በሥራ ቦታ ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ትንኮሳ ምንነትና የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ማውጫ

Share this Article

በሥራ ቦታዎች ጾታዊ ትንኮሳዎች በአብዛኛው በሴቶች ላይ እንደሚፈፀሙ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም በፈፃሚዎች በኩል ድርጊቱ በተለምዶአዊ ሁኔታ ትክክል እንደሆነ አድረጎ የመውሰድና በተጎጂዎችም በኩል ድርጊቶቹ ጾታዊ ትንኮሳ መሆናቸውን ተረድቶ መፍትሄ የመፈለግ ውስንነቶች ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ለጾታዊ ትንኮሳ የተሰጠውን ትርጓሜ እና የሚስከትለውን ተጠያቂነት በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

የጾታዊ ጥቃት ምንነት

በሀገራችን ሰራተኞች አስመልክቶ በፌደራል ደረጃ የወጡ ሁለት አዋጆች ያሉ ሲሆን እነዚህም የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ናቸው፡፡ የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ እራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ በተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት በሚተዳደር የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በቋሚነት በሚሰሩ ሰራተኞች (በልዩ ሁኔታ እንደማይፈፀምባቸው ከተገለፁት ውጪ) ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው፡፡ በሥራ ቦታ ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ ትንኮሳ በተመለከተ በሁለቱም አዋጆች በዝርዝር ተካቶ ይገኛል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 በአንቀጽ 2/11 እና 12 መሠረት “ወሲባዊ ትንኮሳ” ማለት በንግግር፣ በምልክት ወይም በሌላ ማናቸውም አድራጎት አንዱ ሌላውን ከፈቃዱ ውጭ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባበል፣ መገፋፋት፣ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፡፡ እንዲሁም “ወሲባዊ ጥቃት” ማለት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም የዚሁ ድርጊት ሙከራ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶት ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ለጾታዊ ትንኩሳ ትርጉም ከመስጠት ባሻገር ዝርዝር ተግባራትን እና ድርጊቶቹን ለማስፈፀም እንደቅድመ ሁኔታ ሊገለፁ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀምጧል፡፡ ይኸውን በአዋጁ አንቀጽ 2/13 ሥር እንደተደነገገው “ጾታዊ ትንኮሳ” ማለት በሥራ ቦታ የሚፈፀም ሆኖ ከሌላው ወገን ፈቃድ ውጪ የሚቀርብ የወሲብ ሀሳብ ወይም ጥያቄ ወይም ሌላ ወሲባዊ ተፈጥሮ ያለው የቃል ወይም የአካል ንኪኪ ተግባር ሲሆን ይህም

  • ከሌላው ወገን ፈቃድ ውጪ የመሳም፣ የሰውነት አካልን የመዳሰስ፣ የመጎንተል ወይም የመሳሰለውን የሰውነት ንክኪ የመፈፀም ድርጊት
  • ወሲብ አዘል በሆነ ሁኔታ ተጠቂውን መከታተል ወይም እንቅስቃሴውን መገደብ
  • ለቅጥር፣ ለደረጃ እድገት፣ ለዝውውር፣ ለድልድል፣ ለሥልጠና፣ ለትምህርት፣ ለጥቅማ ጥቅሞች ወይም ማንኛውንም የሰው ሀብት ሥራ አመራር ተግባር ለመፈፀም ወይም ለመፍቀድ ወሲብን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥን ያካትታል፡፡

ጾታዊ ትንኮሳ የሚያስከትለው ተጠያቂነት

በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር በአዋጁ አንቀጽ 14 ሥር እንደተደነገገው በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ከተከለከሉ ተግባራት አንዱ ሲሆን ሠራተኛው (ወንድም ሆነ ሴት) በአሠሪው ወይም በሥራ መሪው ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት የተፈፀመበት እንደሆነ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውልን ለማቋረጥ የሚያስችል አንዱ ምክንያት ነው (የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 አንቀጽ 32/1/ለ)፡፡ ይኸውም ሠራተኛው ለተፈፀመበት ጥቃት እንደ ጥቃቱ አይነት አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ መብቱን ማስከበር የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሠራተኛው የሥራ ውሉን በሚያቋርጥበት ወቅት ተገቢውን ካሳ ማግኘት ያስችለዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 41/2 ሥር እንደተገለፀው ሠራተኛው ሥራውን ለማቋረጥ የተገደደው በተፈፀመበት ጾታዊ ትንኮሳ ሳቢያ ከሆነ ከሥራ ስንብት ክፍያው በተጨማሪ የቀን ደመወዙ በ90 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡

በተያያዘ በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 70/13 እና 69 ሥር እንደተደነገገው በሥራ ቦታ ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ከሚያስከትሉ ጥፋቶች አንዱ ሲሆን እስከ 3 ወር ደሞዝ የሚደርስ መቀጮ፣ እስከ 2 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደሞዝ ዝቅ ማድረግ ወይም ከሥራ እስከመሰናበት የሚደርስ ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 የጾታዊ ትንኮሳን ትርጓሜ በመደንገግ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት በግልፅ ያስቀመጡ በመሆኑ ፈፃሚዎች በአዋጆቹ የተመለከቱ እርምጃዎች የሚወሰዱባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ የሚያስጠይቁ ተግባራት በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም ህብረተሰቡ ከመሰል ድርጊቶች መታቀብ እና ድርጊቶቹ ተፈፅመው ሲገኙም ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ