የእስረኛ ማምለጥና ማስመለጥ የወንጀል ተጠያቂነት

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከአንቀጽ 18 እስከ 23 ድረስ የተደነገጉት አንቀጾች ከወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ጋር የተገናኙ ሲሆኑ አራቱ ቀዳሚ አንቀጾች በሕግ ስለተያዙ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች እና በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን በተመለከተ የተደነገጉ ናቸው፡፡ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 13 መሠረት በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሉ በህገ-መንግስቱ የተካተቱትን በሕግ የተያዙ ሰዎች፣ የተከሰሱ እና በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎችም ቢሆን የማረሚያ ወይም የማረፊያ ቤት ህጎችና ደንቦች፣ እንዲሁም የወንጀል ህጉን የማክበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎች ከእስር ማምለጥ እና እስረኛ እንዲያመልጥ መርዳት የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነትን ለማየት እንሞክራለን፡፡

የእሥረኛ ማምለጥ

በቂና አሳማኝ ማስረጃ ከተገኘ፣ ማንኛውንም ሰው መጠርጠርና ተጠርጣሪውን በሕግ መሠረት በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ምርመራ አድርጎ ክስ በማቅረብ ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን ሰዎች በሕጉ መሠረት እንዲቀጡ ማድረግ መሠረታዊ የሕግ ዓላማና መርህ ነው፤ እንዲሁም አንደኛው የሕግ አስፈፃሚዎች ሥልጣንና ተግባር ሲሆን፣ የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ላይ እንደተመላከተው ሰዎች በወንጀል ተጠርጥሮም ሆነ የእስራት ቅጣት ተወስኖባቸው የሚታሰሩት የሕዝብን ወይም የሰዎችን ጥቅምና ሰላም በማስከበር የወንጀል ሕጉን ዓላማ ለማሳካት እንጂ ሌላ ግለሰባዊ ወይም ተቋማዊ ዓላማና ግብ የለውም፡፡ በመሆኑም በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎች ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከእስር ማምለጥ ወንጀል እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎች ማለት ምን ማለት እንደሆነ በወንጀል ህጉ የተሰጠ ትርጉም ባይኖርም በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎች ማለት በፍርድ ቤት በወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸው ከተፈረደ በኋላ የታሰሩ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዙና በምርመራ ላይ የሚገኙትን ጭምር የሚያካትት እንደሆነ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 461 ላይ ከተደነገገው እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም የእስረኛ ማምለጥ ወንጀል ጥፋተኛው የተፈረደበትም ይሁን ገና ያልተፈረደበት፣ በመደበኛ አስራትም ይሁን በማረፊያ ቤት አስራት እንዲቆይ የተደረጉ ሰዎችን እንደሚያካትት ከድንጋጌው መረዳት ይቻላል፡፡

ስለሆነም ማንም ሰው በሕግ አግባብ ተይዞ ወይም ታስሮ ካለበት ቦታ በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ምንም የኃይል ተግባር ሳይፈጽም ያመለጠ እንደሆነ፤ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚቀጣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 461(1) ላይ የተደነገገው ያመለክታል፡፡ ወንጀሉ የተፈፀመው በሰዎች ላይ ዛቻ ወይም የኃይል ተግባር በመፈፀም ወይም በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ እንደሆነ፤ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚያስቀጣም አንቀጽ 461(2) ይደነግጋል፡፡ ጥፋተኛው በመጀመሪያው ወንጀል የተፈረደበት ወይም የሚፈረድበት ሲሆን ስለወንጀሎች መደራረብ ወይም ስለተደጋጋሚነት የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደ አግባብነቱ ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተደንግጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ወንጀል አድራጊው ተደራራቢ ወንጀሎችን አድርጓል ብሎ ቅጣትን የሚያከብደው በወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 60 – 66 እና ከአንቀጽ 184 – 187 መሠረት አንድ ሰው ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ወንጀሎችን የፈፀመ እንደሆነ እና ሁለተኛው ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት መጀመሪያ በተፈፀመው ወንጀል ላይ ፍርድ ያልተሰጠ እንደሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ፍርድ ቤት ወንጀል አድራጊው በደጋጋሚነት ወንጀል አድርጓል ብሎ ቅጣት የሚያከብደው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 67 እና 188 መሠረት የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ከፈፀመበት ቀን ወይም ይህ ቅጣት በይቅርታ ከቀረለት ቀን ጀምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መነሻ ቅጣቱ 6 ወር የሆነ ቀላል እስራት ማስቀጣት የሚችል አዲስ ወንጀል አስቦ ያደረገ እንደሆነ ነው፡፡

እሥረኛ እንዲያመልጥ ማመቻቸትና መርዳት

ማንም ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ሳይሆን በሕግ አግባብ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው እንዲያመልጥ በኃይል ድርጊት፣ በማስገደድ፣ በዛቻ፣ በተንኰል፣ በግል ተሰሚነቱ ያለአግባብ በመገልገል ወይም በማንኛውም ሌላ ዘዴ መንገድ ያመቻቸ ወይም የረዳ እንደሆነ፤ በቀላል እሥራት እንደሚቀጣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 462 ይደነግጋል፡፡ ማምለጡ የተፈፀመው፣ የተሞከረው ወይም የተመቻቸው በቡድን የኅብረት ሥራ፣ በጦር መሣሪያ ወይም በማናቸውም ሌላ መሣሪያ እንደሆነ፤ ወይም እንዲያመልጥ እርዳታ የተደረገለት ሰው ቢያንስ የሃያ ዓመት ፅኑ እሥራት የተፈረደበት ወንጀለኛ እንደሆነ ቅጣቱ ከሦስት ወር የማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከሰባት ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እሥራት እንደሆነ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጓል፡፡ ወንጀለኛው ዕቅዱን ለማሳካት ሁከት አንስቶ፣ በሰው ወይም በንብረት ላይ የኃይል ድርጊት ፈፅሞ፣ ወይም ሠራተኛን ወይም ጠባቂን ደልሎ፣ ወይም ማንኛውም ሌላ ተደራቢ ወንጀል ፈፅሞ እንደሆነ፤ የተደራረቡ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ ቅጣትን ስለማክበድ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ንዑስ አንቀጽ 3 ይደነግጋል፡፡

እስረኛው እንዲያመልጥ የረዳው የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆነ የመንግስተ ሠራተኛ ከተሰጠው ኃላፊነት ጋር ተያይዞ ለሚያደርገው ተግባር ወይም ግድፈት በሙስና ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ጠባቂው ፖሊስ ጉቦ ወይም መደለያ በመቀበልም ሆነ በሌላ በማንኛውም ምክንያት እስረኛው እንዲያመልጥ የረዳ እንደሆነ በአዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 9ን በመጣስ በሥልጣን አላግባብ መገልገል ወይም አንቀጽ 10 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ጉቦ መቀበል ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር የሚወድቁ ወንጀሎችን በተመለከተ ምርመራ እንዲጀመር ለማድረግ፣ ምርመራው በሕግ መሠረት መከናወኑን የማረጋገጥ፣ ክስ አቅርቦ የማስቀጣት፣ እንዲሁም የፌዴራል ሕጎችን የማስፈጸም ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 መሠረት ተሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪም በአንቀጽ 6/8/ሐ ሥር በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን የመጎብኘት፣ አያያዛቸው እና ቆይታቸው በሕግ መሠረት መፈጸሙን የማረጋገጥ፣ ሕገ-ወጥ ተግባር እንዲታረም እንዲሁም ሕግን ተላልፈዋል በተባሉ ሰዎች ላይ በሕግ መሠረት እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል በሚል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም በሕግ አግባብ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎችም በሕግ በተዘረጋ የአሠራር ስርዓት ያላቸውን የመብት ጥያቄ ከማቅረብ ውጪ ሕግን በመጣስ ወይም ከሕግ አግባብ ውጪ ከእስር ማምለጥም ሆነ ለማምለጥ መሞከር እንዲሁም እስረኛ እንዲያመልጥ መርዳት ወንጀል መሆኑ ታውቆ መሰል ወንጀል አድራጊዎች ወደ ፍትሕ አደባባይ እንዲወጡ ለሕግ አስከባሪዎች ተገቢውን እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ