህጋዊነት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ብድር አቅርቦት በተፈለገው መጠን መገኘትን፣ እንዲሁም የወለድ ተመንና ሌሎች ክፍያዎችን የመወሰንና የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ብሔራዊ ባንኩ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓ.ም አንቀጽ 5(4) እና በመመሪያ ቁጥር 12/2010 መሠረት የብድር ውል ለደንበኞቻቸው በሚሰጡበት ወቅት ላበደሩት ብድር የወለዱን ምጣኔ በራሳቸው እንዲወስኑ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ የሚታሰበው የወለድ ምጣኔ ከላይ እንደተመለከተው በፍትሐብሔር ህጉ እንደተመለከተው የወለድ ጣራው በዓመት እስከ 12 % ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሌሎች የፋይናንስ እና የብድርና ቁጠባ ተቋማትም በተመሳሳይ ከፍትሐብሔር ህጉ 12 % በላይ የሆነ የወለድ ጣራ ማድረስ እንደሚችሉ የዚሁ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ እና መመሪያ ያረጋግጣሉ፡፡
የወለድ ወለድ የሕግ ተቀባይነት
የፍታብሄር ህጉ ቁጥር 1804(1) የወለድ ወለድን በተመለከተ መርሁ በብድር ውል ላይ ተዋዋይ ወገኖች ወለዱ ከዋናው ገንዘብ ጋራ ተጨማሪ ሆኖ ወለድ ይወልዳል ብለው አስቀድመው ለመዋዋል እንደማይችሉ ነው፡፡ በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሠረት በብድር ውል ግንኙነት ላይ የወለድ ወለድ የተከለከለ ነው፡፡ በወለድ ላይ ወለድ በመርህ ደረጃ የሌለ ሲሆን በልዩ ሁኔታዎች የወለድ ወለድ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ በዚሁ ቁጥር 1804(1) ስር የተደነገገ ሲሆን ይኸውም፡-
- ባለእዳው በየጊዜው የሚከፍለው ገንዘብ እና ለባለገንዘቡ እንደገቢ (በተወሰነ ጊዜ የሚገኝ እንጂ የተከማቸ እዳን አያመለክትም) የሚያገለግል ሲሆን፤
- እዳውን ለማስከፈል በፍርድ ቤት በባለገንዘቡ ክስ ሲመሠረት፤ እና
- ባለእዳው ለአንድ ዓመት ክፍያውን ሳይከፍል የቀረ እንደሆነ ወይም ባለገንዘቡ ባለእዳውን የሚጠይቀው የአንድ ዓመት ክፍያን ሲሆን ነው፡፡
ባለገንዘቡ ያለውን መብት እና ባለዕዳው ያለበትን ግዴታ በተነፃፃሪ ሁኔታ ባለዕዳው የአንድ ዓመት እዳ ካለበትና ይህንኑ ጥያቄ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶ በባለገንዘቡ ከተጠየቀ ባለገንዘቡ ባለዕዳው ላይ ካለው ያልተከፈለ እዳ እና ወለድ በተጨማሪ የወለድ ወለድ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት እንዳለው መደንገጉ ባለእዳው አንድ ዓመት የባለገንዘቡን መብት በማቆየቱ ያጣውን መብት በማየት እና ባለእዳው ቶሎ ቶሎ መክፈል ያለበት መሆኑን ለማሳየት እና እዳውን አስቸኳይነት ለማየት ያሰበ እንጂ ያለአግባብ ለመበልፀግ አይደለም፡፡ በብድር ለተሰጠ ወለድ የመጠየቂያ ጊዜ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2024 መሠረት እዳው እንዲከፈል መጠየቅ ከሚገባበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት የተወሰነ ጊዜ አለው፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ወለድ አስፈላጊነትን ስንመለከት የወለድ አንዱ ምክንያት ግዴታን ባለመፈፀም ወይም በማዘግየት የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ ግዴታ አለመፈፀም ደግሞ ይሄ ፍሬ ነገሩ መረጋገጥ ታይቶ የሚከፈልም ነው፡፡ ባለእዳውም ብድሩን በማግኘቱ ምክንያት በመጠቀሙ ለባለገንዘቡ የሚከፍለው እና ተበዳሪው ብድር የፈለገበትን ጉዳይ በወለድ ተበድሮ የሚያሳካበት ነው፡፡ ባለዳውም እዳውን በወቅቱ እንዲከፍል የሚያደርግ ሲሆን የውሎች አለመፈፀምንም እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ