በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሰው ህይወት፣ በአካል እና በጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በሀገራችንም ሆነ በተለያዩ የአለማችን አካባቢዎች በማህበረሰቡ የሚተገበሩ የተለያዩ ድርጊቶች ከሳይንስ አንፃር በጤና ላይ በሚያስከትሉት ጉዳት ምክንያት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሁለቱም ጾታዎች ላይ ሊፈፀም የሚችል ቢሆንም በዋነኛነት በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በስፋት የሚስተዋሉ ሲሆን እነዚህ ጥቃቶች በድርጊቱ ፈፃሚዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የባህል አካል ተደርገው ሲታዩ ይስተዋላል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ለድርጊቶች ተገጂዎች ጥበቃን የሚሰጡ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ማፅደቅ፣ አገራዊ ህጎችን ማውጣት እንዲሁም ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መስጠት ይገኙበታል፡፡ በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ጽሑፍ ስለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሽፋን የሰጡ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን፣ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ክልከላ የተደረገባቸውና የወንጀል ቅጣትን የሚያስከትሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንዳስሳለን፡፡

ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሽፋን የሰጡ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች

ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብዓዊ መብት እውቅና የሰጠው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ “ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ እና ሌሎች ምክንያቶች ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በመግለጫ ውስጥ የተቀመጡትን መብቶችና ነፃነቶች የማግኘት መብት አለው” በማለት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ሴቶች እና ሕፃናት በስምምነቱ የተካተቱ መብቶች ተጠቃሚ ለመሆን በጾታና በእድሜያቸው ምክንያት ከሚደርሱባቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡ የሕፃናትን መብት በመጠበቅ ሂደት የመኖር መብት፣ የእድገት መብት፣ ከሁሉም ዓይነት አካልን እና አዕምሮን ከሚያውኩ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት፣ ከስቃይ፣ ጨካኝና ኢሰብዓዊ ወይም ክብርን ከሚነካ አያያዝ እና ቅጣት የመጠበቅ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡

ለሕፃናት መብት ጥበቃ በሚያደርገው በተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መብት ኮቨነንት (Convention on the Rights of the Child,CRC ) በአንቀጽ 24(3) ስር በልጆች ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በማሰብ ውጤታማ እና ተገቢ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡

በአፍሪካ የሕፃናት መብት እና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 21 መሠረት የቻርተሩ አባል መንግስታት የሕፃናትን ደኅንነት፣ ክብር እና መደበኛ እድገትን የሚነኩ ጎጂ ማኅበራዊና ባህላዊ ልምዶች በተለይም ለልጁ ጤንነት እና ህይወት ጎጂ የሆኑ ልማዶች እና በጾታ፣ በእድሜ ወይም ሌላ ምክንያቶች በልጁ ላይ አድሎአዊ የሆኑ ልማዶች ለማስወገድ ተገቢ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ልዩነት ወይም አድሎ ለማስወገድ የወጣ ስምምነት (The Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women (CEDAW), 1979) አንቀጽ 2(g) እንደሚደነግገው በሴቶች ላይ አድልዎ የሚፈጥሩ ልማዶች ለማስወገድ ነባር ሕጎችን፣ ደንቦችን ለማሻሻል ወይም ለመሻር ጨምሮ ሁሉንም ተገቢ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡

በአፍሪካ የሴቶች መብት ቻርተር ፕሮቶኮል (Protocol to the African Charter on the Rights of Women in Africa , Maputo Protocol) አንቀጽ 5 አባል ሀገራት በሴቶች ሰብዓዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ እና ከታወቁት ዓለም አቀፍ ደረጃዎች (international standards) ተቃራኒ የሆኑ ሁሉንም አይነት ጎጂ ድርጊቶችን መከልከል እና ማውገዝ አለባቸው፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 35/4 ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ መሆናቸውን እና ሴቶች ከጎጂ ባህል ተፅዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል የሕፃናትን መብት በሚደነግገው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 36 መሠረት ህፃን በህይወት የመኖርን መብት ጨምሮ ጉልበትን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርቱ፣ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ መብት አለው፡፡

ህገ መንግሥት ጥቅል ሕግ በመሆኑ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሰው ህይወት፣ አካል እና ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ተካተው ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መሠረት የወንጀል ህጉ የተከለከሉ ድርጊቶችን በመዘርዘር የሚያስከትሉትንም ቅጣት ያስቀምጣል፡፡ በወንጀል ህጉ ከተቀመጡት ክልከላዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  • በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በእርጉዝ ሴቶችና ሕጻናት ህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ (አንቀጽ 561)፡- ማንም ሰው የእርጉዝ ሴትን ሆድ በማሸት ወይም በመውለድ ላይ ያለችን ሴት አካል በማርገፍገፍ ወይም አዲስ የተወለደ ሕፃንን እትብት እበት ወይም እንደ እበት የመሳሰለ ነገር በመቀባት፣ ህፃንን ፀሐይ በመከልከል ወይም ቅቤ በማዋጥ፣ የሕፃንን እንጥል በመቁርጥ፣ ግግ በማውጣት ወይም እንዳይከተብ በማድረግ ወይም ይህን የመሳሰሉ ጎጂነቱ በህክምና ሙያ የታወቀ ልማዳዊ ድርጊት በመፈፀም የእርጉዝ ሴት ወይም የሕፃንን ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገ እንደሆነ በመቀጮ ወይም ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
  • በተሳሳይ መልኩ ከላይ የተጠቀሱትን ድርጊቶች በመፈፀም በእርጉዝ ሴት ወይም ህፃን ላይ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ በመቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 562)፡፡
  • ሴትን መግረዝ፡- ማንም ሰው በየትኛውም የዕድሜ ክልል የምትገኝ ሴት የገረዘ እንደሆነ ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት መቶ ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል ( አንቀጽ 565)፡፡
  • የሴትን ብልት መስፋት፡- ማንም ሰው የአንዲትን ሴት ብልት የሰፋ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ይህ ድርጊት የአካል ወይም የጤና ጉዳት አድርሶ እንደሆነ፣ በወንጀል ህጉ ከፍተኛ ቅጣት የሚጥል ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ይሆናል (አንቀጽ 566)፡፡
  • በተጨማሪ ከነዚህ ከተዘረዘሩት ሁኔዎች ውጪ፣ ኢሰብዓዊነቱ በታወቀና ጎጂነቱ በህክምና ሙያ በተረጋገጠ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት ወይም ሞት እንዲደርስ ያደረገ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በአንቀጽ 561 ወይም 562 ከተመለከቱት ቅጣቶች አንዱ ተፈፃሚ ይሆንበታል፡፡ በድርጊቶቹ ተካፋይ የሆነ ወላጅ ወይም ማንኛውም ሌላ ሰው ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 569 ይደነግጋል፡፡
  • ያለ እድሜ ጋብቻ አግባብ ባለው የቤተሰብ ሕግ ከተፈቀደው ውጪ (የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ የጋብቻ እድሜ 18 ዓመት እንደሆነ ያስቀምጣል) ማንም ሰው አስቦ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ ያገባ እንደሆነ የተበዳይዋ ዕድሜ 13 ዓመት ወይም በላይ ከሆነ ከ3 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም የተበዳይዋ ዕድሜ ከ13 ዓመት በታች ከሆነ ከ7 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
  • በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በሽታን ማስተላለፍ በወንጀል ህጉ ተላላፊ በሽታዎችን ስለማባዛት በተደነገገው መሠረት በተደራቢነት ያስቀጣል (የወንጀል ህጉ አንቀጽ 568)

በሌላ በኩል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚከለክሉ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች እንዳይፈፀሙ በይፋም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያነሳሳ ወይም የቀሰቀሰ፣ ይህን ዓይነት ዓላማ ለማስፈፀም ሕዝብን ያደራጀ፣ ለዚሁ ዓላማ በተደራጀ እንቅስቃሴ ያሳተፈ ወይም ለዚሁ ዓላማ ድጋፍ የሰጠ ማንኛውም ሰው ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት መቶ ብር በማያንስ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 570 ስር ተደንግጓል፡፡

በአጠቃላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በአብዛኛው በገጠር አካባቢ ሊፈፀሙ የሚችሉ የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ድርጊቶቹ በሰው ህይወት እና አካል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በመገንዘብ ድርጊቶቹ እንዳይፈፀሙ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ