የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወሲባዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸው ተጎጂዎች በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ የጤና፣ የሕግ፣ የስነልቦና አገልግሎትና ማኅበራዊ ድጋፍ በአንድ ቦታ የሚሰጥ ወይም ስርዓት በተዘረጋለት የቅብብሎሽ አሠራር ስርዓት በመመራት አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ሲሆን ዓላማውም ለወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች በአንድ ጣሪያ ስር የተቀናጀ የጤና፣ የፍትሕ፣ የስነልቦናና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጠት እና በቀጣይ የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶች በቅብብሎሽ ሥርዓት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
በማዕከሉ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው በራሳቸው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ፣ ከህክምና ተቋማት በሪፈር ፣ በጥሪ ማዕከል፣ ከፖሊስ ሪፈር ተደርገው ፣ ከስደተኞች መጠለያ ፣ ከመጠለያ ተቋማት ተልከው ፣ ከስደተኛ ከተፈናቃይ እና ስደት ተመላሽ መጠለያዎች ፣ ከሴቶችና ህጻናት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊና እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከማሕበረሰብ አደረጃጀቶች የሚመጡ ተጎጂች በማዕከሉ የሚሰጡ የህክምና ፣የሕግ ፣የስነልቦና ፣ማኅበራዊ ድጋፍ እና ጊዜያዊ መጠለያ በተቀናጀ የቅብብሎሽ ስርዓት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
በአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች ለተጎጂዎች ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የትኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል እና የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለን ተጎጂ እኩል የሚስተናገድበት ፣ተጎጂዎች በአካባቢያቸው እና በሚረዱት ቋንቋ በቂ ባለሙያን ባሟላ እና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ የሚሰጥ ፣ የተጎጂ ሚስጥር የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ በማዕከሉ የሚሰጥ ማንኛውም አገልግሎት የተጎጂን ፍቃድ መሠረት ያደረገ እና በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ምንም አይነት ክፍያ የማይጠየቅባቸው ናቸው፡፡
በተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ የጤና ባለሙያ ፣ፖሊስ፣ዐቃቤ ሕግ፣የጉዳይ አያያዝ ባለሙያ ፣የስነ ልቦናና ማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የወንድ ሕጻናት እና የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች ፣የህጻናት ሕክምና ስፔሻሊስቶች፣የአእምሮ ጤና ችግር ላለባቸው እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተጎጂዎች የአእምሮ ሕክምና እና ነርስ፣ የልዩ ፍላጎት ሕክምና ፣ራዲዮሎጂስቶች/ ለእድሜ ምርመራ ፣ ተጎጂዎች የሚናገሩትን ቋንቋ አስተርጓሚ እና የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ደግሞ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት በጥሪ የሚገኙ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ማዕከሉ በሁሉም ክልሎች እና በአዲስ አበባ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፍራል ሆስፒታል ውስጥ ሙሉ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በየካ ኮተቤ ሆስፒታል እና አበበች ጎበና የእናቶች እና ሕፃናት ሆስፒታል ማስፋፊያዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ ማንኛውም ጾታዊ ጥቃት የደረሰበት አካል በማዕከሉ በመገኘት አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል፡፡