የውል አለመፈፀም የሚያስከትለው ውጤት በኢትዮጵያ ህግ

ማውጫ

Share this Article

ሰዎች በዕለት ተዕለት በሚኖራቸው ማኅበራዊ ግንኙነት አንዱ ከሌላው ጋር በሕግ ፊት የሚፀና የውል ግዴታ ይገባሉ። በሰዎች መካከል የሚደረገው የውል ግዴታ ፍትሐብሔራዊ ግዴታ ሲሆን ተዋዋይ ወገኖች በውል የገቡትን ግዴታ መፈፀም አለባቸው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በውል የገቡትን ግዴታ ሳይፈፅሙ ቢቀሩ የራሱ የሆነ የሕግ ውጤት የሚያስከትል ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የውል አለመፈፀም በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ የሚያስከትለውን ውጤት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የውል ምንነት

በፍትሐብሔር ህጋችን ቁጥር 1675 መሠረት ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1678 መሠረት የፀና ውል ለመፈፀም

  • ተዋዋዮች ውል ለመዋዋል ችሎታ ያላቸው መሆን (ለምሳሌ እድሜው ለአካለ መጠን የደረሰ መሆን)
  • በነፃ ፍላጎታቸው የተዋዋሉት መሆን
  • የሚዋዋሉበትም ነገር ህጋዊ የሆነ እና ሊፈፀም የሚችል መሆን እና
  • ህጉ ውሉ ሚደረግበት ፎርም ካስቀመጠ በተመለከተው ፎርም መሠረት የተደረገ መሆን አለበት፡፡

እንደሚደረገው ስምምነት በርካታ የውል አይነቶች ያሉ ሲሆን የሽያጭ ውል፣ የኪራይ ውል፣ የሥራ ቅጥር ውል… ወዘተ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ውሎች የሚገዙበት የየራሳቸው ድንጋጌዎች ቢኖራቸውም በፍትሐብሔር ህጉ ስለውሎች ጠቅላላ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ለሁሉም ውሎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

የውል አለመፈፀም የሚያስከትለው ውጤት

በመሰረቱ ህጋዊ ውል በተዋዋዮች መካከል ሕግ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ከተዋዋይ ወገኖች አንደኛው ግዴታውን ለመፈፀም የማይችልበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ በፍትሐብሔር ህጉ ከእንቀጽ 1771-1805 በተመለከተው መሠረት የውል ግዴታውን የተወጣ ወይም ለመወጣት ዝግጁ የሆነ ወገን፡-

  • ውሉ በባለእዳው ወይም በሌላ ወገን እንዲፈጸም የማስገድድ
  • ውሉን የመሰረዝ
  • በውሉ አግባብ ባለመፈፀሙ የደረሰበትን ኪሳራ የመጠየቅ መብት አለው።

ውሉ እንዲፈፀም ማስገደድ

በተዋዋይ ወገኖች የተደረገው የውል ግዴታ መሠረት የውል መፈፀሚያ ጊዜ ደርሶ አንደኛው ወገን እንደ ውሉ አልፈፀመም የሚባለው ባለእዳው ውሉን እንዲፈፅም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ውሉን ለመፈፀም ያልቻለ እንደሆነ ነው። በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1772 መሠረት እንደ ውሉ አልተፈፀመልኝም በማለት ክርክር ለማቅረብ የሚፈልግ አንደኛው ወገን የውል ባለእዳው እንደውሉ እንዲፈፀምለት በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ይገባል።

የውል ባለመብት የሆነ ወገን እንደ ውሉ እንዲፈፅምለት ባለእዳውን ሊያስገድደው እንደሚችል የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1776 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ውሉ በግዴታ እንዲፈፀም ሊታዘዝ የሚችለው ውሉ እንዲፈፀምለት ለጠየቀው ወገን የተለየ ጥቅም የሚሰጠው ከሆነና አፈፃፀሙም በባለዳው ነጻነት ላይ ምንም መሰናክል የማያደርስ ከሆነ ብቻ ነው። ልብ ሊባልና መታወቅ ያለበት ነገር የውል ግዴታን አስገድዶ ማስፈፀም የሚችለው የውል ባለመብት ሳይሆን ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ብቻ እንደሆነ ነው።

የውል መሰረዝ

ከተዋዋይ ወገን አንደኛው በውሉ መሠረት ግዴታውን ያልፈፀመ እንደሆነ ወይም ደግሞ የፈፀመው ሙሉ ወይም ፍፁም ባልሆነ አኳኋን እንደሆነ እንደ ውሉ ያልተፈፀመለት ወገን ውሉ እንዲሰረዝለት ለፍርድ ቤት ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚችል በፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1784 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። ውል ይሰረዝል ጥያቄ ለፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት የተዋዋዮችን ጥቅምና ያላቸውን ቅን ልቦና መሠረት ማድረግ ያለበት ሲሆን ፍርድ ቤቱ ውሉ እንዲሰረዝ ውሳኔ የሚሰጠው በውሉ ላይ አይነተኛ የውል መጣስ መኖሩን ወይም ከተዋዋይ ወገኖች አንዱ ግዴታውን ያልተወጣ መሆኑን ካረጋገጠ ብቻ እንደሆነ በፍትሐብሔር ህጉ እንቀጽ 1785 ላይ ተቀምጦ ይገኛል።

በሌላ በኩል ከተዋዋይ ወገኖች ባንዱ ውል ሊሰረዝ የሚችል ሲሆን ይህ የሚሆንበት ሁኔታ በፍትሐብሔር ህጉ ከቁጥር 1786-1789 ድረስ ተደንግጎ ይገኛል። ውልን በአንደኛው ወገን ብቻ የመሰረዝ መብት የሚገኘው ተዋዋይ ወገኖች ባደረጉት የውል ቃል ውስጥ ውሉ በአንደኛው ወገን ሊፈርስ እንደሚችል የተገለፀ እንደሆነና ለዚህ ቃል ተግባራዊነት የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ብቻ ነው።

በውሉ ላይ በቁርጠኝነት የተመለከተው የውል መፈፀሚያ ጊዜ ውስጥ ወይም ማስጠንቀቂያ በተሰጠበት ጊዜ በአእምሮ ግምት ይበቃል ተብሎ የተሰጠው ቀን ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠው የችሮታ ጊዜ ውስጥ ከተዋዋዩ አንደኛው ወገን የገባውን ግዴታ ሳይፈፅም የቀረ እንደሆነ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ አንደኛው ወገን ውሉን የመሰረዝ መብት አለው።

በተጨማሪም የውሉ አፈፃፀም በተጨባጭ የማይቻል መሆኑ ሲረጋገጥ፣ አንደኛው ወገን የገባበትን ግዴታ ለመፈፀም የማይችል ሆኖ ከተገኘ ወይም የመፈፀሚያውን ጊዜ ካዘገየ እና በዚህ ምክንያት የውሉ መሠረታዊ ስምምነት ከተነካ ሌላኛው ወገን እራሱ ውሉን ያለፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረዝ ይችላል።

ሌላው በአንደኛው ወገን ውሉ ሊሰረዝ የሚችልበት መንገድ አንደኛው ተዋዋይ ወገን ውሉን ለመፈፀም አምቢተኛ ከሆነ ነው። ከተዋዋዮች መካከል አንዱ ግዴታውን የማይፈፅም መሆኑን በግልፅ ካስታወቀ ሌላኛው ወገን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውልን የመሰረዝ መብት ያለው ሲሆን አንደኛው ወገን ግዴታውን የማይፈፅም መሆኑን ያስተሰወቀው በጽሁፍ ከሆነ ግን ሌላኛው ወገን ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳይጠበቅበት ውሉን የመሰረዝ መብት አለው።

የጉዳት ካሳ (Damage)

የጉዳት ካሳ የሚጠየቀው በተዋዋይ ወገኖች መካከል በተደረገ ውል አንደኛው ወገን የገባውን ግዴታ ባለመወጣቱ ምክንያት በሌላኛው ወገን ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1790 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1791(1) መሠረት ከተዋዋዮቹ ወገን አንደኛው ምንም ጥፋት ባያደርግም ያለበትን ግዴታ ባለመወጣቱ የጉዳት ካሳ መክፈል እንዳለበት የደነገገ ሲሆን በዚሁ ቁጥር ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ተዋዋዩ የውል ግዴታውን ያልፈፀመበትን በቂ ምክንያት ካስረዳና ይህም ምክንያት ከአቅም በላይ መሆኑ ከተረጋገጠ የውሉ አለመፈፀም ከሚያመጣው ኃላፊነት የመዳን እድል አለው።

የፍትሐብሔር ህጉ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል የሚለው ሀረግ በተዋዋዮች ተለጥጦ እንዳይተረጎም በመፈለጉ ምክንያት ትርጉም የሰጠው ከመሆኑም በተጨማሪም ከአቅም በላይ የሆኑ ሀይሎች ምን እንደሆኑ ዘርዝሮ አስቀምጧቸዋል። በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1792(1) መሠረት “ከአቅም በላይ የሆነ ሊመልሱት የማይችል ኃይል ደርሷል የሚባለው አንድ ባለእዳ ባላሰበው ድንገት ደራሽ ሆኖበት ግዴታውን እንዳይፈፅም ፍፁም መሰናክል በሆነ አይነት የሚያግደው ነገር ባጋጠመው ጊዜ ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቶታል።

በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1793 ላይ ከዐቅም በላይ የሆነ ኃይል የሚያሰኙ ምክንያቶች የተዘረዘሩ ሲሆን እንዚህ ምክንያቶችም፡-

  • ባለእዳው ሀላፊ የማይሆንበት ያልታሰቡና በሌላ ሰው ላይ የሚመጡ ድንገት ደራሽ ነገሮች፣
  • ውሉ እንዳይፈፀም በመንግሥት የተደረገ ክልከላ
  • እንደ መሬት መናወጥ፣ መብረቅ፣ ማዕበል ይህን የመሳሰለ ፍጥረታዊ መቅሰፍት፣
  • የጥላት የውጭ ሀገር ጦርነትና የሀገር ውስጥ ጦርነት፣
  • የባለእዳው መሞት ወይም ባልታሰበ ሁኔታ የሚደርስበት ከባድ አደጋ ወይም ጽኑ ህመም ናቸው።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች በተፈጠሩ ጊዜ አንድ ተዋዋይ ግዴታውን ባይወጣም የውሉ አለመፈፀም ከሚያመጣው ኃላፊነት ነፃ ሊወጣ ይችላል።

በሌላ በኩል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1794 መሠረት ከአቅም በላይ የሆኑ ኃይል ናቸው የማያስብሉ ሁኔታዎች የተቀመጡ ሲሆን እነሱም፡-

  • በተዋዋዩ ፋብሪካ ቤት ወይም ሥራውን ከሚያከናውንበት በአንደኛው መስሪያ ቤት ቅርንጫፍ ውስጥ የተደረገ የሰራተኞች አድማ ወይም የመስሪያ ቤቱ መዘጋት ጉዳት
  • ለውሉ አፈጻጸም አስፈላጊ የሆነው ዋነኛ ጠባይ ያለው ዕቃ ዋጋ መወደድ ወይም መረከስ
  • ባለእዳው ያለበትን የግዴታ አፈፃፀም ወጪ የሚያከብድበት የአዲስ ሕግ መውጣት ናቸው።

ሆኖም ተዋዋዮች በውላቸው ተቃራኒ የውል ቃል ካስገቡ እና ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል እንደሆነ ከተስማሙ በስምምነታቸው መሠረት የሚፈፀም መሆኑን ከድንጋጌው መረዳት ይቻላል፡፡

የውል አለመፈፀም የራሱን ውጤት የሚያስከትል እና ባልፈፀመው አካል ላይ ኃላፊነት የሚያመጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ሊያሳድ እና ውል ሲገባም ሆነ ሲፈፅም ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ