መግበያ
አንድ ሰው በሕይወት ለመኖር አነሰም በዛ ንብረት ማፍራት ይገባዋል፡፡ ይህን ንብረት ለራሱና ለእርሱ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር በጋራ ይጠቀማል፡፡ ሰው ንብረቱን ከመጠቀም አልፎ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ንብረቱን ለፈቀደው ሰው እንዲተላለፍለት ኑዛዜ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የውርስን ምንነት፣ ውርስ የሚተላለፍበትን ሥርዓት እና የውርስ ይርጋን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የውርስ ምንነት እና አስተላለፍ
የብላክስ የሕግ መዝገበ ቃላት ‘Black’s Law Dictionary’ ውርስን በተመለከተ ትርጓሜ ሲሰጥ “succession is the transmission of the rights and obligations of the deceased to the heirs, also the estates, right and charges which a person leaves after his death” በማለት ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ትርጉሙም “ውርስ ማለት የሟች መብትና ግዴታዎች እንዲሁም ሀብት፣ በሃብቱ ላይ ያለው መብትና ግዴታ በህይወት ላሉት ወራሾቹ የሚተላለፍበት መንገድ ነው” በማለት ይገልፀዋል፡፡ በሀገራችን የውርስ ሕግ ውስጥ በቀጥታ ተተርጉሞ ባናገኘውም አንድ በሞት የተለየን ሰው ንብረት እና ሀብት እንዲሁም ሊተላለፉ የሚችሉ መብት እና ግዴታዎች በሕይወት ላለ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ መሆኑን ከሕጉ ጠቅላላ መንፈስ መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ የሚሆነውም በውርስ ሕግ አማካኝነት ሲሆን የውርስ ሕግ ማለት የሟች (አውራሽ) መብቶች እና ግዴታዎች በሕይወት ወዳሉት ወራሾቹ የሚተላለፍበት ደንብ (ሥርዓት) ነው፡፡ በሀገራችን ይህ የውርስ ሕግ በ1952 ዓ/ም በወጣው የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ በሁለተኛ መጽሀፍ በ5ኛው መፅሀፍ ሥር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም ወራሾችን ማጣራት (መውረስ የሚችሉ እነማን እነደሆኑ ማወቅ)፣ ውርስ ማጣራት እና ውርስ ክፍፍል በውርስ ህጉ መሠረት አንድን የውርስ ንብረት ወደ ወራሾች የማስተላለፍ ሂደቱቶች ናቸው፡፡
ስለ ውርስ መከፈት
ሟች ሲሞት ውርስ የሚከፈተው ሲሆን የሚከፈትበትም ቦታ ሟች በሞተበት ጊዜ ዋና መኖሪያው ስፍራ በሆነበት ቦታ ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 826/1/)፡፡ ኑዛዜ የሚከፈተው ደግሞ ሟች ከሞተ በአርባ ቀኑ ላይ እንደሆነ ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 965/1/ መረዳት ይቻላል፡፡
በውርስ መተላለፍ የሚችሉ መብትና ግዴታዎች
የሟች ንብረት እንዲሁም መብትና ግዴታዎቹ በውርስ ሕግ መሠረት ለወራሾች መተላለፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህ አጠቃላይ ደንብ ሲሆን በባሕሪያቸው አንዳንድ መብቶች እና ግዴታዎች ደግሞ ግለሰባዊ በመሆናቸው ሁሉም መብትና ግዴታዎች ሊወረሱ ወይም ለወራሾች ሊተላለፉ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ ሟች የህክምና ዶክተር ወይም የምክር ቤት አባል ቢሆን ይህን ሙያውን ወይም አባልነቱን ለወራሾች ማውረስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዕውቀት የግለሰቡ ብቻ በመሆኑ እና የተመረጠውም እርሱ እራሱ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በውርስ የሚተላለፉት መብትና ግዴታዎች ከሟች መሞት ጋር አብረው ቀሪ የማይሆኑ እና መተላለፍ የሚችሉት ብቻ ናቸው፡፡
ወራሽ ለመሆን የሚያስፈልጉ ችሎታዎች
ለወራሽነት ብቁ የሚያደርጉ በሕጉ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ እንዲሁም በስመ ወላጅነት ወይም ተወላጅነት ብቻ ወራሽ ለመሆን አይቻልም፡፡ ይልቁንም በሕጉ የተቀመጡትን ወራሽ ለመሆን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ያላሟላ ወራሽ በሕግ ወራሽነቱ ቢገለፅም ከውርሱ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ለወራሽነት ብቁ ለመሆን የሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች በሕይወት መኖርና ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ናቸው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 830) ፡፡
– በህይወት መኖር፡- አንድ ሰው ወራሽ ለመሆን አውራሹ በሚሞትበት ወቅት በህይወት ያለ መሆን አለበት፡፡ አውራሽ ሲሞት ያልነበረ ወይም እሱን ቀድሞ የሞተ እንደሆነ መውረስ አይችልም፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ሟች በሚሞትበት ወቅት ገና ተፀንሶ የነበረ ህፃን ከሆነ ተወልዶ 48 ሰዓት በሕይወት ከቆየ ውርስ ሲከፈት እንደነበረ ተቆጥሮ የመውረስ መብቱ ይጠበቅለታል ((የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 834)፡፡
– ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን፡- አንድ ወራሽ ለወራሽነት የማይገባ የሚሆነው በአውራሹ ወይም ወደ ታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወይም ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ወይም ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት ወይም በመግደል ሙከራ የተቀጣ ወይም በሐሰት በመወንጀል ወይም በመመስከር አንደኛውን የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት በበለጠ የፅኑ እስራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ የተቀጣ ከሆነ ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 838)፡፡ ሌላው አንድን ሰው ለወራሽነት የማይገባ የሚያደርገው ምክንያት አውራሽ ከመሞቱ በፊት ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የአውራሽን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ ኑዛዜ እንዳያደርግ፣ እንዳይለውጥ ወይም እንዳይሽር የከለከለ እንደሆነ ወይም አስቦ ያለ ሟች ፍቃድ የመጨረሻውን ኑዛዜ ያበላሸ፣ እንዳይገኝ ያደረገ፣ ያጠፋ ወይም ጉዳዩን በማወቅ በሐሰት ኑዛዜ የተጠቀመ እንደሆነ ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 840)፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አንድ ሰው ከጥፋቱ መጠቀም የለበትም ከሚለው የሕግ መርህ በመነሳት ነው፡፡
የውርስ ሥርዓቶች
በሀገራችን ሁለት ዓይነት የውርስ ማስተላለፊያ መንገዶች ያሉ ሲሆን እነርሱም፡- ያለኑዛዜ ውርስ (Intestate Succession) እና የኑዛዜ ውርስ (Testate Succession) ናቸው፡፡
- ያለ ኑዛዜ ውርስ፡- አውራሽ (ሟች) ኑዛዜ ሳያደርግ ሲሞት ወይም ያደረገው ኑዛዜ ፈራሽ በሚሆንበት ጊዜ የአውራሹ ንብረት ለወራሾች የሚከፋፈለው በሕጉ በተቀመጡት ያለ ኑዛዜ ውርስ ድንጋጌዎች መሠረት ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች የሚሆኑት የሟች ልጆች ሲሆኑ ለመውረስ ብቁ የሚያደርጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟሉ ድረስ ወራሾች ሆነው የሟችን ንብረት እኩል ይወርሳሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 842)፡፡
አውራሽ ልጆች ከሌሉት ወይም ልጆቹን ተክቶ የሚወርስ ከሌለ የአውራሽ አባትና እናት ሁለተኛ ደረጃ ወራሽ ይሆናሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 843)፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አውራሽ ልጆችም ወላጆችም ወይም የእነሱ ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች የሌሉት ከሆነ ወይም እነሱን ተክቶ የሚወርስ ከሌለ የአውራሽ አያቶች ሶስተኛ ደረጃ ወራሾች ይሆናሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 845)፡፡ አያቶች የሌሉ እንደሆነም የአውራሽ ቅድመ አያቶች አራተኛ ደረጃ ወራሾች ይሆናሉ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 847)፡፡ ምትክ ወራሽነት ማለት አንድ ወራሽ መውረስ የሚችል ሆኖ ውርሱ ሳይጠናቀቅ ያረፈ እንደሆነ የእርሱ ወረሾች በእርሱ ተተክተው የሚወርሱበት ሥርአት ነው፡፡ ለምሳሌ አባት ወይም እናት የወላጃቸውን ውርስ ወርሰው ሂደቱን ሳይጨርሱ የሞቱ እንደሆነ የነሱን ፋንታ ወይም በእነርሱ እግር ተተክተው ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆቻቸው ይወርሳሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ውርሱ መከናወን ካልቻለ እና ወራሾች እስከ አራተኛ ደረጃ ያልተገኙ እንደሆነ የሟች ንብረት ለመንግሥት እንደሚተላለፍ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 852 ላይ ተደንግጓል፡፡
- የኑዛዜ ውርስ፡- ኑዛዜ ሁለተኛው ዓይነት የውርስ ማስተላለፍያ መንገድ ነው፡፡ ኑዛዜ ማለት ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በፍላጎቱ መሠረት ለተተኪዎቹ የሚያስተላልፍበት ሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ ሟች ከሞተ በኋላ ስለ ንብረት ክፍፍል፣ የልጆቹ ሞግዚት ማን እንደሚሆን፣ ንብረቱን ማን እንደሚያስተዳድርና ስለ ቀብር ስነስርዓቱ በኑዛዜው ሊገልፅ ይችላል፡፡ ኑዛዜ በሕግ ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ተናዛዡ በሕግ የመናዘዝ ችሎታ ያለው ሰው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በሕጉ ችሎታ የላቸውም የተባሉት ሰዎች፡- እድሜያቸው ለአካለመጠን ያልደረሰ፣ በፍርድ የተከለከሉ ሰዎችና የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በሕግ ፊት የሚፀና ኑዛዜ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ማሟላት አለበት፡፡ ኑዛዜው መፈፀም የሚችል መሆን፣ የኑዛዜው ቃል ሕጋዊ መሆን፣ ኑዛዜው በተናዛዡ ሙሉ ፈቃድ የተደረገ መሆን ወይም በኃይል ወይም በመንፈስ ጫና ምክንያት የተደረገ አለመሆን ናቸው፡፡ ኑዛዜ እነዚህን ካላሟላ ፈራሽ ይሆናል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 865-868)፡፡
ሟች ከመሞቱ በፊት ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የሕክምና እርዳታ ሲሰጡት ለነበሩ ሀኪሞች ወይም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡት ለነበሩ የእምነት አባቶች በኑዛዜው የሰጠው ስጦታ እንደነገሩ ሁኔታ ሊቀነስ ወይም ሊሻር ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦች ከሟች ጋር በትዳር የተሳሰሩ ወይም የስጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ካላቸው ይህ ደንብ ተፈፃሚ አይሆንም (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 870)፡፡ በኑዛዜው ላይ ምስክሮች ወይም አዋዋዮች ለነበሩ ሰዎች የተደረገ ኑዛዜም በተመሳሳይ ሊቀነስ ወይም ሊሻር ይችላል፡፡
ኑዛዜን ለመቀነስ ወይም ለመሻር ሥልጣን የተሰጣቸው ዳኞች ብቻ ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው በኑዛዜው ተጠቃሚ የሆነው ሰው ኑዛዜው እንዲፈፀምለት ጥያቄ ካቀረበበት ቀን አንስቶ በሶስት ወራት ውስጥ በሕጉ መብት የተሰጣቸው ሰዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ብቻ ነው፡፡
የኑዛዜ ዓይነት/ፎርም
ኑዛዜ የሚፈፀመው ሟች ከሞተ በኋላ በመሆኑ የሟች ፍላጎት በተገቢው እንዲፈፀም አስቀድሞ በማያሻማና ግልፅ በሆነ ፎርም መደረግ አለበት፡፡ የውርስ ህጋችን ሶሶት ዓይነት የኑዛዜ ፎርሞች እንዳሉ ደንግጓል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 880)፡፡ እነዚህም በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ፣ በተናዛዡ ፅሑፍ የሚደረግ ኑዛዜ እና በቃል የሚደረግ ኑዛዜ ናቸው፡፡
- በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ፡- በፅሑፍ የሚደረግ ሆኖ ተናዛዡ እራሱ የሚፅፈው ወይም እሱ እየተናዘዘ ሌላ ሰው የሚፅፍለት ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 881-883)፡፡ ኑዛዜው ከተፃፈ በኋላ በተናዛዡና በአራት ምስክሮች ፊት ተነቦ ስለመነበቡም በኑዛዜው ውስጥ ሰፍሮ ቀኑ ተጠቅሶ ወዲያው በተናዛዡና በምስክሮች መፈረም አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት ካልተፈፀመ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡ በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ የተደረገው ለማዋዋል ሥልጣን በተሰጠው ሰው ወይም ፍርድ ቤት ፊት ከሆነ በሁለት ምስክር ፊት ከተደረገ በቂ ነው፡፡
- በተናዛዡ ጽሑፍ የሚደረግ ኑዛዜ፡- በፅሑፍ ሆኖ ሙሉ በሙሉ በተናዛዡ መፃፍ አለበት (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 884-891)፡፡ በተጨማሪም ፅሁፉ ኑዛዜ መሆኑ በግልፅ “ኑዛዜ ነው” ተብሎ መፃፍ አለበት፡፡ እንዲሁም በእያንዳንዱ ገፅ ላይ ተናዛዡ ቀን ጽፎ መፈረም አለበት፡፡
- የቃል ኑዛዜ፡- ማለት አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ ፈቃድ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚሰጥበት ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 892-897)፡፡ በቃል በሚደረግ ኑዛዜ ተናዛዡ መናዘዝ የሚችለው ስለቀብር ሥነ-ሥርዓት በተመለከተ ትዕዛዞች መስጠት፣ ከአምስት መቶ የኢትዮጵያ ብር ያልበለጠ የንብረት ስጦታ እና ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አስተዳዳሪ ወይም ሞግዚት መሾምን ብቻ ነው፡፡ በአንድ የቃል ኑዛዜ ውስጥ ከአምስት መቶ ብር በላይ የኑዛዜ ስጦታ ከተደረገ ከአምስት መቶ ብር በላይ የሆነው ስጦታ ተቀናሽ ይሆናል፡፡
በተወሰኑ አጋጣሚዎች የኑዛዜ ውሳኔዎች ከአንድ በላይ በሆኑ በተለያዩ የኑዛዜ ፅሁፎች ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ተቀራራቢነት ኖሯቸው በአንድነት ሊፈፀሙ የሚችሉ ሆነው ሲገኙ በአንድነት ይፈፀማሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ ላይ ሊፈፀሙ የማይችሉ ሲሆን በመጨረሻ የተደረገው ኑዛዜ ዋጋ ያለው ሆኖ ይፈፀማል፡፡
የኑዛዜ መሻርና ውጤቱ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 898-908)
ኑዛዜ አድራጊው ሰው በፈለገው ጊዜ ኑዛዜ የማድረግ፣ የመሻር ወይም የመለወጥ መብት አለው፡፡ አንድ ተናዛዥ የተናዘዘውን ኑዛዜ ምንም አይነት ምክንያት ሳያስፈልገው መሻር ይችላል፡፡ ተናዛዡ ይህን የሚያደርገው ኑዛዜውን ባደረገበት ፎርም ነው፡፡ ኑዛዜውን ተናዛዡ በራሱ ፍላጐት ከሻረው የተናዘዘው ቃል ቀሪ ይሆናል፡፡
በቃል የተደረገ ኑዛዜ ከተደረገ ከሶስት ወር በኋላ ተናዛዡ በሕይወት ካለ ኑዛዜው ውድቅ ይሆናል፡፡ ኑዛዜው በተናዛዡ ጽሑፍ የተደረገ ከሆነ ኑዛዜው በተደረገ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማዋዋል ሥልጣን በተሰጠው ሰው ወይም በፍ/ቤት መዝገብ ቤት ዘንድ ያልተቀመጠ እንደሆነ ውድቅ ይሆናል፡፡ ኑዛዜው ከተደረገ በኋላ ተናዛዡ ልጅ ቢወልድም ኑዛዜው እንዲሁ ውድቅ ይሆናል፡፡
ከወራሽነት መንቀል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 937-941)
አንድ ተናዛዥ ያለውን ንብረት በኑዛዜ ለማስተላለፍ ሙሉ መብት እንዳለው ሁሉ ንብረቱን ላለማውረስም ሙሉ መብት አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ተናዛዡ ወራሽ ሳያደርግ በሕግ ሊወርሱት ይችሉ የነበሩትን ግለሰቦች ወይም ከእነሱ አንዱን በግልፅ ከውርስ ውጪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህም ሲሆን ከውርስ ዉጪ የሆነው ወራሽ ከተናዡ በፊት እንደሞተ ተቆጥሮ ውርሱ በሕጉ መሠረት ይፈፀማል፡፡
ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ ከውርስ ወራሹን ለመንቀል የደረሰበትን ምክንያት ካልገለፀ በቀር ልጅን ወይም ወደታች የሚቆጠር ተወላጅን ከውርስ ቢነቅል ውሳኔው በሕግ አይፀናም፡፡ ተቃራኒ የኑዛዜ ቃል ከሌለ በቀር የሁለተኛ፣ የሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ዘመዶች እያሉ በኑዛዜው ለሌላ ሰው ንብረቱን ከሰጠ እነዚህን የተጠቀሱ ዘመዶቹን ከኑዛዜው ውጭ እንዳደረጋቸው ይቆጠራል፡፡ ተናዛዡ ከወራሾቹ አንዱን ወይም ሁሉንም የኑዛዜውን ሙሉ ወይም አንድ ቃል ከተቃወሙ ውርሱን እንዳያገኙ ብሎ ቢናዘዝ ይህ ኑዛዜ በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም፡፡
የውርስ ጉዳይ ይርጋዎች
ይርጋ ማለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረቢያ የጊዜ ገደብ ማለት ነው፡፡ እንደ አቤቱታው ዓይነት ይርጋው ይለያያል፡፡
- የውርስ ሀብት ለማግኘት ወይም ለመካፈል የሚቀርብ ክስ
መብቱና የውርሱ ንብረት በሌላ ሰው የተያዘበት ወራሽ ንብረቱን ከያዘው ሰው ላይ ጠይቆ መውሰድ ይችላል፡፡ ንብረቱን የያዘው ሰው የያዘውን የወራሹን ንብረት ለወራሹ ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ ወራሹ ንብረቱን በሕግ አስገዳጅነት ለማግኘት ክስ የማቅረብ መብት አለው፡፡
ሆኖም ክስ የማቅረቢያው ጊዜ ገደብ ወራሹ ንብረቱ በተከሳሹ መያዙን ካወቀበት ቀን ጀምሮ የሚቆጠር 3 ዓመት ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000(2) መሠረት ይህ መብት የሚያገለግለው አውራሹ ከሞተበት ቀን ጀምሮ ባለው 15 ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ሟች ከሞተ 15 ዓመት ከሞላው በኋላ ወራሹ ንብረቱን በያዘው ሰው ላይ ክስ የማቅረብ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡
በኑዛዜ የተገኘ መብትን ማስፈፀሚያ ክስ የይርጋ ጊዜው ካለፈ ያለኑዛዜ ወራሽ እንደሆነው ሰው ሁሉ መብቱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል፡፡ ኑዛዜ አይጸናም በማለት የሚቀርብ ክስ ወይም በሂሳብ አጣሪው የቀረበውን የድልድልን አመዳደብ ሀሳብ በመቃወም ከስ ለማቅረብ የሚሰጥ መግለጫ ኑዘዜው ከተነበበት አንስቶ የሚቆጠር የ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡ ይህን የተቃውሞ መግለጫ ከተሰጠበት ቀን አንስቶ በ3 ወራት ውስጥ በጽሑፍ ሆኖ ለዳኞች፣ ለውርስ አጣሪው ወይም ጉዳዩ ለመጨረስ ለተመረጡ ሽማግሌዎች ያልቀረበ እንደሆነ ወራሹ የመጠየቅ መብቱን ያጣል፡፡ የኑዛዜ መፅናት እና ስለክፍያው አመዳደብ አጣሪው የሚያቀርበው ሀሳብ ላይ ተቃውሞ ያለ ከሆነ ኑዛዜ ከፈረሰበት ወይም ኑዛዜ በሌለበት ጊዜ ሟች ከሞተ በ5 ዓመት ውስጥ ጥያቄውን ካልቀረበ መብቱ ቀሪ እንደሚሆን የህጉ ቁጥር 973 እና 974 ያስገነዝባሉ፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ አንድ ሰው በሞት ሲለይ ውርስ የሚተላለፍበት ሥርአት ከሞላ ጎደል የተገለፀው ሲሆን የውርስ ባለመብቶች መብትና ግዴታቸውን አውቀው መብታቸውን መጠየቅና ግዴታቸውን መወጣት ይችሉ ዘንድ ያላቸውን የሕግ ግንዛቤ ቢያሳድጉ መልካም ነው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ