ሰዎች በየዕለቱ በሚኖራቸው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ፍትሐብሔራዊ አለመግባባቶች ሲከሰቱ እና ዳኝነት ፍለጋ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱ ይታያል፡፡ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ለማቅረብ ደግሞ የክስ ማመልከቻ መዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡
ሆኖም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ፍርድ ቤት የሚቀርብ ክስ ሊኖረው ሚገባውን ይዘት በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ውስን በመሆኑ ሲቸገር ይስተዋላል። በዚህ አጭር ጽሑፍ አንድ ሰው ክስ ሲመሰርት ክሱ ሊኖረው ስለሚገባው ይዘት እንመለከታለን።
የፍትሐብሔር ክስ ማመልከቻ ይዘት
መብትና ጥቅሜ ተነክቷል የሚል ማንኛውም ሰው የደረሰበትን ጉዳት በመግለፅ አቤቱታውን ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል። በ1958 በወጣው የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርአት ሕግ ቁጥር 222 መሠረት አንድ ሰው የፍትሐብሔር ክስ ሲመሰርት የክሱ ይዘት የሚከተሉትን መሠረታዊና አስገዳጅ ነገሮች ማካተት ይኖርበታል፡፡
ክሱ የሚቀርብበት ፍርድ ቤት ስም፣ የሚያስችልበትን ቦታና ስም
የፍርድ ቤቱ ስም መገለፁ ክሱ ለቀረበለት ፍርድ ቤት ተደራሽ እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪም ተከራካሪ ወገኖች ጉዳዩ የቀረበበት ፍርድ ቤት የሚያስችልበትን ቦታ እንዲያውቁ ያደርጋል።
የክሱ አርዕስት
የክሱ አርዕስት የሚባለው የክሱን ምንነት በአጭሩ የሚገልፅ ነው፡፡
የከሳሽና ተከሳሽን ስም፣ የሚኖሩበትን አድራሻ እና መጥሪያ የሚደርስበትን አድራሻ
- የከሳሽና ተከሳሽ አድራሻ ያስፈለገበት ምክንያት አንድም የፍርድ ቤት ሥልጣንን
- ለመወሰን ሲሆን ሌላው ደግሞ የመጥርያ አደራረስን ለመወሰንና የተከራካሪዎችን
- ማንነት በተገቢው ሁኔታ ለመለየት እንዲቻል ነው።
ከሳሽ ወይም ተከሳሽ በሕግ ችሎታ የሌለው ከሆነ ይሄው በክሱ ላይ መገለፅ ይኖርበታል
ተከራካሪ ወገኖች ህጋዊ ተግባራትን እንዳያከናውኑ በሕግ ክልከላ የተደረገባቸው ከሆነ። ለምሳሌ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ክርክሩ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመወሰን እንዲያመቸው በክሱ ላይ መገለፅ ይኖርበታል።
ከሳሽ ክሱን ለማቅረብ ያለውን ሥልጣን
ክሱን ያቀረበው አካል ነገረፈጅ ወይም ጠበቃ ወይም ወኪል ከሆነ ይህን መግለፅና ማስረጃ አያይዞ ማቅረብ ይኖርበታል።
ለክሱ ምክንያት የሆኑትን ነገሮችና የተፈጠሩበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም ተከሳሽ ተጠሪ የሆነበትን ምክንያት
ለክርክሩ መነሻ የሆነው ነገር መቼ፣ የት እና እንዴት እንደተፈጠረ፣ ከሳሽ በጉዳዩ ላይ መብት ያለው መሆኑ እንዲሁም ከተከሳሽ ለጉዳዩ ሀላፊ የሆነበት ምክንያት እና ከሳሽ ከተከሳሽ ላይ ምን እንደሚፈልግ መገለፅ አለበት፡፡
- ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ጉዳይ የማየት ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ
- አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ለክሱ ምክንያት የሆነው ነገር ግምት፤ በክስ ውስጥ መካተት ያለባቸው ናቸው፡፡
ከሳሽ ለክሱ ምክንያት የሆኑን ምክንያቶች ሁሉ በክሱ ማመልከቻ ላይ አጠቃሎ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ መሠረትም ከሳሽ ክስ ሊመሰርትበት ሲችል ሆነ ብሎ ባስቀረው ጉዳይ ላይ በድጋሚ አዲስ ክስ ሊመሰርት እንደማይችልና ከሳሽ ያቀረበው ክስ በአንድ ጉዳይ ላይ የተመሰረተ ሆኖ የሚጠይቀው ዳኝነት ግን ከአንድ በላይ ዳኝነት መጠየቅ ሲችል ቀንሶ ባስቀረው መብት ላይ በድጋሚ ክስ ሊያቀርብበት እንደማይችል በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 216(2፣3፣4) ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።
የማስረጃ አቀራረብ
አንድ ክስ ለፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ የቀረበውን ክስ ሊያስረዱ የሚችሉ የተለያዩ ማስረጃዎች ከክሱ ጋር ተያይዘው መቅረብ አለባቸው። በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 223 መሠረት ከሳሽ ከሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ጋር የሚከተሉትን ነገሮች አያይዞ ማቅረብ አለበት።
- የምስክሮችን ስም ዝርዝር ከነ ሙሉ አድራሻቸውና ምስክሮቹ የሚቀርቡበት ምክንያት
- ለክሱ መነሻ ወይም መሠረት የሆነውን ሰነድ ዋናውን ወይም ትክክለኛ ግልባጩ
- ማስረጃ ይሆናሉ የተባሉ ጽሁፎችን በከሳሽ እጅ የማይገኙ ከሆነ በማን እጅ እና የት እንደሚገኙ
- የሚያቀርበው ምስክር ወይም የፁሁፍ ሰነድ የሌለው ከሆነ ይህንኑ መግለፅ ይጠበቅበታል፡፡
ከክሱ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የማስረጃ ዝርዘር የፍርድ ቤቱን ስም፣ የከሳሽና ተከሳሽን ስምና አድራሻ የያዘ መሆን አለበት።
የሚጠየቀውን ዳኝነት በዝርዘር ስለማቅረብ
ከስ ያቀረበ ወገን በክስ ማመልከቻው ላይ በተለየ ወይም በምትክ ወይም በተለዋዋጭ የሚጠይቀውን ዳኝነት በግልፅ መጠየቅ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ ክስ የመሰረተው በብዙ ጉዳዮች ወይም በተለያዩ ነገሮች ላይ የሆነ እንደሆነ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የሚጠይቀውን ዳኝነት በግልጽ ማስቀመጥ እንዳለበት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 224 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
ማንኛውም መብትና ጥቅሙ የተነካበት ሰው መብቱን ለማስከበርም ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት የክስ ማመልከቻ ሲያቀርብ ክሱ የሚቀርብበት ፍርድ ቤት ስም፣ የሚያስችልበትን ቦታና ስም፣ የከሳሽና ተከሳሽን ስም እና መጥሪያ የሚደርስበትን አድራሻ፣ የክሱ አርዕስት፣ ለክሱ ምክንያት የሆኑትን ነገሮችና የተፈጠሩበትን ጊዜና ቦታ መገለፅ ይኖርበታል። በተጨማሪም የፍትሐብሔር ክስ ሲቀርብ መጠየቅ ያለበት ዳኝነት ሁሉ ለፍርድ ቤቱ መቅረብ አለበት፡፡ ክሱ ተጠቃሎ ሳይቀርብ ቀርቶ ለክርክሩ ምክንያት በሆነው ነገር ውሳኔ ከተሰጠ ግን በድጋሚ አዲስ ክስ ሊቀርብበት አይችልም። ስለሆነም በፍትሐብሔር ጉዳይ ክስ የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ክሱን በሚያቀርብበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ