የወጭና ኪሳራ አወሳሰን በፍትሐብሄር ክርክር

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ሕግ በቀጥታ ትርጉም ያልተቀመጠለት ቢሆንም ከድንጋጌዎቹ ይዘት መረዳት የሚቻለው ወጭ እና ኪሳራ ማለት አንድ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት በመሄዱ ምክንያት በፍርድ ቤት መዝገብ ከመከፈቱ በፊት ክስ ከማዘጋጀት ጀምሮ ፍ/ቤት መዝገቡ ከተከፈተ በኋላ ባሉ በተለያዩ የክርክር ደረጃዎች የሚወጡ ክፍያዎችን የሚያጠቃልል ሲሆን እንደ ጉዳዩ ዓይነት መጠኑ እና ይዘቱ ሊለያይ ይችላል። ስለሆነም በዋናነት ይህ ክርክር የሚነሳው ዋናው ጉዳይ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ሲሆን በተከራካሪ ወገኖች መካከል በነበሩ ክርክሮች የወጡ ወጭዎችን ማን ይሸፍናል፣ እንዴት ይሸፈናሉ የሚለውን ያካትታል። የኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ሕግ ወጭ እና ኪሳራ የመወሰንን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለፍርድ ቤቶች የሰጠ መሆኑን ከስነ-ስርዓት ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት መረዳት ይቻላል። በዚህ አጭር ጽሁፍ በፍትሐብሄር ክርክር የወጭ እና ኪሳራ ምንነት፣ የመወሰን ሥልጣን፣ ለማን እንደሚወሰን የፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ህጉን እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያወጣውን የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መምሪያ ቁጥር 2/2017ን መሠረት በማድረግ አጠር ባለ መልኩ የሚዳሰስ ይሆናል።

የወጪ እና ኪሳራ ምንነት

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሁፍ ጥናትና ምርምር ማዕከል (1993) ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ወጭ ማለት ለተለያየ ጉዳይ የተከፈለ ወይም ለስራ ወይም ለኑሮ አስፈላጊ የሆነ ገንዘብ እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን። ይኸዉ መዝገበ ቃላት ኪሳራን ከወጭ ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም ሰጥቶት አናገኛለን። በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መምሪያ ቁ.2/2017 አንቀጽ 2(2) መሠረት ወጭ እና ኪሳራ ማለት በፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት ለማግኘት ሲባል ባለጉዳዩ በቀጥታ ያወጣቸው ወጭዎች፣ የፈጸማቸው ክፍያዎች ወይም በቀጥታ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በክርክሩ ምክንያት የደረሰበትን የገንዘብ ወጭ የሚያካትት ሆኖ የተለያዩ ግልባጭ መስጠት፣ የፍ/ቤት ትእዛዝ ወጭ ማድረግ፣ የሚፈለገውን መረጃ ለተገልጋይ መስጠት እና ሌሎች ከችሎት ስራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተግባራት እንደሚያካትት ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን። በኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ሕግ ወጪና ኪሳራን በተመለከተ ቀጥተኛ ትርጉም ባይቀመጥለትም ከድንጋጌዎቹ አጠቃላይ ይዘት (አንቀጽ 462-466) የምንረዳው በክርክር ምክንያት የሚወጡ ክፍያዎችን የሚያጠቃልል መሆኑን ነው። ለምሳሌ ለዳኝነት ክፍያ/Court fee/፣ የጠበቃ አገልግሎት ክፍያ/Advocate fee/፣ ከማስረጃ ጋር ለተያያዙ ወጪዎች ለምሳሌ ባለሙያ የሚያስፈልገዉ ክስ ከሆነ ለባለሙያ ምስክር/expert witness/፣ በችሎት ሂደት አስተርጓሚ የሚያስፈልግ ከሆነ ለአስተርጓሚ የሚከፈል ክፍያ፣ የምስክር አበል (ለምስክር የሚከፈል የትራንስፖርት፣ የማረፊያ እና የቀን አበልን የሚያጠቃልል) ክፍያዎችን እና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎችን ለምሳሌ ሰነዶችን ኮፒ ለማድረግ የሚወጣ ወጪ፣ ከፍርድ ቤት ክርክር ጋር የተያያዘ የትራንስፖርት ወጪዎችን ያጠቃልላል።

ወጭ እና ኪሳራን የመወሰን ሥልጣን እና ስለሚከፍለው ተከራካሪ ወገን

በፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ሕግ ያለዉ መርህ ‘ወጪ ተሸናፊን ይከተላል’ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 463) የሚል ሲሆን በመርህ ደረጃ በክርክሩ የተሸነፈው ወገን ለአሸናፊ ወገን በአጠቃላይ ያወጣቸውን ወጪዎች እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል። ወጪ እና ኪሳራን የመወሰን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ የፍርድ ቤቶች እንደሆነ በፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ህጉ አንቀጽ 462 ተደንግጎ እናገኛለን። በዚህ ድንጋጌ የፍርድ ቤቱ ሥልጣን ወሰንን በተመለከተ እንደሚከተለዉ ተቀምጧል፡-

  • በክስ ምክንያት ስለሚከፈለው ማናቸውም ወጪና ኪሳራ፣
  • ወጪና ኪሳራውን ስለሚከፍለው ወገን፣
  • የወጪና ኪሳራውን ልክ(መጠን)፣
  • ወጪና ኪሳራው የሚከፈልበትን የሃብት ምንጭ፣
  • የአከፋፈሉን ሁኔታ፣
  • እንዲሁም ሌላ ተገቢ መስሎ የታየዉን ዉሳኔ ወይም ትእዛዝ እንደሚሰጥ ተደንግጓል።

ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ባወጣው የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መምሪያ ቁጥር 2/2017 አንቀጽ 7 መሠረት የወጭ እና ኪሳራ መጠን ተከታዮችን ነጥቦች እንደሚያካትት ተደንግጓል፣ ይኸውም፡-

  • በክርክሩ የተገኘ መብት ንጽጽር፣
  • የክሱ ዓይነት፣ ክብደት፣ ውስብስብነት እና የወሰደው ጊዜ፣
  • የተከራካሪ ወገን የአቤቱታ ቀራረብ ስርዓት፣ ጥራት እና ዲሲፕሊን፣
  • የቀረበው ክስ ምክንያታዊነት እና ያልተጋነነ መሆን፣
  • ተከራካሪው ወገን በእርቅ ወይም በስምምነት ጉዳዩን ለመጨረስ ያሳየው ጥረት እና ፍላጎት፣
  • የተከራካሪ ወገን ልዩ ሁኔታ፣ እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ደረጃቸው ከግንዛቤ ውስጥ ገብተው እንደሚወሰኑ ተቀምጧል።

የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መርሆች

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2017 አንቀጽ 5 ስር የወጭና ኪሳራ አወሳሰን መርሆችን የዘረዘረ ሲሆን እነዚህም፡-

  • ፍርድ ቤቶች ወጭና ኪሳራን ሲወስኑ ፍትሀዊነቱን ማረጋገጥ እና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ መሆኑን የማረጋገጥ፣
  • ተከራካሪዎች በተቻለ መጠን ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ክርክራቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ፣
  • ከደረሰው ኪሳራ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የወጭ ዝርዝር እንዲቀርብ ማድረግ፣
  • የጉዳዩን ዓይነት፣ ዉስብስብነት እና የወሰደውን ጊዜ ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ መወሰን፣
  • ወጭና ኪሳራ ላይ የሚሰጥ ውሳኔ በማስረጃ የተረጋገጠ፣ ምክንያታዊ እና በመዝገቡ በአግባቡ መጻፍ እንዳለበት የሚገልጹ ናቸው።

የወጭ እና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ ግዴታ

ተረቺው ለረቺው ወገን ኪሳራና ማናቸውንም ወጭ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ሲያዝ ወጭ ያወጣው ወገን የወጭውን መጠን የሚያሳይ ዝርዝር ማቅረብ ይጠበቅበታል። ይህ የወጭ ዝርዝር የሚቀርበዉ ዉሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት ሲሆን ግልባጩ ለተረቺው ወገን (ወጭውን ለሚሸፍነው ወገን) እንዲደርሰው እንደሚደረግ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 463 ተደንግጎ እናገኛለን።

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መምሪያ አንቀጽ 4 መሠረት ረቺ ሲባል በፍርድ ቤት በተደረገ ክርክር ላይ በፍርድ፣ በውሳኔ፣ በብይን ወይም በትእዛዝ ያሸነፈ፣ የተፈረደለት ወይም የቀረበበት ክስ ውድቅ የሆነለት ወገን ወይም ያቀረበው የዳኝነት ጥያቄ በከፊል ወይም በሙሉ ተቀባይነት ያገኘለት ወገን እንደሆነ ተመላክቷል። ስለሆነም ከዚህ ትርጓሜ እንደምንረዳው በማንኛውም የፍ/ቤቱ የክርክር ሂደት ላይ ለምሳሌ ቀጠሮ ባለማክበር ኪሳራ እንዲከፈል የሚሰጥ ትእዛዝን ጨምሮ የወጭ እና ኪሳራ ዝርዝር ውስጥ የሚካተት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የወጭ እና ኪሳራ ሂሳብ ስለሚመረመርበት ሁኔታ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 464)

የወጭ ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ በቀረበ ጊዜ

የወጭው ሂሳብ ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ወጭው የሚመረመርበትን የቀጠሮ ቀን ወስኖ ባለጉዳዮቹ እንዲቀርቡ ያዛል። ይህ ምርመራ የወጭው ዝርዝር በማስረጃ የተረጋገጠ እና ምክንያታዊ መሆኑ የሚረጋገትበት ሂደት ነው። ፍርድ ቤቱ ሂሳቡን ከመረመረና የተከራካሪዎቹን ሃሳብ ከተቀበለ እና በማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ ተከታዮችን ትዕዛዞች ይሰጣል፡-

  • በቀረበው የሂሳብ ዝርዝር ውስጥ በቂ ባልሆነ ምክንያት ከፍ ብሎ የተገኘውን ይቀንሳል፣
  • በዝርዝሩ ውስጥ የክሱን ጉዳይ ለማስፈጸም ወይም አስፈላጊውን ዳኝነት ለመከታተል ተገቢ ያልሆነ ወጭ ተመልክቶበት ከተገኘ ሊቀንሰው ወይም ሊያስቀረው ይችላል። (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 464 (1) ፣ (2))

የወጭ ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ ባልቀረበ ጊዜ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 464(3-5))

ወጭው ወይም ኪሳራው ሊከፈለው የሚገባው ተከራካሪ ወገን የሚጠይቀውን የወጭ ዝርዝር ባላቀረበ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ይህንን መዝግቦ፡-

  • ሌሎች ተከራካሪ ወገኖች/ወጭ እና ኪሳራ ሊከፍሉ የሚገባቸው ተከራካሪ ወገኖች/ ያወጡትን ወጭ መርምሮ ያረጋግጥላቸዋል፣
  • የሂሳቡን ዝርዝር አንዱ ወገን/ወጭ እና ኪሳራ ሊከፈለው የሚገባው ተከራካሪ ወገን/ ባለማቅረቡ ምክንያት ሌሎቹ ወገኖች እንዳይጎዱ ላላቀረበው ወገን ተገቢ ግምት ያለው ኪሳራ ይወሰንለታል።

ማናቸውም የወጭ ወይም የኪሳራ ገንዘብ በፍርዱ መሠረት እስኪፈጸም ድረስ ዋናው ፍርድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በሕግ የተወሰነ ወለድ ይታሰብበታል። በሕግ የተወሰነ ወለድ ማለት በፍትሐብሄር ህጉ አንቀጽ 1751 እንደተደነገገው 9% (ዘጠኝ በመቶ) ነው። ፍርድ ቤቱ በኪሳራና ወጭ አከፋፈል ምክንያት ለተነሳው ክርክር ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ወይም የመዝገብ ቤት ሹም የቀረበውን ዝርዝር መርምሮና ተከራካሪዎቹ የሚያቀርቡትን ሃሳብ ተቀብሎ የተጣራውን ሂሳብ እንዲያቀርብለት ማዘዝ ይችላል።

ካሳ ስለሚከፈልበት ሁኔታ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 465)

በማናቸውም ክስ ወይም ክርክር ላይ በክስ ወይም በመከላከያ መልክ ከሳሹ ወይም ተከሳሹ ያቀረበው የመከራከሪያ ወይም የመከላከያ ማስረጃ፡-

  • ክሱ፣ ክርክሩ ራሱ ወይም ማስረጃው ሀሰተኛ ነው፣
  • መከራከሪያውንና ማስረጃውን ያቀረበው ወገን በሐሰት የተከራከረዉና ሀሰተኛ ማስረጃ ያቀረበው ክርክሩን ለማሰናከል፣ ጊዜ ለመፍጀት፣ አንደኛውን ወገን ለመበደል፣ ለማጉላላት ሆን ብሎ ያደረገው ነዉ በማለት፣
  • የክርክሩን ወይም ማስረጃውን ሀሰተኛነት እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሆነ ብሎ ማቅረቡን ሲያመለክት፣

ፍርድ ቤቱ ተቃዋሚው ወገን ያቀረበውን ነገር እርግጠኛነት ካረጋገጠ በኋላ ሀሰተኛ ማስረጃ ወይም መከራከሪያ ያቀረበው ወገን ለእያንዳንዱ ላቀረበው ሀሰተኛ ማስረጃ ለተቃዋሚው ወገን ከአምስት መቶ ብር (500.00) ያልበለጠ ካሳ እንዲከፍል ትእዛዝ የመስጠት ሥልጣን እንዳለው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 465(1) ተመላክቷል። ይህ ወገን ካሳ መክፈሉ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 452 በሰጠው ሀሰተኛ ቃል ከመጠየቅ ነጻ እንደማይሆን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 465(2) ተደንግጎ እናገኛለን። በዚህ ድንጋጌ መሠረት ካሳ የተወሰነለት ወገን በሐሰት በመከሰሱ ወይም ሀሰተኛ መከላከያ ወይም ክስ የቀረበበት በመሆኑ ካሳና ኪሳራ ይገባኛል ሲል ሌላ ክስ በማቅረብ ካሳ ወይም ኪሳራ የተወሰነለት እንደሆነ በመጀመሪያው ክስ የተወሰነለት ካሳ በሌላው ክስ ላይ ከሚወሰንለት ካሳና ኪሳራ ላይ ይቀነስበታል (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 465(3)) ።

ወጭ እና ኪሳራ ስለሚወሰንበት የክርክር ደረጃ እና የሚስተናገድበት መዝገብ

ወጭ እና ኪሳራ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በይግባኝ ወይም በሰበር ደረጃ ባለ የክርክር ሂደት በየደረጃዉ ሊወሰን ይችላል። በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የወጭ እና ኪሳራ አወሳሰን መምሪያ ቁ.2/2017 አንቀጽ 6/1/ መሠረት ወጭ እና ኪሳራ ላይ የሚሰጠው ለክርክሩ መነሻ በሆነው በዋናው መዝገብ ላይ እንደሆነ ተደንግጓል። በዚሁ መምሪያ አንቀጽ 6/2/ ላይ ከፍርድ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ለፍርዱ ማስፈጸሚያ የሚውል የወጭ እና ኪሳራ ጥያቄ በአፈጻጸም መዝገቡ ላይ ይቀርባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ልብ ሊባል የሚገባው በፌዴራል ደረጃ ፍርድ አፈጻጸም ፅ/ቤት/ዳይሬክቶሬት ከማስፈጸም ባለፈ ይህንን ጉዳይ የማስተናገድ ሥልጣን የለውም።

ከላይ በተጠቀሰው መምሪያ በአንቀጽ 18 ስር በይግባኝ ችሎት ደረጃ ለሚታይ ጉዳይ ወጭ እና ኪሳራ ስለሚወሰንበት ሁኔታ የሚዘረዝር ሲሆን እነዚህም፡-

  • በይግባኝ ደረጃ ወጭ እና ኪሳራ የሚወሰነው በይግባኝ ምልልስ ሂደት ውስጥ ወጭ እና ኪሳራ መድረሱ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ፣
  • የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሻር ወይም የሚሻሻል ከሆነ በይግባኝ ደረጃ ከደረሰው በተጨማሪ በስር ፍርድ ቤት የደረሰው ወጭ እና ኪሳራ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት፣
  • በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን ወጭ እና ኪሳራ ከተወሰነ በኋላ በይግባኝ ደረጃ ውሳኔው ተሽሮ በድጋሚ እንዲጣራ በነጥብ ተመልሶ እንደሆነ ወይም ውሳኔው የተመለሰው በስር ፍርድ ቤት አተረጓጎም ተቀባይነት አለማግኘት እንደሆነ ተከራካሪ ወገኖች የየራሳቸውን ወጭ እና ኪሳራ እንዲችሉ እንደሚወሰን፣
  • ውሳኔው ተሽሮ በድጋሚ እንዲጣራ በነጥብ የተመለሰው ከተከራካሪ ወገኖች መካከል በአንዱ ወገን ምክንያት ከሆነ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በይግባኝ ደረጃ ብቻ ወጭ እና ኪሳራ እንደሚወስን፣
  • በይግባኝ ታይቶ በነጥብ የተመለሰለት የስር ፍርድ ቤት ክርክሩን በተመለከተ የደረሰውን ወጭ እና ኪሳራ እንዲሁም ከተከራካሪ ወገኖች የሚቀርበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ምክንያቱን በማስቀመጥ እንደሚወስን ተቀምጧል።
  • ከላይ የተጠቀሰው መምሪያ በአንቀጽ 19 ስር ስለወጭ እና ኪሳራ በሰበር ደረጃ የሚወሰንበትን መስፈርት የዘረዘረ ሲሆን፣ እነዚህም፡-
  • የስር ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ ከጸና በሰበር ችሎቱ ደረጃ ብቻ የደረሰውን ወጭ እና ኪሳራ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሚወሰን፣
  • የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከተሻረ ወይም ከተሻሻለ በስር ፍርድ ቤቶች የተወሰነው የወጭ እና ኪሳራ ውሳኔ እንዲሁም የነበረውን ክርክር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በሰበር ክርክር የነበረውንም ጨምሮ ወጭ እና ኪሳራ እንደሚወሰን፣
  • በሰበር ደረጃ የወጭ እና ኪሳራ ዝርዝር ረቺው እንዲያቀርብ ትእዛዝ ተሰጥቶ ከሆነ በረዳት ዳኛ ወይም ሬጅስትራር ተጣርቶ እንዲቀርብ ችሎቱ ውሳኔ መስጠት እንደሚችል፣
  • መዝገብ እንዲጣራ ወደ ስር ፍርድ ቤት እንዲመለስ ትእዛዝ ተሰጥቶ ከሆነ በሰበር ደረጃ የደረሰውን ወጭ እና ኪሳራ በተመለከተ ዉሳኔ ተሰጥቶ ስለአፈጻጸሙ ከመመሪያ ጋር እንደሚመለስ ተቀምጧል።

ስለይግባኝ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 466)

ማናቸውም ተከራካሪ ወገን በስረ ነገሩ ላይ ይግባኝ ባያቀርብም በተወሰነበት የወጭ ወይም ኪሳራ አከፋፈል ብይን ላይ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ይችላል። በዚህ ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ እንደሆነ ተደንግጓል።

ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ስነ-ስርዓት ሕግ ወጭና ኪሳራ የመወሰን ፍቅድ ሥልጣን/discretion/ ለፍርድ ቤቶች የተሰጠ ሲሆን ፍርድ ቤቶች ይህን ፍቅድ ሥልጣን ሲጠቀሙ ምክንያታዊ፣ ወጭ ቆጣቢ፣ ፍትሃዊ እና በማስረጃ የተረጋገጠ ሂደትን መከተል ይገባቸዋል። ተገልጋዮችም የወጭና ኪሳራ ዋና ዓላማ በክርክር ሂደት የወጡ ወጭዎችን መካስ መሆኑን ተገንዝበው የተጋነነ እና ምክንያታዊ ያልሆነ የወጭ ዝርዘር ሲቀርብ ይህንኑ በመቃወም ለፍትሀዊ የወጭና ኪሳራ አወሳሰን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ