መግቢያ
የአሰሪና ሠራተኛ ሕግ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ያለ ግንኙነት የሚያስተዳድር ሕግ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የግል ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኘነት የሚገዙ የተለያዩ ህጎች በስራ ላይ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በ1955 ዓ.ም የወጣው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 210/1955፣ በ1968 ዓ.ም የወጣው የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 64/1968፣ የሠራተኛ ጉዳይ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 85/1968፣ ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 42/1985 እና አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ካለው የማኅበረሰብ እድገት ጋር የሚጣጣም የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ወጥቶ በስራ ላይ ይገኛል። በአዋጁ ከተካተቱ ጉዳዮች ውስጥ የስራ ውል የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች ይገኝበታል። ይኸውም የስራ ውል የሚቋረጠው በአሰሪው ወይም በሠራተኛው አነሳሽነት ወይም በሕግ በተደነገገው መሠረት ወይም በኅብረት ስምምነት ወይም በተዋዋይ ወገኖች በሚደረግ ስምምነት እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 23/1 ስር ተደንግጎ ይገኛል። የስራ ውል ሲቋረጥ ያለማስጠንቀቂ (አንቀጽ 27) እና በማስጠንቀቂያ (አንቀጽ 28) ሊሆን እንደሚችል ከአዋጁ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል። የስራ ውል መቋረጥ ከሚያስከትላቸው ውጤቶች መካከል ደግሞ የስራ ስንብት ክፍያ አንዱ ነው። የዚህ አጭር የንቃተ- ሕግ ትምህርታዊ ጽሑፍ ትኩረት የስራ ውል ሲቋርጥ የስራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ የሚለው ይሆናል።
የስራ ስንበት ክፍያ እና የካሳ ምንነት
የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ በተለምዶ የአገልግሎት ክፍያ እየተባለ ለሚታወቀው የስራ ስንብት ክፍያ ትርጉም ያልሰጠ ቢሆንም በተለያዩ ፅሁፎች ከተሰጠው ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው የሥራ ስንብት ክፍያ ማለት አሠሪው ከቅጥሩ በኋላ ወይም ቅጥሩ ሲጠናቀቅ ለሠራተኛው የሚሰጠው ማካካሻ እና/ወይም ጥቅማጥቅሞች ነው። በአዋጁ ስለስራ ስንበት ክፍያ ከተቀመጡ አጠቃላይ ድንጋጌዎች የሚወሰደው ግንዛቤ ከዚህ ትርጉም ጋር የሚጣጣም ሆኖ ይገኛል። በተመሳሳይ አዋጁ ስለካሳ ምንነት ትርጉም ያልሰጠ ሲሆን ከድንጋጌዎቹ አጠቃላይ መንፈስ መረዳት እንደሚቻለው በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ካሳ ማለት በአሰሪው ጥፋት የስራ ውል ተቋርጦ ወደ ስራ እንዲመለስ ለሠራተኛ ፍርድ ቤት ወስኖለት ሠራተኛው ወደ ስራ ለመመለስ ፍቃደኛ ካልሆነ በስራ መቋረጥ ምክንያት አሰሪ ለሠራተኛው ገንዘብ በካሳ መልክ የሚከፍልበት የክፍያ አይነት ነው። አዋጁ ለስራ ስንብት ክፍያ እና ካሳ ትርጉም ያልሰጠ ቢሆንም ክፍያዎቹ የሚከፈሉበትን ሁኔታ እና የክፍያ ስሌቱን በዝርዝር አስቀመቀጧል።
የስራ ስንበት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች
በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 39 ስር የስራ ስንብት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች ተዘርዝረው ይገኛሉ። ይኸውም የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ እና አግባብነት ባለው የጡረታ ሕግ መሠረት የጡረታ አበል ለመቀበል ብቁ ያልሆነ ሠራተኛ በሚከተሉት ሁኔታዎች የስራ ስንብት ክፍያ ይከፈለዋል።
- ድርጅቱ በመክሰሩ ወይም በሌላ ምክንያት ለዘለቄታው በመዘጋቱ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ( በአዋጁ አንቀጽ 24/4 ተመልክቷል )፣
- በሕግ ከተደነገገው ምክንያት ውጪ በአሰሪው አነሳሽነት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ( የስራ ውል በአሠሪ አነሳሽነት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ህጋዊ አግባቦች በአዋጁ አንቀጽ 26 ተመልክተዋል)፣
- በአዋጁ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት ሠራተኛው ከስራ ሲቀነስ (የሠራተኛ የስራ ቅነሳ በአንቀጽ 29 ተመልክቷል)
- በአሰሪው ወይም በሥራ መሪ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ትንኮሳ የተፈጸመበት እንደሆነ ወይም ድርጊቱ በሌላ ሠራተኛ እንደተፈጸመ ሪፖርት ተደርጎለት አሰሪው ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ያቋረጠ እንደሆነ (ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል በሠራተኛው አነሳሽነት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች በአዋጁ አንቀጽ 32(1)ለ ተመልክቷል)፣
- አሠሪው በሠራተኛው ላይ ሰብዓዊ ክብሩንና ሞራሉን የሚነካ ወይም በወንጀል ሕጉ መሠረት የሚያስቀጣ አድራጎት በመፈጸሙ የተነሣ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ያቋረጠ እንደሆነ ( በአንቀጽ 32(1)ሀ ስር ተመልክቷል)፣
- አሠሪው ለሠራተኛው ደኅንነት ወይም ጤንነት የሚያሰጋ አደጋ እንዳይደርስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እርምጃ ባለመውሰዱ የተነሳ ሠራተኛው የስራ ውሉን ሲያቋርጥ (ያለመስጠንቀቂያ የስራ ውል በሠራተኛው አንሳሽነት ሊቋረጥ የሚችልበት ምክንያት እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 32(1)ሐ ተመልክቷል)፣
- ሙሉ ወይም ዘላቂ የአካል ጉዳት በመድረሱ ሠራተኛው ሥራ ለመሥራት አለመቻሉ በሕክምና ተረጋግጦ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ(በአዋጁ አንቀጽ 24(5) ተመልክቷል)፤
- ቢያንስ አምስት ዓመት በአሠሪው ዘንድ የሥራ አገልግሎት ኖሮት በህመም ወይም በሞት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ወይም በሥራው ላይ የሚያስቆይ ከሥልጠና ጋር የተያያዘ ለአሠሪው የውል ግዴታ ሳይኖርበት ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅ፤
- በኤችአይቪ/በኤድስ ህመም ምክንያት በራሱ አነሳሽነት የሥራ ውሉን ያቋረጠ እንደሆነ፤ ከአሰሪው የስራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው።
አንድ ሠራተኛ የስራ ስንብት ክፍያ ከማግኘቱ በፊት ቢሞት የሥራ ስንብት ክፍያው በአንቀጽ 110/2 ለተመለከቱት ጥገኞቹ ማለትም የሟች የትዳር ጓደኛ፤ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የሟች ልጆች እና በሟች ድጋፍ ይረዱ የነበሩ የሟች ወላጆች ይከፈላል። ለሟቹ ጥገኞች የሚከፈለው የስራ ስንብት ክፍያ በአዋጁ አንቀጽ 110 በሚከፈለው የካሳ አከፋፈል መሠረት የሚፈፀም ይሆናል።
የስራ ውል ሲቋረጥ ካሳ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች
አንድ አሰሪ ወይም ሠራተኛ የስራ ውልን ሲያቋርጥ በአዋጁ ወይም አግባብ ባለው ሌላ ሕግ የተወሰኑትን አስፈላጊ ሁኔታዎች ያላሟላ እንደሆነ የሥራ ውሉ መቋረጥ ህገ-ወጥ እንደሆነ የአዋጁ አንቀጽ 42 ይደነግጋል። ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ ከሚያስከትላቸው ውጤቶች መካከል ወደ ስራ ከመመለስ ባሻገር የካሳ ክፍያ አንዱ ነው። በአዋጁ አንቀጽ 43/1 ስር እንደተደነገገው በአዋጁ አንቀጽ 26(2) በተመለከቱት ምክንያቶች አሰሪው የስራ ውሉን ቢያቋርጥ ሠራተኛውን ወደ ስራ የመመለስ ግዴታ ያለበት ሲሆን ሠራተኛው ወደ ስራ ለመመለስ ካልፈለገ ግን ካሳ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት አለው። በአዋጁ አንቀጽ 26(2) ስር እንደተደነገገው የሚከተሉት የሥራ ውልን ለማቋረጥ ተገቢ ምክንያቶች ሆነው ሊቆጠሩ የማይችሉ በመሆኑ የስራ ውል ሲቋረጥ ሠራተኛው ከስራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ የካሳ ክፍያ የማግኘት መብት አለው። እነሱም፡-
- ሀ) ሠራተኛው በሠራተኞች ማኅበር አባል መሆኑ ወይም በማኅበሩ ሕጋዊ ተግባሮች ተካፋይ መሆኑ፤
- ለ) ሠራተኛው የሠራተኞች ተጠሪ ሆኖ ለመሥራት መፈለጉ ወይም መሥራቱ፤
- ሐ) ሠራተኛው በአሠሪው ላይ ቅሬታ ማቅረቡ ወይም በፍርድ ቤት በቀረበ ክስ ወይም በሌላ ሰው ክስ ተካፋይ መሆኑ፤
- መ) የሠራተኛው ብሔር፣ ጾታ፣ ሐይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ዘር፣ ቀለም፣ የቤተሰብ ኃላፊነት፣ የዘር ሐረግ፣ እርግዝና፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ወይም ማኅበራዊ አቋም፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ምክንያቶች የስራ ውልን ያቋረጠ አሰሪ ሠራተኛውን ወደ ስራ የመመለስ ወይም የካስ ክፍያ የመፈፀም ግዴታ አለበት።
በተጨማሪ በአንቀጽ 32(1) (ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውልን ማቋረጥ) መሠረት የስራ ውልን የሚያቋርጥ ሠራተኛ በአንቀጽ 40 (የስራ ስንብት ክፍያ መጠን) ከተመለከተው የስራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደሞዙ በ30 ተባዝቶ ካሳ ይከፈለዋል። ይህ ክፍያ አግባብ ባለው የጡረታ ሕግ በተሸፈነ ሠራተኛ ላይም ተፈፃሚ እንደሚሆን አዋጁ ይደነግጋል። ሆኖም ሠራተኛው የስራ ውሉን ያቋረጠው በአንቀጽ 32(1)ለ ላይ በተመለከተው ምክንያት የሆነ እንደሆነ ከሥራ ስንብት ክፍያው በተጨማሪ የቀን ደመወዙ በ90 ተባዝቶ የሚከፈለው ሲሆን ይህ ክፍያ አግባብ ባለው የጡረታ ሕግ በተሸፈነ ሠራተኛ ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 41(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል።
በሌላ በኩል ሠራተኛው ለአሰሪው ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የሚኖርበት ሁኔታ በአዋጁ የተመለከተ ሲሆን ይህም በአንቀጽ 31(በማስጠንቀቂያ የስራ ውል ስለማቋረጥ) ወይም በአንቀጽ 35(2) (የማስጠንቀቂያ ጊዜ) ስለማስጠንቀቂያ የተጠቀሱትን አስፈላጊ ሁኔታዎች ያላሟላ ሠራተኛ ለአሠሪው ካሣ ይከፍላል። በዚህ መሠረት የሚከፈለው ካሣ አሰሪው ለሠራተኛው ከሚከፍለው ቀሪ ክፍያ ውስጥ ከ30 ቀናት የበለጠ መሆን እንደሌለበት በአዋጁ አንቀጽ 45 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
በአጠቃላይ የስራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች በአዋጁ የተመለከቱ በመሆኑ ሠራተኛው በሕግ አግባብ ክፍያዎቹን የመጠየቅ እና የማግኘት መብት አለው። አሠሪም እንደዚሁ።
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የቀረብ