የፍቺ አፈፃፀምና ህጋዊ ውጤቶቹ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ጋብቻ በሰው ልጆችን ሁለንተናዊ ክዋኔ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው የተከበረ ማኅበራዊ ተቋም ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ የሚቋቋም ሆኖ ራሱን የቻለ ልዩ የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት ትልቅ የቤተሰብ ብሎም የሀገር መሠረት ነው። ይሁንና ይህ በተጋቢዎች ሙሉ ፈቃድ በመርህ ደረጃ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ ድረስ በአብሮነት ለመዝለቅ የሚመሰረተው ጋብቻ ፍቺን ጨምሮ በተለያየ ምክንያቶች ሊፈርስ ይችላል፡፡ በአገራችን ለጋብቻ ከተሰጡት ልዩ ጥበቃዎች ውስጥም አንዱ ጋብቻ የሚመሠረትባቸው ሰፋ ያሉ መንገዶች ቢኖሩም ፍቺን በተመለከተ ግን በተደነገገው ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት በአስገዳጅነት ተቀምጧል። በዚህም ጋብቻው የተፈፀመው በህጉ ከተመላከቱት የትኛውም አይነት ሥርዓት ቢሆንም የጋብቻው መፍረስ አንዱ መንገድ የሆነው ፍቺን በሚመለከት ግን በአንድ ዓይነት መንገድ የሚመራ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ የፍቺን ምንነት፣ የአፈፃፀም ሁኔታ እንዲሁም ፍቺን ተከትለው የሚመጡ ህጋዊ ውጤቶችን እንመለከታለን።

የፍቺ ህጋዊ ትርጉም

የቤተሰብ ህጉ በአንቀጽ 75 ፍቺን ጨምሮ ጋብቻ የሚፈርስባቸውን ምክንያቶች ያስቀምጥ እንጂ ለፍቺ ቀጥተኛ ትርጉም አልሰጠም። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት “ፍቺ፣ ፈታ”፣ የሚለውን ቃል ሲተረጉም “ትዳሩን አፈረሰ፣ ከሚስቱ ተለያየ፣ በማለት ያስቀምጠዋል። በአጭሩ ፍቺ ትዳር ከሚፈርስባቸው መንገዶች አንዱ ሆኖ ልዩ ልዩ ህጋዊ ውጤቶች ያሉበት ሂደት ነው።

ፍቺ ስለሚፈፀምበት መንገድ

ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ፍፁም ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንደመሆኑ ጋብቻውን በፍቺ ለማፍረስም የተቀመጠ መስፈርት ወይም ምንም ዓይነት ቅድመ-ሁኔታ የለም። በተሻሻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 76 ላይ ጋብቻ በፍቺ ስለሚፈርስባቸው ምክንያቶች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም ጋብቻ በሁለት መንገዶች ማለትም በተጋቢዎች ስምምነት ወይንም በአንዳቸው የአቤቱታ አቅራቢነት በፍርድ ቤት ውሳኔ በፍቺ ሊፈርስ ይችላል።

በስምምነት የሚፈፀም ፍቺ

የመጀመሪያው ፍቺ የሚፈፀምበት መንገድ ባልና ሚስቱ በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ስምምነታቸውንና ፍቺው የሚያስከትለውን ዝርዝር ህጋዊ ውጤት በጽሁፍ ስምምነት ለፍርድ ቤት እንዲፀድቅላቸው ሲያቀርቡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ስምምነት ተቀብሎ ሲያፀድቀው ነው።በስምምነት መፋታት ሲባል እንዲሁ ፈትቼሻለሁ፣ ፈትቼሃለሁ ወይም ተስማምተን ተለያይተናል መባባል ብቻውን በቂ አይደለም። ይልቁን ስምምነቱ በጽሑፍ ሆኖ ሁለቱም ተጋቢዎች ፈርመውበት ዝርዝር ውጤቶቹን ለምሳሌ የንብረት፣ የልጅ ወይም ሌላ መሠረታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር የስምምነት ነጥቦችን ያካተተ መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ተጋብተው ገና ስድስት ወር ያልሞላቸው ተጋቢዎች በስምምነት መፋታት አይፈቀድላቸውም፡፡

በስምምነት የፍቺ ሂደት ወቅት የፍርድ ቤትን ሚና በተመለከተ ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት ባልና ሚስቱን ለየብቻ ወይም በአንድ ላይ በማስቀረብ በፍቺ ጥያቄያቸው ዙሪያ ያነጋግራቸዋል፡፡ አያይዞም የመፋታት ሀሳባቸውን እንዲለውጡ ተገቢውን ጥረት ያደርጋል። ለዚህም ከሦስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ በመስጠት በቀጠሮ ሊያሰናብታቸው ይችላል። ከዚህም ጊዜ በኋላ ሀሳባቸውን በመፋታት ያፀኑ ከሆነ የማሰላሰያው ጊዜ ካበቃበት ቀን አንስቶ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን እንደገና አንቀሳቅሰው የፍቺ ስምምነታቸውን እንዲያፀድቅላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ይህ የ6 ወር ገደብ ባልና ሚስቱ አዲስ ወይም የተሻሻለ የፍቺ ስምምነት እንዳያቀርቡ አያግዳቸውም፡፡ አንቀጽ 79(2)ን ይመለከቷል።

የባልና ሚስቱ የፍቺ ፍላጐት ትክክለኛና ፈቃዳቸውን በነፃ የሰጡ መሆኑ ተረጋግጦ ስምምነቱ ከሕግና ከሞራል ጋር ካልተቃረነ ፍርድ ቤቱ የፍቺ ስምምነቱን ያፀድቀዋል፡፡ ፍቺውን ሲያፀድቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ያደረጉትን ስምምነትም አብሮ ያፀድቃል፡፡ ባልና ሚስቱ ስለፍቺው ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጆቻቸውን ጥቅምና ደኅንነት በበቂ ሁኔታ የማያስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጐዳ ሆኖ ካገኘው ፍርድ ቤቱ ፍቺውን ብቻ አፅድቆ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹ እንዲስተካከሉ ተገቢ መሰሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር ማንኛውም ፍቺን የሚጠይቅ ወገን ለመፋታት የወሰነበትን ምክኒያት እንዲገልጽ ግዴታ የሌለበት መሆኑ ነው።

በአቤቱታ አቅራቢነት በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚፈፀም ፍቺ

ሌላኛው ፍቺ የሚደረግበት ዘዴ ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም በአንድነት በመሆን የፍቺ ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርድ ቤቱ የፍቺውን ውጤት እንዲወስንላቸው ሲጠይቁ የሚሰጥ የፍቺ አይነት ነው፡፡ በዚህ አይነት የፍቺ መንገድም ፍርድ ቤቱ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር አለመግባባቱን በስምምነት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያግባባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በአንቀጽ 82 ላይ እንደተደነገገው ፍርድ ቤቱ ሰፋ ያለ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን ይህም ሽማግሌ የመሰየም ወይም ባልና ሚስቱ ራሳቸው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች ከፍርድ ቤት ውጭ ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ ሊጠይቃቸው ይችላል፡፡ ይህ ካልተሳካ አሁንም ከሦስት ወር ያልበለጠ የማስላሰያ ጊዜ በመወሰን ሊያስናብታቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ጥረቶች ተደርገው የአስታራቂ ሽማግሌዎች ሪፖርት ከደረሰው ወይም ለተጋቢዎች የተሰጠው የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ ፍርድ ቤት በአንድ ወር ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

የፍቺ ጥያቄ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ ባልና ሚስቱ ስለሚተዳደሩበትና ስለሚኖሩበት ሁኔታ፣ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ ስለሚኖሩበት ስፍራና ሰለአኗኗራቸው እንዲሁም ስለንብረታቸው አስተዳዳር ተገቢ መሰሎ የታየውን ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ከሁለቱ ተጋቢዎች የአንዳቸው ከጋራ መኖሪያቸው መውጣት የግድ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ የጋራ መኖሪያቸውን ለቆ ቢወጣ የባሰ ጉዳት የሚደርስበት ወገን የትኛው መሆኑን እንዲሁም የልጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ አመቺ የሚሆነውን ሁኔታ ሁሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡

በፍቺ ጥያቄ መሠረት ጋብቻው የፈረሰ እንደሆነ በፍቺው ውጤት ላይ እንዲስማሙ ፍርድ ቤት ባልና ሚስቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ የፍቺው ውጤት በስምምነት በሚያልቅበት ወይም በሽማግሌዎች ወይም በባለሞያዎች በሚወስንበት ጊዜ ውሳኔው ተፈፃሚነት የሚኖረው ለፍርድ ቤቱ ቀረቦ ተቀባይነት ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ የማይሰማሙ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በራሱ ወይም በሽማግሌዎች ወይም ፍርድ ቤቱ በሚሾማቸው ባለሙያዎች አማካኝነት ወይም አመቺ መስሎ በሚታየው በማናቸውም ዘዴ የፍቺውን ውጤት መወሰን አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍቺውን አስቀድሞ በመወሰን የፍቺውን ውጤት በተመለከተ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደሁኔታው ከፍቺ በኋላ ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊያዘገየው ይችላል፡፡ የፍቺው ምክንያት የሆነውን በደል ከተጋቢዎቹ አንዱ የፈፀመ እንደሆነ በሌላው ተጋቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በዳዩ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ሊወስን እንደሚችል በአንቀጽ 84 ላይ ተደንግጓል።

የፍቺ ውጤቶች

ፍቺ ከላይ በተመለከትናቸው ሁለት መንገዶች በሚፈፀም ጊዜ ሁለት አይነት የተለመዱ ውጤቶችን የሚያስከትል ሲሆን ውጤቶቹም በንብረትና በልጆች ላይ የሚኖር ውጤትን ማለታችን ነው።

ፍቺ በንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት

በመሰረቱ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ የንብረትና ሌሎች ጉዳዮችን ተጋቢዎቹ ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ወቅት ወይም ከዛ በኋላ ባለ ጊዜ በሚገቡት የውል ስምምነት መሠረት የሚመራ እንደሚሆን የህጉ አንቀጽ 42 አስቀምጧል። ይሁንና ጋብቻው በፍቺ ከፈረሰ በኋላ በንብረታቸው ላይ ያለውን ውጤት በጋብቻ ውላቸው ላይ ያላስቀመጡ ከሆነ ባልና ሚስቱ የየግል ንብረታቸውን መልሰው ይወስዳሉ፡፡ የጋራ ሀብታቸው ደግሞ ለሁለቱም እኩል የሚከፋፈል ይሆናል፡፡

በጋብቻ ውስጥ የግልና የጋራ ሐብት ምንነት

የጋብቻ መመስረት በጠባብ ሁኔታም ቢሆን ተጋቢዎቹ የግል ንብረታቸውን ይዘው ከመቀጠል አያግዳቸውም። ተጋቢዎቹ በጋብቻቸው ቀን ወይም ከተጋቡ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በግል ስማቸው ያገኙት ንብረት የግል ሀብት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በዚህም በፍቺ ጊዜ ወይም ጋብቻቸው በሚፈርስበት ጊዜ ባልና ሚስቱ የግል ሀብት መሆኑን በማስረዳት የግል ንብረታቸውን መልሶ የመውሰድ መብት ይኖራቸዋል (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 57፣ 86(1))፡፡

በመርህ ደረጃ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ለሁለቱም እኩል የሚከፍፈል ሲሆን እያንዳንዱ ተጋቢ ከጋራ ሀብቱ የተወሰነ ንብረት እንዲደርሰው በማድረግ የጋራ ሀብቱ በዓይነት እንዲከፍፈል ይደረጋል፡፡ ይሁንና እኩል ለማከፋፈል የማይቻል ሆኖ ከተገኘ ልዩነቱ በገንዘብ እንዲካስ ይደረጋል፡፡ የሀብት ክፍፍሉ በሚደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ተጋቢ ይበልጥ ጠቃሚነት ያላቸውን ንብርቶች እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት መድረግ ይኖርበታል፡፡ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 91)

የጋራ ንብረቱ ለክፍፍል የማያመች ወይም ለማከፍፈል የማይቻል ከሆነና ንብረቱ ለአንዳቸው እንዲሰጥ ለማስማማት ካልተቻለ ንብረቱ ተሽጦ ገንዘቡን እንዲከፋፈሉ ይደርጋል፡፡ ስለአሻሻጡ ሁኔታ የማይስማሙ እና አንደኛው ጥያቄ ያቀረበ ከሆነ ሽያጩ በጨረታ የሚፈፀም ይሆናል፡፡

(የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 92)

ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳው እዳ ሲሆን ጋብቻው ፈርሶ ንብረቱ ከተከፋፊለ በኋላ የሚጠየቅ ዕዳ በጋራ መከፈል የነበረበት ከሆነ ሁለቱም በየድርሻቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ ከቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 93(1) መረዳት ይቻላል፡፡ በአንፃሩ ዕዳው አንደኛውን ተጋቢ ብቻ የሚመለከት ከሆነ በአንቀጽ 93(2) መሠረት ባለዕዳ የሆነው ተጋቢ ብቻ እንዲከፍል ይጠየቃል፡፡ የግልና የጋራ እዳን አስመልክቶ የህጉ አንቀጽ 70-71 ባሉት ስር የተመላከተ ሲሆን በዚህም ማንኛውም በጋብቻ ውስጥ ያለ እዳ የጋራ ነው ሊባል የሚችለው ለቤተሰቡ የእለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት የተገባ፣ ባል ወይም ሚስት እርስ በእርስ ያለባቸውን ቀለብ የመስጠት ግዴታ ለመወጣት ወይም ከባልና ሚስት በአንደኛው ወይም በእዳ ጠያቂው አመልካችነት ለትዳር ጥቅም ስለመሆኑ ፍርድ ቤት የተቀበለው እዳ እንደሆነ በህጉ ተመልክቷል።

የጋብቻ መፍርስ በልጆች ላይ የሚኖረው ውጤት

የጋብቻ መፍረስ ከሚያስከትለው ትልቁና አሳሳቢው የሕግ ጉዳይ የልጆች ቀጣይ የአስተዳደግ እና የኑሮ ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ የጋብቻ መፍረስ ውጤት በተቻለ መጠን የልጆችንም ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍቺን በሚወስንበተ ጊዜ ልጆች ከማን ጋር ሊኖሩ እንደሚገባ፣ ስለትምህርታቸውና ስለጤናቸው አጠባበቅ፣ ስለቀለባቸውና በአጠቃላይም ስለአኗኗራቸው እንዲሁም ወላጆችና ልጀች ለመጠየቅ ስላላቸው መብት መወሰን አለበት፡፡ ይህን ውሳኔ ሲያደርግ የወላጆችን የገቢ ሁኔታ፣ የልጆችን ዕድሜ፣ የጤና እና የአኗኗር ሁኔታ እንዲሁም ፍላጐታቸው የሚጠበቅበትን ሁኔታ ማገናዘብ ይኖርበታል፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሁኔታዎች ሲለወጡና ውሳኔው እንዲሻሻል ጥያቄ ሲቀርብ ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ ይችላል፡፡

ማጠቃለያ

ጋብቻ ህጋዊ ጥበቃ የተሰጠው ተቋም እንደመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ በቆይታው እንዲሁም በሚፈርስበት ጊዜ ሕግን ተከትሎ መሆን የሚገባው ሲሆን ጋብቻ በፍቺ የሚፈርስ ከሆነም በተጋቢዎች ግላዊና ንብረት ነክ ግንኙነቶች ረገድ የሚያስከትለው ውጤት ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ በፍርድ ቤት ሊወሰን ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ