መግቢያ
አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠው በኋላ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል የሚባል ከሆነ መሠረታዊ የሕግ ስህተቱ ሳይታረም እንዳይቀር በሰበር ለመታየት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ቀደም ሲል መሠረታዊ የሕግ ስህተት ምንነት የሕግ ትርጉም ያልተሰጠው የነበረ በመሆኑ ጉዳዮች መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለባቸው በሚል በብዛት ሲቀርቡ ይስተዋል ነበር፡፡ ይህን ለማስቀረት አዲሱ የፍርድ ቤቶች አዋጅ መሠረታዊ የሕግ ስህተትን ምንነት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የመሠረታዊ የሕግ ስህተት ምንነትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
የመሠረታዊ የሕግ ስህተት ምንነት
በአዲሱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 2(4) መሠረት “መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት” ማለት
- ሀ. የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን
- ለ. ሕግን አላግባብ የሚተረጉም ወይም ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን ሕግ የሚጠቅስ
- ሐ. ለክርክሩ አግባብነት ያለው ጭብጥ ያልተያዘበት ወይም ከክርክሩ ጋር የማይዛመድ አግባብነት የሌለው ጭብጥ የተያዘበት
- መ. በዳኝነት ታይቶ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ውድቅ የተደረገበት
- ሠ. በፍርድ አፈፃፀም ሂደት ከዋናው ፍርድ ጋር የማይገናኝ ትእዛዝ የተሰጠበት
- ረ. ጉዳዩን አይቶ የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን ሳይኖር ውሳኔ የተሰጠበት
- ሰ. የአስተዳደር አካል ወይም ተቋም ከሕግ ውጭ ውሳኔ የሰጠበት
- ሸ. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትን አስገዳጅ ውሳኔ በመቃረን የተወሰነ
እና ፍትሕን የሚያዛባ ጉልህ የሕግ ስህተት ያለበት የመጨረሻ ውሳኔ፣ ፍርድ፣ ብይን፣ ትእዛዝ ሲሆን መሰል ስህተት ያለባቸው ጉዳዮች በዚህ አዋጅ አንቀጽ 10 መሠረት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚታረሙ ይሆናል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ ማለት በፍርድ ቤት፣ በሕግ የመዳኘት ሥልጣን በተሰጠው አካል፣ በተቋማት ወይም በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች የተሰጠ እና ለጉዳዩ እልባት የሚሰጥ ፍርድ፣ ብይን፣ ትእዛዝ ውሳኔ ሲሆን የይግባኝ ሂደቶችን የጨረሰ ፍርድ፣ ብይን፣ ትእዛዝ ወይም ውሳኔን እንደሚጨምር በአዋጁ አንቀጽ 2(5) ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥልጣን
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥልጣን የመነጨው ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 80(3)(ሀ) ሲሆን መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 10 መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለባቸውን የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይም የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በህገ መንግስቱ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን ፌደራል ጉዳይን አይተው መጨረሻ ውሳኔ የሰጡበት ጉዳይ
የአዲስ አበባ ወይም የድሬደዋ ከተማ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቶች አስገዳጅ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሕግን አለአግባብ ከመተርጎም እና ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን ሕግ ከመጥቀስ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው እና ጉዳዮቹ ለሕዝብ ጥቅም ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ውሳኔዎች በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ተሰጠው አካል ወይም በሌሎች አካላት የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ አግባብነት ያላቸው የሕግ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በፌደራል ፍርድ ቤት ሊታይ ይችል በነበረ ጉዳይ ላይ በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች መሠረት የተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች እንዲሁም በሌሎች ህጎች የተጠቀሱ ጉዳዮች በሰበር አይቶ የማረም ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
አንድ ጉዳይ በሰበር ሲታይ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች ሊሰየሙ እንደሚገባ በአዋጁ አንቀጽ 25(2) ተደንግጓል፡፡ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው ከአንቀጽ 10(2) መረዳት ይቻላል፡፡
ይህን አምስት ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የተሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ሰባት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት በድጋሚ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው በባለጉዳዮች አመልካችነት ወይም በችሎቱ በራሱ አነሳሽነት ቀድሞ የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተለያዩ ምክንያቶች ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በሰባት ዳኞች ችሎት እንዲታ በቂ እና አሳማኝ ምክንያቶችን ተንትኖ በመግለፅ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሲያቀርብ እንደሆነ ከአንቀጽ 26(1) መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ ጥያቄ ሲቀርብ ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩ ሰባት ዳኞች በሚሰየሙበት ችሎት እንዲታይ የሚያደርግ ሲሆን በችሎቱ የሚሰጠው ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በማንኛውም ደረጃ ፍርድ ቤት አስገጃጅ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ከሰባት ያላነሱ ዳኞች የተሰየሙበት የሰበር ችሎት ቀድሞ የሰጠውን የሕግ ትርጉም ከሰባት ባላነሱ ዳኞች በተመሳሳይ ጭብጥ በሌላ ጊዜ ሊሻሻል ይችላል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የሰበር ሥርዓት መሠረታዊ ሕግ ስህተት ያለበት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ የሚታይበትና እና የሚታረምበት የዳኝነት ሂደት ነው፡፡ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ምንነት ደግሞ በአዋጁ የተገለፀ በመሆኑ ለሰበር የሚቀርቡ ጉዳዮች ይህንን ተከትለው መቅረብ አለባቸው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ