ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ሥነ-ሥርዓት

ማውጫ

Share this Article

አዲሱ የሀገራችን የንግድ ሕግ (አዋጅ ቁጥር 1243/13) በአዲስ ካካተታቸዉ ጉዳዮች መካከል ለቅድመ ጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማወቀር፣ መልሶ የማደራጀት እና የመክሰር ሕግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለቅድመ ጥንቃቄ ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ስርዓት ተዳሰዋል፡፡

ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ሥነ-ሥርዓት

ምንነት

ዕዳን መልሶ ማዋቀር ማለት ባለዕዳን ከመክሰር ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሥነ- ሥርዓቶችን በመለየት ድርጅቱ (ኩባንያዉ) ቀጣይነት እንዲኖረዉ ለማድረግ የሚረዳ ሂደት ነዉ፡፡ ይህ ሥነ-ሥርዓት ከገንዘብ ጠያቂዎች ጋር በመሆን ዕዳን በተመለከተ ያሉ መፍትሔዎችን የማፈላለግ ሥርዓት ሲሆን ዕዳን መልሶ ማዋቀር መሠረታዊ የንግድ ሥራዎችን እና የአቅርቦቶችን ሂደት የሚጨምር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በሌላ በኩል ዕዳን መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት በንግድ እንቅስቃሴያቸው ለመቀጠል ተስፋ ያላቸው ነገር ግን ዕዳቸውን ለመክፈል እክል የገጠማቸው የንግድ ተቋማት ከገንዘብ ጠያቂዎች እና ከፍ/ቤት ጋር በመሆን ዕዳቸውን መልሰው የሚያደራጁበትና የሚያገግሙበት ሥነ-ሥርዓት ነው። ዕዳን መልሶ ማደራጀት ከዋናዉ የንግድ አሠራር ተፅዕኖ በመውጣት ጥቂት የሚባሉ የንግድ ስራዎችን የመቀየር ሂደትን ለመግለጽ የሚጠቅም ነዉ፡፡ ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ሥነ-ሥርዓት በሌሎች ሀገሮች ተሞክረዉ ዉጤታማ የሆኑ እና እየተሰራባቸዉ ያሉ ናቸዉ፡፡

ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ-ሥርዓት (Preventive Restructuring)

ይህ ሥነ ሥርዓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሕጎች ውስጥ ተካቶ የማይታወቅ ሲሆን ሙሉ በሙሉ በአዲስነት በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ እንዲካተት የተደረገ ነው።

ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዓላማ

የሚመለከታቸዉን ገንዘብ ጠያቂዎች በሙሉ ድምፅ የሚፈቅዱ ከሆነ የፋይናንስ ችግር ዉስጥ ያሉ ተስፋ የሚጣልባቸዉ ተበዳሪዎች ውልን መሠረት ባደረገ መልኩ በጊዜ ዕዳቸዉን ቀልጣፋ እና ዉጤታማ በሆነ መልኩ መልሰዉ እንዲያወዋቅሩ እና ሥራቸዉን እንዲቀጥሉ ወይም የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዉ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የንግድ ሥራ ለመሸጥ መዘጋጀት እንዲችሉ ማድረግ መሆኑ በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 588 ሰፍሯል፡፡ በተጨማሪም ቀልጣፋና ዉጤታማ በሆነ እና ጊዜዉን ጠብቆ በሚከናወን ስርዓት አማካኝነት የኢኮኖሚ መረጋጋትን ማስፋፋት የንብረቱን ዋጋ ከፍ ማድረግ እና የሕግ ተገማችነትንና ግልጽነትን ማረጋገጥ መቻል ነዉ፡፡

ዕዳን መልሶ የማዋቀር ጥቅም

  • የፋይናንስና የኢኮኖሚ እክል ስላጋጠማቸው ዕዳቸውን ለመክፈል የማይችሉ የንግድ ተቋማት መደበኛ የንግድ ሥራቸውን እያከናወኑ ዋና ዋና ከሆኑ ገንዘብ ጠያቂዎቻቸው (ለምሳሌ ከባንኮች፤ አቅራቢዎቻቸውና ተቀባዮቻቸው) ጋር ዕዳቸውን በሚስጥር እንዲያደራጁ ዕድል ይከፍትላቸዋል።
  • ዕዳን በማዋቀር ሂደት ከሚሳተፉት ገንዘብ ጠያቂዎቻቸው በስተቀር ሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች (ለምሳሌ ሰራተኞች) ሥርዓቱ ስለማይመለከታቸው የንግድ ሥራ እንቅስቃሴው ያለምንም መስተጓጎል እንዲቀጥል ይረዳል።
  • ይህ ሥርዓት በሕግ በተወሰነ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ህጉ ስለሚያስገድደው ባለዕዳዎች ዕዳቸውን በጊዜው እንዳይከፍሉ እንዳይገፋፉ ያደርጋል።
  • ይህ ሥርዓት በፍ/ቤት የሚፀድቀው ሁሉም በሥነ-ሥርዓቱ የተካተቱት ዋና ዋና ገንዘብ ጠያቂዎች ሙሉ በሙሉ የተስማሙበት ከሆነ ብቻ ስለሆነ ገንዘብ ጠያቂዎች ላይ ያለፈቃዳቸው ምንም አይነት ግዴታ አይጥልም።
  • የማዋቀር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በሚስጥር እንዲያዝ ህጉ ስለሚያሰገድድ ባለዕዳዎች ያለምንም መሸማቀቅ በሥነ-ሥርዓቱ እንዲሳተፉ ያበረታታል።

ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት ስለመክፈት

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 617 መሠረት ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት የሚከፈተዉ ክፍያዎችን ገና ያላቋረጠ ወይም ክፍያዎችን ካቋረጠ 45 ቀናት ያልሞላዉ እና የኢኮኖሚ ወይም የፋይናንስ ችግር በተጨባጭ ያጋጠመዉ ወይም ያጋጥመዋል ተብሎ የሚጠበቅ ባለዕዳ ሲያመለክት ብቻ ነዉ፡፡ ባለዕዳዉ የቅርብ ጊዜ የሒሳብ መግለጫዎችን፣ የገንዘብ ችግሮችን ሁኔታ እና የሚፈቱበትን መንገድ የሚያስረዳ ጽሁፍ እንዲሁም የገንዘብ ፍሰት ቅድመ ትንበያ ኪሳራን ለሚመለከተዉ ፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ናቸዉ ብሎ የሚያምናቸዉን ሌሎች ማናቸዉም ሰነዶች እና መረጃዎች ባለዕዳዉ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሊሰጥ ወይም እንደባንኮች እና የታክስ ባለሥልጣን አካላት ያሉ 3ኛ ወገኖችን እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

አስገዳጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ዕዳን መልሶ የማዋቀር የባለዕዳዉን ንብረቶች እና እዳዎች ወይም ሌላ ማንኛዉንም የባለዕዳዉን የካፒታል መዋቅር ክፍል አወቃቀር፣ ሁኔታዎች ወይም መዋቅር መቀየርን ወይም የንግድ ሥራዉን ንብረቶች ወይም ክፍሎች ወይም አጠቃላይ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዉን በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የንግድ ሥራ መሸጥን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ማናቸዉንም የሥራ ሂደት ለዉጦችን ማድረግን ወይም ከእነዚህ ዉስጥ የተወሰኑትን ወስዶ ማቀናጀትን ሊያካትት ይችላል፡፡ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዘርፍ ባለሙያ ይሾማል፡፡ የተሿሚዉ መብትና ግዴታ በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 621 እና ተከታዮቹ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የሥነ-ሥርዓቱ የቆይታ ጊዜ

በአዲሱ የንግድ በሕግ አንቀጽ 618 መሠረት ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ ከሚመለከታቸዉ ገንዘብ ጠያቂዎች ጋር በ4 ወራት ዉስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ቢኖርም ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ በሚመለከታቸዉ ገንዘብ ጠያቂዎች በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ባለዕዳዉ ካስረዳ ፍርድ ቤቱ ጊዜዉ እንዲራዘም ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ማራዘሚያዎችን እና እድሳቶችን ጨምሮ ዕቅዱ የሚጠናቀቅበት አጠቃላይ ጊዜ ከ8 ወራት መብለጥ የለበትም፡፡

ስለ ገንዘብ ጠያቂዎች ጥቅሞች ጥበቃ እና የገንዘብ ጠያቂዎች ተሳትፎ

በአዲሱ የንግድ ሕግ ሶስተኛ መጽሀፍ ዉስጥ የተቀመጡት ሥነ ሥርዓቶች አጠቃላይ መርህ የገንዘብ ጠያቂዎችን ትክክለኛ ጥቅም ማስጠበቅ ነዉ፡፡ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ በሁሉም በሚመለከታቸዉ ገንዘብ ጠያቂዎች ሙሉ ድምጽ መጽደቅ አለበት፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎች በሥነ-ሥርዓቶች ወቅት በአጠቃላይ አስተያየታቸዉን የማቅረብ እና ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በሚሰማበት ጊዜ የመሰማት መብት እንዳላቸዉ በአዲሱ በህጉ አንቀጽ 597 እና 598 ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እና ስለሚቀርቡ የክስ ዓይነቶች

ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓትም ሆነ በሌሎቹ በዚህ መጽሀፍ በሚገኙ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በኢትዮጵያ ሥልጣን ያለዉ ፍርድ ቤት የግለሰቡ መደበኛ ቦታ ወይም የማኅበሩ ወይም በሕግ የሰዉነት መብት ያለዉ ሰዉ የተመዘገበበት ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት ቦታ ያለዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 600 ተደንግገዋል፡፡ ይህን ሥርዓት የከፈተዉ ፍርድ ቤት ከነዚህ ሥነ-ሥርዓቶች በቀጥታ በሚመነጩ እና ከእነሱ ጋር በቅርበት በሚገናኙ የሚከተሉት ጉዳዮች ክሶች ላይ ሥልጣን አለዉ፡-

  • ሀ. መልሶ የማዋቀርና መልሶ የማደራጀት ዕቅድ፣
  • ለ. በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያለን ድርጅት በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ እንዲሸጥ ማጽደቅ፣
  • ሐ. በሂደት ላይ ያሉ ዉሎች፣
  • መ. የተቆጣጣሪ ዳኞች፣ የባለዕዳዉ ንብረት ጠባቂዎች፣ ተቆጣጣሪዎች እና ዳይሬክተሮች ኃላፊነት፣
  • ሠ. የክፍያ ጥያቄዎች አቀራረብ፣ ማረጋገጥ እና አቀባበል፣
  • ረ. ከንብረት የሚመነጩ መብቶች፣
  • ሰ. መቻቻል፣
  • ሸ. የንብረቶች መሸጥ ወይም መተላለፍ፣
  • ቀ. የክፍያ ጥያቄዎች ቅደምተከተል፣
  • በ.በሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ክፍፍል፣
  • ተ. የድርጊቶች ፈራሽ መደረግ፣
  • ቸ. ዉሎችን ማጽናትና እና ተፈፃሚነት፣
  • ነ. የባለዕዳዉ ነፃ መዉጣት፣
  • ኘ. የሥነ-ሥርዓቱ መዘጋት፡፡

ዕዳን መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት (Reorganization)

ሌላው እና ዋነኛው በአዲሱ የንግድ ሕግ የተካተተው ጉዳይ ዕዳን መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት ነው። ነገር ግን በ1952ቱ የንግድ ሕግ የመጠበቂያ ስምምነት (schemes of arrangement) በሚል ተቀምጦ ነበር፡፡

ማንኛውም ነጋዴ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ሲሰማራና ገንዘብና ጊዜውን ሲመድብ ይሳካልኛል የሚል እምነት ቢኖረውም ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ግን እንዳሰቡት ሳይሳካላቸው ይቀርና ወደኪሳራ ያመራሉ። ነባሩ የኪሳራ ሕግ አንድ ነጋዴ ያሉበትን ዕዳዎች መክፈል ማቋረጡን እንደ ዋና ምክንያት በመያዝ የአበዳሪዎችንና ሌሎች መብት ጠያቂዎችን ጥቅም ለማስከበር ሲባል የመክሰር ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ያትታል። አዲሱ የንግድ ሕግ ዕዳን እንደገና ስለማደራጀት የሚገልፅ ክፍል በመክሰር ሂደት ውስጥ እንዲካተት አድርጓል። ለማሻሻያው ዋና መነሻ የሚሆነው የህጉ ዓላማ በጊዜያዊ የገንዘብ ችግር ምክንያት ዕዳ መክፈል ያቋረጡ ወይም ለማቋረጥ የተቃረቡ ነጋዴዎች እንደገና ተደራጅተው እንዲያገግሙ እድል መስጠት ነው።

እዳን እንደገና ማደራጀት የሚባለው ባለዕዳው ያለበትን የዕዳ መጠን፣ አይነት እና የአከፋፈል ሁኔታዎች በሌላ የዕዳ ወይም የመብት አይነት፣ መጠንና የአከፋፈል ሁኔታዎች በፍርድ ሲለወጡ ነው። ዕዳን እንደገና የማደራጀት ተግባር የመክሰር ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ወይም ከተሰጠ በኋላ ሊከናወን የሚችል ሲሆን በዋነኝነትም የገንዘብ መብት ጠያቂዎች ፍላጎትና የፍርድ ቤት ውሳኔ እንደቅድመ ሁኔታ የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው።

ዕዳን መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት ለመክፈት ስለሚቀርብ ጥያቄ

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 635 መሠረት ፍርድ ቤቱ ባለዕዳው መወጣት የማይችለው የገንዘብ ችግር ያገጠመው መሆኑ ሲረጋገጥ እና ክፍያዎችን ያላቋረጠ ከሆነ ወይም ክፍያዎችን ካቋረጠ አርባ አምስት ቀናት ካልሞላው ባለዕዳው ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ፤ ባለዕዳው ክፍያዎችን ያቋረጠ ከሆነ እና በሂደት ላይ ያለ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት ከሌለ፤ ማንኛውም ገንዘብ ጠያቂ ወይም ዐቃቤ ሕግ ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ፤ ማንኛውም ገንዘብ ጠያቂ ወይም ዐቃቤ ሕግ የመክሠር ሥነ ሥርዓት ለመክፈት አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜ ባለዕዳው ጥያቄ ካቀረበ እና ክፍያ ያቋረጠበት ሁኔታ ከተፈጠረ 45 ቀናት እንዳልሞላው ማስረዳት የሚችል ከሆነ፤ መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት ሊከፈት ይችላል።

ሥነ- ሥርዓቱ የሚከፈተዉ የፍርድ ቤት አባል ባልሆነ አካል (ሰዉ) ነዉ፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ገንዘብ ጠያቂ ወይም ዐቃቤ ሕግ በሚያቀርበው ጥያቄ ወይም ፍርድ ቤቱ በራሱ ሥልጣን እና ተነሳሽነት ማናቸውንም የንብረታቸውን ክፍል በማጭበርበር ለደበቁ፣ ለማጭበርበር በማሰብ አንዳንዴ ገንዘብ ጠያቂዎችን ሳይገለጹ ሲቀሩ፣ ያለምክንያት ኃላፊነታቸውን ከፍ ላደረጉ ወይም ሌሎች ማናቸውንም የማጭበርበር ተግባራት ለፈጸሙ ሐሰተኛ ባለዕዳዎች መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓቶችን አይከፍትም።

በተጨማሪም ዕዳን መልሶ ለማደራጀት ፍርድ ቤቱ ተቆጣጣሪ ዳኛ (ከፍርድ ቤቱ አባላት መካከል)፣ እንደ ሁኔታዉ እስከ ሁለት ኃላፊዎች እና ከገንዘብ ጠያቂዎቹ ዉስጥ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት እስከ 5 ድረስ ተቆጣጣሪዎችን ይሾማል፡፡ እነዚህ ተሿሚዎችም የየራሳቸዉ ሥልጣንና ኃላፊነት እንዳላቸዉ በህጉ ላይ ተደንግጓዋል፡፡በአጠቃላይ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ሥነ-ሥርዓት በንግድ ሥራ ዉስጥ አስፈላጊ፣ ለማኅበራት ዕድሜ መራዘም እና መልሶ ማንሰራራት ጠቀሜታዉ የጎላ በመሆኑ ባለዕዳዎች የዕዳቸው ሁኔታ ከመባባሱ በፊት ቀድመው በሥነ-ሥርዓቱ እንዲጠቀሙ ስለሚያደርግ የንግድ ተቋማት ዕዳቸውን እንደገና በማደራጀት ከኪሳራ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ይረዳል።