ወንጀሎች ክብደታቸውን እና የሚያስከትሉትን ጉዳት መነሻ በማድረግ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ እና በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስከስሱ (የግል አቤቱታ የማያስፈልጋቸው) ተብለው በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የወንጀል ዓይነቶች በክብደታቸው፣ በሚያስከትሉ ጉዳት መጠን እንዲሁም ከወንጀል ጥቆማ ጀምሮ እስከ ክርክር ሂደት ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ይኸውም:-
- በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎች በባህሪያቸው ቀላልና ጉዳታቸው በግለሰቦች ላይ ተወስኖ የሚቀር ሲሆን በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስጠይቁት ግን ከባድ፣ ውስብስብና ከግለሰብ አልፈው በሕዝብና በሀገር ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስድብ፣ ዛቻ፣ ስም ማጥፋትና የመሳሰሉት በተበዳይ የግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ ወንጀሎች ሲሆኑ ውንብድና፣ ሽብርተኝነት፣ ሙስና፣ ግድያና የመሳሰሉት ወንጀሎች ደግሞ በወንጀል ክስ አቅራቢነት (በማንኛውም ሰው ጠቋሚነት) የሚያስከስሱ ወንጀሎች ናቸው፡፡
- በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጣ መሆኑ በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ወይም በሌላ ማሟያ የወንጀል ሕግ ተደንግጎ በተገኘ ጊዜ በግል ተበዳይ ወይም በሕጋዊ ወኪሉ አቤቱታ ካልቀረበ በቀር የወንጀል ክስ ማቅረብ እንደማይቻል በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 212 ስር ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል በባህሪያቸው ከግላዊ ይልቅ ህብረተሰባዊ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ፣ የህብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎችን በሚመለከት ጥቆማዎችንና መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል መስጠት የሁሉም ዜጎች መብትም ኃላፊነትም ነው፡፡ ሆኖም ከባድ ወንጀሎችን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ግዴታ ሆኖ የሚደነገግባቸው ሁኔታዎችም አለ፡፡ ለአብነትም የሽብር ወንጀልን በተመለከተ ያወቀውን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ግዴታ ሲሆን ይህን ግዴታ አለመወጣት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 15 መሠረት የወንጀል ተጠያቂነት የሚስከትል ነው፡፡
- ሌላው ልዩነት በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎች በዕርቅ ሊቋረጡ የሚችሉ ሲሆን በማንኛውም ሰው በሚቀርቡ ጥቆማዎች መሠረት በተመሰረተ ክስ ግን የበዳይና ተበዳይ መታረቅ ቅጣት ሲጣል በማቅለያነት ከሚያዝ በስተቀር ክስ ሊያቋርጥ አይችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ክስ ቀጣይነት በተበዳይ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስጠይቁት ግን የተበዳይ ፍላጎት ተፅኖ አያሳድርባቸውም፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ