በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 እና 55 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2006 ዓ.ም የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃን በአንድ የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ ያዘጋጀ ሲሆን ዓላማውም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መግቢያ ላይ ከተቀመጡ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ለሸማቹ ማኅበረሰብ ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እና ሸማቹ ካወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ እቃ ወይም አገልገሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው። ይህን ጠቅላላ ዓላማም በአዋጁ ውስጣዊ ክፍሎች በተካተቱ በርካታ የሸማቾች መብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ግዴታዎች ድንጋጌ ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሯል። የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ እና በዘመናችን ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለመቋቋም በሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር መደራጀት አስፈልጓል፡፡
በዚህ ጽሁፍ የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማኅበራት ታሪካዊ አመጣጥ ባጭሩ፣ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ምንነት፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራት አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ፣ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት አሠራር እና የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ገበያን ከማረጋጋት አንፃር ያላቸው ሚና የሚሉትን ጉዳዮች እንመለከታለን፡፡
የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማኅበራት ታሪካዊ አመጣጥ ባጭሩ
የመጀመሪያው የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር በ1769 ስኮትላንዳዊ ሸማኔዎች በዱቄት ጥራት እና በዋጋ ውድነት ስላልረኩ ይህን ምርት በጅምላ በመግዛት ላይ የተሰማራውን ማኅበረሰብ አደራጅተዋል፡፡ በዚህም በጅምላ እራስ በመግዛት ስኮቶች የዱቄት ጥራት ማረጋገጥ እና ለማኅበሩ አባላት ዋጋ መቀነስ ችለዋል፡፡ ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እያደገ መጥቶ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሸማቾች ማኅበረሰቦች ግቦችና ዓላማዎች አልተቀየሩም፡፡ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በተመቸ ሁኔታ ለመግዛት ተደራጅተዋል፡፡
በሀገራችን የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ዋነኛ አነሳስ ከድህረ አብዮት (1967) ጀምሮ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 31/1967 (የመሬት ላራሹ አዋጅ) ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህን አዋጅ ለማስፈፀም ኃላፊነት ከተሰጣቸው አካላት አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪና የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስቴር የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራትን እንዲያቋቁም ተደርጎ ነበር፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የህዝባዊ ማህበራት አደረጃጀቶች መመስረትና እንደ ህብረት ሱቅ መሰል የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ1983 መጨረሻ ጀምሮ እየተቀዛቀዘ የመጣ ቢሆንም ሁሉንም የሕብረት ሥራ ማኅበራት ዓይነቶች ወጥ በሆነ ሁኔታ መምራት የሚያስችል አዋጅ ቁጥር 147/1991 ሊወጣ ችሏል፡፡ ይህም በአዋጅ ቁጥር 402/1996 የተሻሻለ ቢሆንም አሁን በስራ ላይ ባለው የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 ተተክቷል፡፡ ሸማቾችን የሚመለከት እራሱን የቻለ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 ወጥቶ በሥራ ላይ ውሏል፡፡
የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ምንነት
የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማኅበራት ከሕብረት ሥራ ማኅበራት ዓይነቶች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ስለ ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት እ.ኤ.አ በ1986 ይፋ የሆነው የሸማቾች ጥበቃ ሕግ “ማንኛውንም ሸቀጥ ወይም አገልግሎት የሚገዛ ሸማች ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ይህ ኬኔዲ ሁላችንም ሸማች ነን ካሉት ጋር ይቀራረባል፡፡ የአሜሪካው 35ኛ ፕሬዝዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲ በአንድ አጋጣሚ “ሁሉም ሸማች ነው፣ በግሉም ሆነ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ፣ በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ አግባብ ጥቅሙ የሚነካ በሌላ በኩል የሸማቹ ውሳኔ በግሉም ሆነ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ነው” ሲሉ ሸማች በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማኅበራዊ እርካቦች ያለውን ድርሻ አመላክተዋል፡፡ በዚህ ትርጉም እንደተባለውም ሁላችንም ሸማች መሆናችንን፣ ሻጩ ሸማች፣ ሸማቹ መልሶ ሻጭ ይሆናል፡፡ ሁለተኛውና ትልቁ መልዕክት በሸማቹ፣ በሻጩ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ ግንኙነት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ/ም የታተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ሸማችን ጠበብ አድርጎ “እህልን ለንግድ ሳይሆን ለምግብነት የሚገዛ በላተኛ” በማለት ትርጉም ሰጥቶት እናገኛዋለን፡፡ ይህ ግን የአገልግሎት ዘርፉን የዘነጋ ይመስላል፡፡
የእንግለዝኛው ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ደግሞ “ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን የሚገዛ ሰው” “a person who buys goods and services” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ሸማችነት ሸቀጥንም አገልግሎትንም እንደሚያካትት በሚያረጋግጥ ሁኔታ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ1986 ስለ ሸማቾች መብት ጥበቃ ባወጣው እና አባል ሀገራት እንዲተገበሩት ጭምር በሚያሳስበው ሕግ ሀገራት፣ መንግስታት የሸማቾችን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ደረጃ ከጥራት፣ ከጤና አንፃር ማውጣት በግንባር ቀደምትነት ይጠቅሳል፡፡
አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 2(4) መሠረት “ሸማች” ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው፡፡ ሸማቾች በአንድ የኢኮኖሚ ሥርዓት ካሉ የተለያዩ ተዋናዮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች “ፍላጎት” (Demand) በማለት የሚገልጹትን ሀሳብ ከሚወክሉት ውስጥም ይመደባሉ፡፡ ይህም ማለት ሸማቾች በንግድ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ወደ ገበያ የሚቀርቡትን የተለያዩ ዕቃዎችና አግልግሎቶች የሚገዙ ናቸው፡፡
በሕብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 አንቀጽ 2(1) መሠረት “የሕብረት ሥራ ማኅበር” ማለት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እና በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሏቸውን ችግሮች በጋራ ለማቃለል ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሰዎች በፈቃደኝነት የሚያቋቁሙት፣ በጋራ ባለቤትነት የሚያስተዳድሩት፣ በኅብረት ሥራ ማህበራት መርህ መሠረት የሚመሩትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚቆጣጠሩት ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የሕብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡” የሕብረት ሥራ ማኅበራት የአባላትን የማምረት አቅም በማሳደግ ወይም ለአባላት የሥራ ዕድል በመፍጠር የአባላትን ምርትና ገቢ ለመጨመር በአባላት ሙሉ ፍላጎት የሚቋቋሙና ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያሣትፉ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡
ከዚህ በመነሳት የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማሕበራት የሸማቹን ህብረተሰብ (ለተጠቃሚው) ጥራት ያለውን ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ በተፈለገ ጊዜና ቦታ ለማቅረብ የሚረዱ እና የሸማቹን መብትና ፍላጎት የሚያስጠብቁ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ በሀገራችን የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት መደራጀት ከጀመሩ ከ45 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በመሆኑም ማኅበራቱ የአባለቱን ብሎም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ለአባሎቻቸው ከሚያስገኙት ጥቅም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በሀገራቱ ጠንካራ የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በመፍጠር የሕብረተሰቡን ዘላቂና አስተማማኝ የልማት ተሳታፊ ማድርግ ያስፈልጋል እንላለን፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ